ከአክብሮት ጋር የቀረበ መለዕክት  – ከጣሰው

1 min read
1

ለ ኢትዮጵያ አገሬ ናት፤ ሌላም አማራጭ የለኝም፤ ዴሞክራቲክ ባትሆንም፤ ፋሺስትም ቢገዛት፤ ድሃም ብትሆን ሃብታም፤ መኖሪያም ሆነ መቀበሪያየ እሷ ብቻ ነች ብላችሁና አብረን ልንኖርባት፤ ይገባል፤ እንፈልጋ ለንም፤ እንችላለንም ብላችሁ ለምታምኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤-

1ኛ/ አጼ ሃይለ ሥላሴ ሕገ-መንግሥት ሰጥተውን ነበር፤ በሱም የገዙትን ያህል ገዝተው በመጨረሻም ከሳቸው ጋር ወደመቃብር ወርዷል፤

2ኛ/ ደርግም እንዲሁ ሕገ-መንግሥት ሰጥቶን ረጅም ጊዜ ባይሆንም በሱው ሲገዛን ሰነባብቶ በመጨረሻም ከደራሲው ጋር አብሮ ተሸኝቷል።

3ኛ/ መለስ ዜናዊ (ወያኔ) የሰጠን ዛሬ የምንገዛበት ሕገ-መንግሥት አሁን አለ።

ይህ ሶስተኛው ከቀደሙት ሁሉ በእጅጉ ይለያል። ዋና መለያውም እንዲያከናውን በታለመለት ተግባር ላይ የሚታይ ነው። ይህ ተግባር ምንድነው ብትሉ፤ ብዙ ጥናት ተደርጎበት፤ እንደሚነገረንም ብዙ ህይወትም ጭምር ተከፍሎበት በጥንቃቄ፤ በልዩ የተወሳሰበ ዘዴ የተቀናጀው ኢትዮጵያን የመበታተን አላማ ነው። ይህንን አሌ የሚል ካለ ይደመጣል።

ለዚህም ነበር፤ ይህ ሕገ-መንግሥት ከመጀመሪያው ጀምሮ፤ በተለይም ከ 1997 ዓ. ም. ሥራ ላይ መዋል ከጀመረበት 15 አመት በኋላ በተጠናከረ መልክ በመጀመሪያ መለስ በነበረበት ጊዜ፤ ይህን ሕገ-መንግሥት ሳይንደን መናድ አለበት በማለት ከዋናው አርቺቴክት መለስ ጋር ሰንወዛገብበት ቆይተን፤ ከመለስ ህልፈትም በኋል ከወራሾቹ ጋር ስንዳረቅበት፤ እነሱም ሕገ-ምንግሥታችንን ሊንዱ ተንስትዋል ብለው የጠረጠሩትን የጎዳና ተዳዳሪ ሳይቀር፤ ሳርና ቅጠሉ ኮሽ ባለ ቁጥር ያገኙትን ሁሉ ሲያስሩ ሲፈቱና ሲያሰቃዩበት ኖረው ዛሬ ያለንብት የመጨረሻው መጀመሪያ ላይ አድርሰውናል። ምልክቶቹን ልዘርዝር ብል በግልጽ የሚታየውን ማበ ላሸት ካልሆነ ትርፍ የለውም።

ታዲያ ምን ይደረግ? መልክቴ እንዲደርሳችሁ የሆናችሁት ሁሉ አንድ ሆነን ይህንን ለሶስተኛ ጊዜ በስጦታ ያገኝነውን የመተላለቂያና የመበታተኛ ሕገ-መንግሥት ንደን ጥለን፤ ከኛው፤ በኛው፤ ለኛው የሆነ ሕገ-መንግሥት እንጻፍ። ይህን ማድረግ ካቃተን ግን  የጊዜ ጉዳይ እንጂ እጣ ፋንታችን የሚሆነው ተላልቆ መበታተን ሲሆን፤ አንድ የሚቀር ዕውነት ግን አለ። መተላለቁም ሆነ፤ መበታተኑ እንዳለ ሆኖም ኢትዮጵያ አትጠፋም። እሷ የምትጠፋው ኢትዮጵያውያን ሲጠፉ  በቻ ነው። ሰማይና ምድር ያልፋሉ እንጂ ኢትዮጵያውያን አይጠፉም። ትጠፋለች ብላችሁ ለምትሰጉ አትስጉ፤ ኢትዮጵያን እናጠፋለን ብላችሁ የምትቃትቱ ተስፋ ቁረጡ!! ከዚህ ውጭ ስለሕገ-ምንግሥት የሚዘየረው ሁሉ ጉንጭ አልፋ የሆነ አኞ ስጋ ነው።  አበቃሁ።

tass7012@yahoo.com