የአማራውን ድምፅ ለማፈን የተጀመረው የኦዴፓ ዘመቻ! – ጌታቸው ሽፈራው

1 min read
3

ኦዴፓ/ኦህዴድ አማራው ላይ ከዘመተ ቆይቷል። ዋናው ስልት ደግሞ አማራው እንዳይደራጅ አብን፣ የአማራው ድምፅ የሆነውን አሥራትን ማፈን ነው።

የአብን አባላትና የአሥራት ጋዜጠኞች ሰበብ ተፈልጎላቸው የታሰሩትም በዚህ ምክንያት ነው። በሰኔ 15 ሰበብ ጠርጥረናችኋል ተብለው ጨለማ ቤት የገቡት የአሥራት ጋዜጠኞች በምርመራ የሚጠየቁት ለምን የአጣዬውን ጉዳይ ዘገባችሁ ተብለው ነው። የአጣዬውን ወረራ ማን እንደፈፀመው እናውቃለን። በአጣዬ፣ ከሚሴ፣ …ወረራ የታሰሩትን ፅንፈኞች ከታሰሩ በኋላ እነዚህን ሰዎች ለማስፈታት ብቻ ሳይሆን አካባባቢውን ለመበጥበጥ የድርጅት ከፍተኛ አመራር ሆኖም ሲቀሰቅስ የነበረ ሰው እንዳለ መረጃዎች አሉ። የአሥራት ጋዜጠኞች እየተጠየቁ ያሉት የኦዴፓ አመራሮች በሕዝብ በደል ይፈፅማሉ፣ የኦዴፓ የበላይነት አለ ብላችኋል የሚል ነው። ኦዴፓ አማራን ሕዝብ ልሳን ለማዝጋት ያልቆፈረው ድንጋይ የለም። አሁንም ቀጥሏል!

ለምሳሌ ትናንት የኦዴፓ ከፍተኛ አመራር የሆነው አቶ ታዬ ደንድኣ አጀንዳ በሚሰጡበት ኤል ቲቪ ቀርቦ ከሰኔ 15 ሁለትና ሶስት ቀን በፊት በአሥራት እና ABN “ተደራጅተን መዋጋት አለብን። መታጠቅ አለብን የሚል ቅስቀሳ ሲደረግ ነበር” ሲል ተናግሯል። ይህ የአቶ ታዬ ደንድኣ ንግግር ኦዴፓ አማራውን ለማጥቃት የጀመረውን መጠነ ሰፊ የሀሰት ዘመቻ የሚያጋልጥ ነው። ከሰኔ 15 ሁለትና ሶስት ቀን በፊት ያስተላለፍናቸው ፕሮግራሞች ዝርዝር አለን። ABN መሰል ፕሮግራም ሊያስተላልፍ ቀርቶ በወቅቱ ስርጭት አቁሞ ነበር። እነ ታዬ ደንድኣ አማራውን ለማጥቃት ሲቋምጡ የሚከሱን ግን መሰል ፕሮግራም ባላስተላለፈ ብቻ ሳይሆን ስርጭት ካቋረጠ በቆየ ጣቢያም ጭምር ነው።

የእነ ታዬ ደንድኣ ንግግር የማን አለብኝነት ብቻ አይደለም። ከተረኝነትም ጭምር ነው። ባልተጨበጠ የሀሰት ማስረጃ የአማራውን ድምፅ ለማፈን እየተደረገ ያለው ዝግጅታቸው አንድ አካል ነው። ትህነግ/ሕወሓት ሲያደርገው ከነበረው በባሰ በሀሰት ማስረጃ ሕዝብን ለማፈን የያዙት ዘመቻ አካል ነው።

የአሥራት ጋዜጠኞች እየተከሰሱ ያሉት ለምን በሕዝባችሁ ላይ የተፈፀመውን ወረራ አጋለጣችሁ ተብለው ነው። በእስር ላይ ያሉ ከፍተኛ የፀጥታ ኃላፊዎች በአጣዬ ጉዳይ ጥርስ ተነክሶባቸዋል። ወራሪዎቹ ከታሰሩ በኋላ አማራውን እንደገና ለመበጥበጥ ጥረት ተደርጎ በፀጥታ ኃይሉ ብርታት ተመክቷል። በመጀመርያውም ሆነ ባልተሳካው የወረራ ሙከራ ማን እጁ እንዳለበት እናውቃለን። ግን እንደነሱ ዝም ብለን ስም አንጠራም።

ተረኞቹ እነሱ የሚፈልጉትን ያስባሉ እንጅ ሌላው፣ ስህተታቸው እንኳ አይታያቸውም። የሚጋለጡትም ለዚሁ ነው። የአማራው ፖለቲካ አጋላጭ የሆነው ትግሉ በሀሰትና በሀቅ መካከል በመሆኑ ነው። እነሱ በሀሰት መረጃ ሊከሱ ሲሞክሩ የአማራው ጠጣር እውነትም አለ። ይህን እውነት ይዘን ዝም የምንል መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል። ፍርድ ቤቱንም እንታዘበዋለን እንጅ የሀሰት ውንጀላ ራሱ ወንጀል መሆኑን የምናጣው መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል።