ኢትዮጵያዊ የሁለትዮሽ ፌደራሊዝም (Ethiopian Dual Federalism )   ለብሄራዊ አንድነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለባህል ጥበቃና ለብልጽግና

1 min read
2

Ethiopian Dual Federalism (EDF)

ለ8ኛው የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ የቀረበ ጥናታዊ ጽሁፍ
አቅራቢ ገለታው ዘለቀ
ሰኔ 2012
ባህር ዳር

ረቂቅ (Abstract)

በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦች የተለያየ መተሳሰሪያ መርሆ እየፈጠሩ ሲኖሩ  የነዚህ ሃገረ ብሄር ትስስር መርሆዎች ጥንካሬ ከሶስት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል። አንደኛው ከመተሳሰሪያ መርሆዎቹ ጥራት (good qualities of the governing principles) እንጻር ሲሆን ሁለተኛ የመተሳሰሪያ መርሆዎቹ በዚያ ሃገረ ብሄር ውስጥ ያላቸው ክብርና ልእልና (Respect and Sovereignty ) ነው። ሶስተኛው ደግሞ የሲስተም ምርጥነት ነው። እነዚህ ሶስት ጉዳዮች ለአንድ ሃገረ ብሄርና መንግስት ጥንካሬ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።

በዚህ ጽሁፍ ስር የሚቀርበው ቁም ነገር በሁለቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። እነዚህም ኣንደኛ ጥራት ያለው የመተሳሰሪያ መርሆዎችን ለመፍጠርና አሁን ያሉትን የመተሳሰሪያ መርሆዎች ለማሻሻል የሚያስችል ኣሳብ ማቅረብ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ምቹ የሆነ ሲስተም ለማሳየት ነው። በመሆኑም በዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ስር በትኩረት የምናየው ኣሳብ ኣንደኛ የመተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን ለማሻሻል የፈደራል ስርዓቱን ባለሁለት ክንፍ (Two wings Federal System) ማድረግ ወይም የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት መፍጠር ሲሆን ይህ ሲስተም የሚመሰረተው በዜጎች ሁሉ ሃገራዊ ቃል ኪዳን ላይ ነው። በስምምነት ላይ ነው። ሁለቱ የፌደራል ስርዓቶች የባህል ፌደራልና የዜጎች ፌደራል ስቴት የሚባሉ ሲሆን እነዚህ ስቴቶች ባህልንና ፖለቲካን ለይተን የብሄር ማንነትንና የሃገረ ብሄር ማንነትን ሳናጋጭ ማስተናገድ ያስችሉናል። ይህ የፌደራል ስርዓት ኢትዮጵያዊ የፌደራል ስርዓት ተብሏል። በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሃገረ ብሄር ግንባታው የሚያስፈልገውን  መስዋእትነት ለመክፈልና የጋራውን ቤት የማይፈርስ ኣድርጎ ለመገንባት ሁለት ቃል ኪዳኖች ያደጋሉ። አንደኛው ቃል ኪዳን በሄራ (Constitution) የማይገለጹ ነገር ግን የሃገረ ብሄር ዋና መተሳሰሪያ የሆኑ ኤለመንቶችን በማውጣት  ዶግማዊ ቃል ኪዳን ማድረግ ነው። ሁለተኛው ቃል ኪዳን ደግሞ ሄራ ወይም ህገ መንግስት ሲሆን ይህ ህገ መንግስት የሃገሪቱ የህግ መሰረት ሆኖ ይኖራል። በነዚህ ጉልህ የሃገረ ብሄር ግንባታ መርሆዎች ዙሪያ ይህ ጽሁፍ ያትታል። ጽሁፉ ኢትዮጵያውያን በመስዋእትነት ላይ የመተመስረተ የማይከፋፈል ማንነት የሚፈጥሩበትን አቅጣጫ የሚያሳይ ሲሆን  ሃገር በቀል በሆነ የመተሳሰሪያ መርሆዎችን ያቀረበ ጽሁፍ ነው።

ቢጋር

ረቂቅ (Abstract)

 1. የ EDF አምክህኖቶች
  • የብሄሮች ሥነ-ኑባሬ (Ontology)
  • የዴሞክራሲ መርሆዎች
  • ጽንፈኝነት
  • የዓለም ህዝብ ግንዛቤ
  • ሃይማኖት
  • መተማመን፣ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና
  • ባህልን ማስመለስ (Restoration of culture and heritages)
  • የፖለቲካ ስበት ህግ (Political gravitational force)
 2. የ EDF ስቴት ቅርጽና ይዘት
  • የባህል ፌደራል ስቴት
  • የዜጎች የፌደራል ስቴት
 3. የEDF መሰረቶች
  • ዶግማዊ ኪዳን
  • ሄራ
 4. የ EDF ጠቀሜታ
  • ባህልና ቅርስን ለመንከባከብ
  • ለብሄራዊ ኣንድነት
  • ለሰላም ግጭትን ለማስወገድና ለሁለንተናዊ ልማት
  • መተማመን እንዳይተን ለማድረግ (prevent trust evaporation)

ማጠቃለያ

መግቢያ

የሰው ልጅ ለኑሮው ሲል ብዙ ስብስቦችን እየፈጠረ ይኖራል። ከሚፈጥራቸው ስብስቦች መካከል ትልቁ ስብስብ ሃገር ሲሆን ለዚህ ስብስቡ የተለያየ መተሳሰሪያ መርሆዎችን (organizing principles) ያዘጋጃል። መተሳሰሪያ መርሆ ስንል በዚህ አገባብ ዋና ዋና ሃገራዊ የሆኑ ገዢ ሃሳቦችን የሚመለከት ነው። አንድን ማህበረሰብ አንድ የሚያደርገው ኣንዱ ዋና ጉዳይ በአንድ የመግቢያና የመውጫ ስምምነትና ህግጋት ስር መስፈሩ ነው።  በዚህ መሰረት ኣንድ ሃገር ዜጋውንና ቡድኖቹን የሚያያይዝ የሚያስተሳስር መርሆዎች ይኖሩታል። በዚህ መሰረት ብሄር ከብሄር እንዴት ባለ ትስስር የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኑሯቸውን ያካሂዳሉ? የፌደራል መንግስትና የፖለቲካ ዮኒቶች እንዴት ይያያዛሉ? ኢትዮጵያዊነትና አካባቢያዊ ማንነት ወይም ሌሎች ማንነቶች በምን ገዢ ህግ ይያያዛሉ? የሚለውን መሰረታዊ የሃገር ኣስተዳደር ጉዳይ ይመለከታል። ለነዚህ ጉዳዮች የምንስማማበት መተሳሰሪያ ከፍተኛ መርህ (High  Governing organizing principles)  እየተዘረዘረ ወደ ህግና ፖሊሲ ኣሰራር ይወርድና ሃገሪቱን ያስተዳድራል ማለት ነው።

ሃገር የሚባለው ትልቅ ጠገግ ሲዋቀር የሚታሰብ ነገር ያለ ሲሆን ይህም ሃገሩ ሲዋቀር ወይም ሲታነጽ (Reinvent) ሲደረግ የተፈጥሮ ስብስቦችና ግለሰቦች ይታሰባሉ። ትልቁ ጠገግ እነዚህን የተፈጥሮ ስብስቦች ሳይጨፈልቅና ሳያጠፋ የሚመሰረት መሆን ኣለበት። ጠገጉ የግለሰቦችን ግላዊና ማህበራዊ ተፈጥሮ የሚጠብቅ መሆን ኣለበት። በመሆኑም የመተሳሰሪያ መርሆዎች ሲቀረጹ የቡድንና የግለሰብን መብቶች ቀድሞ ያገናዘበ ውቅር ያስፈልጋል ማለት ነው።  የሰው ልጅ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኖ ደግሞ የአንድ ሃገር ሰው ሲሆን ጊዜ የሃገረ ብሄር ግንባታ ኣሳብ የፖለቲካ ምሁራንን ምርምር ጠየቀ። ዛሬ በዓለም ላይ ወደ  6,500 የሚሆን ቋንቋ የሚናገር ማህበረሰብ ወይም በእኛ አጠራር ብሄር ይኖራል። ይህንን ቁጥር 195  ለሚሆኑ የዓለም ሃገራት ብናካፍለው  በአማካይ  33.3  የሚሆኑ ብሄሮች በአንድ የፖለቲካ ጥላ ስር ወይም ሃገር ስር አንድ ላይ ሆነው ሲኖሩ በአንድ በኩል የባህል ማንነታቸው እንዲጠበቅ በሌላ በኩል ሃገረ ብሄር ማንነታቸው ጠንካራ ሆኖ እንዲኖር ይፈልጋሉ። ስለሆነም የየሃገሩ ህዝቦች ይህንን መሰረታዊ ፍላጎት የሚመልስ የመንግስት ሲስተም ይሻሉ ማለት ነው። የፌደራል ስርዓትን የሚከተሉ ሃገራትም ይህንን መሰረታዊ ፍላጎት እንዴት ሊያሟሉ እንደሚችሉ ማሰብ ሊኖርባቸው ነው። እነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በጋራው ቤታቸው የሚኖረው ፍላጎት መከበር ይኖርበታል። ዴሞክራሲ ማለትም ይሄ ነው። የቡድኖችን ባህላዊ ማንነት ቋንቋቸውን መንከባከብ የዴሞክራሲ መርሆ ነው።  እነዚህ ብዙህ ሆነው የሚኖሩ ቡድኖችና ዜጎች ሃገረ ብሄር ሲመሰርቱ በአንድ በኩል ማንነትን የሚጠብቅ በሌላ በኩል ለሃገረ ብሄር ማንነት ምሰሶ የሆኑትን ነገሮች በጋራ ለማቆም መስማማት አለባቸው፣ መስዋእትነት መክልፈል ኣለባቸው።

