የአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) ልሳን  ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 8              

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

 ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 8                                                 ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም.

ትግላችን ለኢትዮጵያ አንድነት ከሆነ . . .

የድምጽ ቅጂውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ (https://youtu.be/OcTmK72H68M)

በቅድሚያ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በሀገራችን ኢትዮጵያ ለተሰማው የኢሕአዴግ አገዛዝ ባለሥልጣናት ግድያ የተሰማንን ሀዘን ልንገልጽ እንወዳለን። ድርጊቱና ጥፋተኛው ማነው? ሳንል በጥቅሉ የተከሰተው ድርጊት ለጆሮ አስደንጋጭ፣ ለሀገር አሳፋሪ፣ ለቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶቻቸው መሪር ሀዘንና ቅስም ሰባሪ  ሁኖ አግኝተነዋል። ለሁሉም መጽናናትን እንመኛለን።

አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ  የኢትዮጵያን የግዛት ሉዓላዊነትና የሕዝቧን አንድነት አስመልክተን መሠረታዊ የሀገሪቷ ችግሮች ላይ ያተኮረ ምክክር በማድረግ መፍትሄ መሻት እንደሚገባ በተደጋጋሚ ገልጸናል። አሁንም እናነሳዋለን። ኢትዮጵያችን ለአለፉት 28 ዓመታት ዘረኝነትን ተሸክማ ኖራለች። ይህ የኢሕአዴግ/ህወሓት የዘር ፖለቲካ በሕገ መንግሥት ተረቆ ተወደደም ተጠላ ሕዝብ እንዲቀበለውና ለአልፉት 28 ዓመታት የሀገሪቷ ገዢ ሕግ መሆኑ ለሀገር መከራን፣ ለሕዝብ ሰቆቃን ከማበርከት ያልዘለለ፣ ሀገር አፍራሽ ለመሆኑ ዛሬ የጥፋቱ መጨረሻ ላይ እያንዣበበ ሳይሆን አንዣቧል። ህወሓት ከ17 ዓመት የጫካ ተጋድሎው በቀጣይነት የሀገሪቷን በትረ መንግሥት ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያን ዘርንና/ቋንቋን መሠረት አድርጎ ሲከፋፍል፣ ሲገዛ በአንድ በኩል ለአገዛዙ ዕድሜ መራዘም ሲጠቅመው፤ በሌላ በኩል ህወሓት ያልገዛትና ያልቦጠቦጣት ሀገር እንድትበጣጠስ ላቀደው ተልዕኮ  28 ዓመት ሙሉ በሀገርና በሕዝብ ላይ የተሰነቀው ዘመቻ ውጤት ቁልጭ ብሎ እተታየ ነው።

የዛሬ 28 ዓመት ህወሓት በኢሕአዴግ ጭምብል በትረ መንግሥቱን ሲቆጣጠርና የኢትዮጵያን ታሪክ “ተረት ተረት” በማለት አዲስ ታሪክ ለመፍጠር ማንቋሸሽ ሲጀምር ጀምሮ ከሕዝብ ዘንድ ተቃውሞ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች ትግል የገጠመው አገዛዝ ሀገር እንዳትበታተን፣ ተተኪ ትውልድ ኢትዮጵያዊነቱን እንዳይስት፣ ኢትዮጵያ ለልጆቿ በልጆቿ እንድትሆን የተካሄደ ያልተቋረጠ ጉዞ ነበር። ትግሉ ከመለስ ዜናዊ፣ ከኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከዶር ዐቢይ አሕመድ ሳይሆን ከመሠረታዊ የሀገሪቷ ቁልፍ ችግር አንፃር ተግባራዊ ሊሆን ስለታሰበውና ስለሆነው ዘርንና ቋንቋን መሠረት ስላደረገው አደገኛ የግዛት ክፍፍል መፍትሄ አግኝቶ ዓለም ያወቃት ኢትዮጵያ በኢትዮጵያነቷ ለዘላለም ትቀጥል ዘንድ ነው። የሀገራችንን ዘላለማዊ ሕይወቷን ለመበጣጠተስ ከቅኝ ገዢዎች አድራጎት በቀጣይነት በመንግሥት ደረጃ የተሳካለት ቢኖር ህወሓት/ኢሕአዴግ ነው። በኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው ክልላዊ መንግሥትነታቸውን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና ያሉ የዘር ድርጅቶች ዛሬ ኢትዮጵያ “በለውጥ ጎዳና ላይ” በተባለችበት ወቅት መንግሥት እየተባሉ ሲጠሩ ሊከፋፍሏት ያሰቧትን ኢትዮጵያ ለጆሯችን አዲስ እንዳይሆንብን በየዜና ማሰራጫው፣ በየጋዜጣው/መጽሔቱ፣ በየማህበረሰባዊ ገፆች፣ በየሕዝባዊ ስብሰባው ሲያመቻቹን እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባናል።

