አማራጭ የሌለው የሠላም ጎዳና   (ጆቢር ሔይኢ-ከሁስተን ቴክሳስ)

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

ኢትዮጵያ አገራችን የብዙ ብሔር ብሔርሰብ አገር ነች፡፡እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብም የራሱ ቋንቋ፤ባኅል፤እምነት፤ ታሪክና የምኖሪያ አካባቢ አለው።  ነገሥታቱ ሲያስከብሩ የቆዩት ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን፤ባኅል፤ ቋንቋና እምነታቸውን ነበር። ቤተ ክርስቲያን እንኳ ከሕዝቡ ከተወረሰው መሬት  የሲሶ መንግሥት ይዞታ ነበራት።

ከዚህም የተነሳ የምሥራቅ፤የደቡብና የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፤  አብዛኛው በመደብ፤ በብሔርና፤ በሃይማኖት ጭቆና ሲማቅቁ ኑረዋል።ስለሆነም ሥርዓት ካስከተለባቸው ጭቆና ነጻ ወጥተው በእኩልነት መኖርን ይፈልጋሉ።

በአንፃሩም  በመሳፍንታዊ አገዛዝ  ርስታቸው ያልተነጠቀ፤  ባህል፤ ቋንቋና እምነታቸው የተስፋፋ የቀደመውን ሥርዓተ መንግሥት ያወድሳሉ፤ወደ ሥልጣን እንዲመለስም ይፈቅዳሉ።

ከዚህም የተነሳ በሕዝባችን መካከል መሠረታዊ የአቋም ልዩነትና የጥቅም ግጭት አለ።ይህ የአቋም ልዩነትና የጥቅም ግጭት ሳይፈታ፣ በተስፋ ተደመር፣ እርጥብን ከደረቅ ጋር ማጋጋም ይሆናል።ስለዚህም በቅድሚያ  የሕዝቡን መሠረታዊ ችግር ፍትቶ መደመሩን ማስከተል ይገባል።

ይህን ቅራኔ ለመፍታት ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ በብዙ ጥረዋል፤ ግን አደረጃጀታቸውና አቋማቸው ስላልፈቀደ ከሁለቱ  መካከል በመዋለል ከሁለቱም ሳይሆኑ ቀሩ። በመሠረቱም ተቃራኒ ፍላጎት ያለውን ኅብረተሰብ በአንድ ፓርቲ ለመምራት መሞከር ራሱ ስሕተት ነው።ለዚህ ነው ተወዳዳሪ ፓርቲ ያስፈለገን።

ለዚህም በቅድሚያ የሕዝባችን ፈቃድ ማወቅ ያስፈልጋል። ከዕድገት ደረጃችን፤ ከመልካ ምድር አቅማመጣችን፤ ከኢኮኖሚ ትስስራችን  አንፃር፤ መከተል ያለብን ርዕዮተ ዓለም የቱ ነው?ሕብረተሰባችን ወዴት ነው ማደግ የሚፈልገው? ምን ዓይነት ማኅበራዊው  አደረጃጀት  እንዲኖረው ነው የሚሻው፣  ባህሉ ፤ቋንቋውና እምነቱ እንዴት እንዲከበሩለት ነው የሚወደው፣ ይህንንስ ማን ነው የሚያጠናለት? ከመደብ ጥቅሙ፤ ከብሔር  ማንነቱ ፤ከባኅሉ፣ ከቋንቋውና ከእምነቱ ነጻ የሆነ ማን ይገኛል? ከተግባር እንደምናየው፣ ሁሉም  የራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስቀደም ነው አሸምቆ የሚገኘው።

የተወዳዳሪ ፓርቲ ምሥረታን በሚመለከት ኢሕአዴግ ከንድ መቶ በላይ የሆኑ  የፖለቲካና የብሔር ድርጅቶችን አሰባስቦ ፓርቲ አንዲ መሠርቱ መድረክ አዘጋጅቶላቸዋል። በተወዳዳሪ ፓርቲነት ለመደራጀት የቀረቡት ግን ልክ  እንደ  ኢሕአዴግ  ከህብረተሰቡ በጅምላ የወጡ ናቸው። በመሆኑም በመካከላቸውም መሠረታዊ ቅራኔ አለ።

