ህይወት ለማንም አታዳላም፣እናም ዕድል ብሎ ነገር የለም – መኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

1 min read
 የሰው የህይወት ጉዞ በተሰጠው መክሊትና ፣በመክሊቱ ተጠቅሞ በሚያገኘው ፋይዳ  የሚወሰን ነው።
   ሰዎች እንጂ ይህቺ ዓለም ለማንም አታዳላም።  ህይወት ለማንም አታዳላም።በህይወት ሥንኖር መድሎ ፣ግፍ፣ሐጥያት ወዘተ የተሰኙ ክፋቶች በራሳችን በሰዎች ይፉጠራሉ። ራሳችንንም ይጎዳሉ።ራሳችንንም ይጠቅማሉ።
     ለአንዱ ሥጋዊ ና መንፈሳዊ ደሥታን ያጎናፅፋሉ።ሌላውን መቀመቅ ያወርዳሉ።
   አንዱ ፣ (ግለሰቡን ባያስገድደውም) አስቅሞ ፣አሥክሮ እንዲሁም መዘሞቻ አልጋ አዘጋጅቶ ገንዘብ ሰብስቦ ፣ የተዘባነነ ኑሮ ይኖራል። በማባከን ላይ የተሰማራው፣ በአርባ ቀን ዕድሉ ያማርራል።የአንድቀን፣የአሥር ቀን፣የአርባ ቀን፣የሰማንያ ቀን ወዘተ።ዕድል ብሎ ነገር የለም። ዕድል ብሎ ነገር የለም።የአጋጣሚ ና የምርጫ ጉዳይ ነው።ለመኖር በምታደርገው ጥረት ልክ  በአጋጣሚ ሀብታም ሀገር ትፈጠራልህ። ወይም ደደግሞ በተፈጥሮ በረከት ላይ ጥገኛ ሆነህ ፣ ያለሥራ በመቀመጥህ በሥራ የበለፀገውና በቴክኖሎጂ የተራቀቀው ፣ ዘው ብሎ ወደ መኖሪያ ሀገርህ መጥቶ በቴክኖሎጂው እያሥፈራራህ፣በቴክኖሎጂው ተጠቅሞ ይዘርፍሀል።አንተ ና ሀገርህም በራስህ ሥፍና ደሃ ይሆናሉ።
      ደሃ ሀገር ፣ ላይ በግለሰብ ደረጃ ሀብታም የሆኑት ፣ በሥልጣን እና በሥልጣን ዙሪያ ያሉት በአጋጣሚው የተጠቀሙ  እና ጥቂቶቹ ደግሞ  ፣ሰርተው ወይም ነግደው የሚያገኙትን ፣ ለበለጠ ትርፍ ለማዋል የሚተጉ፣ከብክነት የራቁ ግለሰቦች ናቸው። ከዚህ በተረፈ በውርስ ሀብታም ትሆናለህ።ወይም ደሃ ትሆናለህ።
     ወይ ከናጠጠ ሀብታም ትወለዳለህ ወይም ድንቡሎ ከሌለው ደሃ ተወለዳለህ። ሀብታም ሀገር ላይ ከሀብታም ብትወለድም ፣ በምርጫህ ና በአጋጣሚ የድሃ ኑሮ ልትኖር ትችላለህ። በእንደኛ ዓይነቱ ሀገር ከደሃ ብትወለድም፣በአጋጣሚ ና በምርጫህ ሀብታም ልትሆን ትችላለህ። ይህም እውነት ነው።
  ይህ እውነት የአርባ ና የሰማኒያ ቀን ዕድል ጉዳይ በህይወት ሥንኖር ሥፍራ እንደሌላቸው ያሳየናል።
    “የኮኮባችን ጉዳይስ ሊሆን አይችልም?” ብላችሁ ልጠይቁ ትችላላችሁ።
