ግምታዊ ዋጋው ከ 14 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ወረቅ እና የዉጪ አገር ገንዘብ በቁጥጥር ስር ዋለ

1 min read
2

የጉምሩክ ኮሚሽን ግምታዊ ዋጋው 14 ሚሊየን ብር የሚገመት ወርቅ የዉጪ አገር ገንዘብ ህገወጥ በሆነ መንገድ ከሀገር ሊወጣ ሲል መያዙን አስታወቀ፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ከደቂቃዎች በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት ህገወጥ ወርቁ ሲጓጓዝ የነበረው መነሻውን አዲስ አበባ ባደረገ ያሪስ መኪና ሲሆን የሰሌዳ ቁጥሩም ኮድ 2 A 08104 አ.አ ነው፡፡ የወርቁ አጠቃላይ ክብደትም 8.7 ኪሎ ግራም እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ተሸከርካሪው በትንናው እለት ከቀኑ 10 ሰዓት ከአዲስ አበባ በመነሳት ከሌሊቱ 10፡30 ጅግጅጋ አቅራቢያ በምገኘውና ልዩ ስሟ ቦምባስ በምትባል ቦታ በጉምሩክ ፈታሾች፣ በፌደራልና የክልል ጸጥታ አካላት የተቀናጀ ስራ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በተሸከርካሪው ውስጥ 41 ሺ ዩሮ እና 55 ሺ 600 የሳውዲ ሪያል የውጪ ሀገር ገንዘቦች ተገኝተዋል፡፡ የውጪ ሀገር ገንዘቦቹም ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆኑም ታውቋል፡፡ አህመድ ሃሰን ሃሚድ የተባለ ተጠርጣሪ ግለሰብም የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በተያዙበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል፡፡ኮምሽነሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየታየ ያለውን የኮንሮባንድ ፍሰት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የህብረተሰቡ ተሳትፎም ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በተያዙበት ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ ላደረጉ የጉምሩክ ፈታሾች እና የጸጥታ አካላት እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራትም ኮንትሮባንድን በመቆጣጠሩና በመከላከሉ ረገድ አመርቂ ስራ የተሰራ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር የዋሉ እቃዎችንና ገንዘብ የምንገልፅላችሁ ይሆናል፡፡