ለእነ ገዱ እና ደመቀ አዲሱ አጋጣሚ – ታምራት ነገራ

1 min read
14

እንደምናየው ኢሕአዴግ ሞቷል፡፡ እህት ፓርቲዎች በይፋ ጠመንጃ መማዘዝ ቀራቸው እንጂ አገሪቷ ወደ ዮጎዝላቪያ እጣ ፋንታ እያንደረደሯት ነው፡፡ ቲም ለማ የተባለው የእነ ጠ/ሚ ዓብይ ቡድን ባሕርዳር ላይ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው::” ሲል ላለፉት 50 ዓመታ የኦሮሞ ልሒቃን ከነበሩበት የደንቆሮ ጎጠኝነት ቅርቃር ውስጥ እራሱን ያወጣ ፤ ኢትዮጵያን በቅቡልነት ለመምራት፤ ታሪካዊ አጋጣሚውን ለመጠቀምም እራሱን ያዘጋጀ ቡድን ከኦህዴድ የተገኘ መስሎን ነበር፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ጠ/ሚ ዓብይ መራሹ ኦህዴድ የወሰዳቸው ተከታታይ እርምጃዎች እና ሊወስዳቸው ሲገባ ችላ ያላቸው እርምጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ቡድን እና መሪዎቹ ለታሪካዊው አጋጣሚ አልመጠኑም፡፡

የማይወደደው ግን የሚያስፈልገው ፓርቲ

ኢህአዴግን ባንወደውም አገሪቷ ፖለቲካዊ አመራር ለመስጠትም ሆነ የመንግስትን መዋቅር ቀንተቀን ለማንቀሳቀስ አስፈላጊ መዋቅር ነው፡፡ ቅቡልነት ያጣው ፓርቲ እነደ አዲስ ለመቀጠል ግን መታደስ ነበረበት፡፡ ጠ/ሚ ዓብይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ሊወስዱ ይችሉት የነበረው ይገባቸውም የነበረውም አንድ ትክክለኛ እና አስፈላጊ ውሳኔ ኢህአዴግን በአዲስ ትርክት እና አወቃቀር ማደስ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በኦህዴድ እና በብአዴን አመራሮችም ሆነ ካድሬዎች መካከል በቂ የሚባል መተማመመን እና መግባባት ይታይ ነበር፡፡ እጅ እና እግሩ ባይታወቅም ይህን መጠነኛ ተግባቦት ኦሮማራ በሚባል ስም ለለመስረት ተችሎም ነበር፡፡

እነ ጠ/ሚ ዓብይ ቢገባቸው፤ በደንብ ቢያስቡበት ኖሮ በብአዴን እና ኦህዴድ መካከል የነበረውን መተማመመን በመጠቀም ኦህዴድን፤ ብአዴንን፤ ደህዴንን አጋር ፓርቲዎችን በማዋሓድ አንድ ትልቅ ሃገር አቀፍ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ ያው ወያኔ ማኩረፏ ኤቀርም፡፡ ይህ እርምጃ አስፈላጊም ነበር፡፡ ጠ/ሚ ዓብይ ግን ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ እና ግዴታም የኦህዴድን እና ብአዴንን ብራንድ (ስም እና አርማ ) ወደ መቀየር ብቻ አሾቁት፡፡ ፓርቲው ያስፈልገው የነበረው ግልፅ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ጥምቀት፤ በውስጡ ስላለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጥቅም ድልድል የማያሻማ ውይት ተዘሎ ነገሩ ሁሉ ፎቶ ኦፕ ሆነ፡፡ እስከነጭራሹ አሁን በብአዴን እና ኦህዴድ መካከል ያለው አለመተማመመን በበእአዴን እና ወያኔ መካከል ካለው ያላነሰ ነው፡፡ ይህ አገራዊ አደጋ መቀልበስ አለበት፡፡

