በረከት ስምዖንና ታደሠ ካሳ ዛሬ በባሕር ዳር ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡

Filed under: የዕለቱ ዜናዎች |
ዋዜማ ሬዲዮ

1.፡ችሎቱ ቀሪ የሰው ምስክሮችን ከሰማ በኋላ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 18 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

2. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ከተማዋን እያስተዳደር እንደሚቆይ መግለጹን ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 ዘግቧል፡፡ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመኑ ሃች አምና ያበቃ ቢሆንም ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሻሻለለት አዋጅ ላንድ ዐመት እስከ ሰኔ 30 ከተማዋን ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ፓርላማው ለምርጫው ቀነ ገደብ ስላላስቀመጠ የአስተዳደሩ ሥልጣን ዘመን ሰኔ 30 ላይ አልቋል የሚባለው ሐሰት ነው- ብሏል የምክር ቤቱ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ፡፡

3. የገቢዎች ሚንስቴር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2011 በጀት ዐመት ካቀደልኝ 213 ቢሊየን ብር 198 ቢሊዮኑን ሰብስቤያለሁ ብሏል፡፡ ዘንድሮ የተሰበሰበው ገቢ ከ2010 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ22 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው፡፡ ከገቢው የሀገር ውስጥ ገቢ ድርሻ 61 በመቶ ሲሆን ከቀረጥ ደሞ 39 በመቶ ነው፡፡ ለቀጣዩ ዐመት ደሞ ከ248 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱን ሚንስትሯ አዳነች አቤቤ መናገራቸውን ጠቅሶ DW ዘግቧል፡፡

4. አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነገ ለሁለት ታዋቂ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ የክብር ማዕረጉ ተቀባዮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረ ማርያምና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና ኡለማዎች ሰብሳቢ የሆኑት ግራንድ ሙፍቲ ሼክ ለሐጅ ኡመር እድሪስ ናቸው፡፡

5. ቦይንግ ኩባንያ በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በደረሱት አውሮፕላን አደጋዎች ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች 100 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መድቤያለሁ ቢልም ባለ ጉዳዮቹ ግን ስለ ካሳው የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡ ቦይንግ እነማንን ለካሳው እንደሚመርጥም አልታወቀም፡፡ ካሳይ ከፋዮቹ ከአየር መንገዶቹ ሳይሆን የአውሮፕላኑ አምራች መሆኑም ያልተለመደ ነው- ብሏል ሮይተርስ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቃል አቀባይ ስለ ካሳው ምንም መረጃ የለንም ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያና ኬንያ መንግሥታትም ከቦይንግ ጋር ስለ ጉዳዩ አልተነጋገሩም፡፡ አውሮፕላኑ የተከሰከሰባቸው ሰፊ ማሳዎች ባለቤት አርሶ አደሮችም ማሳዎቻቸው እስካሁን ታጥረው ያሉ ሲሆን ካሳ ስለመፈቀዱ በይፋ የሰሙት ነገር የለም፡፡

6. በቀጣዩ ዐመት የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ሕዋ ታመጥቃለች- ብሏል የፋና ብሮድካስት ዘገባ፡፡ ሳተላይቷን የሚያመጥቀው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር ነው፡፡ ሳተላይቷ ስትመትቅ የውሃ፣ ግብርና፣ ማዕድን፣ ከተማ ልማትና አየር ንብረት መረጃዎችን ትሰበስባለች፡፡ ሳተላይቷ የተገነባችው በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከል ነው፤ 95 በመቶው ግንባታዋም ስለተጠናቀቀ ከመጭው መስከረም ጀምሮ ትመጥቃለች፡፡

7. የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ማምሻውን ባወጣው የከረረ መግለጫ ባልተለመደ ሁኔታ ሕወሃትን ከምስረታው ጀምሮ ሊድን የማይችል አማራ ጠል በሽታ የተጣባው ሲል አውግዞታል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ትሃነግ (የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር) በሚል ኢፊሴላዊ ያልሆነ መጠሪያም ተጠቅሟል፡፡ መግለጫው ሕወሃት ትናንት አዴፓ ላይ ላቀረበው ትችት ምላሽ ሲሆን የሕወሃት መግለጫ ከትግራይ ሕዝብ ስነ ልቦና ጋር የሚጻረር መሆኑንም ገልጧል፡፡ በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች የሕወሃት እጅ አለበት በማለትም ከሷል፡፡

8. የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤትና ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያና አፍሪካ ኅብረት ያቀረቡላቸውን ሰላም ሃሳብ በተቀበሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ በካርቱም መፈንቅለ መንግሥት እንደተሞከረ ወታደራዊው የሽግግር ምክር ቤት ትናንት አስታውቋል፡፡ ሆኖም ምክር ቤቱ ሙከራውን ወዲያውኑ አክሽፌ 16 ተጠርጣሪዎችን አስሬያለሁ ብሏል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ሰላም ስምምነቱ ያልተዋጠላቸው ጡረተኛና ሥራ ላይ ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው፡፡ ሁለቱ ወገኖች ሰላም ስምምነቱን ገና አልፈረሙም፡፡

One Response to በረከት ስምዖንና ታደሠ ካሳ ዛሬ በባሕር ዳር ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡

  1. The satelite could help look for Getachew Assefa in space.

    Yifate
    July 14, 2019 at 10:56 pm
    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.