ቅዱስ ጊዮርጊስ ለጥያቄዎቹ ምላሽ እስከሚያገኝ ከፕሪምየር ሊጉ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ

1 min read

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮቸ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ፡፡የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ 
ተጫወቱ በማለት ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጎል ብሏል፡፡

ይህን ጨዋታ ከዚህ በፊት የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታወችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አላስተናገደም ሲል በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

እንዲሁም በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከነማ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው፡፡

አዲስ ከመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻል እና በመተጋገዝ ለመስራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷልም ነው ያለው፡፡

በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የወሰናቸውን ኢ – ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