የኢትዮጵያ የግዛት አከላለል እንደተጠበቀ ለመንግሥታዊ አስተዳደር እንዲያመች በጥንት ጊዜ በጠቅላይ ግዛት፣ በቀጣይ አገዛዝ በክፍለ ሀገር ስያሜያቸውን የያዙ የሀገሪቷ ግዛቶች ዛሬ በዘርና ቋንቋ ተሸንሽነው አሁን በአለው የኢሕአዴግ ወያኔ አገዛዝ የኦሮሚያ ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል ወዘተ ሽንሸናቸው እድገት አሳይቶ ዛሬ በ “ለውጥ ሂደት” የኦሮሚያ መንግሥት፣ የትግራይ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት ወዘተ አባባል ኢትዮጵያን ሊገነጣጥሉ ካኮበኮቡ የዘር ድርጅቶች መንግሥትነታቸውን በረቀቀ ዘዴ እንቀበለው ዘንድ የሚደረግ ስነልቦናዊ ጨዋታን ልንረዳው ጊዜው ይጠራናል።

የሀገር፣ መንግሥትንና ሕዝብ ትርጓሜ ለማደናገርና ፍላጎታቸውን ለማሳካት አወቅን ባይ ምሁራን ከማስተማር ይልቅ አደናጋሪ ብዕራቸውን ሲያሾሉ፣ አንደበታቸውን ሲሸጡ የተከሰተው ዛሬ ቢብስበትም ከ50 ዓመት በፊት ነበር። ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገር ሕዝብ ስብስብ ለማስመሰል የ1960ዎቹ ትውልድ ሕዝቦች የሚለውን ቃል ማስነበብ ሲጀምር ለሀገራችን ጠንቅ መሆኑን አለመረዳት ወይም ለድብቅ የመገንጠል ዕኩይ ዓላማቸው መሣሪያ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም። የትኛውም ዓለም ከጥንት ሲፈጠር ሀገር ሁኖ አልተፈጠረም። ጥንታዊው ኅብረተሰብ ለእራሱ ኑሮና ለከብቶቹ ውሃን ተገን እያደረገ ለምና የግጦሽ መሬትን እየፈለገ በመስፈር ቋንቋውን፣ ባህሉን እየተጋራ ሲኖር፣ ሲጋጭ ብሎም ሲዋጋ ኖሯል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል የተለያየ ጎሳና ነገድ አካል እንደመሆኑ ከቤተሰብ ወደ ጎሳ-ነገድ-ህብረተሰብ በመሸጋገርና ወደ አንድ ክልላዊ አስተዳደር ሲጠቃለል ሕዝብ በመባል የራሱን አስተዳደራዊ አካል መንግሥት በማለት ፈጥሯል። በዚህ እረገድ ጥናት ለማቅረብ ባይሆንም የዚህ ጽሁፍ እቅዳችን ሕዝቦች ስንል፣ መንግሥት ስንል ድብቅ ተልዕኮን እንዳቀፈ ለመግለጽ ነው። በዚህም የኅብረተሰብ እድገት ደረጃ ዓለማችን በእርስ በርስ ግጭት፣ በጦርነት፣ በቅኝ ግዛት ወረራ፣ በዓለም ጦርነት፣ በአካባባዊ ግጭት አልፋ በሰባት አህጉራት ተከፋፍላና በተለያዩ ሀገራት ታውቃ የሰው ዘርን ታቅፋለች። አፍሪካ እንደ ሀጉርነቷ ወደ 52 ሀገሮች አቅፋለች። እያንዳንዱ ሀገር የተለያየ ዝርያ፣ ቋንቋን፣ ጎሳ፣ ነገድ ያካተተ ሕዝብ ሲኖረው አጠራሩም የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ፣ የሱዳን ሕዝብ፣ የአልጄሪያ ሕዝብ፣ የግብጽ ሕዝብ፣ ወዘተ ሲባሉ ምነዋ ለኢትዮጵያችን ሕዝቦች ተሰነቀረባት? በአጭሩ ቃሉ ሲጠነሰስ ኤርትራን ለማስገንጠል የተጠነሰሰ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በማለት ሕዝቦች በ60 ዎቹ ትውልድ ሲወረወርና “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል” መፈክር ማታገያ ሲሆን የችግሩ እርሾ ተጠነሰሰ ቢባል ያስኬዳል።

ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሕግሓኤ/ሻቢያ) ኤርትራ የራሷ መንግሥት የነበራት ሀገር አድርጎ በፈጠራ ታሪኩ እንቅስቃሴውን ሲጀምር ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እንደነበር አጠያያቂ አልነበረም። እንደተዶለተውም ኤርትራ ተገነጠለች፣ ኢትዮጵያዊነቷን አጣች፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰበካ ተግባራዊ ሆነላት። ሻቢያና መሪው ኢሳያስ አፈወርቂ ለዚህ ሂደት ውጤታማነት በአምሳያው የፈጠረው ወያኔ/ህወሓት ለኤርትራ መገንጠል ያደረገው አስተዋጽዖ ተዘንግቶ “በለውጥ ጎዳና ላይ” ያሉት ኃይሎች “ኢሱ. . .ኢሱ. . .” ሲያሰኙ ይሁና ብለን ተመልክተናል። ወያኔ ሕገ መንግሥቱን በጫካ ትግሉ አርቅቆ በሰኔው 1987 ዓ.ም. ሸንጎ ለማጸደቅ ሲያቀርብ አደገኝነቱን ተረድተው የተቃወሙ ቢኖሩ አፈሩ ይቅለላቸውና ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስና ጥቂት ሌሎች አገር ወዳዶች ነበሩ። የህወሓት ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመከፋፈል፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስሜትን ለመሸርሸር፣ ስለ ሀገር ሳይሆን ስለ ጎጥ በማሰብ እንድንዳከም፣ ኢትዮጵያን እንደ ወራሪና ተስፋፊ በመዝገባቸው ለማስፈር በብሔር/ብሔረሰብ መብት ላይ የተጠነሰሰና ሀገርን ለ28 ዓመት የገዛ አደገኛ ሠነድ በመሆኑ ነው ተቃውሞው እጅግ የሚከረው፤ አሁንም መቀጠል የሚኖርበት።

የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማይቀበሉ የዘር ፖለቲካ ድርጅቶች አመቺ መሰላል ነው። የኢሕአዴግ መንግሥት “ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት” በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39 “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል” ይፈቅዳልና ተግባራዊነቱን ሊከለክል አይችልም። የ28 ዓመቱ ገዢ ኢሕአዴግ የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ የወራሪና የጡት ቆራጭ ሰንደቅ ዓላማ ነው ያስባለ ብቻ ሳይሆን፣ ለጭካኔው አምላክና ታሪክ ይፍረደውና ለእምዬ ምኒልክን በጡት ቆራጭነት መታሰቢያ ሐውልት ያቆመ የታሪክ አተላ አገዛዝ ነው። ሀገራችንን ከነድህነቷ ከተራራው ጫፍ ያስቀመጣትን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ዐድዋን ከታሪክ መዝገብ ለመሠረዝ ጥረት ቢደረግም ዐድዋ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ዐድዋ ናቸውና አልተሳካለትም፤ አይሳካለትም። ታሪካዊ ቅርሶቿንና ሐውልቶቿን ሊደረምስ ይችል ይሆናል እንጂ ታሪኳን ከቶም እንደማያጠፋ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የወያኔ ህወሓት መሠሪ ተንኮልና “የአክሱም ሐውልት ለደቡቡ ምኑ ነው፣ ባንዲራ ጨርቅ ነው፣ አሰብ ከግመል መጠጫ የላቀ ተግባር የለውም” እባባዊ አባባል ቀላል አይምሰለን። አሁን ለተደረሰበት በአንዳንድ የዘር ድርጅቶች ኢትዮጵያን ጥላቻና ክልላችን ሀገር ይሁን ሂደት የአራጋቢ ምሁሮች ትንታኔ ያበረከተው አስተዋጽዖ ውጤት ነው። የሚያስተዛዝበው እነኚህ አንዳንድ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር ምሁራን ከአካዳሚክና የሙያ ልምዳቸው ውጪ የሚያደርጉት መዘላበድ ነው። የኢኮኖሚ፣ የቋንቋ፣ የሂሳብ፣ የሕግ፣ ወዘተ ፕሮፌሰር የሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ላይ የፈለጉትን ለመናገርና ለመፃፍ ፈቃድ ለራሳቸው ሰጥተዋል። ብዙዎቹ በተለይ በውጭ ያሉት በሚኖሩባቸው ሃገራት እንዲህ አይነት ሁለገብ አዋቂ ነኝ የሚል መኮፈስ ሊያደርጉ አይችሉም – ራሳቸውን ስለሚያዋርዱና የመስኩ ባለሙያዎች ስለሚሞግቷቸው። በድሃ አገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ ሲሆን ግን “ከእኔ በላይ አዋቂ” በሚል እሳቤ ያውም ለመጥፎ ዓላማ ሲያቦኩ ትንሽም ህሊናቸው አይወቅሳቸውም። በጥቅሉ በተደጋጋሚ ይህንን የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት፣ ሀገር፣ መንግሥትና፣ ሕዝብ አካሄድ ያነሳነውና ማብራሪያ የሰጠንበት ግልጽ ለማድረግ ትግላችን አቅጣጫውን እንዳይስትና ማነጣጠር ያለብን የ28 ዓመት የወያኔ/ህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝና ሕገ መንግሥት ላይ መሆን ስለሚገባው ነው። ትግላችን ኢትዮጵያን ለመውደድ፣ ለኢትዮጵያ ለማጨብጨብ፣ ከኢትዮጵያ ጎን ለመሰለፍ፣ እኔም ኢትዮጵያ ነኝ! ለማለት፣ ደግመን ደጋግመን ኢትዮጵያችን! ለማለት መሆን ይኖርበታል።