መተሳሰሪያ መርሆ ስንል በዚህ አገባብ ዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። በዚህ መሰረት ብሄር ከብሄር እንዴት ባለ ትስስር የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኑሯቸውን ያካሂዳሉ? የፌደራል መንግስትና የፖለቲካ ዮኒቶች እንዴት ይያያዛሉ? ኢትዮጵያዊነትና አካባቢያዊ ማንነት ወይም ሌሎች ማንነቶች በምን ገዢ ህግ ይያያዛሉ? የሚለው ጥያቄ በጣም ወሳኝ ነው። ለነዚህ ጉዳዮች የምንስማማበት መተሳሰሪያ ከፍተኛ መርህ እየተዘረዘረ ወደ ህግና ፖሊሲ ኣሰራር ይወርዳና ሃገሪቱን ያስተዳድራል ማለት ነው።

ታዲያ የየሃገራቱ ጥንካሬ ምን ያህል የተሻለ ሲስተም አላቸው? ምን ያህል ጥራት ያሏቸው መተሳሰሪያ መርሆዎች አሏቸው? ምን ያህል የመተሳሰሪያ መርሆዎች ክብርና ልእልና አለ? በሚለው ልክ ሊለካ ይችላል። እነዚህ ሶስት የሃገር ጥንካሬ መሰረቶች ሳይነጣጥሉ በአንድ ጊዜ መታየት አለባቸው። ጥራት ያላቸው መተሳሰሪያ መርሆዎችን (organizing principles) ፈጥረን ነገር ግን እነዚህ መርሆዎች ህብረተሰቡ፣ ዳኞች፣ አስፈጻሚዎች የማይሞቱላቸው በተግባር ክብር የተነፈጉ ከሆነና በተለያየ ሃይል የሚገሰሱና ልእልና የሌላቸው ከሆነ የዚያ ሃገረ ብሄር ትስስር ነገር ችግር ይኖረዋል። በሌላ በኩል ጥሩ ህግ ኣስከባሪ ኖሮ፣ ጥሩ ዳኛ ኖሮ ነገር ግን መተሳሰሪያዎቻችን ጥራት የሚጎድላቸው ከሆነ በሚገባ ያልተጠኑ ከሆነ ደግሞ እድገታችንን ይጎትታል ሄዶ ሄዶ ሃገረ ብሄሩን ሊያፈርስም ይችላል። ሶስተኛው ደግሞ ዴሞክራሲን፣ መልካም ኣስተዳደርን ያሉንን መተሳሰሪያ መርሆዎች ሁሉ የሚያንሸራሽር ቧንቧ ወይም ዲቫይስ ደግሞ ሲስተም  ነው። የተመቸ ሲስተም ካልፈጠርን የቱንም ያህል ጥራት ያለው መርሆ ብንቀርጽ፣ የቱንም ያህል ጥሩ ዳኛ ቢኖረን እንደምንፈልገው ልንራመድ ኣንችልም። ስለዚህ ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ እድገት አንደኛ የመርህ ጥራት፣ ሁለተኛ ቁርጠኝነት፣ ሶስተኛ የጸዳ ሲስተም የተቋማት ግንባታ ያስፈልጋል።

ሃገራችን በተለይ በአሁኑ ሰዓት በሽግግር ላይ ያለች ሲሆን ይህ የሽግግር ጊዜ እስከዛሬ ገዢ የሆኑትን የመተሳሰሪያ መርሆዎች የምንገመግምበት  የጽሞና ጊዜ  ብሎም እነዚህን መርሆዎች ከዴሞክራሲና ከኢትዮጵያውያን ብሄሮች ስነ ኑባሬ (ontology) አንጻር አሻሽለን ሃገራችንን ወደ ተሻለ ስርዓት የምናሻግርበት በመሆኑ ይህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ግንባታ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ለቅርስ ጥበቃ፣ ለሰላምና ለልማት ጉልህ አስተዋጾ ይኖረዋል። አማራጭ ሮድ ማፕ ይሆናል።

በዚህ ጽሁፍ ስር የምናነሳው ሃሳብ ታዲያ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የመተሳሰሪያ መርሆዎች ለማሻሻል እንዲቻል የተሻለ መተሳሰሪያ መርሆዎችን ለማቅረብ ነው። በዚህ መሰረት በዚህ ጽሁፍ ስር አራት ዋና ዋና የመተሳሰሪያ መርሆዎችን እንጠቁማለን። አንደኛው የመተሳሰሪያ መርሆ ሃገራዊ ኣዲስ ኪዳን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሄራ ነው። በሶስተኛ ደረጃ የሚነሳው የመተሳሰሪያ መርሆና የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረት ደግሞ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ግንባታ ነው። አራተኛው የመተሳሰሪያ መርሆ የቋንቋ ጉዳይ ሲሆን በዚህ ጽሁፍ በጥቂቱ ይጠቀሳል። ከፍ ሲል እንዳልነው ጽሁፉ የሚያተኩረው የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ግንባታውን በሚመለከት ሲሆን ይህ የፌደራል ስርዓት የብሄር የባህል ፌደራል ስቴት ምስረታንና የዜጎች ፌደራል ስቴት ምስረታን ይመለከታል። ይህ ስርዓት ለሃገራችን ኢትዮጵያ የብሄር ጥያቄና ለማንነቶች ኣያያዝ ብሎም ለሁለንተናዊ ልማት ተመራጭ የሆነ ሲስተም እንደሆነ ጸሃፊው ያምናል። በዚህ ጽሁፍ ስር የምንነጋገረው በዚሁ ዙሪያ ነው።

 1. የ EDF አምክህኖት

በዓለም ላይ ካሉ ዋና ዋና የሃገር መተሳሰሪያ መርሆዎች ውስጥ የአሃዳዊ ስርዓት፣ የፌደራል ስርዓትና የኮንፌደሬሽን ስርዓት የተለመዱ ናቸው። ርግጥ ነው እጅግ ብዙ የዓለም ሃገራት የመረጡት የአሃዳዊና የፌደራል ስርዓትን ነው። ይሁን እንጂ አሃዳዊም ይሁን የፌደራል ስርዓትን ሲመርጡ ሃገራት ሁሉ ከሃገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የፌደራል ስርዓቱንም ሆነ የአሃዳዊ ስርዓቱን እያሻሻሉ ይኖራሉ። ለዚህ ነው በዓለም ላይ ያሉ የፌደራል ስርዓትም ሆኑ የአሃዳዊ ስርዓት ተከታይ ሃገሮች ከትንሽ እስከ ትልቅ ልዩነት የሚለያዩት።

ወደ ሃገራችን ስንመጣ ከአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ ወዲህ ኢትዮጵያ ልትከተለው የሚገባው የመተሳሰሪያ መርህ የፌደራል ስርዓት መሆኑ ሰፊ ስምምነት ቢኖርም ነገር ግን ይህ የፌደራል ስርዓት ኢትዮጵያዊ ቀለም ይዞ እንዴት ሊቀረጽ እንደሚገባው፣ እንዴት የብሄር ማንነትንና ሃገረ ብሄር ማንነትን አስተሳስሮ ማኖር እንደሚገባው ጥያቄዎች ይነሳሉ። አሁን ያሉትን ገዢ መተሳሰሪያ መርሆዎች ስናይ ብዙዎቹን ስብስቦች የፖለቲካ መደራጃ የማድረግ ኣቅጣጫችንንና ራስን በራስ ማስተዳደር ትርጉማችን ከፍተኛ ቅሚያን ያመጡና መተማመንን የጎዱ መተሳሰሪያ መርሆዎች ሆነው እናያለን። ከራስ በራስ መተሳሰሪያ መርሆዎቻችን በተጨማሪ ሃገረ ብሄራችንን ፈራሽ ኣድርገን በዚህ ፈራሽ ቤት ውስጥ መተሳሰር መሞክራችን ዘላቂ መሃላ ውስጥ ባለመግባታችን ብዙ ችግሮች ውስጥ ከቶናል። በፈራሽ ቤት ውስጥ እንዴት ነው የምንተሳሰረው? የሚለው ጥያቄ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወታችንን ያመሳቅላል። ዘላቂ የሆነ ትስስር ውስጥ ያልገባ ሃገራዊ ስብስብ ደግሞ ኔሽን ቢዩልዲንግ ሊያደርግ አይችልም። ታዲያ እነዚህ መተሳሰሪያ መርሆዎች ችግር ካመረቱብን እንዴት ነው የተሻለ መርሆዎች የምንቀርጸው? የሚለው ዋና የሽግግር ጥያቄ ለዚህ ለሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት መፍትሄ መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ከዚህ ጥያቄ በሁዋላ የዚህ ሃሳብ አመንጪ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እያነሳ መላ አፈላልጓል።

አንድ ሃገራዊ መተሳሰሪያ መርህ ሲቀረጽ ከሚከተሉት ስድስት ጉዳዮች ኣንጻር መገምገም ስለሚኖርበት ለሁለትዮሽ የፈደራል ስርዓቱ እነዚህ ጉዳዮች መነሻ ሆነዋል።

 • የብሄሮች ሥነ-ኑባሬ (ontology)

ብሄሮች ያላቸው እሴትና ተፈጥሮ ለጋራው ቤታችን ግንባታ ለሃገረ ብሄር ግንባታና ለፌደራል ስርዓታችን ወይም ለዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎቻችን ያላቸውን ባህርያት ማጥናት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ የብሄር ፖለቲካና የብሄር ፌደራል ስርዓት የብሄሮችን ስነ-ኑባሬ የሰበረ ሆኖ እናያለን። ብሄሮች በየባህሎቻቸው ውስጥ የሚያደንቁትና ከፍ አድርገው የያዙት እሴት ኣብሮነት፣ ማካፈል፣ መከባበር፣ መተማመን ነው። የተፈጠረው የፌደራል ሲስተምና የብሄር ፖለቲካው ግን ይህንን የሚሰብር ኤለመንት በብዛት የያዘ በመሆኑ በዚህ በኩል የመተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን እንድንመረምር ማድረጉ ከብሄሮች ስነ-ኑባሬ  ጋር የሚሄድ መርሆዎችን ማፍለቅ ኣስፈላጊ መሆኑ ኣንዱ የዚህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ጽንሰ ሃሳብ መነሻ ነው።