 ” ኮኮቤ  ነው።” ወይም ” ግንባሬ ነው።” ይላሉ ብዙ ሰዎች።  ሌሎች ያለግንባር እንድተወለዱ በመቁጠር። ኮኮብ ሀብታም ና ባለሥልጣን የሚያደርግ ከሆነ፣ዓፄ ምኒልክ፣ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ኮ/ሌ መንግሥቱ (መንጌ) መለሥ ዜናዊ(መሌ) ኃ/ማርያም ደሳለኝ (ንጉሥ ሆነው እንዳልመሩ ብትክዱም) ዶ/ር አብይ አህመድ  (ንጉሥ ለመሆን እየጣሩ ነው፣ይባላሉ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ያደረጉትን ንግግር በማሥታወስ።)  ፥በነዚህ በኢትዮጵያ መሪዎች ቀን ና ወር የተወለዱ ለምን ንጉሥ አልሆኑም?? በእነዚህ ቀን እና ወራት  እኮ በሺ የሚቆጠሩ ህፃናት ተወልደዋል።ሆኖም በኮኮብ ፍቺው መሰረት መሆን አልቻሉም።ሰዎች አትሳቱ በአሥራ ሁለቱም ወር በዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ይወለዳሉ።ነገር ግን የህይወት አጋጣሚያቸውን የሚወስኑት፣ቤተሰቦቻቸው፣የተወለዱበት ሀገር ና ሥፍራ፣ለመኖር እንዲችሉ የተመቻቹላቸው ሁኔታዎች ወሳኝ ናቸው። እርግጥ ነው ፣በባህሪ መመሳሰል ፣ በኮኮብ ቆጣራ ፍቺ ላይ ሊኖር ይችላል።ትርጉሙ ግን የሰው አጠቃላይ ባህሪን አካቶ ጠቅለል ያለ አማካኝ ትርጉም ሥለተሰጠ  ነው ተመሳስሎሹ።(በነገራችን ላይ የእያንዳንዱን የሀገር መሪ ባዮግራፊ ከዊኪፒዲያ ወስዳችሁ ኮኮቡን ማወቅና ፣አስትሮሎጂ ብላችሁ በመግባት አጠቃላይ የኮኮቡን ማንነት ማወቅ ትችላላችሁ።እንደ ኮኮቡ ነው፣ብላችሁ ማመን ያለማመን የግላችሁ ጉዳይ ነው።ግን እውነት አይደለም።)
     “ሎቶሪስ ?” ብላችው ብጠይቁኝ ፣ ሎቶሪ ቁማር እንጂ ዕድል አይደለም።   ዘውድ ወይ ጎፈር ነው።
      “ቁማር ጫወታ ተጫውቼ አጨብጭቤ ቀረሁ ተበልቼ
        ምንኛ ዕድሌ በሰመረ ዘውዱን ገልብጬ በነበረ”
   እናስ?ገባችሁ፣”ለአንድ ቁጥር ሳተኝ ብላችሁ ትቋጫላችሁ።ከቆረጥከው ሎተሪ ፊት ወይም ኋላ 10 ሚሊዮን የሚያስገኝ ቁጥር ነበረ።ዘለህ ይህኛውን ቆረጥክ ለአንድ ቁጥር ያ ሁላ ረብጣ ብር አመለጠህ።ቁማር ተበላህ።በመቶ ሺ  የሚቆጠሩ ሰዎችም እንደ አንተ ተበልተዋል።ብራቸውን ሰብስበው፣ለአቋማሪው እና ለባለዕድለኛው ሰጥተዋል። አናሥተውልም  እንጂ ህይወት ራሷ ቁማር ጫወታ ናት።
    ሰው፣”ዕድል! ዕድል!” እያለ ይሞዘዛል እንጂ ፣ ህይወትን ሊያጣፍጣትም ሆነ ሊያመራት የሚችለው የራሱ እኩይ ና ሰናይ ተግባር ነው።
      ሰው ሰናይ ተግባሩ እንዲጎለብት ከፈለገ ፣ የህይወት ትርጉም የገባቸው ፣በመሪነት እንዲቀመጡለት የሚያሥችል   ሥርዓት በየሀገሩ ሊመሰርት ግድ ይለዋል።ፍትህ ሳይሆን በፍትህ ላይ  ሰው የነገሠበት ሀገር እስከወዲያኛው አያልፍለትም።