ወታደራዊው ደርግ በአፍላ የሥልጣን ዘመኑ፤ ምሁራንን ከውሮፓና ከአሜሪካ ሰብስቦ፤  የሕዝብ ደርጅትን መሥርቶ፤ኅብረት ፈጥረው አንድ ፓርቲ እንዲመሠርቱ ኃላፊነት ሰጥቶአቸው ነበር። ምሁራኑ ግን  ራሳቸውን እንደ ኮሚኒስት ፓርቲ በመቁጠር፤ የጭቁን ሕዝቦች ድርጅት ከነበርው  ከኢጭአት ጋር አንደራጅም በማለት  ሲሻኮቱ ቆይተው፤ መድረኩን ለደርግ  አመቻችተው፤   ወደ ስደታቸው ተመለሱ  እንጂ፤ሕዝቡን  ለመንግሥት ሥልጣን አላበቋም።

በሽግግር መንግሥት ምሥረታ ወቅትም የብሔርና የፖለቲካ ድርጅቶች፤በአቋም ከኢሕአዴግ ተለይተው በተወዳዳሪነት ለመቆም ፈልገው ነበር፤ ግን ማናቸው ከማንም ጋር አልተዋሃዱም አንዱ ሌላውን ሲተች፤  የሁለት አመት ዕድሜ እንኳን  ሳይኖራቸው ነው፣ ተራ በተራ በኢሕአዴግ ተገፍተው የወደቁት።ይህም ለኢሕአዴግ በተለይም ለሕወሐት ሠፊ በር ከፈተ፤ኦነግ በለቀቀው ቦታ ተተካ። ከዚያም ያለ አንዳች ተቀናቃኝ ቁልፍ የሥላጣን ቦታዎችን ተቆጣጠረ።

ከዚህ አንጻር ካየን ዛሬስ  የብሔርና የፖለቲካ ድርጅቶች በጅምላ ተሰባስበው ምን ዓይነት ተወዳደር ፓርቲ ሊመሠርቱ ነው?ያሰኛል።ሌላው ደግም  በአገራችን  ለሃያ ሰባት አመት በመንግሥት ሥልጣን  ላይ የቆየነ፤ ሕዝቡን  አንድ ለአምስት በሥሩ  ያደራጀ ፓርቲ  በሥልጣን ላይ ይገኛል።  ሓቁ ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ፤ ከስደት ተመላሾች  የማንን ሰርጎ ገብ ነው፤ በማን ላይ የሚያደራጁት? ታሪክ ራሱን እንዲደግም ካልተፈለገ በቀር።

ከዚህስ ይልቅስ  ከስደት ተመላሾቹ ራሳቸው፤ እንደየ አቋሟቸው ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር ቢዋኻዱ  የሚሻል ይሆናል። አገሪቱን እየመራ ያለው የኢሕአዴግ አባላትም፤ ከዓቋሟቸው አንጻር  በሶስት ጎራ ቢሰለፉ፤ ባላቸው ልምድና ሥልጣን በመታገዝ ደከም የሚሉትን በይበልጥ ሊያጠናክሩ ይችላሉ።

ይህን ግልፅ ለማድረግ፤  በአገልግሎት ላይ ያለው  ሕገ መንግሥት  የብሔር ብሔረሰብን የራስን ዕድል  በራስ የመወሰን  መብት ይፈቅዳል፤ በአፈጻጸም ረገድ ግን ችግር አለበት።ሌላው ቀርቶ  የብሔር ጥያቄ ያነሱ    የኢሕአዴግ አባላት እንኳ   በጠባብ ብሔርተኝነት ተወንጅለው ከድርጅቱ ይባረሩ ነበር።አንዳንዶችም የአንድ ሳንቲም ግልባጮች ናቸው፤ እየተባሉ   በማንነታቸው ሲከሰሱ  ነበር።

በርግጥም የቋንቋ ጥያቄ ሁሉንም በየጎራው የሚያሰልፍ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጥያቄ ላይም፤ የኢሕአዴግ አባላት በአንድ ጎራ ተሰልፈው አያውቁም።  በአቢዮታዊ ዲሞክራሲ፤የአንድ ፖለቲካ ማህበረሰብ አደረጃጀትንም በሚመለከትም፤ማን አቢዮታዊ ፓርቲ፤ማንስ የብሔር ድርጅት   እንደሚሆን  ግልጽ አቋም አልነበራቸውም።

ሕገ መንግሥቱ  “ከታሪካችን የወረስነው የተዛባ ግንኙነት መኖሩን” ይፋ ያደርጋል። ከታሪካችን ከወረስነው የተዛባ ግንኙነት ደግሞ ዋናው፤ የብሔር ብሔረሰብ ጭቆና ነበር። የዓለም ሕዝቦች የዚህ ዓይነቱን ጭቆና፤  ከቅኝ ገዥዎች ቀንበር ጋር  ከትከሻቸው አሽቀንጥረው ጥለዉታል።በአገራችንም ጀብሓና ሻቢያ፣ ሕወሐት እና የኦሮሞ ድርጅቶች፣የሱማሌ፣ የአፋር፣የሲዳማ፣የከፋና የሌሎቹም የብሔር ብሔረ ሰብ ድርጅቶች፣ ለሕዝባቸው ነፃነት ከመሳፍንትና  ከወታደራዊ መንግሥት ጋር ታግለዋል።