ለእነ ገዱ እና ደመቀ አዲሱ አጋጣሚ

ለማ መገርሳ እና ጠ/ሚ ዓብይን እጅግ ተቀባይነት ያለው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ የመሆን እናም በሰፊው ኢትዮጵያን የመግዛት አጋጣሚ አምልጣቸዋለች፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቢሉም የሚያምናቸው አምብዛም መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጠቅሎ የመግዛት አጋጣሚ አሁን የእነ ገዱን እና ደመቀን በር ደግሞ እያንኳኳች ነው፡፡ ይህን አጋጣሚ ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀመም ፓርቲውን ከአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲነት ወደ ቀድሞው ኢህዴን ወይንም ሌላ ብቻ ኢትዮጵያዊ ስም እና አወቃቀር ወዳለው ፓርቲነት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያ ግን እነ ገዱ በር ላይ ያለችው አጋጣሚ የእነ ለማ በር ጋር ከነበረችው አጋጣሚ ጋር ሙሉ በሙሉ አንድ አይነት አለመሆኗን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ቲም ለማ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሲጠጋ ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኛም ከብአዴንም፤ ከአማራ ብሔርተኞችም፤ ከኦሮሞ ብሔርተኞችም ይሁንታን አግኝቶ ከወያኔ ግን ተቃውሞ ነበረበት፡፡ አሁን ግን ብአዴን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ለመሸጋጋር ቢፈልግ ከጠ/ሚ ዓብይ መራሹ ኦህዴድም፤ ከኦሮሞ ብሔርተኞችም፤ ከወያኔም ተቃውሞ ሲገጥመው ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኞች እና ከአማራ ብሔርተኞች ብቻ ድጋፍ ያገኛል፡፡ በተጨማሪም የእነ ጠ/ሚ ዓብይ እና ለማ ወቅታዊ ሹቀት ከኢህአዴግ የሚመጣን ሰው በሙሉ ለማመን ሌላው ሰው እየቸገረው እንደሆነ መገንዘብ እናም ለዚህ የተዓማኒነት ችግር ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መምጣት ብአዴንን እንዲህ ከጠንካራ ሓይሎች ጋር የሚያላትመው፤ በርካታ ተግዳሮቶች የሚገጥሙትም ከሆነ ለምን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ይምጣ? ምክንያቱም ኢትዮጵዊ ብሔርተኛ በመሆን የሚገኘው እድል ከተግዳሮቶ እጅግ እጅግ እጅግ ስለሚበልጥ፡፡
ጠ/ሚ ዓብይ ታሪካዊ የሚባል ቅቡልነት አግኝቶ የነበረው መልኩ ስላማረ፤ ትንቢት ስለተነገረለት፤ የሚገርም አይምሮ ስላለው ወዘተ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ዓለ ኢትዮጵያውያን ወደቁለት፡፡ ኢትዮጵያ ብሎ መቀጠል አልቻለም ወደቀ፡፡ ይሄው ነው!!! ኢትዮጵያን ብሎ የተነሳ አማራ ሆነ ኦሮሞ ትግሬ ሆነ ጉራጌ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱንም እስካስመሰከረ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያን ይማርካል፡፡ ይህ ማለት ግን ስራው እና ምርጫው እራሱ ቀላል ነው ማለት አይደለም፡፡

ከብአዴን ወደ ኢህዴን አንዴት?

የብአዴን አመመራሮች ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሊሸጋገሩ ሲሉ በክልላቸውም በመላው ዓለመምም ካለው የአማራ ብሔርተኝነት ንቅናቄ ጋር ሳይጣሉ መሆን አለበት፡፡ የአማራውንም ሆነ የሌላውን ኢትዮጵያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያዊውም አማራዊውም አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ በግልጽ በጉባኤዎች በመወያየት ከሕዝባቸው አባላቶቻቸው እና ከብአዴን ውጭ ካሉ አማራ ብሄርተኞች ጋር መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ ላይ፤ ሕገመንግስት ላይ፤ የአማራ ክልልም ሆነ በአጠቃላይ ኤትኒክ ፌደራሊዝሙ ላይ መወያየት የግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ ወደፊት የአማራ ክልልንም ሆነ ሌሎች በጎጥ የተደራጁ ክልልሎችን ማፍረስ የአዲሱ ኢህዴን የፖለቲካ ፕሮግራም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሌሎች ጎጦች ክልላቸውን እስከያዙ ድረስ የአማራ ክልል አስፈላጊነት ላይ መተማመን ሊደረስ ይችላል፡፡ ወይንም የአማራ ክልልን አዲሱ ኢህዴን እና አማራ ብሔርተኞች/ አብኖች እናፍርሰው አአናፍርሰው ብለው በግልጽ ዩኒላተራል ውሳኔ ስለመውሰድ መወያየት አማራ ክልልን ሊፈርሱትም ይችላሉ፡፡ ይህን የሚያድጉ ከሆነ የእያንዳንዳቸው አወቃቀር እንዴት አንደሚሆን መወያየት መመካከር፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብአዴን እራሱን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝት ሲያዋቅር ምርጫ የሚመጣ ከሆነ የምርጫ ወረዳዎችን ከእነ አብን ጋር እንዴት ሊከፋፈል እንደሚችል የሚወያይባቸው መዋቅሮችንን ማቋቋም፡፡ እነ ገዱ ይህን ሲጠነስሱ ከጀርባ ዞሮ ለኦህዴድ አዲሱ ብአዴን ሆኜ ላገልግል ቅብጥርስዮ የሚል አሸርጋጅ አለመኖን ማጣራት እንዳይኖርም መስራት፡፡