    ፍትህ የነገሠባቸው፣መሪዎቹ በፍትህ ቁጥጥር ሥር የሆኑበት ሀገር ፤   የበቁ፣የነቁ ፣ ሌብነትን የሚጠየፉ ና ሌቦችን የማይታገሱ … በማሥተዋል የተሞሉ ሰዎች   የሀገር መሪዎች በሆኑበት በኢሲያ ፣ በአውሮፓ ና አሜሪካ ተጨባጭ የሆነ የኑሮ ሥኬት ተገኝቷል።
     በአፍሪካ በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያ ፣ ጥቂት ሰዎች በጥቂት ጊዜ የበለፀጉበት መንገድ በዳቦ ሥሙ  ሙሥና የሚሉት ሌብነት ና ዘረፋ መሆኑ ይታወቃል።
     በየክልሉ ፣ መንግሥት ሥልጣን ከሰጣቸው፣ቁልፍ ከሆኑ አገልግሎት መሥጫ ቦታዎች ፣ ከተሾሙ  የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ግንባር ፈጥረህ፣ለመበልፀግ እንደምትችል ትላንት ተረጋግጧል።ዛሬሥ?ሙሉ ለሙሉ ተወግዶል ትላለህ?ወንድሜ ዛሬም ተረቱ አትሩጥ አንጋጥ ነው። “አንጋጥ!” ምን ዓይነት ተአምረኛ ቃል ነው።”አንጋጥ!”
     “እያልከን ያለኸው ሀገራችንም ሆነች አፍሪካ ያልታደሉ “አንጋጣጭ” ናቸው ነው ወይ? ” ብላችው ልጠይቁኝ ትችላላችሁ።
          እኔ ግን እያልኳችሁ ያለሁት ህይወትን ለግላችሁ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መኖር ሥትሉ የማትኖሯት ካልሆናችሁ ፣ በራሳችሁም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ አወንታዊ ለውጥ አታመጡም ነው።
     በእርግጥ ዛሬን እየኖራችኋት ነው። እየኖራችኋት ባለችው ማይክሮ ሰከንድ ግን ምን እንደሚፈጠር አታቁም።  ህይወት በሚቀጥሉት ሰኮንዶች ውስጥ  መራራ  ፅዋዋን አንቃ ልትግታችሁ ትችላልች።እንዳልኳችሁ ህይወት አታዳላም።
   ዛሬ ሥጋህን ልታንደላቅቀው ትችላለህ።እጅግ በተቀናጣ ኑሮ(አርቴፊሻል ቢሆንም)ህይወትህ ጣፋጭ እንድትሆን ትጥራለህ።ይህ ሁሉ ግን ዘለቄታ የለውም።ገንዘብ የሚያስገኝልህ ደስታ ሁሉ፣የእንቦይ ካብ ነው።
በዙሪያህም ያሉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ገንዘብህን እንጂ አንተን ስለማይወዱ፣ድንገት ቀን ቢጥልህ አታገኛቸውም።
   የሰው ህይወት በህይወትነትዋ ለማንም አታዳላም።እያንዳንዱ ሰው በህይወቱ እግዚአብሄር(ፈጣሪው) የሰጠውን ሚና ተጫውቶ ያልፋል። በህይወት ሲኖር ግን የተሰጠውን መክሊት ማወቁ ላይ ግን ችግር አለበት።ይህም በመሆኑ ነው ህይወትን እንደአድሎኛ በመቁጠር “የአርባ ቀን እድሌ ነው”የሚለው።
     ህይወት የማታዳላ እንደሆነች ለማወቅ ከፈለግህ ቀላል ምሳሌ እሰጥሃለሁ።ይኸውም ሰው ሁሉ ራቁቱን መወለዱ ና ሲሞትም ራቁቱን መሄዱ ነው።”ወደመቃ–ብሩ። “(….)