የሕገ መንግሥቱ ባለ መብት ሕዝብ እስከሆነ ድረስ ይስተካከል፣ ይሻሻል፣ ከዚያም አልፎ ሙሉ በሙሉ ይቀየር ሊባል መብቱ የሕዝብ ነው። ከመለስ ዜናዊ ጀምሮ በሀገሪቷ የሚካሄዱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ከሕገ መንግሥቱ ጋር በማያያዝ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊንዱ” የሚል ቋንቋ በጠ/ሚር ኃይለማርያም ዘመን ዛሬም በለውጥ አራማጁ ዶር ዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ይደመጣል። ትግሉ እኮ ለሀገራችን አንድነት ነውና አንድነቷን ደግሞ እየተፈታተነ ያለው ሕገ መንግሥቱ በመሆኑ ይናድልን ማለት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ማለት መሆኑን አበክረን እንናገራለን፣ እንሰብካለን። ሕዝባችንን በባርነት ሰንሰለት አፍኖ የያዘው የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ሕዝብ ከፋፋይነቱን አስፍቶ ዛሬ ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊወስደንና ተስፋ አስቆራጭ መበታተን ላይ ሀገሪቷን እየገፋት በመሆኑ ከሀገሪቷ ጫንቃ ላይ በ“ሀገር አድን ሕዝባዊ ጥሪ” ሊነሳ ይገባዋል። ሕገ መንግሥት ለሕዝባዊ ትግል ማስፈራሪያ ሊሆን አይገባውም። “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ!” ስንል ኢሕአዴግ/ህወሓት እና ሕገ መንግሥቱ የአንድነት ፀሮች ናቸውና አገዛዛቸው ያብቃ ማለታችን ነው፤ በአጭሩ። 28 ዓመት በሀገራችን ያመጡት ነገር ቢኖር ኦሮሞው ከአማራው፣ ከትግሬው ሌላውም ሌላው እንዳይፋቀር፣ እንዲናከስ፣ እንዳይተቃቀፍ፣ አኩሪ ባህላቸውን እንዳይጋሩ፣ በእምነትም ብንቃኘው እስላሙ ከክርስቲያኑ በአንድ ቤት እንዳይኖር እንቅፋት የሆነው ሕገ መንግሥት ሲወደስ መስማት እጅጉን ያሳፍራል። እውን ለኢትዮጵያ አንድነት ከሆነ ትግሉ ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥቱ መወገዝ ያለባቸው፣ በኢትዮጵያችን የ28 ዓመት ተጠያቂነት ዕዳቸውን ሊከፍሉ የሚገባቸው መሆኑን ሕዝብ እንዲያውቀው እንታገላለን። ሕገ መንግሥቱን ተገን አድርጌ ለውጥ አመጣለሁ ማለት ኦሮሞን ከአማራ ነጥዬ፣ የትግራይን መገንጠል አስሬ፣ ደቡቡን እንደ መንግሥት ሀገር ሰጥቼ፣ ምሥራቁን ለታላቋ ሱማሌ አስረክቤ፣ አማራውን ቀለበት ውስጥ አስገብቼ እቀጥላለሁ ከሚል የአጥፊዎችና የሀገራችንን አንድነት ሚፈታተኑ ባዕዳን ኃይሎች አስተሳሰብ ሥር መውደቅ መሆኑን እንናገራለን። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 2010 የተጀመረው “ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና” ጉዞ ዓመታቸውን በአስታወስንበት ወቅት ትንታኔ የሰጠንበትን ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 4 (http://www.ethiopiachen.org/images/pdf/Eth_Vol3/071411_1H1H_Ethiopiachin_Vol_3_No_4.pdf) ማንበብ ይቻላል። በዚህ የለውጥ ሂደታቸውና ሰሞኑን በተከሰተውና እስካሁን በተዘገበው የስድስት ባለሥልጣናት ግድያና በቀጣይነት ለምርመራ ትፈለጋላችሁ እየተባለ የሚካሄደው እስርና አፈሳ ኢትዮጵያችን ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ ሲጠቁም ከላይ ያቀረብነውን ትንታኔ መንደርደሪያ በማድረግ ኢሕአዴግ፣ ህወሓትና ሕገ መንግሥቱ አንድም ሦስትም መሆናቸውን በማስገንዘብ ነው።