 • የዴሞክራሲ መርሆዎች

መርሆዎቻችን ከዴሞክራሲ መርሆዎች ኣንጻር ሲታዩ የዴሞክራሲ መርሆዎችን የሚጥሱ ኤለመንቶች በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ መኖራቸው ነው። ዴሞክራሲ ኣብሮነትን፣ ህብረትን የሚያበረታታ ሲሆን የገባንበት መርሆ ግን ይህንን የሚሰብር ሆኖ በብዙ መንገድ ይገለጻል። ኣግላይና ገፊ የፖለቲካ ዩኒቶችን የፈጠረ ስርዓት በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል በሚል ነው ይህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት የታሰበው።

 • አርበኝነት (patriotism)

በአንድ ሃገር ጥላ ስር ያሉ ዜጎች የአርበኝነት ስሜታቸውን በተገቢው መንገድ መግለጽ አለባቸው። የብሄር ኣርበኝነትና ብሄራዊ ኣርበኝነት ስሜትን ከተጫነውና የብሄር አርበኝኘት (ethnic patriotism) ከገነነ ጽንፈኝነት ያድጋል ዜሎትሪ (zealotry) ወይም የአካባቢ ተቆርቋሪነት ኮሙኒኬሽናችንን ያጠፋል ።  በአዳራሹ ቤታችን ውስጥ የብሄር ኣርበኝነት ጡንቻው ከበረታና ብሄራዊ ኣርበኝነት ስሜት ከደከመ ቤታችን ውስጥ መግባባት ኣይታሰብም። ብሽሽቅና ስድብ አዳራሹን ያምሰዋል። የረጋ ቤት ኣይኖረንም። ለጋራ ጉዳይ ኣንሰራም። ስለዚህ ይህን የአርበኝነት ስሜት በተገቢው መንገድ ለመግለጽ ጥራት ያለውና ተገቢ የሆነ ሲስትም መቅረጽ ይገባል። የአካባቢና የብሄራዊ ኣርበኝነት ስሜቶቻችንን የምንወጣበት መስመር መፍጠር ተገቢ ነው። ፖለቲካችን በብሄርና በብሄራዊ ኣንድነት አደረጃጀት ስም ከፍተኛ ልዩነት ፈጥሮ ጽንፈኝነትን እያረባ ነው። ይህ የሁለትዮሽ የፈደራል ስርዓት መነሻ እነዚህን ሁለት ጎራዎች በማዳመጥ ከሁለቱም ያሉትን እውነቶች በሰከነ ሁኔታ በመውሰድ የተፈጠረ ቤት ለማዋቀር ነው።

 • የዓለም እውቀት ( World’s perception about our organizing principles)

ኣራተኛው መነሻ ያለንባቸው የመተሳሰሪያ መርሆዎች ከውጭ ወደ ውስጥ ሲታዪ ዓለም እንዴት ይረዳቸዋል? የሚል ጥያቄን ያነሳል። በብዙ ሃገራት የብሄር ፖለቲካና ፌደራሊዝም የተከለከለ ነው። የፖለቲካ ሳይቲስቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተመራማሪዎች ሁሉ የመንነት ፖለቲካን በሰፊውና በመረረ ሁኔታ ይነቅፋሉ። ይህ የዓለም ህዝብ ለብሄር ፖለቲካና ፌደራሊዝም ያለውን መረዳት (perception) ያሳያል:: ሃገራችን በዓለም ስትኖር ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ለዓለም ኣቀፍ ግንኙነቷም ስትል የመርህ ማሻሻሻያ ማድረግ ስላለባት ይህ የሁለትዮሽ ስርዓት ታስቧል።

 • ሃይማኖት

የአለም ኢኮኖሚክ ፎርም ከሶስት ዓመታት በፊት Pew የተባለ የጥናት ተቋም ያወጣውን ምርምር መሰረት ኣድርጎ 98% ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት እጅግ ጠቃሚ የህይወታቸው ክፍል እንደሆነ ያምናሉ ብሏል። ይህ አሃዝ ኢትዮጵያን ከተጠኑት የዓለም ሃገራት 1ኛ ያደርጋታል። ይህን ዓይነት ማህበረሰብ የሚያስተዳደር መንግስት የህዝቡን ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚሰብር ሲስተም ሊዘረጋ ኣይችልም። የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች አይሁዳውያንና ሙስሊሞች በሃይማኖታቸው ውስጥ ያሉ አብሮ የመኖር፣ የመከባበር የመካፈል እሴቶቻቸውን የሚጋፋ ሲስተም ሁል ጊዜም የህዝብ አመጽ (resistance) አያጣውምና ይህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ይህንን ያገናዘበ ነው። አንዳንዱ ሰው የብሄር ፖለቲካውን የጠላው የብሄር ፖለቲካውን ከፖለቲካ ትምህርት አንጻር የመገምገም ብቃት ኖሮት ሳይሆን ነገር ግን የብሄር ፖለቲካ ያመጣቸው ተጽእኖዎች የሃይማኖቱን እሴቶች ሲጋፋበት በማየቱ ነው። ይህ የመረረ ስሜት ከዚህም ይመነጫል።

 • መተማመን፣ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና

ሲስተም ሁሉ ለእድገትና ብልጽግና የሚመች ካልሆነ ከድህነት መውጣት ኣይቻልም። በመሆኑም የዚህ የፌደራል ስርዓት ዋና ኣንዱ ዓጀንዳ ለእድገት ምቹ ሲስተም መፍጠር ነው። ያሉንን ተጨባጭ የሁኑና ያልሆኑ ሃብቶች ኢንቨስት በማድረግ የተሻለ ልማት ለማምጣት ጥሩ ሲስተም ያስፈልጋል። ጥሩ ሲስተም ከሌለንና የተሻለ መተሳሰሪያ መርህ ከሌለን የረጋ ሃገር መስርተን ወደ ልማት ማዘንበል ኣንችልም። በተፈጥሮ ሃብትና በድንበር ጥያቄ ቡድኖች እርስ በርስ ከተያያዙ ልማት ኣይመጣምና። ስለሆነም ለእድገት ምቹ የሆነ ሲስተምና ዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎችን ለመፍጠር ነው የአዲስ ሃገራዊ ኪዳኑና የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ አሳብ የቀረበው። በሌላ በኩል ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት ታጥቀን እንዳንሰራ ሰላምና መተማመን ወሳኝ ነው። የማይተማመንና ግጭት የበዛበት ማህበር ከድህነት አይወጣም ብቻ ሳይሆን በሆነ አጋጣሚ ሃብት ቢያገኝም እንኳን ሃብቱን ሊጠቀምበት ኣይችለም። በመሆኑም ለአንድ ሃገር ሰላም የሚያመጣ ሲስተም መፍጠርና ብሄራዊ መግባባትን እርቅን የሚያመጣ መርሆ መቅረጽ ዋና ነገር ነው።  እንዴት ሰላምን እንደምናሰፍን ልዩ ልዩ ጥበቦች በየባህሎቻችን ውስጥ ኣሉ። ስለሆነም ይህንን ጥበብ ወደ ገበያ ማውጣትና ለሰላምና ለብሄራዊ መግባባት መስራት ያስፈልጋል። አንዱ የዚህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ኣጀንዳ በየባህሉ የተደበቁትን የግጭት ኣፈታት ዘዴዎች ከፍ ኣድርጎ በማውጣት ለሃገር ሰላም መሳሪያ ኣድርጎ መጠቀም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መተማመን በከፍተኛ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተነነ ስለሆነ ይህንን ለመቀልበስ መተማመንን ለማምጣት ይህ የጋራው ቃል ኪዳንና የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ መላ ይሆናሉ።

 • ባህልን መጠበቅና ማስመለስ (Preservation and Restoration of cultural heritages)

ኢትዮጵያውያን ባለፉት ጊዚያት በተለይም በሶሻሊዝም ጊዜ እጅግ የሚጠቅሙንን እሴቶች በጎጂ ባህል ስም ኣጥተናል። የተሻለ ባህል ኣጠባባቅ ዘዴ ስላልነበረን ብዙ ባህሎቻችን ተረስተዋል። ኣሁንም ኣደጋ ላይ ናቸው። ስለዚህ የጠፉትን ለማስመለስ፣ ያሉትን ባህሎቻችንን ለመጠበቅ የሚያስችል ሲስተም መፍጠር ኣንዱ ዋና የዚህ ስርዓት መነሻ ነው። ባህሉን ያጣ ማህበረሰብ ሁል ጊዜም ሙሉነት ኣይሰማውም። የቱንም ያህል አዳዲስ ነገሮች ቢያይም ሊጥላቸው የማይገቡ እሴቶቹን ከጣለ ያ ማህበረሰብ ለማህበራዊ ቀውሶች ይዳረጋል። በትውልዶች መካከል ክፍተት ይኖራል። የሰው ልጅ የዛሬና የነገ ብቻ ሳይሆን የትናንትም ነውና እሴቶቹን ባህሉን መጠበቅ ሙሉ ያደርገዋል። የሚጠቅሙትን ዋና ዋና እሴቶች እየጣለ የሚሄድ ትውልድ በወደፊት እድገቱ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥርበታል። ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ታሪክ ባለቤት ስትሆን ይህን ያህል ዘመን የተከማቸ ግሩም ባህል ባለቤት ናት። ይህቺ ሃገር ታዲያ ያሏትን ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆኑ ባህሎቿን በሚገባ እምብዛም ኣልያዘችም። አንዴ በአሲምሌሽን፣ ኣንዴ በመለያየት ባህሎቿን ጎድታለች። አሁን ኣዲስ ስርዓት ያስፈልጋል። ባህሎቿን የምታስመልስበትና የምትጠብቅበት። ከአሲምሌሽን የሚያተርፍ ጥላ መስራት ኣለባት። ከመለያየት ኣውጥቶ በኢትዮጵያዊነት ኪዳን ስር የሚያሰባስብ ቃል ኪዳን ያስፈልጋል። ለዚህ ነው ይህ የሁልትዮሽ የፌደራል ስርዓት የሚያስፈልገን።