     የሰው የህይወት ጉዞ ፣በተጓዡ ምርጫና መክሊቱን  በመቀበልና አለመቀበል የሚወሰን መሆንንም ማስተዋልን የተጎናፀፈ ቀባሪ ያኔ ይገነዘባል።
   የማይገነዘበውን አብዘኛውን ሰው ፣ህይወት በዝንጋታ ገመድ እየጎተተች ወደማቅብሩ ታደርሰዋለች።
      ሰው ሁላ ራቁቱን ነው የተወለደው።ወደዓለምም  ምንም ይዞ አልመጣም ።ምንም  ይዞም አይሄድም።ይህንን እናውቃለን።ግና እንዘነጋዋለን።ምንም ይዘን ወደዚች ዓለም እንዳልመጣን ሁሉ ምንም ይዘን ባንሄድም ለነገ በብርቱ ማሰብ የየሰኮንድ ተግባራችን ነው።ነገ ያሳስበናል።መሽቶ በነጋ ቁጥር ሥለኑሮ እናስባለን።መኖራችን የሚረጋገጠው ትርፍ ነገር፣ብቻ ሳይሆን ከሌሎች በላይ የተትረፈ
ረፈ ሐብት ሲኖረን ይመስለናል።…
    ይመሥለናል እንጂ ሀብት ና ንብረት ጤና፣ሠላም ና በበዛ ደሥታ የታጀበ ኑሯን እንድንኗር አያደርጉንም።   በተትረፈረፈ ሀብት ና በንብረት ብዛት በህይወት የመቆየት ዋሥትናም የለንም።እርግጥ ነው የተቀማጠለ ና የተዘባነነ አኗኗር ብርቅ ላይሆንብን ይችላል።በተላላፊ በሽታዎች የመጠቃት እድላችንም አነሥተኛ ይሆናል።ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እና ከአደጋዎች ግን ፣ (የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ)ልናመልጥ አንችልም።
   ሰው ነፍሥ ካወቀ በኋላ፣  ያለእረፍት  በመስራት ክፉ ቀን በህይወት ዘመኑ ቶሎ አይከሰትም ብሎ የሚኖር የዋህ ፍጡር ነው። ሀይማኖተኛውም በፀሎቱ ብርታት ፣ ዛሬ ና ነገውን እያደላደለ ኗሪ ነው። በእርግጥ ፈጣሪ ለሁሉም ሰው አያዳላም። የዓለም ሰዎች ግን እጅግ ያዳላሉ። የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ኃያላኑ ቡድኖች -ቡድን 2-3-4-5-6-7-8-… እያሉ ለገዛ ጥቅማቸው የሚጣመሩት- የሚያደሉት ለራሳቸው ጥቅም ነው።ያውም ባልበለፀጉት ሀገሮች ኪሣራ ነው ጥቅማቸው የተገነባው። ቅን እየመሰሉ በመሰሪነት አፍሪካን ደሟን መጠዋል።እርስ በእርስ እንድንባላም የዕብድ ገላጋይ ሆነዋል።በጎሣ ፣በዘር፣በኃይማኖት ልዩነት ላይ በማተኮር፣ሰው መሆናችንን እንድንረሳ አድርገዋል።ኋላ ቀር ባህላችንን እንድንጠብቅ ና ዛሬም እራቁታችንን እንድንሄድ ያበረታቱናል።
     በመላው አፍሪካ ድህነትን አሥፋፍተዋል። በብዝበዛ አልጠግብ ባይ ሆነዋል ።ከጥንት እሥከዛሬ እንደተስገበገቡ ነው። ሥግብግብነታቸው አላባራም።መሥገብገባቸው ሣያንሥ  ፣በጥጋብ ሰማይን በእርግጫ ማለታቸው ያሥገርማል።….
