ነ በ ረ !! – ተፃፈ በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊሥ

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |
ተፃፈ
በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊሥ
  ነሐሴ 7/2011 ዓ/ም
     ነ በ ረ !!
ይህስ ትዕንግርት ነው።
የሄስ ተዓምር ነው።
በህሊናዬ የሚዜመው
” ሰወ፣ሰው፣ሰው ፣ሰው ነን እኛ… ! “
የሚል አዝማች ያለው
ማራኪ የማንነት ዜማ
ለእኔ ብቻ የሚሰማ።
የእውነቶች እውነት
ቃላት የማይገልፁት።
ትክክል የሆነ
ፍጹም የታመነ።
” ሰው፣ሰው፣ሰው ፣ሰው  ነን እኛ ! “
የሚል አዝማች ያለው
ማራኪ የማንነት ዜማ
ለእኔ ብቻ የሚሰማ።
ነበረ !ነበረ !ነበረ! …
ግና ፣ ቃላት የታለ?
ቃላት ባገኝለት
በአደባባይ ባዜምኩት።
   ይህንን ፣መቀበዣዠር
   ይህንን  ” የአፆለሌ” ሸር
   ይህንን  “የነቢሊጮን” ተረት
  ” ይህን የቡሄ በሉ ” ሁከት
   ” የአበባየሆይ ? ” ሹፈት
     የእንጀራ ናት ግርፋት ።
   ” የአሸንዳዬን ” ጣጣ
    ባዶ አንጀት ሲሰጣ።
    በክፍፍል፣በግርግር
    እርስ በእርስ በመጠራጠር…
እያየሁ ዝም ባላልኩ
ይህንን ግር ግር
ይህን እግር እግር
ይህንን ክፍፍል
ይህንን ንጥጥል…
ይሄን ዘረኝነት
ይሄን አውራጃዊነት
ይሄን መንደርተኝነት
ይሄን ጎጠኝነት….
ከልቦች ባወጣሁት።
 ” በሰው ዜማ”፣ በተካሁት።
ትዕንግርት በሆነው…
ተአምር በሆነው…
በህሊናዬ በሚዜመው
” ሰው፣ሰው፣ሰው፣ሰው ነን እኛ … !”
   የሚል አዝማች ባለው።
በልቤ ተዳፍኖ በሚቀለፀው
በሆድ ይፍጀው በተቀበረው።
በገፄ ላይ በማይነበበው
በአንጀቴ በሚተራመሰው።
በእህህ በማዳምጠው
ዜማው ውሥጤን በሚንጠው።
አርቃኑን አሥቀረው
ከንቱነቱን አሳውቀው
ነ በ ረ ! ነ በ ረ !  ነ በ  ረ !
ቃላት ጠፋ እንጅ
በከፋፋይ ና በዘረኛ ደጅ።
ቃላት ባገኝለት
ዜማዬ በእውነት
ያሥረዳልኝ ነበር
ትላንት ማን ምን እንደነበር።
ትላንት አልቀሶ ሲወለድ
ዛሬ፣ሰው ሆኖ ሰው ፣ሰው ሲወልድ።
ሰው ሆኜ ሥቀበር !….
እራቁቴን መጥቼ
በራቁት ሥሰወር።
ሥደባለቅ ከአፈር…
ነ በ ረ ! ነ በ ረ !…
የፈጣሪ ዜማ
በውሥጤ የሚሰማ።
ታዲያ  ፣በምን ቋንቋ ልፃፈው?
እንዴት ለሁሉም ሰው ላሥረዳው ?
ዜማዬ ፣ ከሆነ አምሳያዬን የሚያንቀው
በምን ቋንቋ ልግለፀው???
” ይኽ ቋንቋዬ ” ሥለማይወደድ
  ሃሳቤ እንዴት ይመንደግ???
 ለዜማዬ ሌላ ቋንቋ ባገኝለት
    ይህንን ዘር ቆጠራ !….
    ይህንን የምድረ አፈር ጉራ!
    ይህንን የተራሟቾች ሽለላ !…
    የምድረ ሸክላ ጉራ !….
” ከንቱ ና የከንቱ ከንቱ ”  እንደሆነ
 ማሥረዳት እችል ነበረ።
 ነ በረ ! ነ በ ረ ! ነ በ ረ !….
 ግና……..
ቋንቋ መግባብያ  መቼ ሆና !
በራቁቱ ሰው ፣ተጣማ
መምህር ሆና የጨለማ !!
የመለያየት ቀንዲል ሆና-“ጥቁር ሻማ !”
ሥለዚህ …
    ቋንቋ ኬት ይመጣል?!
    ሁሉን የሚያባብል ?!
    የፍቅር ዜማዬን የሚያሰማ
     ህዝብ አዳምን የሚያስማማ !!
ሁሉን የሚሸመግል
” የብረት ቦክሳቸውን ” የሚያሥጥል።
 ሁሉም ሰው፣ሰው ሆኖ የሚቀበለው
 ልቡን አንድ የሚያደርገው።
 ገል ፣አፈርነቱን የሚያሥገነዝበው።
 ከተኛበት ፣ የድንቁርና እንቅልፍ የሚያነቃው።
ፍፁም አዲሥ ቋንቋ ፣” በፈጣሪ ” ቢፈጠር
ሁሉንም ሰው የሚያሥማማ ፣ የሚያነጋግር
” የእኔ ! የእኔ ! የእኔ ! ” እያሰኘ የማያሥፎክር
በወገንተኝነት ፣የማያቧድን ፣የማያሸብር ።
ያንን አዳሱን ቋንቋ ፣ሁላችንም ብንናገር
ይህ….
“ሰው፣ሰው፣ሰው ፣ሰው ነን እኛ!
ብንሆን ቆለኛ! ብንሆን ደገኛ….
ብትናገር ኦሮምኛ!
ብትናገሪ ጉራጊኛ!
ብትናገር ትግሪኛ!
ብትናገሪ አማርኛ!
ብትናገር ሱማሊኛ!
ብትናገሪ ሲዳምኛ!
ብትናገር ወላይትኛ!
ብትናገሪ ጉራጊኛ !…..
ሰው ፣ሰው፣ሰው፣ሰው ነን እኛ !…
……………………………….
የሚለው ፣ ” ነጠላ ዜማዬ ” ያማልል ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.