ሰኔ 15 ቀን የተሞከረው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል “መፈንቅለ መንግሥት” ከተፈጸመው ግድያ ባሻገር ኢትዮጵያ በዚህ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ጉዞዋ ምን ላይ እንደደረሰች አመላካች ነው። በየትኛውም አካባቢ መንግሥት ሀገሪቷን መቆጣጠር እንዳልቻለ ጠቋሚ ነው። አንድ ሀገር የሚያስተዳድር መንግሥት ዴሞክራት ሆነ አምባገነን በቅድሚያ ሀገሪቷን እንደ አንድ ቤተሰብ የመቆጣጠር፣ መረጃ የመስጠትና የመቀበል፣ ለሚከሰቱ አላስፈላጊ ክስተቶች አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት አቅሙ ወሳኝነት አለው። በዘመነ ዐቢይ አሕመድ አገዛዝ አየሩን የሞላው ዜና “የጎሳ ግጭት ተከሰተ፣ የሰው ሕይወት ጠፋ፣ ቤታቸው ፈረሰ፣ ቤታቸው ተቃጠለ፣ አካባቢውን እንዲለቁ ተደረገ፣ የተፈናቀሉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፣ መንግሥት ይድረስልን፣ . . .” የብሶት፣ የሰቆቃ፣ የዕንባ፣ የሀዘን አቤቱታዎች ናቸው። “በኦሮሚያ ክልል ባንኮች ተዘረፉ፣ ሦስት ኢትዮጵያውያንና ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎች ተገድለው ከነመኪናቸው ተቃጠሉ፣ ወዘተ” ለአየርና ለመገናኛ ያልበቁትን መገመት አያዳግትም። ሂደቱ እየቀጠለ በሄደ ቁጥር መንግሥት አለ ወይ? ጥርጣሬ ሁሉም ላይ ቢያንዣብብ፣ ተስፋ የተጣለበት ለውጥ ለጥያቄ ቢቀርብ አያስደንቅም።

በየክልሉ “ልዩ ኃይል” በሚል የተደራጁ ወታደራዊ ኃይሎች ለምን አስፈለጉ? በማዕከላዊ መንግሥትና በክልል አስተዳደሮች መካከል ያለው የሥልጣን ተዋረድ እየላላ መምጣቱን እየተገነዘብን ምን መደረግ አለበት? ብሎ ትንታኔ መስጠት አስፈላጊ የማይሆንበት ምክንያት ይህንን የዘርና ቋንቋ ክልል ስለማናምንበት ነው። ሆኖም የዘርና ቋንቋ ክልል ያመጣው ጣጣ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን። ዛሬ የጠ/ሚር ዐቢይ አገዛዝ የትግራይ ክልል ከዕዙ ውጭ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ቀጣይ ባለተራ ኦሮሚያ ክልል እየሆነ እንደመጣ መታዘብ አያዳግትም። ደቡብ አካባቢም ለሌላ የተቸረ መብት የሚነፈግበት ጉዳይ የለምና የራሱን መንግሥት ለመመሥረት እመጨረሻው ቋፍ ላይ ይገኛል። በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል አሁንም ያለው ከክልላችን ውጡና ወከባ በክልሉ “ልዩ ኃይል” የሚካሄድ ተግባር ነው። የየክልሎቹ “ልዩ ኃይል” የተጠናከረው ማንን ለማጥቃት ነው የተዘጋጀው? ይህ “ልዩ ኃይል” የማደራጀት መብት አይገባውም ካልተባለ በቀር በአማራው ክልል “ልዩ ኃይል” ቢደራጅ ሊያስደንቀን አይገባም። በጥቅሉ ወያኔ/ህወሓት/ኢሕአዴግ የወሳሰበው የ28 ዓመት መሰሪ ተንኮል ዛሬ ክልሎችን ወደ መንግሥትነት አሻግሮ የማዕከላዊ መንግሥትን ትዕዛዝ መናቅና አለመቀበል ሂደቶች ከግምት ስናስገባ በዚህ ሁኔታ ሀገር እንደ ሀገር መቀጠሏ እያሳሰበ መጥቷል። ኢትዮጵያ ከነብሶቷ፣ ችግሯ፣ መከራዋ በአንድ መንግሥት ጥላ ሥር አንድነቷን ጠብቃ እንዳልኖረች ዛሬ ግና ነገ ምን ይመጣ ይሆን? ስጋት ውስጥ የገባችው ዶር ዐቢይ አሕመድ ያመጡት ጣጣ ሳይሆን የህወሓት/ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥቱ የ28 ዓመት የሥራ ውጤት ነው እንላለን። ነውም!

ኢትዮጵያችን ዛሬ ወራሪ አይምጣባት እንጂ ጦርነት ላይ ነች። የዘር ጦርነት! ይህንን መቀበል ይኖርብናል። ይህንን ስንቀበል ነው እንዴት አድርገን ከእርስ በእርስ ግጭት እንውጣ? ብለን ልንመክር የምንችለው። በኦሮሚያ ክልል የሚደረገውን እንሰማለን እንመለከታለን። በምሥራቁ፣ በደቡቡ፣ በሰሜን፣ በምዕራቡ፣ በትግራይም፣ በአማራው በሁሉም ያለው አለመረጋጋትና ስጋት ሀገሪቷን ወደ እርስ በርስ ግጭት የመክተቱ ሂደት ተጀምሯል። መንግሥት በአለባት ኢትዮጵያ በርካታ ባንኮች ሲዘረፉ “ጆሮ ዳባ ስጠኝ” ያለ መንግሥት የቸገረው ጉዳይ አለ። በየአካባቢው በርካታ ቤተሰቦች እየተፈናቀሉ በሕይወትና ሞት መካከል ተከበው “የመንግሥት ያለህ!” ሲሉ ማንቀላፋት አገዛዙ ሊፈታው ያልቻለው ወይም ያልፈለገው ጉዳይ አለ ማለት ነው። “አዲስ አበባ ኬኛ” ተብሎ የኢትዮጵያችን ሰንደቅ ዓላማ ተረግጦ ሜጫና ዱላ ሲውለበለብ ተከላካዩ ባልደራስ ላይ ጦርነት ማወጅ እውን ለውጥ ይህ ነው? ያሰኛል። እውን ለኢትዮጵያ አንድነት ከሆነ ሰበካው፤ ወደ ክላሽ የሚቀየረው ብዕር ማነጣጠር ያለበት ዘረኝነት ላይ ሊሆን ይገባል።

የዛሬ ዓመት ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ላይ በአብዮት አደባባይ ሰልፍ የተሞከረው ግድያ ጉዳይ ምን ደረሰ? የዐባይ ግድብ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ጉዳይስ ተድበስብሶ ቀረ? በመቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ቤተ መንግሥት መግባትና ጠ/ሚሩን ፑሽ አፕ የማሠራት ሂደትስ ምን ነበር ተልዕኮው? በወለጋ ጊምቢ ተገድለው ከነመኪናቸው የተቃጠሉት አምስት ሰዎች ጉዳይስ? እነኚህን ዕልባት ያላገኙ ጉዳዮች እያስታወስን የሰሞኑስ “መፈንቅለ መንግሥት” ለምን ተፈለገ? እውን “መፈንቅለ መንግሥት” ወይስ የእርስ በርስ አለመግባባት? በዚህ ጉዳይ የተለያዩ ጥርጣሬዎች ቢሠነዘሩ አያስደንቅም? ሆን ተብሎ አማራውን ለመምታትና ትጥቅ ለማስፈታት የታቀደ ሰይጣናዊ ዕቅድ? ይህ ዕቅድ እውን ከአዲስ አበባው ግድያ ጋር ተያያዥነት አለውን? እውን ስለ ኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ወገኖችን “በመፈንቅለ መንግሥት” ስም ለማጥፋትና ሌሎች ሀገር ወዳድ ቅን አሳቢዎችን ለማስደንገጥና ለማሸማቀቅ የታቀደ መሠሪ ተንኮል? የጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ያላቋረጠ ኢትዮጵያዊነት ሰበካ ያበቃ ዘንድ ፍላጎት ያላቸው ማድረግ የሚችሉትን ለማሳየት የተወጠነ ድርጊት? ወይስ በኢሕአዴግ ውስጥ ሊኖር የሚችል አለመግባባትን ግምት ውስጥ በማስገባት የወያኔ/ህወሓት የማስጠንቀቂያ ደወል? አዲስ አበባን በተመለከተ መሠረታዊ ጥያቄ ይዞ የተነሳውን በእስክንድር ነጋ የሚመራው የባልደራስ እንቅስቃሴ አድማሱን እያሰፋ ጥያቄው የኢትዮጵያ መሆኑን የሚያደርገውን ሂደት ለመቅጨት? በኦሮሚያ የሚታየውን ብዙ ወራት ያስቆጠረ አለመረጋጋት በባህርዳሩ ፍጥነት ለመፍታት ለምን አልተሞከረም? ሌላም ሌላ።

እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ትንታኔ ቢሰጥባቸው አያስገርምም። ተስፋ የተጣለበት የአንድ ዓመት የሦስት ወር ለውጥ አዎ! የፖለቲካ እስረኞች ፈትቷልና እናድንቀው ቢባል አያስደንቅም። የዓፄ ኃ/ሥላሴ አወራረድ በመጠኑም ቢሆን ለታሠሩ የፖለቲካ እስረኞች፣ በግዞት ላሉ፣ ሽፍታ ተብለው ለተሰወሩ ምህረት በማድረግ ነው የለውጡ ጅማሬ። ደርግ ሲወገድና ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የቀይ ሽብር ተሳታፊዎችን ማሰር የድጋፍ ማሰባሰቢያው ካርድ ነበርና ሁሌም የለውጥ ሂደት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል። ለውጡ ሰመረ፣ አቅጣጫውን ይዟል፣ ግቡን መታ የሚባለው ግና መሠረታዊ የሀገሪቷንና የሕዝብ ጥያቄዎችን እየተመለከተና በግልጽ ሕዝብን እያሳተፈ ሲጓዝ ነው።

አዎ! ለጠ/ሚሩ ምስጋና ይግባቸውና ለበርካታ ዓመታት ሀገራቸውን የራቁ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በቅተዋል። የፖለቲካ ድርጅቶችም እንዲሁ። ግና ትግሉና ለውጡ አቅጣጫውን እየሳተ ነው። በቅድሚያ የኢትዮጵያን አንድነት እንፈልጋለን። ለዚህ ደግሞ አንድነቷን የሚያናጋው ሕገ መንግስት መናጋት ይኖርበታል እንላለን። ከሰሞኑ መፈንቅለ መንግሥት” በቀጣይነት እንደ መለስ ዜናዊ ዘመን “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊንዱ” እየተባሉ እሥር ቤት እየተጋዙ ያሉ ወገኖች እንዳሉ ይደመጣል። ወጣቶችን ማዋከብና እያፈሱ ለእሥር መዳረግም እንዲሁ። አዎ! ለኢትዮጵያ አንድነት ከሆነ ትግሉ የኢሕአዴግ/ህወሓት ሕገ መንግሥት ያለ ምንም ጥያቄ ቃሉን ለማቅለል መለወጥ አለበት እንበል እንጂ፤ እንደ ህወሓት/ወያኔ ሀገር ማድቀቅ ከሆነ መናድ አለበትም ያንሰዋል። ለሕዝባችን ኢትዮጵያዊነትና መብት ከሆነ ትግሉ አዎ! ዘርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ አከላለል ከቶም ማብቃት አለበት። ሕዝባችን መከራና ችግሩን እንደያዘ ከፊታችን ያለውን የመበታተን አደጋ ለመቅረፍ እነኚህን ሁለት ቁልፍ መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ወደድንም ጠላን ኢሕአዴግ የተባለን የዘር ድርጅትና 28 ዓመት በህወሓት መሠሪ ፖለቲካ የተደወረ አገዛዝና ቢሮክራሲ ማብቃት ይኖርበታል።

ምን መደረግ አለበት?

የለውጡ ሂደት ከተጀመረ ዓመት አልፎታል። ከዚህ ለውጥ በፊት ባሉት ዓመታትም በተለይ የመጨረሻዎቹ 2 ዓመታት በኢሕአዴግ/ህወሓት አገዛዝ ላይ ከፍተኛና ያልተቋረጠና ብዙ ግፍ የተፈፀመበትና መስዋዕትነት የተከፈለበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ሀገሪቷን ያናወጡበት ጊዜያት ነበሩ። ጠ/ሚ ዐቢይ፤ የአገዛዙ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም፣ ግድያና ሌሎችም የኢሕአዴግ/ህወሓት ተንኮሎችም ተዳምረው ይህን ሕዝባዊ ተቃውሞ ማቆም ስላልቻሉ ነው ወደ ሥልጣን የመጡት። ኢሕአዴግ/ህወሓት ታዳስኩ፣ አንደገናም ጥልቅ ተሃድሶ አደርኩ፡ የአፈፃፀም ችግር ወዘተ እያለ ውሸት ሲያልቅበትና ሲያቅተው፣ መላው ሲጠፋው ነው የውስጥ የኃይላት አሰላለፍና ሚዛን ተቀይሮ  ዐቢይ አሕመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት። በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ግን ኢሕአዴግ/ህወሓት ራሱ ዋናው የለውጥ ዕንቅፋት መሆኑ ለማንኛውም ሰው ግልፅ ነው። ይህንን ኢሕአዴግ/ህወሓትን ሥርዓት፣ ክልልና ሕገ መንግሥት ይዞ ምንም ዓይነት ለውጥ ማድረግ አይቻልም። ይህን ለመቀየር እውን እንደ አፍ ተግባራዊነቱና ቅንነቱ ካለ ሕዝቡን ከጎን በማሰለፍ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለውጡን ማስቀጠል ኢትዮጵያን የማዳን ሥራ ነው። ብዙ አገራት ሕገ መንግሥታቸውን እንደ አስፈላጊነቱ ይቀይራሉ። ጠ/ሚ ዐቢይ አንዳሉት ለምሳሌ ሕንድ ባልፉት 70 ዓመታ ከመቶ ጊዜ በላይ የሕገ መንግሥት ለውጦች አድርጋለች። ይህ ማለት በየዓመቱ ከአንድ ሕገ መንግሥታዊ አንቀፅ በላይ ለውጥ ስታደርግ ነበር ማለት ነው። በዚህ መለኪያ ብቻ ያለምንም ለውጥ 28 ዓመት የቆየው የኢሕአዴግ/ህወሓት ሕገ መንግሥት የአገልግሎት ዘመኑ አልፎበታል። አይነካም፣ አይቀየርም አባባል አምባገነናዊ አስተሳሰብ ነው።

ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ የ “መፈንቅለ መንግሥቱን” ሙከራ ለሕዝብ ሲገልጹ በተናገሩት መሠረት “ኢትዮጵያ አትፈርስም!” ብለዋል። አዎ! ኢትዮጵያ አትፈርስም! እንደግመዋለን። እንዳትፈርስ ግን ሕይወት ሊፈርስ ይችላል፣ ንፁሃን ሕፃናት፣ አዛውንት እናት አባት አሁንም ተጀምሯል እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ፍጅት ሊከናወን ይችላል። እየዬ የሚያሰኝ እልቂት እንዳይከተል፣ ማን ለማን ማልቀስ እንዳይቸገር፣ የሰው ልጅ ቀባሪው አሞራና ጅብ እንዳይሆን ካስፈለገ ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ ቆራጥ አመራራቸውን የሚያሳዩበት ወቅት አሁን ነው። ሁሉንም የዘር ፖለቲካ ድርጅቶች በመለማመጥና እሽሩሩ በማለት የሚጓዙበት አካሄድ የዘር ፖለቲካ ድርጅቶችን መሣሪያ አስታጠቀ፣ ዘረኝነትን የበለጠ አጦዘው፣ ተፈናቃዩን አበራከተ እንጂ የፈጠረው ተዓምር የለም። የዘር ፖለቲካንና አከላለልን ይዘን ስንዳክር እንኖራለን እንጂ በምንም መልኩ ኢትዮጵያ ሕዝቧን መመገብ ችላ ወደ እድገትና ስልጣኔ ጎዳና አያስኬዳትም። ተበታትኖ የኦሮሚያ መንግሥት የራሱን፣ የትግራይ መንግሥት የራሱን፣ የአማራ መንግሥት የራሱን የሌላውም መንግሥት የራሱን መንግስት መሥርቶና ፕሬዜዳንት ሰይሞ እንዲቀጥል የቅዠት ሩጫ ይቀጥል ካልተባለ። ይህ ደግሞ የተፈለገው ሀገር የመበታተንና የማጥፋት መንገድ ነውና አያዋጣም።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ችግር ላይ ብቻ ሳይሆን የእርስ በእርስ ጦርነት ስጋት ላይ ናት። ሁሉም ነገ ምን ይከሰት ይሆን? እያሉ አምላካቸውን መማጸን ይዘዋል። በመንግሥት በኩል ያለው አመኔታ እየተመናመነ የመጣበት ሁኔታ ያለምክንያት አይደለም። የሚወራውና ምድር ላይ ያለው እጅግ የተራራቁ ናቸውና። ጠ/ሚር ዶር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን ከመበታተን ለማዳን በቅድሚያ ያለውን የዘረኝነት ችግር ለሕዝብ ይፋ አድርገው ሀገራችን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታ በማሳወቅ ሕዝባዊ ጥሪ ማድረግ ይገባቸዋል። ሀገሩን፣ ሰንደቅ ዓላማውንና ሕዝቡን ወዳድ ኃይል ከጎናቸው ይሰለፍ ዘንድ ክተት! ማለት የሚገባቸው ወቅት ላይ እንደሆኑ ልንጠቁም እንወዳለን። “አድበስብሰው ቢያርሱ . . .” እንዳይሆን ችግሩን ለሀገሩና ለሰንደቅ ዓላማው ግምባሩን ከማያጥፈው ሕዝባችን ጋር ለመመከት በግልጽ መጋፈጥ ያለባቸው ወቅት መሆኑን እናሳስባለን። ይህ ካልሆነ አሁንም ዙሮ ዙሮ ኢትዮጵያ አትፈርስም! ግና አስደንጋጭ እልቂት ባንፈልገውም ፈላጊዎች ታጥቀዋልና፣ ባንመኘውም የተመኙ አሉና፣ ኢትዮጵያችን ስንል “ተረት ተረት” ባዮች ከበውናልና እግዚዮ! ከማለት ሌላ አማራጭ የለም።

በመጨረሻም ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ አሁንም እውን ኢትዮጵያን ከመበታተንና ከእርስ በርስ ግጭት ለማዳን ቁርጠኛ አቋም ካላቸው የዘር ድርጅቶችንና ሕዝቡን ለይተው ማየት የኖርባቸዋል። ከጎናቸው ማሰለፍ የሚገባቸው ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ ቤኒ ሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ሐደሬ፣ ደቡቡ፣ ምሥራቁ ሁሉም ሕዝባችን ሀገሩን ወዳድ፣ ሰንደቅ ዓላማውን አክባሪ ነውና ይህንን ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል ስንል “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” የማያቋርጥ ድምጻችንን እናስነብባለን።

ኢትዮጵያ ለልጆቿ ማልቀሷ ያብቃ!!!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ”

 

ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. (July 04, 2019)

 

ማሳሰቢያ ፡

  • ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» «ኢትዮጵያችን» ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
  • «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

 

ስልክ፡  703 300 4302

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com

ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.