     የሚሉሱት ና የሚቀምሱት  አፍሪካውያኑ በማጣት፣ በህይወት ለመሰንበት ዘወትር ሲታገሉ፣ የሚለግሶቸው የጦር መሣሪያ ነው።…
 እንዲህ ነው እንግዲህ የዝንጋታቸው ጥግ። ምንዱባኑን አፍሪካዊም ሆነ ቅንጡውን አውሮፖዊ  ህይወት በዝንጋታ ገመድ እየጎተተች ወደመቃብሩ ታደርሰዋለች።።
    እስከ   ዛሬ ድረስ እንኳ ስንት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣አባትና እናቶቻችን  በዝንጋታ ገመድ እየተጎተቱ በሞት ተለዩን?
     ይህ ትውልድም እንደትናንትናው ትውልድ ፣ ሞትን በጉያው ይዞ እንደሚቀሳቀስ እና በሞት ሰልፍ ውስጥ እንዳለ የዘነጋ ነው።
     ትውልዱ፣ “ሁሌም የሚሞተው በሬሣ ሣጥን ውስጥ ያለው ብቻ እንደሆነ ፤”እያሰበ በሞኝነቱ መፅናናቱን አስካላቆመ ጊዜ ድረስ፣በዚች ሀገር  ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ለውጥ ማምጣት አይቻልም።
         በልቶ ከመሞት ይልቅ፣ከአድማስ ባሻገር የምትታይ፣ የበልፀገች፣የታፈረች እና የተከበረች ልዕለ ኃያል የሆነችውን ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ በንፁህ ልብ እና በሃቅ መስራት፣ይሄ ወቅት ይጠይቀናል።(ሥላልፈጠርነው መሬት የምንጨነቀውን ሩቡን ለዜጎች ብንጨነቅ በኢትዮጵያ ህይወት መራራ አትሆንም ነበር። )
      ይሁን እንጂ ብዙዎቻችን፣ የፍቅር ትርጉም ንፁህ ልብ መሆኑ አልገባንም።
       በፍቅር ሰውን ሁሉ መማረክ ይቻላል ብለው የሚያምኑት ንፁህ ልብ ያላቸው፣   አንድ ቀን እንደሚሞቱ የሚገነዘቡ ናቸው።
     እኔ የአለም ሰው ነኝ።እንደ ሰው ራሴን ከቆጠርኩ።ኃየማኖት ካለኝ (ክርስትያን ወይም ሙሥሊም ከሆንኩ፣  ሰው ወይም እኛ ፣  7 ቢሊዮን የሆነው ከሁለት ሰዎች ተነስተን ነው። በመዋለድ ።3,000 ሺ ዓመት ወደኋላ ተጉዘን ታሪክን ብንፈትሽ ፣ በዛን ዘመን በዛሬዋ ኢትዮጵያ ስንት ሰው ይኖር ነበር???1,000,000 ?2,000,000?5,000,000 …?እነዚህ ሁላ  ግን ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነበሩ። እነዚህ እንደሞቱ ሁሉ እኔም እሞታለሁ የሚሉ።
         እርግጥ ነው፣ተራ ሞቹ ሰው፣በጣም ግልፅ የሆነውን ፣በየቀኑ የሚመለከተውን፣የሚያስተውለውን፣ እና ተጨባጭ የሆነውን ሞት እንኳን ይዘነጋል። (እንዘነጋለን)ለዚህም ነው፣”የሰው ሁሉ የክፋት ምንጭ የሞትን መኖር መዘንጋት ነው።”የሚባለው።