የመለስ ዜናዊን ነቅለን ሳንጨርስ አብይ ተሰቀለ!

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

ዛሬ በሃድያ ዞን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተደረገው አቀባበል ከወትሮው በተለየ በጣም ደማቅ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ ረገድ የዞኑ መስተዳድር እና የከተማዋ ነዋሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል። እንዲህ ያለ ደማቅ አቀባበል ማድረግ ለዞኑ ገፅታ ግንባታ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሆኖም ግን በዞኑ ጉብኝት ያደረገው ሌላ ሳይሆን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው። ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረግ ሥራና ሃላፊነቱ ነው። በዚህ መሠረት ጠ/ሚ በሃድያ ዞን የተገኘው ለመደበኛ ሥራ እንጂ የተለየ ዝግጅት ወይም ክብረ-በዓል አሊያም ለምርጫ ቅስቀሳ አይደለም።

ይህ ከሆነ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሥራ በሄደበት ከተማ በየህንፃው እና አዳራሹ ላይ የእሱን ምስል መስቀል፣ አጉል ማሞገስና ማቆላመጥ ምን አመጣው? ለመሆኑ እነዚህ ሁሉ ፖስተሮች በከተማ መስተዳድሩ ወጪ የተሰሩ ናቸው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኑ አብረዋቸው የነበሩ ሃላፊዎች ይህን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? “ታላቁ መሪ፣  አባይን_የደፈረ፣ ቅብጥርሶ እያሉ የሰቀሏቸውን የአቶ መለስ ዜናዊ ምስሎችና ፖስተሮች ተለቅመው ሳያልቁ ደግሞ #አብይ_አህመድ፣ ከጎንህ ነን ቅብጥርሶ በሚሉ ምስሎች ልታጨናንቁን ነው?

በእርግጥ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ በጣም ያስደሰተኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ተሰቅሎ የነበረውን የመለስ ዜናዊ_ፎቶን ማንሳቱ ነው። የሀገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት በሆነው ምክር ቤት ላይ የዚያ ድኩማን ፎቶ ተሰቅሎ ስመለከት አምባገነንነት አናቴ ላይ ቁጭ ብሎ የሚፀዳዳብኝ ይመስለኝ ነበር። የመለስ ፎቶ ፓርላማ ውስጥ ከመሰቀሉ በፊት ልክ ዛሬ በሃዲያ ዞን እንደሆነው በየህንፃውና አዳራሹ ውስጥ ታላቁ መሪ፣ የህዳሴው መሪ እየተባለ ይሰቀል ነበር። ባለፈው አመት ጠ/ሚ ፓርላማ ላይ ቀርበው “መሪዎች አምባገነን የሚሆኑት በህዝባቸው ግፊትና ጥያቄ ነው” ማለታቸውን አስታውሳለሁ። ከዚህ አንፃር ዛሬ በሃዲያ ዞን ከስብሰባ አደራሹ እስከ አደባባይ በአጉል ውዳሴ የታጀበ ምስላቸው ተሰቅሎ ሲመለከቱ ህዝቡ እንደ መለስ ዜናዊ እንዲሆኑ እየጠየቃቸው መሆኑ ሳይገባቸው የቀረ አይመስለኝም።

በመሆኑም በቀጣይ እንዲህ ያለ ተግባር እንደማይደገም ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ ካልሆነ ግን መጨረሻው አያምርም። ይሄ ህዝብ ሰው አምላኪ ነው። ስልጣን ላይ የወጣን ሁሉ ማሞገስና ማንቆለጳጰስ ይወዳል። ከስልጣን ሲወርዱ ደግሞ ከፍ አድርጎ ከሰቀለው ቆጥ ላይ አውርዶ ይከሰክሳል። ለዚህ ደግሞ በስልጣን ላይ እያሉ እምዬ፣ ፀሃዩ፣ ቆራጡ፣ ታላቁ ሲላቸው የነበሩትን መሪዎች ዛሬ ምን ብሎ እንደሚጠራቸው ማየቱ ብቻ በቂ ነው።

ስዩም ተሾመ FB የተወሰደ

One Response to የመለስ ዜናዊን ነቅለን ሳንጨርስ አብይ ተሰቀለ!

  1. PM Meles’s photo yetesekelew kemote behala new.yeleloch gin behiwet eyalu
    Meles phote meskel ayfeligm neber

    Abel
    September 26, 2019 at 2:38 am
    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.