/

ፈርተን ዝም አንልም …ገሃነምባይቀዘቅዝም!   ተፃፉ በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

1 min read
 ነሐሴ 12 ቀን 2011 _ ዓ/ም
እንናገራለን
“በአፍ ይጠፉ
በለፈለፉ”
ብንባልም፤
ፈርተን  ዝም አንልም
ገሃነም ባይቀዘቅዝም ።
አፋችንን አንዘጋም  “ገሃነም እሥቲ ይቀዝቅዝ”  ብለን
እንቀልጣለን እንጂ እቶኑ ውሥጥ ገብተን
መብራታችን አይቀርምና ሻማ ሆነን።
…………………………………..
ደሃን አሥጨናቂ ጭቃ ሹም ምሥለኔ በዝቶ በየቀበሌው
እየሰለቀጠ የአዞ እንባ የሚያነባ ፣በዝቶ  ፎጋሪው።
እያየን ዝም አንልም
ገሃነም ባይቀዘቅዝሞ።
መለስ መለሰ እያለ ሲጮኽ ትላንትና
“በራእይ ፣ በሌጋሲው” ሲል ጎበሥ ቀና
በምላሥ በመሆኑ  የእርሱ ህልውና
ዛሬም “ቲም ለማ !” እያለ፣ ሲኖር በጤና።
ሥላየን
እንናገራለን
ፈርተን ዝም አንልም
ገሃነም ባይቀዘቅዝም።
በየመንገዱ ላይ ደሃን እየገረፈ
በሥልጣን ብዝበዛ ፣  ሺ እያተረፈ
በህግ ተከልሎ፣በግልፅ እየዘረፈ
በመደመር ዙሪያ ፈንጂ እያነጠፈ
“ቆሚያለው  “ይለናል  ከቲም ለማ ጋራ
በደርግ ያልታየ ነው ፣የዛሬው ፉገራ።
ይህንንም ሥላየን
እንናገራለን
ፈርተን ዝም አንልም
ገሃነም  ባይቀዘቅዝም።
…………………..
የደርግ ሐጢያት ነበር  …
ተማሪ ለእውነት ሲል፣ሲወድቅ ሲነሳ
“በለውጥ ሥም ” እያሠረ ማሳየት አበሳ።
“በቀይ ሽብር ና በነጭ አብዮት”
እንደዋዛ ሲጠፋ የትውልድ ህይወት
አብዮት ጠባቂ ና አብዮታዊ ካድሬ
ነግሦ ነበር በግልፅ ፣ በድፍን ሀገሬ።
ይህንንም ሥላየን
እንናገራለን
ታሪክን እናሥታውሳለን።
የዛሬው ግን ይለያል “ከደርግ ብዝበዛ”
ጫወታው ሆኗል “በቋንቋ እንግዛ።”
ለዓመታት ሲከወን የወያኔ ብዝበዛ
ካድሬ አፍዛው ነው ፣ ህዝብን አደንግዛ !!
ይህንንም ሥላየን
እንናገራለን
ፈርተን ዝም አንልም
ገሃነም ባይቀዘቅዝም።
……………………….
ዝም አንልም
እንናገራለን
እውነቱን
ማለት እንደሆነ እሥኪገነዘቡ ፣ ቀንቀሎ ሥልቻ
ዝም ብለን አናይም
“በቋንቋ ሥም” ዜጋ ሲሆን መጫወቻ !
ሀገርም በዓለም ፊት ስትሆን መዘባበቻ!
ፖለቲካችንም ሲሆን ታላቅ ሥላቅ ፣ የዓለም መተረቻ!
እንናገራለን
“በአፍ ይጠፉ
በለፈለፉ።”
ብንባልም፤
ፈርተን ዝም አንልም
ገሃነም ባይቀዘቅዝም።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.