አዲስ የሚዋቀረው የኢትዮጵያ ብሔርተኛ አደረጃጀት የሚፈጥረው አንዱ ምርጥ አጋጣሚ ከዚህ በፊት የብአዴን አባል ያልነበሩ አባላትን፤ ካድሬ ለመሆን የሚችሉ አመራሮችን፤ ምሁራንን፤ ቴክኖክራቶችን ከአማራ ብሔርም ከሌሎች ብሔሮችም ለመሳብ መቻሉ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን እነማን ከድሮው ብአዴን ወደ አዲሱ ኢህዴን ይቀጥላሉ፤ በምን መስፈርትት፤ እነማን ወደ አብን መዋቅር ይሸጋገራሉ አዲሶቹ አባላት፤ ካድሬዎች ምሁራን ቴክኖክራቶች ምን ያህል ይጠበቅባቸዋል የሚለው ላይ ያለመታከት መስራት፤ መከራከር፤ መደራደር ይጠይቃል፡፡ አዲስ ለመሆን በሚደረገው ሽግግር አዲሶቹንም ዋጋ የከፈሉ የጥንቶቹንም የማያስደስት መዋውር መስራት አያስፈልግም፡፡
እነ ጠ/ሚ ዓብይ፤ ጃዋር፤ ጋሼ ደብረጽዮን እንደለመደባቸው ነፍጠኖች ትምክሕተኞች ገለመሌ ይበሉ፡፡ የኢትዮጵያዊው ብሔርተኛ ግን ኢህዴንን እንደ አዲስ ሆ ብሎ ይቀበለዋል፡፡ ኢህዴን ጠንካራ ሆኖ እራሱን ለማስመስከር ብዙ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ይህን ካደረገ ቅንጅት በ97 ካስመዘገበው በላይ ውጤት በኢትዮጵያ የማስመዝገብ አጋጣሚው አለ፡፡ ኢዜማ የሚሉት ሙትቻ ፓርቲ አይደለም ከአዲስ አበባ ውጪ አዲስ አበባ ላይ በአብን ካልተጠለዘ ምናለ በሉኝ፡፡ ብአዴን እራሱን ወደ ኢህዴን ከቀየረ ግን አዲስ አበባን ብቻ አይደለም በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችም ከድሮም የጎጥፌደራሊዝም የደበረንን እኛን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ አቅጣጫ አስግቷቸው በጎጥ ፌደራሊዝሙ ላይ ጥርጣሬአቸው እየጨመረ የመጡትን የቀድሞ ጎጠኞችን ሁሉ ለመማረክ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጠ;ሚ ዓብይ እና አሽጋጆቹ ሙፓዎች (ሙትቻ ፓርቲዎች ) ላይ የበለጠ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጫና ማሳደርም ይቻለል፡፡
ኢህዴን ከመጣ በእጁ ክልል ያለው፤ በመላዉ ኢትዮጵያ ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ መዋቅር ያለው በፌደራል መስራቤቶች ሁሉ የተዘረጋ መስመር ያለው ድርጅት ስለሚሆን ጉዞውን በከባድ አድቫንቴጅ ይጀምራል፡፡ ጉዞውን የሚጀምረው አንደ ቅንጅት ከውጭ ወደ ውስጥ ለመግባት ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጭ ሪፎርም ለማድረግ ስለሚሆን በጣም ብዙ ነገር ይቀልለታል፡፡

መከርን መከርን መከርን

የኦህዴድ ፕሮቴስት እንደተቀጣጠለ ከመንጋው ጋር እጄን ቀስሬ ከመስቀል መታቀብ ብቻ አይደለም ወያኔ ወሬ ትቶ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ሆኖ ኦህዴድን አንዲጠራርገው መከርኩ ሲያቅማማ እድል አመለጠው፡፡ ጠ/ሚ ዓብይ ስልጣን እንደያዘ ኢሕአዴግን ወደ አንድ ፓርቲ ቀይሮ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ እንዲያደርገው ስልጣኑንም እንዲያጸና፤ ኢትዮጵያንም አንዲታደግ መከርን እሱ ምን በወጣው ፎቶ ይነሳል፤ ችግኝ ይተክላል ወዘተ፡፡ እስቲ እናንተ ደሞ ትሰሙ እንደው አሁን መከርን፡፡

ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!!!