ኢሕአዴግ ዛሬ እና ትላንት (ፍትሕ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሁፍ)

1 min read

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ‹ቲም ለማ›ን በመምራት፣ በኦሮ-ማራ ጥምረት በመንጠላጠል፣ ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ስንጥቃት በመመርኮዝ የምንሊክ ቤት-መንግሥትን ከረገጡ 18 ወራት አስቆጥረዋል።
በዚህ ዐውድ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚንስትሩ (በመንግሥታቸው) የተስተዋሉ ተጻርዮሽ ንግግሮች (እርምጃዎች) በቀጣዩ አዲስ ዐመት እንዳይደገሙ የተወሰኑትን በማሳያነት ጠቅሰን እናሳስባለን።

የርብ ግድብ

በዐማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ‹በአራት ዐመት ተገንብቶ ያልቃል› ተብሎ የተጀመረው የ‹ርብ መስኖ ልማት ግድብ› አስር ዐመት ፈጅቶ፣ ከተያዘለት የ1.1 ቢሊዮን ብር፣ ሁለት እጥፍ (2.7 ቢሊዮን ብር) ተጨማሪ ወጪ ጠይቆ፣ በወርሃ ጥቅምት ዶ/ር ዐቢይ መጠናቀቁን አብስረው ተመርቋል። በወቅቱ ባደረጉት የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግርም፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ዘርዝረው ሲያበቁ፣ ‹ዳቦውም ቅርጫቱም በእጃችን ገብቷል› አይነት አንድምታ ያለው መልዕክት ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
ይሁንና ግድቡ ‹ተመረቀ› ከተባለ አስር ወር በኋላም ያለመጠናቀቁ ምስጢር ሾልኮ ወጥቷል። ሁነቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን በዘመነ ኢሕአዴግ ካየናቸው መሪዎች ተርታ አሰልፏቸዋል። በምረቃው ዕለት በተላለፈው ፕሮፓጋንዳ ‹ከዚህ በኋላ አልፎልሀል› ተብሎ የተዋሸው የአካባቢው ነዋሪ፣ ግድቡ ባለመጠናቀቁ ተጠቃሚነቱ ቀርቶ ያለውንም የሚያሳጣው ክፉ-ባለጋር ሆኖበታል። የግድቡ ውሃ በሚሞላበት ጊዜ ‹ማስተንፈሻ› የሚሆነው ግንባታ ዛሬ ድረስ ባለመሰራቱ በክረምቱ ምክንያት ከባድ አደጋ እያደረሰ እንደሆነ መንግሥታዊ ሚዲዎች ጭምር ዘግበውታል። በቅርቡ ባስከተለው አደጋ ሁለት ሰው ከመሞቱም በላይ፣ በአካባቢው ያሉ ሩዝ አምራች ገበሬዎች ከምርታቸው ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው ወድሞባቸዋል፣ መኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ፈርሷል፣ ንብረታቸው ተወስዷል፣ በርካታ የቤት እንሰሶች ሰጥመውባቸዋል።
እንዲህ አይነቱ ተራ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ከሩብ ክፍል ዘመን በላይ ሲተገበር የቆየ ሲሆን፤ በሕዝብና መንግሥት መካከልም ለተፈጠረው መንፈራቀቅ ገፊ-ምክንያት እንደነበረ በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የተዘነጋ ይመስላል።

ትላንትን ያስናቀ ብክነት

ኢሕአዴግ ባለፉት ሁለት አስርታት መንገራገጭ በገጠመው ቁጥር የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን የመንግሥት ገንዘብ በመርጨት ለማባበል ጥረት ያደርግ እንደነበረ ይታወሳል። ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሆነው የኢንጅነር ታከለ ኡማ አስተዳደር የከዚህ ቀደሙን ብክነት ባስናቀ ደረጃ ከፍተኛ ገንዘብ ለወራት ሲያባክን መቆየቱ የ2011 ዓ.ም አስደንጋጭ ዜና ሆኗል። በሚዲያ ጭምር በተላለፈ ማስታወቂያ በተደገፈ ጥሪ ለወጣቶች በ‹ብድር ስም› በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መበተን፣ ‹መጣ› የተባለው ‹ለውጥ› ተቋማዊ አይደለም ወደሚል ጠርዝ ይገፋል።
በ2009 ዓ.ም በሕዝባዊ ተቃውሞ ከባድ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ የነበረው የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግሥት፣ ‹በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ሥራ-እጥ ወጣቶች አከፋላለሁ› በሚል 10 ቢሊዮን ብር በ‹ተዘዋዋሪ ፈንድ› መድቦ እንደነበረ ይታወቃል። ከዚህ ውስጥ የ2011 ዓ.ም ቀሪ ድርሻውን ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የወሰደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ተጨማሪ 2 ቢሊዮን ብር በመመደብ የተለመደውን የብድር አሰጣጥ ሂደት ባልተከተለ መንገድ፣ ለአንድ ሰው ከግማሽ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሲያድል ቆይቷል። ጉዳዩ ሚዲያና ሕዝብ ጋር ደርሶ መነጋገሪያ ሲሆን፣ የወል ተጠያቂነቱን፣ የብክነቱን ‹ፕሮጀክቱ› ወደ አስፈፀመው ‹አዲስ ብድርና ቁጠባ› ተቋም ኃላፊ በመወርወር፣ ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርጎ ነገሩን ለማድበስበስ ተሞክሯል።

