/

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ድባብ – ዋልያዎቹ ከሌሴቶ ያደርጉት ጨዋታ -ታርቆ ክንዴ

1 min read

“90 ደቂቃ ያለእረፍት ከጎናችን በመሆን ያበረታንን ደጋፊ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡” አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ
“በቴክኒካል አቅሙ ከፍ ያለ እና ጥሩ ቡድን የገነባውን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ፡፡” አሰልጣኝ ታቦ ሴኔንግ

ለ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የሌሴቶ አቻውን በማስተናገድ የጀመረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ያለምንም ግብ ተለያይቷል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን የሰጠው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ “ከምንግዜውም በተሻለ ጥሩ ተጫውተናል፤ በርካታ የግብ እድሎችንም መፍጠር ችለናል፤ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎላ የመጣው የአጥቂ መስመር ክፍተት ጎል ሳናስቆጥር እንድንወጣ አድርጎናል” ብሏል፡፡
በቀጣይ ጊዜ ግብ የማስቆጠር ችግራችን ለመቅረፍ በርትተን እንሰራለንም ብሏል አሰልጣኙ፡፡

ተጫዋቾቼ 90 ደቂቃ ሙሉ የአቅማቸውን አድርገዋል ያለው አሰልጣኙ በተጫዋቾቹ እንቅስቃሴም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ “በጨዋታው የተቃራኒ ቡድናችን የጨዋታ ዘይቤ አይተናል፤ የእኛን ስህተት አርመን በመልሱ ጨዋታ ለማሸነፍ እንጫዎታለን፤ 90 ደቂቃ ያለእረፍት ከጎናችን በመሆን ያበረታንን ደጋፊ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ” ብሏል አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ፡፡

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር ያለው የሌሴቶ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ታቦ ሴኔንግ ኢትዮጵያ በቴክኒካል አቅማቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾች አሏት፤ በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም እኛ በመከላከል የተሻልን ስለነበርን ግብ ሳይቆጠርብን ወጥተናል ብሏል፡፡

“ለሚቀጥለው ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን፤ በቴክኒካል አቅሙ ከፍ ያለ እና ጥሩ ቡድን የገነባውን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ” ብሏል አሰልጣኝ ታቦ ሴኔንግ።

የመልሱ ጨዋታ ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሌሴቶ ይካሄዳል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.