 • የፖለቲካ ስበት ህግ (Political gravitational force)

በፖለቲካ ዩኒቶቻችን መሃል የተቀመጠው የፖለቲካ ስብት (political gravitational force) ተመሳሳይነትን የሚስብ ሲሆን በአንጻሩ ልዩነትን የሚገፋ ሃይል ኣምርቷል። በአንድ የፖለቲካ ዩኒት ውስጥ ተመሳሳይነትን መሳብ ስንፈልግ የዘር ማጽዳትን በሌላ በኩል እየጋበዝን መሆኑ ነው። ብዙህ  በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የስበት ህግ ማኖሩ ግጭትና መፈናቀል ከማምረቱም በላይ ወደፊት የረጋ ሃገር መስርቶ ለመኖር አያስችልም። ሃገርን የሚያፈርስ እምቅ ሃይል  በውስጡ የያዘ መተሳሰሪያ መርህ በመሆኑ ይህንን ለማሻሻል አዲስ ሃሳብ መምጣት ኣለበት። በመሆኑም የዚህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት መነሻ አንድም የስበት ህጎቻችንን የሚያሻሽል መርህ ለመቅረጽ ነው።

በአጠቃላይ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት በኢትዮጵያ የተነሳባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ከፍ ሲል የተነሱት ጉዳዮች ሲሆኑ ዓላማውም እነዚህን ችግሮች ለማሻሻልና የተረጋጋ ስርዓት መፍጠር ነው። ይህ ስርዓት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ የፌደራል ስርዓት ተብሏል። የፌደራል ስርዓትን የሚያዳብር የስርዓት ዓይነት ነው።

ሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ማለት በአንድ በኩል የብሄር ባህላዊ ፈደራል ስቴት መፍጠር በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎች የፌደራል ስቴት መፍጠር ነው። አሁን እነዚህ ሁለት የፌደራል ስርዓቶች ምን እንደሚመስሉ ዝቅ ሲል እንወያይባቸው።

 1. የ EDF ቅርጽና ይዘት
 • የባህል ፌደራል ስቴት

የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስቴት ማለት ብሄሮች ማንነታቸውን በተለይም ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚጠብቁበት ስቴት ማለት ነው። ይህ ስቴት በመሬት ላይ የሚነበብ ወሰን አይኖረውም። የማይነበቡ ስቴቶችን ይፈጥራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች ሁሉ ይህ ስቴት ይኖራቸዋል። አመሰራረቱ በአንድ ዶግማዊ ቃል ኪዳንና ሄራ ስር የኢትዮጵያን የልጅነት ስልጣን በመቀዳጀት ነው። ኪትዮጵያውያን ኪዳን ስር የሚውል  እንደየባህሉና ወጉ ተወካይ የሚኖረው አንድ የባህል የፌደራል  አስተዳደር ይኖራል። ይህ ኣስተዳደር በስሩ ማለትም በየስቴቶቹ የሰላም ስራን፣ የባህል ጥበቃና ማስተማር ስራን፣ የኬር ቴከር ስራን፣ የሙዚየም ስራን፣ የሽምግልና ስራን እየሰራ ይኖራል። የብሄር ማንነት መገለጫ የሆኑትን ሁሉ እየተንከባከበና ብሄሮች ባህል እየተካፈሉ እንዲኖሩ ያደርጋል። የጠፉ ባህሎችን የማስመለስ ስራን ይሰራል። የተቆረጡ እሴቶቻችንን ይቀጥላል። ይህ ስቴት ባህልን ከማሳደግ በተጨማሪ የፍትህ ስርዓታችንን ለመደገፍ የሽምግልና ስራን ይሰራል። ግጭቶችን ለመፍታት ግንባር ቀደም ሆኖ የሚሰራ ሲሆን በዚህም ሃገራዊ መረጋጋትን ያመጣል። ተሰሚነት ያላቸውን ሽማግሌዎች ያመርታል። የብሄር ጥያቄ የተባለውን የባህል ኢእኩልነት ችግር ቀርፎ እኩልነትን ለማምጣት ያስችላል። ይህ የአርበኞች ቤት የፖለቲካ ቀውስ ሲመጣ የኬር ቴከር ስራን በመስራት ሃገርን ይጠብቃል። ተጨባጭ የሆኑና ያልሆኑ ባህሎችን በማሳደግ ለቱሪዝም እድገት ክፍተኛ ኣስተዋጾ ያደርጋል። የዚህ ፌደራል ስቴት ስራዎች በህገ መንግስት በግልጽ እንዲቀመጡ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ የፌደራል ስቴት መኖሩ የሀገራችንን ጽንፍ ፖለቲካ በማርገብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ለባህል ኣርበኞች ስልጣን ስለሚያካፍል የማንነት ፖለቲካ በሃገራችን እንዳይኖር ያደርጋል። ሃገራችንን በተሻለ መሰረት ላይ ለማቆም ያስችላል። በዚህ ስቴት ስር ከታቀፉ አባላት በሚገኝ ገቢና ከቱሪዝም በሚገኝ ገቢ መንግስቱን ይመራል ሃገሩን ያሳድጋል። ከዜጎች የፌደራል መንግስት ጋር አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮችና ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ተባብሮ ይሰራል። ምርጫ ሲመጣ የትዝብት ስራን ይሰራል።

 • የዜጎች የፌደራል ስቴት

የሁለትዮሽ የፌደራል ስቴት ኣሳብ አመጣጥ በተለይ ብዙህ ለሆነ ማህበረሰብ (plural society) የተሻለ የፌደራል ስርዓት ለመፍጠር ነው። በርግጥ ሃሳቡ ለብዙህ ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ነጠላ ለሆነ ህብረተሰብም ይሆናል። የፌደራል ስርዓት ባህልን ጠቃሚ እሴቶችን በጎኑ ይዞ እንዲራመድ የሚያደርግ ስርዓት በመሆኑ ለማንኛውም ሃገር ያገልግላል። ይሁን እንጂ በተለይ ብዙህ ለሆነ ማህበረሰብ የተለየ ጠቀሜታ የሚኖረው አንደኛ በቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ቡድኖች ሳይጨፈለቁ እንዲኖሩ፣ ሁለተኛ ባህላዊ እኩልነትን ለማምጣት ሶስተኛ ያለውን ከፍተኛ ባህላዊ ሃብት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ እጥፍ ድርብ ጥቅም ያለው ሲሆን በተለይ ለረጅም ጊዚያት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከባህላዊ ማንነት ጋር ተጣብቆ የቆየብን ስለሆነ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ይህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ግንባታ ልዩ ገጸበረከት አለው። በኢትዮጵያ  የፌደራል ስርዓታችን በማንነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ባህልና ፖለቲካ ተጣብቀው እንዲኖሩ ማድረጋችን ባህልን ራሱን ቀለሙን እያሳጣው መጥቷል። በርግጥ የምንከተለው የፌደራል ስርዓት ቀለሙን ያሳጣው ባህልን ብቻ ሳይሆን የፌደራል ስርዓትን ጽንሰ ሃሳብም ጭምር ነው። ስለዚህ በአንድ በኩል የባህል የፌደራል ስቴት ፈጥሮ በሌላ በኩል ግን የዜጎች ወይም በሌላ አነጋገር የሃገረ  ብሄር የፌደራል ስቴት ግንባታ ያስፈልጋል። እኛን ኢትዮጵያውያንን የሚያተሳስሩን ጉዳዮች ባህላዊ ጉዳዮች ብቻ ኣይደሉምና የፖለቲካ የኢኮኖሚ ጉዳዮቻችንን የሚመለከት የፌደራል ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል። ይህ የፌደራል ስርዓት ለአስተዳደርና ለእድገት እንደሚመች ኣድርጎ  የፖለቲካ ዩኒቶች የሚኖሩት ሲሆን በመሬት ላይ የሚነበብ ካርታዎችን ይሰራል። እነዚህ ካርታዎች ግን የስቴቶች ድንበሮች ሳይሆኑ ለአስተዳደር ያመች ዘንድ ነው። በዚህ መሰረት የፖለቲካ ዩኒቶችን ይቀርጻል። እነዚህ ዩኒቶች ታዲያ የስበት ህጎቻቸውን በተመሳሳይነት ላይ ኣያደርጉም። በመሆኑም የየስቴቶቹ ህገ መንግስታትና ሌሎች አነስተኛ ህጎችና ደምቦች ሁሉ ዜጎችን ሁሉ እኩል የሚስቡ እንዲሆኑ ማድረግ ኣንዱ ዋና ጉዳይ ነው። በአሁኑ ሰዓት ያለውን የፌደራል ስርዓታችንን ስናይ የክልሎች ህገ መንግስቶችና የፖለቲካ ትርክቶች ተመሳሳይነት የሚስቡ በመሆናቸው ልዩነትን መሸከም ኣቅቶናል። ይህ መለወጥ ኣለበት። በመሆኑም የሁለትዮሽ ስቴቶች ስንፈጥር ሁለቱም ስቴቶች ማለትም የብሄር ፌደራል ስቴቱም ሆነ የዜጎች የፌደራል ስቴቱ ዜጎችን ሁሉ ኣቃፊ ይሆናል። የብሄር ፌደራል ስቴቱ የዚያን ብሄር ባህልና ቋንቋ እስከለመደና ባህልህ ባህሌ ቋንቋህ ቋንቋየ ብሎ እስከኖረ ድረስ በዚያ ስቴት ውስጥ እኩል ሆኖ ይኖራል። የዜጎች የፌደራል ስቴቶች በበኩላቸው በየፖለቲካ ዩኒቶቹ ውስጥ ዜግነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስበትን ይፈጥራሉ።