በትግሉም ኤርትሪያውያን  ሙሉ ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ፣  ከሕወሐት ጋር አንድነትን የመረጡት ግን፤አሁንም የእኩልነትን መብት አልተጎናጸፈም።በመሆኑም በብሔር ጥያቄ አፈታት  ረገድም በኢሕአዴግ አባላት መካከል የአቋም  ልዩነት አለ።

ከዚህም የተነሳ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በየብሔራቸው በፓርቲ  ተደራጅተው፣በመንግሥት ባጀት ልዩ ኃይል በማሰልጠን፣  ሕዝቡን በብሔር፣በጎበዝ አለቃ፣በአባት ጦር፣ በእድሜ፣ በሙያና፣ በሃይማኖት ለያይተው ለፍልሚያ በማዘጋጀት፣ ፌድራላዊውን መንግሥትና ሕገ መንግሥቱን በመፈታተን ላይ ይገኛሉ።

ስለዚህም ከሕዝባችን ጥያቄዎች አፈታት ረገድ ፤ተመሳሳይ አቋምና ስነ ሊቦናዊ ዝይቤ ያላቸው  የኢሕአዴግ አባላትም ሆኑ ተቃዋሚዎች፣መለስተኛ ቅራኔዎችን በማቻቻል፣ እንደ ሕዝባቸው ፈቃድ፣ ከአዴፓ ከሕወሐትና ከኦዴፓ ጋር በማበር በፓርቲ ቢደራጁ፣ በተመጣጠነ ኃይልና ሥልጣን በመጠቀም፣ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ወደ ዴሞክርሲያዊ ሥርዓት ሊያሸጋግሩን ይችላሉ።

የትምህርትና የሥራ ቋንቋን በሚመለከት፤  ከቋንቋዎች ሁሉ  ይልቅ እንግሊዘኛ ፤በሳይንስና በቴክኖሎጂ ቃላት በጣም የበለጸገ፤ የጥበብ ማሰራጫ፤ የዓለም ሕዝብንም እርስ በርስ የሚያግባባ ቋንቋ ነው።በአገርችንም አማርኛ የአጼ ምንሊክ ቋንቋ  ስለ ነበር፤ በግዛታቸው ሁሉ የሥራ ቋንቋ ሆኖ፤ ከላይ ወደ ታች ወረደ። ይሁንና አማርኛ እንደ እንግሊዝኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ቃላት የበለጸገ አይደለም፤ከኢትዮጵያ ውጭ አማርኛ ተናጋሪ የሆነ ሕዝብ ያለው አገር የለም። የዓለም ሕዝብ እየተማረ ያለው አንደበቱን በፈታበት ቋንቋ ነው። ትምሕርት በጀመረውም ቋንቋ እስከ መጨረሻው ይማራል።ከእኛ  በስተቀር ቋንቋ በመቀያየር  በትውልዱ ላይ ችግር የሚፈጥር አገር የለም።

አብዛኛው የዓለማችን ሕዝብ እየተግባባ ያለውም  በእንግሊዘኛ ቋንቋ  ነው፤ የአፍሪካ አገሮችም እንዲሁ።በአገራችንም  ቢሆን ቀድሞ የትምህርት ቋንቋችን  ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ እንግሊዘኛ ነበር። ዛሬም ቢሆን ሃብታሞችና ባለሥልጣኖች ከአጸደ ሕፃናት ጀምረው ልጆቻቸውን በእንግሊዘኛ እያስተማሩ ናቸው። በቋንቋዎች መቀያየር ተጠላልፈው እየወደቁ ያሉት የገበሬዎችና የድሃ ልጆች  ናቸው።

