ፍርድ ቤቱ በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የምርመራ መዝገብ የተጠየቀውን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ይግባኝ ውድቅ አደረገ

1 min read

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 22፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የምርመራ መዝገብ የተጠየቀውን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ይግባኝ ውድቅ አደረገ፡፡

ፍርድ ቤቱ በትናትናው ዕለት የእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የቀዳሚው ምርመራ መዝገብ ለማየት ለዛሬ ቀጠሮ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት ሃምሌ 29 ቀን 2011 የባህርዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ የጠየቀውን ተጨማሪ ቀዳሚ የምርመራ ጊዜ መዝጋቱን ተመልክቷል፡፡

በዚህም አቃቤ ህግ ለባህርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል፡፡

የባህርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቂ የምርመራ ጊዜ መሰጠት አለመሰጠቱን ለማጣራት በዳኞች አብላጫ ድምፅ ይግባኝ ቀርቧል፡፡

ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ህግ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በቂ ምክንያት የለውም በማለት ተከራክረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር በማዳመጥ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የይግባኝ ቅሬታ ውድቅ በማድረግ የጊዜ ቀጠሮው ላይ የባህርዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማፅናት መዝገቡን ዘግቷል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