ይህ የፌደራል ስቴት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በህዝብ ቀጥታ ምርጫ በሚመረጡ ተወካዮችና በህዝብ ቀጥታ በሚመረጥ ፕሬዚደንት የሚመራ ቢሆን ይመረጣል። ይህ የፌደራል ስርዓት የሚኖረው ኣስተዳደር መድብለ ፓርቲ ስርዓት መርሆው ይሆናል። መድብለ ፓርቲው የሚፈጠረው ደግሞ ከስብስቦች መሃል ኣንዱን ለመደራጃ በመምረጥ ሲሆን  ሃገራዊ ስብስብ ብቻ ለፖለቲካ መደረጃነት ይመረጣል። በዚህ መሰረት የፌደራሉ ስልጣን ምንጭ ዜግነት ይሆናል ማለት ነው። ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ወደ ዜጎች ባወረደ የፖለቲካ ፍልስፍና የሚመሰረት የፌደራል ስርዓት ነው። ከባህልና ሃይማኖት ጋር የጎኖሽ የሚሰራ ግን ራሱን በሃይማኖትና ባህል ውስጥ የማያስገባ ስርዓት ማለት ነው።

ይህ የፌደራል ስቴት በህገ መንግስቱ ውስጥ ለሚኖረው የቼክና ባላንስ ስርዓት ተገዢ ሆኖ ይኖራል። ልማትን እያፋጠነ ይኖራል። በአጠቃላይ የሁለቱ የፌደራል ስቴቶች ጠቀሜታ በኢትዮጵያ ውስጥ ተጣብቆ የኖረውን የባህልና ፖለቲካ ተፈጥሮ በመለየት የተረጋጋ ስርዓት ለመፍጠር የታለመ ነው። ከሁሉ በላይ ከሃገራችን ልዩ ሁኔታዎች ጋር የሚሄድ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ የፌደራል ስርዓት ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ነው።

 1. የ EDF ስርዓት መሰረቶች

የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት  በኢትዮጵያውያን ኣዲስ ሃገራዊ ኪዳን ላይ ይመሰረታል ስንል አንደኛው ኪዳን ዶግማዊ ሃገራዊ ኪዳን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሄራ ወይም ህገ መንግስት ነው።

 • ዶግማዊ ኪዳን ( Eternal Covenant)

ህብረተሰብ ኣብሮ ሲኖር ሁል ጊዜም መተሳሰሪያ መርሆዎች ያበጃል ብለናል። ወይም ለማህበራዊ ህይወቱ ህልውና የሆኑ ኤለመንቶች ኣሉ ብለናል። እነዚህ ኤለመንቶች ሁሉ ግን በህገ-መንግስት ኣይገለጹም። ነገር ግን በህገ-መንግስት ሳይገለጹ እንዲሁ እንደ ህቡእ (hidden) ኪዳን ሆነው ህብረተሰብን አስተሳስረው ሲኖሩ እናያለን።

በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት የሚለው ሃገር በቀል የሆነው አሳባችን ግን እነዚህን ረቂቅ እጅግ ኣስፈላጊ የህብረተሰብ መተሳሰሪያዎችን በጽሁፍ ገልጸን ቃለ መሃላ ልናደርጋቸው አይገባም ወይ? የሚል መሳጭ ጥያቄ አንስቷል። እነዚህን መርሆዎች በጽሁፍ ገልጾ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የመተሳሰሪያ መርሆዎቻችን ሞገስ ማድረግ ለሃገር ብሄር ግንባታችን፣ ለሃገር ኣንድነትና ለጠራ ፖለቲካ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያውያን እነዚህን ረቂቅ ኤለመንቶች አውጥተን ጽፈን ኣንድ ዶግማዊ ዶክመንት ይኑረን።  ለምሳሌ ያህል መከባበር፣ መረዳዳት፣ ደስታንንና ሃዘንን መካፈል፣ ኣብሮ መኖር፣ መፋቀር፣ አንዱ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም እንዲኖር፣ ታማኝነት፣ የማንከፋፋል መሆናችን፣ ለልማትና ለስራ ቆርጠን መነሳታችን፣ ለዓለም ሰላም፣ ለፍትህ መቆማችን በጽሁፍ ተገልጾ ዶክመንት ሊዘጋጅለት ይገባል። ህገ መንግስት የህብረተሰብ መተሳሰሪያ ዋና መርህ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን የሞራል ነክ ጉዳዮችና ሌሎች ረቂቅ መተሳሰሪያ መርሆዎች በግልጽ ህብረተሰቡ መሃላ ሊገባባቸውና ሊገዛላቸው ይገባሉ። እነዚህ መተሳሰሪያ መርሆዎች በጽሁፍና በቃል ኪዳን መልክ መዘጋጀታቸው ለሃገረ ብሄር ግንባታ መሰረት ናቸው። ኢትዮጵያውያን በባህላቸው በሃይማኖታቸው ውስጥ ያሉትን እነዚህን መተሳሰሪያ ኤለመንቶች መግለጽ የዚህ ስርዓት ዋና መሰረት ነው።  ይህ ዶግማዊ ቃል ኪዳን በዜጎች ሁሉ ከጸደቀና ከተፈረመበት በሁዋላ ከዚህ ስር በሚወጣው ህገ መንግስትና ሌሎች ህጎች ክብርና ልእልና ይሰጠዋል። ብሄራዊ መዝሙር ኪዚህ ኪዳን ላይ ተቀድቶ ይጻፋል። የዜግነት ቃል ኪዳን ከዚሁ ይቀዳል።

ለምን ዶግማዊ ቃል ኪዳን ያስፈልጋል? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ከላይ ያነሳነው ኣንድ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ ሃገረ ብሄር በተፈጥሮው ዶግማዊና ቀኖና ስምምነቶች ስለሚኖሩት ነው። ሃገር በተለይ ዶግማዊ አካል ኣለው። የማይፈርስ፣ በዘመናት መሃከል ጸንቶ የሚኖር ነው። ስለዚህ ይህን ተፈጥሮውን የሚያጸና ቃል ኪዳን ያስፈልጋል። በመሆኑም በዘመናት መሃል ፖሊሲ ስንለውጥ፣ ህግ ስናሻሽል የማንለውጠውን የአብሮነታችን መገለጫ የሆኑ መተሳሰሪያ ኪዳኖችን አንጥረን አውጥተን ዶግማዊ ስምምነት ኣንጥረን ኣውጥተን በግልጽ ማስቀመጣችን ለትውልድ ሁሉ ለማሳለፍ ይረዳናል። በአጠቃላይ ሃገረ ብሄር የሚቆመው በሁለት ህጎች ነው ማለት ነው። አንደኛው ቀኖናዊ የሆነው ህጉ ነው። ይህ ቀኖናዊ ህጉ በፖሊሲ መልክ ሊሆን ይችላል፣ በህግ መልክ ሊሆን ይችላል፣ በደምብና ኣሰራር መልክ ሊሆን ይችላል በየጊዜው እያሻሻለው ተሳስሮ የእለት ኑሮውን ይገፋበታል። ነገር ግን ማህበረሰብ ዶግማዊ ጎኖችም አሉት። የማይቀይራቸው ለዘመናት የሚጠብቃቸው ለትውልድ የሚያስተላልፈው ኪዳንም ኣለው። ይህ ኪዳን ተነጥሎ ወጥቶ መጻፍ ኣለበት የሚል ነው የዚህ የአዲስ ሃገራዊ ኪዳን ኣሳብ መነሻ። የህዝቡን ዶግማዊ ህይወት በቃል ኪዳን መልክ ማስቀመጣችን ከህብረተሰቡ ከትውልዶች ህይወት መልካም ሃይልን እንድናመነጭ ይረዳናል። ሌላው የዚህ ፍልስፍና መሰረት ደግሞ በተለይ የሞራል ጉዳዮች ህብረተሰብን የሚያስተሳስሩ ብቻ ሳይሆኑ ነገር ግን ግንኙነትን የሚያለሰለሱ (lubricate የሚያደርጉ) ብሎም ማህበራዊ ሃብትን (social capital) የሚያመርቱ በመሆናቸው ነው። የመተማመን፣ የመረዳዳት፣ የመዋደድ፣ የሃላፊነት ስሜት የመሳሰሉት የሞራል ጉዳዮች ለሃገር ወሳኝ ኤለመንት በመሆናቸው እነዚህ ላይ መሃላ መያዝ ማህበራችንን በጸና መሰረት ላይ ስለሚያቆመው ነው።