እስከ አሁን  ያለው የቋንቋ በየፌርማታው መቀያየርና የተምህርት ጭነት አለመመጣጠን  አገራችንንና ሕዝባችንን እጅግ እየጎዳ ነው፤ አንደበታቸውን በአማርኛ የፈቱ የከተማ ልጆች፤ እንግሊዝኛን ብቻ ነው አዲስ ቋንቋ  የሚማሩት፤ በሌሎች ቋንቋዎች አንደበታቸውን የፈቱ ተማሪዎች ደግሞ  ሁለት አዲስ ቋንቋ፤ማለትም አማርኛና እንግሊዘኛ የመማር ግዴታ አለባቸው። ከዚህ የትምሕርት ጫና ልዩነት የተነሳ ብዙዎቹ በፈተና ይወድቃሉ፤ፈተናውን ያለፉትም ቢሆን ነጥባቸው አነስ ስለሚል ከፍተኛ ትምሕርት የመከታተል ዕድላቸው የመነመነ ነው።      ሌላው ቀርቶ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው እንኳን፤ በእንግሊዘኛ ከተማሩት  ጋር   በመወዳደር ሥራ ማግኘት ስላልቻሉ፤ወደ ግብርናና ንግድ መመለስ ግድ ሆኖባቸዋል።

አገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና ናት፤ከምሥራቅ አፍሪቃ አገሮችም ጋር በኢኮኖሚ የተሳሰረች ነች፤ነገር ግን የመግባቢያ ቋንቋችን  እንግሊዘኛ ባለመሆኑ፤ እንደሚገባ የዕድሉ ተጠቃሚ አልሆንም።ስለዚህም ብዙ የአፍሪካ ቅርንጫፎች በናይሮቢ እየትከፈቱ ናቸው።ቀድሞም እኮ ቢሆን ለኤርትራ ከኢትዮጵያ መለየት መንስኤው ይሔው የቋቋችን ጉዳይ ነበር። በመሆኑም ከጎሮቤቶቻችን ጋር ለመተባበርም ሆነ፤ ከመጠቀው ካዓለም ሥልጣኔ  ጋር እኩል ለመራመድ፤እንደ አፍሪካና ኤሽያ አገሮች የቋንቋ ችግራችንን መፍታት ይኖርብናል።ይህ ቢሆን  ማንኛውም ሰው የትም ሂዶ፤ ያለ ስጋት  በተማረው ቋንቋ  ሊሠራ ይችላል ።

ሕገ መንግሥት፤ በሚመለከት፤ማንም ቢሆን  በአንድ ጊዜ የጠራ  ሕገ መንግሥት የቀረጸ አገር የለም።ነባራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ሕግ መንግሥቱም ከሁኔታው ጋር መጣጣም ይኖርበታል። አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የረቀቀውም ሆነ የጸደቀው በኢሕአዴግ መሪነት  በመሆኑ፤በተወዳዳር ፓርቲዎች ዘንድ ቅሬታ አላ።ይህን ቅሬታ ለማስወገድና የመንግሥትን ሥልጣን ለባለመብቱ ሕዝብ ለመመለስ፣ ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ይገባል።

የፌድሬሽን ማክር ቤትን  በሚመለከት፤የፌድሬሽን ምክር ቤት ያስፈለገው ለብሔር ብሔረ ሰብ ውክልና ነበር።ነገር ግን  ኢሕአዴግ ራሱ የብሔር ድርጅቶች ግንባር ነው።የተወካዮች ምክር ቤትም እንዲሁ። አብዛኛዎቹ ክልሎችም  የሚያስተዳድሩት የብሔራቸውን ሕዝብ ነው።ስለዚህም ሕዝባችን በቀበሌ በወረዳ፤በዞን መሪዎቹን ራሱ  ከመረጠ የፌድሬሽን ምክር ቤት አያስፈልጉትም።

ስለዚህም በፌድሬሽን ምክር ቤት ምትክ፤ ከመደበኛው ምርጫ በፊት፣ከየዞኑ አንዳንድ ከፍተኛ የሸንጎ አባላት ቢመረጡ፤ አባላቱ የመረጣቸውን ሕዝብ በመወከል  ሕገ መንግሥቱን ሊያሻሽሉ፣ የመረጣቸውንም ሕዝብ መብት ሊያስከብሩ ይችላሉ።

በተጨማሪም አሁን የኢሕአዴግ ሥራ አስፍጻሚ  እያከናወነ ያለውን ተግባር በመፈጸም፣ መንግሥታዊ ስምምነቶችንና ብድሮችን፤ የባለሥልጣን ሹመቶችን በማጽድቅ፤በሕዝብ ታወካዮች  የረቀቀን ሕግ መርምረው የመወሰን፤ባጄትን የማጽደቅ፤ ዲሞክራሲያዊ አሰራርን የማስከበር ተግባር  በመፈጸም፤ የመንግሥትን ተግባር በመከታተል፤ ኅብረተሰቡን የሚጠቅም፣ ሰላማዊ ሽግግርን የሚያፋጥን ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ።

