የኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ም. በጀት 386.9 ቢሊዮን ብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ጸደቀ

1 min read
5

parlamaከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 109.5 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪ 130.7 ቢሊዮን ፣ ለክልሎች ድጋፍ 140.8 ቢሊዮን እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 6 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይ እየተደረጉ ስላሉ ማሻሻያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የገቢዎች ሚኒስቴር በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ከአገር ውስጥ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው አድንቀዋል። ኢትዮጵያ ከነበረባት የንግድ ብድር 47 በመቶ ገደማ የሚሆነው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሃገራት በዝቅተኛ ወለድ የሚሰጡ ብድሮች መካከል (concessional loan) እንዲሆን መደረጉን ጠቅላይ ምኒስትሩ አስረድተዋል። በዚህም አገሪቱ በየዓመቱ ለቻይና መክፈል ከሚገባት «ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ማትረፍ ችለናል» ብለዋል።
ጠቅላይ ምኒስትሩ መንግሥታቸው የሰለጠኑ ወጣቶችን ለሥራ ወደ ውጭ አገራት የመላክ ዕቅድ መያዙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል። «ከአጭር ጊዜ አንፃር ወደ ውጭ አገር የሰለጠኑ ሰዎች መላክ እንደ እቅድ ይዘናል። በቀጣይነት ወጣቱን አስተምሮ አሰልጥኖ መላክ ኪሳራ ነው። አያዋጣም። ከአጭር ጊዜ አንፃር ያለውን ውዝፍ ለመቀነስ ግን ወጣቱ ሔዶ ሥራ እንዲለማመድ፤ ገቢ እንዲያገኝ፤ ያገኘውን ገቢ ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገባ፤ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ እያደገ እና እየተቀየረ ሲሔድ የሰለጠነ ልምድ ያለው ወጣት መልሶ በማምጣት ለመጠቀም ዕድል ይሰጣል» ሲሉ ተናግረዋል።