ከልቡ የሚመርቅ እና የሚገስጽ ሽማግሌ አያሳጣን (በታምሩ ገዳ)

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

የኢትዬጵያኖች የዘመን መለወጫን በዓል በማስመልከት በብሔረዊ ቤ/መንግስት ውስጥ ተካሄዶ በነበረው ልዩ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች ካቀረቡት ወጣት የጥበብ ሰዎች መካከል በበሳል ግጥሞቿ የብዙዎች ስሜትን ለመኮርኮር እና ቀልብን ለመሳብ የቻለችው ወጣት ገጣሚት ህሊና ደሳለኝ ከአንድ ታዋቂ እና አንጋፋ ኢትዬጵያዊ ዲፕሎማት ታላቅ አክብሮት ተቸራት።

ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በታደሙበት “ጷጉሜን በመደመር፣ብሔራዊ አንድነት ሀገር በሕብር” በተሰኘው ምሽት ላይ የማጀት ስር ወንጌል” በሚል ርእስ ድር ግጥሟን የቀረበችው ወጣት ገጣሚት ህሊና ደሳለኝ በግጥም ስንኞቿ ውስጥ “ከመንጋ ፖለቲካ እንውጣ፣ ረቂቅ እና ክቡር ለሆነው ለሰው ልጅ ክብር እንስጠው ፣አይምሯችንን አናጥብበው፣ የልዩነት ግንብን ከመገንባት የአንድነት ድልድይ ግንባታ ላይ እናተኩር ፣በኢትዬጵያ ሰላም እና አንድነት ላይ በጭራሽ መደራደር የለብንም…ወዘተ” በማለት በብዕራ መክራለች።

ገጣሚት ህሊና ደሳለኝ በግጥም ስንኞቿ የማንንም ብሔርን ፣ዘርን ፣ሀይማኖትን፣ቋንቋን እና ጾታን ሰትነካ ላቀረበችው ልብን የሚያረሰርሰው ግጥሟን ያዳምጡ አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃኖች እና አክራሪ አቀንቃኞች( እክቲቪስቶች ) ተብዬዎች ምን ያለበት እንዲሉ ” ግጥሙ እኛን በእጅ አዙር ለመንቀፍ ታስቦ ነው” በማለት ሰሞኑን አቧራ ለመስነሳት መውረግረጋቸው ተስተውለዋል።

ታዲያ ከወጣትነት እድሜ የመነጠቀው የግጥም ለዛዋ እና መልእክቱ ከአጥንታቸው እና ከደማቸው ዘልቆ የገባው በቀኃስ ዘመን በተለያዩ ከፍተኛ ሀላፊነት ላይ ኢትዬጵያን እና ህዝቦችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነት ያገለገሉት እና ዛሬም የዚህች አገር ጉዳይ እንደ እሳት ከሚያንገበግባቸው ስመ ጥር እና የቁርጥ ቀን ኢትዬጵያኖች መካከል አንዱ የሆኑት አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ገጣሚት ህሊና ደሳለኝን በተመለከተ በሰጡት ሰሞነኛ አጭር አስተያየት” የተገባደደው የኢትዬጵያኖች የዘመን መለወጫ ዋዜማ አንድ መቶ አምስት ሚሊዬን ለሚገመት ህዝቧ እንዲት ታላቅ ጀግና አበርክቶልናል፣ እርሷም ህሊና ደሳለኝ ነች። ወጣቷ እና ደፋሯ ህሊና ደሳለኝ ፣ዘረኞችን ፣አገርን በጠራራ ፀሐይ ለመዝረፍ ፣መጻኢ እድላችንን ለማጨለም የወጠኑትን በአደባባይ ተቃውማለች።ለዚህች ወጣት ገጣሚት ለድፍረቷ፣ለጅግንነቷ ፣ለአስተዋይነቷ ልዩ አክብሮት አለኝ” ብለዋል።

አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር እምሩ ዘለቀ አስተያየታቸውን ሲያራዝሙም ወጣቷ ህሊናን ደሳለኝን “እመቤቴ” በማለት ከቀደምት የኢትዬጵያ እንስት ጀግኖች መካከል ተጠቃሾች ከሆኑት ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል እና ከጦር አርበኛዋ ሸዋረገድ ገድሌ ጋር አመሳስለዋታል።

ስድቡ፣ሙገሳው፣ሽልማቱ፣እርግማኑ በደቦ(በቲፎዞ) ፣ማጥላላቱ በደቦ ፣ጭብጨውም እንዲሁ በደቦ በሆነበት ፣በተቃራኒው መደማመጥ እና መከባበር በጠፋበት በዚህ ዘመን ከልብ የመነጨ እውነተኛ ክብር፣ምርቃት እና ውዳሴን መስጠት እና ለመቀበልም መብቃት መታደል ነው።

ኢትዬጵያን እና ህዝቦቿን ከምእራብ አፍሪካዊቷ ጋና እስከ ጀርመን፣ስዊዲን፣ፈረንሳይ በአምባሳደርነት እና በዲፕሎማትነት በማገልገል ከዚያም አልፎ በተለያዩ ጌዜያት በተባበሩት መንግስታት ጉባኤዎች ላይ በልዩ ልኡክነት በመገኘት ለኢትዬጵያ ከፍታ ሲሉ ፣ የግል ጥቅም ሳያሸንፋቸው ያገለገሉት አምባሳደር እምሩ ዘለቀ የልጅ ልጅ፣ልጅ፣ልጃቸው ለትሆነው የምትችለው ገጣሚት ህሊና ደሳለኝን “እመቤቴ ነሽ” ብለው እራሳቸውን ዝቅ አድርገው መጥራታቸው ቅዱስ መጽሐፍ “እራሳቸውን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉ ከፍ ከፍ ይላሉ” እንደሚለው ለብልህነታቸው እና ለታላቅነታቸው ማሳያ ሲሆን ለወጣት ገጣሚት ህሊና ደሳለኝም ቢሆን ይህን አይነቱን ምርቃት እና ውዳሴ ከአገር ባለውለታ እና ከታላቅ አባት ለማግኘት መብቃቷ ለአወቀበት ከአላፊው እና ከጠፊው ከአልማዝ ፣ ከወርቅ እና ከገንዘብ (አዱኛ) እንዲሁም ነገ ከጆሮቻችን ከሚጠፋው ሆሆታ እና ጭብጨባ የላቀ ነው። ፈጣሪ ለኢትዬጵያ እና ለህዝቦቻችን አንድነት ከልብ የሚጨነቅ የሚጸልይ፣ልጆቿንም የሚመርቅ እና የሚገስጽ ሽማግሌ አያሳጣን።

(በታምሩ ገዳ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.