በሌላ በኩል የዚህ የቃል ኪዳን ነገር በተለይ ለኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም አለው። በተለምዶና በባህል ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ኣሃገር ናት። ይህ ባህል መከበር ኣለበት። ቃል ኪዳን መሃላ በሃገራችን ትልቅ ቦታ ኣለው። በመሃላ የጸና ጓድነት ይከበራል። ሃገራዊ ስብስባችንን በዚህ ዶግማዊ ኪዳን ላይ ለማድረግ የኢትዮጵያውያን ስነ ኑባሬ (ontologies) ግድ ይለናል። የኢትዮጵያውያን ሳይኮሎጂም ይህንን ይደግፋል::  በሌላ በኩል ይህ ዶግማዊ ኪዳን ቃለ መሃላ ከሆነ በሁዋላ ህጋዊ ስለሚሆን ዶጋሚ መተዳደሪያችን ይሆናል ማለት ነው። የሲቪክ ሶሳይቲዎች ሲመሰረቱ እነዚህን ኪዳኖች መሰረት እያደረጉ መከባበርን፣ መረዳዳትን መሰረት እያደረጉ እንዲሰሩ እድል ይሰጣቸዋል። መንግስት ይህንን ኪዳን ከፍ ኣድርጎ ለልማት ለሰላም ይጠቀምበታል። የዶግማዊ ኪዳን አስፈላጊነት ዋና አምክህኖት ለማህበረሰብ ትስስር ዋና መሰረት የሆኑትና ለሃገራዊ ስብሰብ ወይም ሃገረ ብሄር ህልውና እጅግ አስፈላጊ(essential) የሆኑት ኤለመንቶች በህገ መንግስት በግልጽ አለመገኘታቸው ነው። ለምሳሌ ከላይ ያነሳናቸው መረዳዳት፣ ፍቅር፣ መከባበር፣ መስዋእትነት የመሳሰሉት የህብረተሰብ ህልውና መሰረቶች ሲሆኑ አንዳንድ በጎ ኣድራጎት ድርጅቶች ለበጎ ስራ ሲነሱና እነዚህን ኤለመንቶች መሰረት ማድረጋቸውን ሲገልጹ የተጻፈ የማህበረሰቡ ኪዳን ስለማይኖር እነዚህን ኤለምንቶች ከፍ ኣድርገው ወደያዙ ባህሎች፣ ሃይማኖቶች እየሄዱ ለመጥቀስ ይሞክራሉ። ለነዚህ ድርጅቶች መሰረት የሆናቸውን ነገር ለማሳመን እንዲህ ዓይነት ኪዳን መኖሩ ለቅስቀሳቸው ትልቅ ሃይል ይሆናቸዋል። ወታደሩ በሙያው ተግቶ እንዲሰራ፣ ኣስተማሪው ተግቶ እንዲያስተምር፣ ባለሙያው እንደሙያው እንዲተጋ፣ ኣስተዳዳሪው ተግቶ እንዲያስተዳድር ይራዳል። ይህ ኪዳን መኖሩ ሃገራዊ ትስስራችንን ያጠነክራል። ኢትዮጵያውያን ያላቸውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህል ለመጋራት ከተስማሙና በሌላ በኩል ብዝ ሃነታቸውን አክብረው ለመኖር ከተስማሙ ይህንን ስምምነት መሰረት ያደረገ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ለመፍጠር ይቻላል። በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ውስጥ አንዱ መሰራትዊ ግጭት በብሄራዊ ማንነትና በብሄር ማንነት መካከል ግልጽ የሆነ የመተሳሰሪያ መርሆ አለመኖሩ ነው።  ይህ ደግሞ ሃገሪቱን እንደ ሃገር ዜግነትንና ቡድንን ኣያይዞ ለመግዛት ሳይስችል ቀርቶ ዛሬ የዜግነት ጉዳይ ወሳኝ ጥያቄ ሆኗል። በመሆኑም የዚህ የሃገራዊ ኪዳኑ አንዱ ተግባር ይህንን ክፍተት በመሙላት ዜግነትንና ቡድንን ለማስተሳሰር፣ ዜጎችንና ዜጎችን፣ ቡድንና ቡድንን ለማስተሳሰር የሚያስችል ሃሳብ ነው። በመሆኑም ይህ ኪዳን ለሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ ዋና ጠቅላላ መነሻ ሲሆን ሁለተኛው ዝርዝር መነሻ ደግሞ ሄራው ይሆናል። በአጠቃላይ ለዶግማዊ ቃል ኪዳኖቻችን መነሻ የሚሆኑት ሃሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

የኢትዮጵያውያን ሃገራዊ ዶግማዊ ቃል ኪዳን

እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉን በሚችለው እግዚአብሄር ፊት የሚከተለውን ቃል ገብተናል። ይህ ቃል ኪዳናችን በዘመናት መሃል የማይሻርና የማይሰበር መሃላችን ሲሆን ትውልድ ኣልፎ ትውልድ ሲተካ እየተቀባበልነው እንኖራለን።

 1. ከእግዚኣብሄር በታች የማንከፋፈል አንድ ህዝብ!
 2. ባህልህ ባህሌ ቋንቋህ ቋንቋየ፣ ባህልሽ ባህሌ ቋንቋሽ ቋንቋየ
 3. ታሪክህ ታሪኬ ታሪክሽ ታሪኬ
 4. ሃይማኖታችን የግላችን ሃገራችን የጋራችን። ጽንፈኝነት ጠላታችን።
 5. የተፈጥሮ ሃብታችን የጋራችን። በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያሉ ህያዋንና ግኡዛን ፍጥረታትን ሁሉ እንጠብቃለን።
 6. ፍቅር መሰረታችን። ብዝሃነት ጌጣችን። መረዳዳት መከባበር መገለጫችን:: ቸርነትና በጎነት ደስታችን::
 7. ለነጻነት፣ ለሰላም፣ ለህግ የበላይነት፣ ለእኩልነትና ለልማት በሙሉ ሃይላችን እንሰራለን። ሙያና እውቀታችንን ሳንቆጥብ ለሃገር ልማት እናውላለን።
 8. ለተተኪው ትውልድ ቅርስ እየተውን ታሪክ የምንሰራ ጀግና ህዝብ ነን::
 9. ለደካሞችና ለተገፉ እንቆማለን፣ ከለላ እንሰጣለን::
 10. ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ባህላዊ እሴቶቻችን ዘወትር ከፍ ብለው ይኖራሉ:: የጀግኖች ሃገር ኢትዮጵያን እናስከብራለን።
 11. ከአለም ህዝቦች ጋር ለሰው ልጆች ሰላምና እድገት እንሰራለን። እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ነን።
 12. መንግስታችንን በነጻ ምርጫችን እየመሰረትን ስንኖር መርጠን ለመሰረትነው መንግስት እንገዛለን። እኛ የህዝብ አገልጋዮች ደግሞ ኢትዮጵያን በቅንነትና በታማኝነት እናገለግላለን።

(እነዚህ ቃል ኪዳኖች ለህዝቡ በቀላል ቋንቋ እንደዚህ ተቀምጠው ሲያበቁ፣ በእያንዳንዳቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሚሰጥ አስራ ሁለት ምእራፍ ያለው የኪዳኑ ሰነድ ይዘጋጃል::)

 • ሄራ

ሌላው የዚህ ስርዓት መሰረት ደግሞ ህገ መንግስታችን ነው። ህገ መንግስታችን Constitution የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በምልዓት ስለማይገልጽ ሄራ የሚል ስያሜ ቢሰጠው መልካም ነው።  ሄራ  ማለት የኦሮምኛ ቃል  ሲሆን ህገ መንግስት ከሚለው ቃል ይልቅ የበለጠ ገላጭ  ነው። በዚህ መሰረት ሄራችን ቼክና ባላንስ ያለው፣ የአስፈጻሚውን፣ የፍትሁን፣ የፕሬዚደንቱን የሰኔቱን ሃላፊነትና ስልጣን በግልጽ የሚያስቀምጥ ነው። በአጠቃላይ ሄራችን:-

 1. ኢትዮጵያን እንደ አንድ የማትከፋፈል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብነት ወይም ኔሽንነት የሚገልጽ ዶክመንት መሆን ይኖርበታል
 2. ለኢትዮጵያዊያን ዶግማዊ ኪዳን ክብርና ልእልና ይሰጣል። ይህንን ለመጠበቅ ዘብ ይቆማል።
 3. የብሄር ፌደራል ስርዓቱንና የዜጎች ፌደራል ስርዓቱን የሃላፊነት ልክ ይገለጻል
 4. በስቴትና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ይገለጻል
 5. የፌደራል መንግስትና ስቴቶች የሚጋሯቸውን ስልጣናት ይገልጻል።
 6. የባህል ፌደራል ስቴቶችና የአርበኞች ቤት የሚኖራቸውን ሃላፊነቶች ይገልጻል።
 7. የባጀት ፌደራሊዝሙን የሚመለከቱ መሰረታዊ ጉዳዮችን ያስቀምጣል
 8. መሰረታዊ የዜጎች መብቶችን ያስከብራል
 9. መሬት ለአራሹ ይሰጣል
 10. ሶስቱ የመንግስት ኣካላትን በቼክና ባላንስ ያዋቅራል
 11. ዴሞክራሲያዊ ሃሳቦችን የያዘ ዶክመንት ይሆናል
 12. የሱፕሪም ክላውዝ አንቀጽ ይኖረዋል።

በአጠቃላይ ህገ መንግስቱ የሃገሪቱ ህጎች መሰረት ሲሆን ይህ ዶክመንት ሁለተኛው የሃገራችን ከፍተኛ ቃል ኪዳን ይሆናል ማለት ነው። በአሁኑ ሰዓት ያለን ህገ መንግስት ዋና ችግር ኢትዮጵያን ፈራሽ ኣድርጎ ማዋቀሩና እንደ አንድ ፖለቲካዊ ኔሽን አለማየቱ ነው። ኢትዮጵያን ፈራሽ ኣድርጎ ማሰብ ከመነሻው ኢትዮጵያን ውዳቂ ሃገር (failed state) ያደርጋታል። ይሄ በዓለም የሌለ አንቀጽ መሻሻል አለበት። በሌላ በኩል ብሄር ማለት ኔሽን ማለት ኣይደለም። ብሄር በእንግሊዘኛው (ethnicity) የሚለውን የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። ኔሽን የሚለው አገላለጽ ግን ለፖለቲካ ስብስብ የሚሰጥ ነው። አሜሪካውያን ከእግዚኣብሄር በታች የማንከፋፈል አንድ ህዝብ ነን ሲሉ ብዙ ብሄርና ቋንቋ የለም ማለታቸው ኣይደለም። አንድ የማይከፋፈል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበር ነን ማለታቸው ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያም በህገ መንግስቷ ኢትዮጵያውያንን እንደ ኣንድ ኔሽን የማየቷ ነገርና በአንጻሩ ባህላዊ ማንነትን ማክበሩ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ መሰረት ይሆናል።

 1. የ EDF ጠቀሜታ

 

