አማራ ያርጋል! (በላይነህ አባተ)

1 min read
1

የአማራ ሰቆቃ ቁና ሞልቶ ፈሷል፣
ዛሬም ከርቸሌውን ጢም አርጎ ሞልቶታል፣
ተቤቱ ተባሮ ተመንገድ ዳር ወድቋል፣
በጨለማ ቦታ ሲገረፍ ይውላል፣
ባለ እስተንፋስ ሁሉ በቃ ሊል ይገባል!

የእየሱስን እድሜ ግፍ ጽዋ ጨልጧል፣
ገደልነው ቀበርነው ብለው ፎክረዋል፣
ነገር ግን አማራ ይነሳል ያርጋል!

ልክ እንደ ክርስቶስ በአንቀልባ ተሰዷል፣
ተሰፈር መንደሩ በሙርጅ ተጠርጓል፣
እንደ ማርያም ጠላት ተመንበር ተነቅሏል፣
በጦር በገጀራ ተወግቶ ተገሏል፣
ዳሩ ግን አማራ በሳልስት ይነሳል፣
ወደ ሰማይ ጉኖ በቀኝ ይቀመጣል፡፡

አብ ልጁን በምድር ፈተና እንደሰጠው፣
አማራንም አምላክ እየሞከረው ነው፡፡

መቃብርን ፈንቅሎ ወልድ እንደተነሳው፣
አማራም ፈተናን በጥሶ አላፊ ነው፡፡

ፍትፍት አጉራሹን ሕዝብ የከዳሃው ባንዳ፣
አገር ገንቢውን ሕዝብ የሸጥከው ይሁዳ፣
ሰላሳ ዲናርህን ለዘላለም ብላ!

ታረብ ተግብጦቹ እየዶለትክ ደባ፣
ተእጅ አዙር ቀኝ ገዥ እየፈተልክ ሴራ፣
አማራን ለመቅበር ሌት ተቀን ብትሰራ፣
ዳግም ላይቀበር ያርጋል አማራ!

ክርስቶስ ንጉስ ነኝ የሚል ቃል ሳይወጣው፣
ፈሪስ ለቄሳሩ ዋሽቶ እንዳቃጠረው፣
ባንዳና ኸርማን ኮን አማራን የሚያማው፣
ንጉስ ታልሆንኩ ብሏል አማራ እያለ ነው፡፡

የዚህ ዓይነቱ ሸውክ ደባውና አላማው፣
አማራን መስቀል ላይ በምስማር መምታት ነው፡፡

ታሪክ እንደሚያውቀው አማራ ጽኑ ነህ፣
ልክ እንደ ክርስቶስ ዘመንም ቢከዳህ፣
ቀጥቅጠን ገደልነው ቀብረነዋል ቢሉህ፣
ፈንቅለህ ተነስተህ ዳግም ታርጋለህ፡፡

አማራ ሆይ አንተም አምልካህን እርዳው፣
ወንድምህ ሲያጠፋ ምከረው ውቀሰው፣
ዳሩ ግን በመጥፎ በክፉ ዓይን አትየው፡፡

በአማራ ሰቆቃ እጅግ የረካኻው፣
ገለን ቀብረነዋል እያልክ የምትዝተው፣
በገነባት አገር ኑሮን የነሳሃው፣
ክፋትህ ተንኮልህ የሰዶማውያን ነው፣
ሐጥያትህን ብላ አማራ እሚያርግ ነው፡፡

እንደ ዘጽአት ሕዝብ ቢፈስ ቢፈናቀል፣
እንደ ሰማእታት ቢገረፍ ቢታሰር፣
እንደ ክርስቶስ እጅ ቢመታበት ምስማር፣
እንደ ጎን አጥንቱም ቢጨቀጨቅ በጦር፣
ገለነዋል ብለው ቢቆፍሩም መቃብር፣
ድንጋዩን ፈንቅሎ አማራ ያርጋል!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.