የአሸንዳ በዓል የፊታችን ነሃሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይከበራል – በደስታ ተካ

1 min read
2

ከሀገራችን በርካታ የባህል መገለጫ እሴቶች መካከል ተጠቃሽ የሆነው የአሸንዳ በዓል በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና አዲስ አበባ በልዩ ልዩ ዝግጅቶችና በድምቀትና ለማክበር የሚያስችል መርሃ-ግብር መውጣቱም የከተማ አስተዳድሩ ከንቲባ ፅሕፈት ቤት አስታውቋል።

በበዓሉ ላይም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የከተማው መስተዳድር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የትግራይ ክልል ተወላጆችና የአሸንዳ ልጃገረዶች በአደራሹ በመገኘት ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በዓሉን ያከብራሉ።

የአሸንዳ በዓል፥ “አሸንዳ የሰላም፣ አንድነትና ልማት ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 16 ጀምሮ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ መሆኑ ይታወቃል።

በትግራይ ክልል በነሐሴ ወር የሚከበሩ የአሸንዳ፣ ማሪያ እና ዓይኒ-ዋሪ በዓላት፥ የክልሉን ባህል፣ ትውፊትና የቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና የሚጫወቱ በዓላት ናቸው።

በዚህም አሸንዳ እና ማሪያ ከነሃሴ 16 ቀን ጀምሮ እየተከበሩ የሚገኙ ሲሆን፥ ዓይኒ-ዋሪ ደግሞ ነሃሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በአክሱም ከተማ እና አካባቢው የሚከበር የልጃ ገረዶች በዓል ነው።

በዓሉ በህዝቦች መካከል ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር እንዲኖር ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ለቱሪዝም መስህብነት በማገልገል ለኢኮኖሚው አስተዋዕኦ እንዳለው ይታወቃል።

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 22፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ)
በደስታ ተካ