በዚህ መልኩ የሕዝባችን ጥያቄዎች ከተፈቱና  የመንግሥት ሥልጣን ለባለ መብቱ ሕዝብ ከተመለሰ፤ በተሻሻለው ሕገ መንግሥት መሠረት ሁለት አመት ባልበለጠ ጊዜ፣ፓርቲዎቹ የሚሳተፉበት መደበኛ ምርጫ መካሄድ ይገባል።

ይህ  ቢሆን አንዱ ብሔር በሌላው  ላይ፤ የትኛውም ፓርቲ በሕዝቡ ላይ ፈላጭ ቈራጭ መሆኑ ይቀራል። ኢኮኖሚያችንንም ከማዕከላዊ እዝ አላቆ ፈጣን እድገትን ለመጨበጥ ያስችላል። ኢንቬስተሮችንም ከአቢዮታዊ ዲሞክራሲ ፍራቻና ሥጋት በማላቀቅ  የውጭ መዋዕለ ነዋይ በመሳብ፤ከኋላ ቀርነትና ከሥራ አጥነት የድነናል። የአፍሪካ አንድነትንና የምሥርቅ አፍሪካን ውኽደት ያፋጥናል።

እንግዲህ ይህ  ያለመድሎ የሁሉንም መብት በእኩልነት ለማስከበርና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በአገራችን  ለማስፈን፣ ይረዳ ዘንድ የቀረበ የመፍትሄ  ሃሳብ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያን አንድነት፣ የሕዝቡን ነጻነትና እኩልነት ለማስፍን የሚፍልጉ ሁሉ ሊቀበሉት ይገባል።

ስለዚህም የአገራችንና የሕዝባችንን ዘላቂ ጥቅም ከሁሉ በማስቀደም፣ሰከን ብለን  ከሚመስሉን ጋር ብንደመር፣ ጭቆናን አስወግደን በእኩልነት አብረን ለመኖራ ያስችለናል።ሥልጣንን ብቻ ተመልክተን እርስ በርስ ብንጠላለፍ ግን፣ አገራችንን በመገነጣጠል ሕዝባችንን ለእርስ በርስ እልቂት እንዳርጋልን።

ስለዚህም የሰላም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ፤ ትዕግስቱን ሰጥቶ፣ ከግብታዊነትና ከእርስ በርስ ጥላቻ አላቆ፤ ጎረቤቶቻችንን እንደራሳችን የምንወድበትን ፍቅሩን ይስጠን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና  ሕዝቦቿን ይባርክ!

 

ጆቢር ሔይኢ

ከሁስተን ቴክሳስ

3 Responses to አማራጭ የሌለው የሠላም ጎዳና   (ጆቢር ሔይኢ-ከሁስተን ቴክሳስ)

 1. First of all I am glad to see this name after a long time. It’s a name we used to listen reporting for Ethiopian News Agency (ENA) Those three names: “Jobir Hiey’e Ke Djimma”; “Goitom Bihon Ke Asmera”; and “Sulatn Alemu Ke Debremarkos”. A news report of different activities via Telephone.
  I was so surprised when I saw Ato Jobir in Djimma for the first time. The first person I wanted to see after I set my feet in Djimma was Jobir Hiey’e.

  Having said this, regarding the article you contributed here, I want to extend my appreciation for the matured view and decency I saw in your presentation. Keep on sharing your views.

  Thank you.

  Ayalkibet Adem
  September 20, 2019 at 4:46 am
  Reply

 2. It is simply nonesense and unwise

  Amhara
  September 20, 2019 at 8:26 am
  Reply

 3. አቶ ጆቢር ስለ ኢትዮጲያ ገድዎት ሀሳብ ማዋጣትዎ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ሆኖም ስለብሔር ጭቆና ያለወት አስተያየት እና ይኸን ተከትሎ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋችን እንግሊዝኛ ይሁን፡፡ ለዚህም መነሻ ሌሎች የአፍሪካ እና የኤሽያ አገሮች ይኸን በማድረጋቸው ተጠቅመዋል ፡፡ የእኛ ልጆች አማርኛ በመማራቸው ወደሇላ ቀርተዋል ያሉት ስሕት ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻችን በቅኝ ገዥዎች ምክንያት የባእድ ቋንቋ ቢከተሉም ከኤሽያ ግን አንድም የለም፡፡ ለመሆኑ እርስዋ ኢትዮጲያዊ ሆነው በአሜሪካ ሲኖሩ ከሌሎች ጋር ለመግባባትስ ሆነ ተወዳዳሪ ለመሆን ተቸግረዋል አይመስለኝሞ፡፡ይኽ የኢትዮጲያዊነት ውጤት ነው፡፡

  ኃይለ ሚካኤል
  September 20, 2019 at 10:19 pm
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.