 • ባህልና ቅርስን ለመንከባከብ

ኢትዮጵያ ከዓለም ሃገራት መካከል ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት ያላት ታሪክና ባህላዊ ቅርሶች ያሏት ሃገር ናት። ይሁን እንጂ ቅርሶቻችንን በመጠበቅና ያሉንን ማህበራዊ ሃብቶች ወደ ኢኮኖሚ የመቀየሩ ጉዳይ ላይ እምብዛም ኣልሰራንም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ያሉንን ባህላዊ እሴቶችና ቅርሶች አጥተናል። በርግጥ ባህል ኣንዴ ከጠፋ ኣለቀለት ማለት ኣይደለም። የባህል ማስመለስ (Restoration of culture and heritages) ስራ እየሰሩ የጠፉ ባህሎችን ማስመለስ ይቻላል። ኢትዮጵያ ከንግስት ሳባ ጋር የተገናኘውና ለረጅም ጊዜ ይዛው የቆየችውን የ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ኣስትዳደር ሃገራችን ለውጥ ሲያምራትና ወደ ደሞክራሲ ስትገባ ሜዳ ላይ የምትጠለው ጉዳይ ኣልነበረም። ይህንን ታሪካዊ ሰንሰለት ጠብቀን ባህላዊ ኣድርገነው ነገር ግን ዴሞክራቲክ የሆነ መንግስት መመስረት እንችል ነበር። እንደ እንግሊዝ የመሳሰሉ ሃገራት ወደ ሪፐብሊክ ሲመጡ ያደረጉት ነገር ስርዓታቸውን ኮንስቲቱሽናል ሞናርኪ ማድረግ ነበር። በዚህም ባህላዊ ኣስተዳደራቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። ህዝቡም በዚህ ደስተኛ ነው። ኢትዮጵያ ያጣችውን ይህን ሄሪቴጅ በዚህ ስርዓት ማስመለስ ያስፈልጋል። ይህ ትውልድ ሃላፊነት ኣለበት። በተለያዩ ብሄሮች ውስጥ ያጣናቸውን ባህላዊ ኣስተዳደሮች እንዲመለሱ ማድረግ ኣለብን። ባህልን ማስመለስ (Restoration of Culture) ማድረግ ይቻላል። የባህል ፌደራል ስቴቱ ኣንዱ ዋና መነሻና ጥቅም ሄሪተጆቻችን እንዲመለሱ ማድረግና ከጸጸት የጸዳ ሙሉ ማህበረሰብን መፍጠር ነው። እሴቶቻችንን ለተተኪ ትውልድ ማድረስ ነው።

 • ለብሄራዊ ኣንድነት

ብሄራዊ ኣንድነት ወይም ሃገረ ብሄር የሚመሰረትባቸው ኤለመንቶች ኣሉ። እነዚህ ኤለመንቶች ደግሞ በዜጎች በቡድኖች መስዋእትነት ላይ ይመሰረታል። ብሄራዊ ኣንድነት ማለት የቡድን ማንነትን ሁሉ ጨፍልቆ ኣንድ ብሄራዊ ማንነት መፍጠር ኣይደለም። ልዩነትንና ኣንድነትን ኣብሮ የማኖር ጥበብ ነው ብዝሃነት ማለት።  ብዝሃነት  ማለት ኣንድነት ለልዩነት፣ ልዩነት ለአንድነት ተግዳሮት ሳይሆኑ ተቻችለው መኖር የሚችሉበት ስርዓት ማለት ነው። ስለዚህ ይህ የሁለትዩሽ የፌደራል ስርዓት ዋናው ኣጀንዳው እነዚህን ልዩነቶች ሳይጨፈላለቁ በህብረት በአንድ ኪዳን ስር መኖር እንዲችሉ ማድረግ ነው። ብሄራዊ ኣንድነትን የሚያጠናክረው ነገር ብዝሃነትን በሚገባ ማጠናከር ነው። የብሄራዊ ማንነት መስሪያ ኤለመንቶች በተለይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዝንባሌዎችን መስዋእት ማድረግና በአንድ ሃገራዊ ጥላ ስር ማኖር ሲሆን ይህንን ማድረግ ኣንዱ ዋና ኣጀንዳ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዉያን በሙሉ በአንድ ብሄራዊ ማንነት የፖለቲካ ቤታቸውን ለመስራት መስማማት ኣለባቸው። በሌላ በኩል ያሉዋቸውን ባህላዊ እሴቶች ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በመሰዋት የአንዱ ባህል ለሌላውም እንዲሆን መስማማት ኣንድነታቸውን ያጠነክራል። ይህ ቤት የኔ ብቻ ሳይሆን የአንተም ነው የሚል ስሜት የሃገር ኣንድነት መሰረት ነው። ኮንሶ ብሄር የሚፈጥረው ባህላዊ ስቴት ይህ ቤት የኮንሶን ባህል ባህሉ ኣድርጎ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ስቴቱ ነው የሚል ስምምነት ያስፈልጋል። ይህ ነው ብሄራዊ ኣንድነትን የሚያጠናክረው። በመሆኑም ይህ ሲስተም ለብሄራዊ ኣንድነት መጠናከር ትልቅ ሚና ኣለው። በሌላ በኩል የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ አንዱ የሚጨነቅለት ነገር የቋንቋ ጉዳይን ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቋንቋ አያያዝ መሻሻል አለበት። በዚህ ሞዴል መሰረት የብሄሮችን ሁሉ ቋንቋዎች የብሄራዊነት ደረጃ በመስጠት በህገ መንግስት ስሞቻቸው ሊመዘገቡ ይገባል። በሌላ በኩል እንደ አንድ የሃገር ህዝብ የሚያገናኘን አንድ የህብረት ቋንቋ እንዲኖረን ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ያሉንን ቋንቋዎች በሙሉ በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ኦፊሺያል በማድረግ ቋንቋዎችን ሁሉ መጠበቅና ለዜጎች አገልግሎት መስጠት ይቻላል። ይህ ኣሰራር ኣንድነትንና ልዩነትን ኣቻችሎ የሚሄድ ይሆናል።

 • ለሰላም ግጭትን ለማስወገድና ለሁለንተናዊ ልማት

የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት ግንባታው ትልቁ ጥቅም በተለይ ብሄር ተኮር የሆኑ ግጭቶችን ለመቀነስ ነው። ይህ ስርዓት በሁለት መንገድ ኣስተዋጾ ኣለው። ኣንደኛ ብዙ ጊዜ የግጭት መንስኤ የሆኑትን የተፈጥሮ ሃብትና የአስተዳደር ጥያቄዎች ይመልሳል። በተለይም በዚህ ስርዓት ውስጥ መሬት የግል ስለሚሆን በቡድኖች መካከል የግጭት መንስኤ ይጠፋል። ከሁሉ  በላይ ግን የተፈጥሮ ሃብትን መቀራመት ስለሚቀርና የኔ የኔ የሚባል ነገር ስለሚያከትም የግጭት ምንጭ ይደርቃል። በሌላ በኩል ማንነት ስለሚጠበቅና ባህላዊ የግጭት ኣፈታት ዘዴዎቻችን ምቹ ሁኔታ ስለሚያገኙ ይፋፋሉ። ያድጋሉ። ከሁሉም በላይ የሚፈጠረው የብሄር ባህላዊ ስቴት  ፖለቲካዊ ያልሆነ (non-political ) በመሆኑ በገለልተኝነት ግጭት የመፍታት ኣቅም ይኖረዋል ተሰሚነት ይኖረዋል። ሽምግልናን ፖለቲከኛ ስናደርግ ኣንዱ ያጣነው ነገር ሽማግሌ ነውና የሁለቱ ስቴቶች ምስረታ ኣንዱ ጥቅም ይሄ ነው።

ሁለንተናዊ ልማት ለማድረግ ምቹ ሲስተም ወሳኝ ነው። ህብረተሰብ ስጋቶች ቀንሰውለት ዋስትናዎች ሲበዙለት በሙሉ ልቡ ኣልሚ ይሆናል። ነጋዴው ይነግዳል በሃብት ላይ ሃብት እየጨመረ ሃገሩን ማሳደግ ይሻል፣ ተማሪው ተምሮ በእውቀቱ ሃገሩን ማገልገል ይሻል፣ ገበሬው በሰላም ወጥቶ ሲገባና ዋስትናው ሲበዛ ኣርሶ ያመርታል። አስተማሪው ኣስተምሮ ሰው ይለውጣል። ሃኪሙ የዜጎቹን ህይወት እየቀጠለ ያግዛል። ወዘተ። ይሁ ሁሉ የማህበረሰብ እንቅስቃሴ የተሻለ መርህ ሲኖር፣ መርሁ ሲከበር ምቹ ሲስተም ሲኖር ነው በተገቢው መንገድ የሚከውነው። ስለዚህ ለሁለንተናዊ ልማታችን ይህ ሲስተም ወሳኝ ሚና ኣለው።

 • መተማመን እንዳይተን ለማድረግ( Prevent Trust evaporation)

ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የቱንም ያህል ሃብታም ብንሆን መተማመን ከሌለን የገዛ ሃብታችን የግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በመንግስትና በህዝብ መካከል፣ በዜጎች መካከል (interpersonal trust ) በብሄሮች መካከል (cross-cultural trust) ወይም በማንነቶች መካከል መተማመንን የሚያዳብር ስርዓት ያስፈልጋል። ይህ የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት መቆሚያ መሰረት የሆነው የጋራው ቃል ኪዳን እንዲያመርት የታሰበው ነገር ፍቅርን፣ መተማመንን ነው። እነዚህ ዋና የህበረተሰብ  ህልውና በመሆናቸው ለነዚህ ኤለመንቶች ምቹ ሲስተም የሚፈጥር ነው የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ። ማንነቶች እንዳይገለሉም እንዳይጨፈለቁም የሚያደርግ ሲስተም መሆኑ በራሱ በቡድኖች መካከል መተማመንን ያመጣል። በተለይ ኣነስተኛ ሰው ያላቸው ብሄሮች የሚገጥማቸውን የአሲምሌሽን ስጋት ይቀርፋል። እየተነነ ያለውን የብሄር ተኮር መተማመን ችግር ይቀርፋል። የተሻለ ሲስትም ስንፈጥርና በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን ስንገነባ በዜጎች መካከል የተሻለ መተማመንን እንገነባለን። የባህል ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት በነጻነት ኣባላቶቻቸውን ሲያስተምሩ አንዱ የምናመርተው ፍሬ መተማመንና ፍቅርን መረዳዳትን ነው።

 