ከእስራኤል መልስ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ 10 ቀናትን የፈጀ ጉብኝት በኮሪያ፣ ጃፓን እና እስራኤል አድርገው ነሐሴ 26 ምሽት አገራቸው ተመልሰዋል። ለይፋዊ የሥራ ጉዳይ ከሄዱባቸው አገራት መሀልም ‹የመጀመሪያ ሊባል› የሚችል የፊት-ለፊት ተቃውሞ በእስራኤል ገጥሟቸዋል። ይሁንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከተሳተፉበት ከዚህ የተቃውሞ ትዕይንት ይልቅ፣ ጠቅላዩ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ክስተቱን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት አሸማቃቂና የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሆኗል።
አውራ ጓዳና ላይ የወጡት ከመቶ የሚበልጡ ሰልፈኞች በዋነኛነት የሴራ ፖለቲካ እንዲቆም እና በግፍ የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ ሲጠይቁ በማኀበራዊ ሚዲያ የተመለከትናቸው ቢሆንም፤ በሁነቱ የተበሳጩት ዶ/ር ዐቢይ ሚዲያ ፊት ቀርበው ከእውነታው ጋር ፍፁም የሚቃረን፣ ከአንድ አገር መሪ የማይጠበቅና አሽሙር የተቀላቀለበት አስተያየት ሰጥተዋል። አጋጣሚው ርሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ‹ከወዳሴ በቀር ምንም ነገር መስማት አይፈልጉም› በሚል የሚነቅፋቸውን የማኀበረሰብ ክፍል ሙግት አጠናክሯል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ለማስተባበል በሞከሩበት ወቅት ቃል በቃል እንደሚከተለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡-
‹‹አንድ አስር የሚጠጉ ሰዎች፣ አስራ አምስት ሰዎች አላውቅም፣ እኛ ቴላቪቭ እያለን እዚህ ለስሞታ መጥተው ነበር ሲባል ሰምቻለሁ። ግማሾቹ ኤርትራውያን ናቸው ቢባልም፣ የእነዚህ ሰዎች ዋናው መልዕክት የ‹አሳይለም› ጉዳይ ነው። ‹አሳይለም› ላይ ያላቸውን ጉዳይ ለመንግሥት በሚያሰሙት ተቃውሞ የእስራኤል መንግሥት ‹አቴንሽን› እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ።››
ይህ በተቃርኖ የተሞላና በስህተቶች የታጨቀ ምላሽ ነው። በኢሕአዴግ ቤት የተለመደውን ቁጥር የመሸቀብ ስልት ከመድገማቸው በተጨማሪ፣ በአይናቸው እንኳ ያላዩአቸውን ሰዎች ‹ኤርትራዊያን ናቸው› ሲሉ ኢ-ምክንያታዊ ሆነው ፈርጀዋቸዋል። መቼም በወቅቱ ሰልፈኞቹ በእጃቸው የያዙት መፈክር እንጂ፣ ፓስፖርት እንዳልነበረ የታወቀ ነው። የጠቅላዩን መከራከሪያ ‹ይሁን› ብለን ብንቀበል እንኳ፣ አጀንዳው ‹አሳይለም› ከሆነ ኤርትራውያን፣ የኢትዮጵያን መሪ በመቃወም የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት የሚያገኘው በየትኛው አገር ሕግና አመክንዮ እንደሆነ ከርሳቸው በቀር የሚያውቅ የለም።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከወዲሁ መላመድ ያለባቸው ቁም-ነገር፣ እንዲህ አይነት መረር-ከረር ያለ ነቀፌታ ከዚህ ቀደም በተጨበጨበላቸው አገራትም ጭምር የሚጠብቃቸው መሆኑን ነው። በተጠለፈ አብዮት ቀርቶ፣ በተወደሰ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን የያዘ መሪም፣ በበሰበሰ ቲማቲምና በገማ እንቁላል የ‹ደመቀ› አቀባበል ሲደረግለት ደጋግመን አስተውለናል። እናም ከሞላ ጎደል ከእንዲህ አይነቱ ውግዘት የመታደጊያው አማራጭ አገሪቱን ከእውነተኛ ማሸጋገሪያ ባቡር ላይ ማሳፈር ብቻ ነው። በተቀረ የያዙት ወንበር፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ መንግሥታዊ ግፍና መከራ የሰርክ ተግባር በሆነበት አገር፣ ከጭብጨባ ይልቅ ተቃውሞ የቅርብ ጎረቤት መሆኑን አለመዘንጋት ቢያንስ የብስጭትና ንዴት መጠንን ለመቀነስ ይጠቅማል።
በነገራችን ላይ መንገዱ አንዲህ እንደ ዛሬው መሰናክል እየበዛው፣ ምሬቱም እየናረ ከሄደ፣ ከቤተ-መንግስት እስከ ማባረር እንደሚያደርስ ተገንዝቦ መዘጋጀት ብልህነት ነው።