ማጠቃለያ

ይህ ጽሁፍ ሃገራችን ኢትዮጵያ ለሽግግር የያዘችውን የመደመር ፖለቲካ በተግባር (Medemer in action) የያዘ ሮድ ማፕ ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእውቀት ላይ የተመሰረተና የሰከነ ርምጃዎችን የምትሻበት ዘመን ላይ ነን። በተለይ ባለፉት ዓመታት የገባንበት የብሄር ፖለቲካ ለሃገራችን ሰላምና እድገት ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። የብሄራዊ ደህንነት ኣማካሪ ሚንስትር  በቅርቡ በሰጡት መግለጫ የብሄር ፖለቲካ የሃገራችን ብሄራዊ ደህንነት ስጋት ነው ሲሉ ገልጸውታል። ይህንን ጉዳይ ለብዙ ዓመታት የኢትዮጵያና የውጭ ሃገር ምሁራን ሲጮሁበት የነበረ ጉዳይ ነበር። ርግጥ ነው የብሄር ፖለቲካ የሃገር ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ነው። ታዲያ ጥያቄው ከዚህ ፖለቲካ ለመውጣት ሁለት ነገር በሰከነ ልቦና ማሰብ አለብን።

 1. አንደኛው እንዴት ወደዚህ ፖለቲካ ገባን? የሚለውን ጉዳይ ነው።
 2. ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ እንዴት እንውጣ ? ነው። እንዴት ዘጸዓት (exodus) እናድርግ

አገባባችንን ማጥናትና አወጣጣችንን  ማሳመር የሚገባን ሽግግራችን በአነስተኛ ስጋቶች  እንዲራመድልን ነው። እንዴት ወደዚህ ፖለቲካ ገባን ምን እግር ጣለን? የሚለውን ስናጠና ከምናገኛቸው መልሶች ኣንዱ የማንነት ጥያቄ ወይም ሃገራችን ማንነትን አጠባበቋ ችግሮች ስለነበሩ እንደሆነ አንዱ ዋና ምክንያት ነው። ታዲያ እንዴት እንውጣ? የሚለው የበለጠ ጥንቃቄ ይሻል። 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የቆየንበትን  ፖለቲካ ስንላቀቀው ወይም ዘጸዓት ስናደርግ ለዚህ ለብሄር ፖለቲካ መነሻዎች ምላሽ ሰጥተን ተስማምተን መሆን አለበት። ዘጸዓታችን በአንድ ቀጭን ትእዛዝ ወይም ቀጭን ህግ የሚሆን ኣይደለም። የብሄር ፖለቲካ ከዛሬ ጀመሮ በቃ ብሎ ካቢኔ ስለወሰነ ሃገራችን ከብሄር ፖለቲካ ተላቀቀች ማለት ኣይደለም። እንዴውም ይሄ ነገር ከፍተኛ ግጭት ኣምጥቶ ሃገር ሊያፈርስ ይችላል። እውነት ነው የብሄር ፖለቲካ መቼም ቢሆን ህዝባዊ ሰፊ መሰረት የለውም ሊኖረውም ኣይችልም። ይሁን እንጂ በዚህ ፖለቲካ ውስጥ ስንከርም ብዙ የብሄር ኢንተርፕሩነርስ ስላፈራን ሃገራችንን ከዚህ ስናላቅቅ በጥንቃቄ መሆን አለበት። በተለይ ኣሁን ያለው ወቅታዊ ጉዳይ ይህንን ጥንቃቄ ይፈልጋል። ስለሆነም ከብሄር ፖለቲካ ዘጸዓት የምናደርገው::

 1. አዲስ ሃገራዊ ኪዳን ህዝቡ እንዲገባ በማድረግ ነው። ይህ ኪዳን ለውጡን መሰረት ያለውና መሰስ ብሎ እንዲሄድ ያደርጋል። ይሄ አዲስ ሃገራዊ ኪዳን የምለው ሃሳብ ደግሞ ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የሞራልና ማህበራዊ ጉዳዮችን የያዘ ኣንድ ዶግማዊ ኪዳን መግባት ሲሆን በሌላ አገላለጽ ይህ ሃሳብ  ብሄራዊ መግባባት ነው። ይህ በራሱ አንድ የዘጸዓት ርምጃ ቢሆን ሽግግራችን ያምራል።
 2. ዘጸዓት ሁለት ቀድሞ ወደ ብሄር ፖለቲካ ለከተተን የማንነት ጥያቄ ወይም የብሄር ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስርዓት መፍጠር ነው። ከላይ የተገለጸው የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓት አንዱ የዘጸዓት ሮድማፕ ነው።
 3. ዘጸዓት ሶስት ኢትዮጵያን እንደ ኣንድ ፖለቲካዊ ኔሽን የሚያይ ሄራ ማዘጋጀት። ከፍ ሲል የተነሱትን መነሻ ሃሳቦች መሰረት በማድረግ ህገ መንግስታችንን በጣም ዘመናዊ ማድረግ::
 4. ዘጸዓት አራት የቋንቋን ጉዳይ ማስተካከል ሲሆን ይሄውም የህብረት ቋንቋ እንዲኖረን ማድረግና በሌላ በኩል ሁሉንም ቋንቋዎች በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ኦፊሺያል ማድረግ ያሻግረናል።

በስምምነት ላይ የተመስረተ ዘጸዓት ካደረግን የብሄርን ፖለቲካ በህግ ከልተን ወደ ዴሞክራሲ በፍጥነት መራመድ እንችላለን። ነገር ግን ከዚህ ፖለቲካ የምናደርገው ኣወጣጥ ካላማረ እንደገና ሃገራችንን ብዙ ዋጋ ልናስከፍላት እንችላለን። የሁለትዮሽ የፈደራል ስርዓት ግንባታ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የሆነ ጥቅም ኣለው። በተለይም በሽግግር ወቅት ለተነሳው የመደመር የሽግግር ኣሳብ ተግባራዊ ሲስተምን ያሳያል። መደመር ማለት ልዩነትን ሳይደፈጥጡ ነገር ግን ደግሞ ኣንድነትን ማጠናከር ነው። ይህ የሁለትዮሽ ሲስተም የሚያሳየው እውነት ይህንን ነው። በቃል ኪዳን ተደምረን የኔ የኔ ቀርቶ የእኛ ብለን ግን ደግሞ ልዩ ልዩ ባህሎቻችን ሳይደፈጠጡ፣ የእጅ ጥበቦቻችን ሳይደፈጠጡ መኖር እንችላለን የሚል ነው።

ይህ ሲስተም ከፍ ሲል እንዳልነው በተለይ የመተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን ለማሻሻል ይጠቅማል። የመተሳሰሪያ መርሆዎቻችን ሲሻሻሉና ዶግማዊ ኪዳን ስናደርግ አንዱ የሚተርፈን ነገር መተማመን ነው። ይህ ደግሞ ለሃገር መሰረት ነው። ከዚህ  በተጨማሪ የብሄራዊ ኣንድነታችን መገለጫ ይሆነናል። ኢትዮጵያውያን የትም ሆነን የአንድ ኪዳን ልጆች ነን  ማለታችን በራሱ መሰባሰቢያ ጥላ ስለሚፈጥር ለብሄራዊ ኣንድነታችን፣ ለሰላም ትልቅ ሚና ኣለው። ከዚህ በተጨማሪም የሃገራችንን የተፈጥሮ ሃብትና ባህል ለኢኮኖሚ እድገት በማዋል ከድህነት ለመውጣት ይረዳናል። በተለይ ዶግማዊ ኪዳን ያለን ህዝብ መሆናችን ደግሞ ለዓለም ህዝብ ምሳሌ የሚያደርገን ይሆናል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይኮራብናል። የኢትዮጵያ ወዳጆች ይደሰታሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ኣሳብ ከኢትዮጵያውያን የብሄሮች ስነ-ኑባሬ (ontology)ና ሃይማኖት ጋር ስለሚሄድ ትልቅ ማህበራዊ ሃብት እናዳብራለን። ህብረተሰቡ በሁለቱም የፌደራል ስርዓቶቹ ላይ እምነቱ መጨመሩ ለሰላም ለብልጽግና መሰረት ነው። በቅርብ ጊዜ በሃገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በሚመለከት ከሚሰጡ ገንቢ አስተያየቶች መካከል አንዱ ሽግግሩ ግልጽ በሆነ ሮድ ማፕ ይመራ የሚል ነው። ይሄ ለለውጥ አራማጆች ወሳኝ ምክር ነው። ሮድ ማፕ ይኑረን ማለት በሌላ ቋንቋ እንዴት ነው ዘጸዓት የምናደርገው? የሚል ነው። ስብስቦችን ሁሉ እያግተለተልን ፖለቲካ ኣድርገን ወደ ዴሞክራሲ ልንሻገር ኣንችልምና ይህ የሁለትዮሽ የፈደራል ስርዓት በተለይ የብሄር ስብስብን ጠገግ ስለፈጠረለት ግጭቶችን ይቀንሳል። ከዚህ በተጨማሪም ሲስተሙ ስልጣን የሚያካፍል ስለሆነ የብሄር ለሂቃን የብሄራቸውን ባህል የሚዘክሩበት ጠገግ መፍጠራችን በፖለቲካው ኣካባቢ ያላቸውን ግፊያ ይቀንሳል። ይህ ጽሁፍ ያለው ጥቅም ይሄው ነው። ለለውጥ የሚሆን ሮድ ማፕ ለማቅረብ ነው የሁለትዮሽ የፌደራል ስርዓቱ የተቀረጸው። ከሁሉ በላይ ለችግሮቻችን መፍትሄ የሚሆን ሃገር በቀል መፍትሄ ስለሆነ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ጸሃፊው ያምናል። የሽግግሩ መንግስት የመደመርን ጽንሰ ሃሳብ ይደግፋልና ይህንን የመደመር ሲስተም ለሽግግሩ ቢጠቀምበት ሃገራችን የተሻለ ሽግግር ታያለች። እግዚኣብሄር ይርዳን።

Ethiopian Dual Federalism