የትምህርት ሚንስትር ‹ግሽበት›

የትምህርት ሚኒስትር በዚህ ሳምንት ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ችግር የሰጠው የ‹መፍትሔ› እርምጃ አደገኛ ስህተት ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም። በትውልድ ላይ የዘር-ማጥፋት ወንጀል ከመፈፀም ተነጥሎ የማይታይ ነው።
የ2011 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ውጤት መለቀቅን ተከትሎ፣ የፈተና ወረቀቶቹ ከመርሀ ግብሩ አስቀድሞ ስለመሰረቃቸው መረጃ ያለ ለማስመሰል መሞከሩ ይታወቃል። ጉዳዩን የበለጠ አደናጋሪ ያደረገው ደግሞ ተቋሙ በሰጠው መግለጫ ላይ የ‹ውጤት ግሽበት› ከማለት ያለፈ የተብራራ ነገር አለመኖሩ ነው። የዚህ ምክንያት ምንድን ነው? የተማሪዎቹ ብቃት የፈጠረው ነው? ወይስ በዘወርዋራ እንደተናፈሰው የፈተናው ጥያቄዎች መጀመሪያውኑ ተሰርቀው ወጥተው ስለነበረ?
በርግጥ ይህ ነውረኝት ተፈፅሞ ከሆነ፣ ብቸኛው ተጠያቂ መንግሥታዊውን ኃላፊነት የተረከበው አካል እንጂ፣ ለዐመታት የለፉና የተጉ ተማሪዎች የሚሆኑበት ምክንያት የለም። ትክክለኛውና ተመጣጣኙ እርምጃም አጥፊዎቹን ለሕግ ማቅረብ፣ ተማሪዎቹን ደግሞ እንደገና መፈተን ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የሲቪክስ፣ ታሪክ፣ ፊዚክስ እና ኬሚስትሪ ትምህርቶችን ውጤት ‹በጅምላ ደምስሻለሁ› የሚል ፍርደ ገምድልነት፣ በየትኛውም አገር፣ የመንግሥት መፍትሔ ሆኖ አያውቅም።
መቼም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በየቀበሌው እንደ ፈንድሻ በሚበተንባት ኢትዮጵያ፣ ተማሪዎቹን በድጋሚ ለመፈትን የአቅም ችግር እንደ ምክንያት ይጠቀሳል ተብሎ አይገመትም። እናም ለረዥሙ የህይወት ዘመን ተስፋ ሰንቀው ለዐመታት ሲደክሙ የነበሩ ተማሪዎች ሂሳብ ማወራረጃ የሚሆኑበት አመክንዮ ስለሌለ፣ ውሳኔውን በቶሎ መቀልበሱ የተሻለ ነው።
በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱት የ2011 ዓ.ም ግዘፍ-የነሱ ግድፈቶች እና ተቋማዊ ምንግዴነት የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥትን ገመና አደባባይ ማስጣቱን መካድ አይቻልም። በርሳቸው አንደበት የተነገሩ ተጣራሽ አንድምታ ያላቸው መልዕክቶችም የፖለቲካውን አካሄድ የሚጠቁሙ ተደርገው ይወሰዳሉ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.