አገራችን ከገባችበት የህልውና አደጋ ትወጣ ዘንድ የጥላቻ ፣ የመጠላለፍና የእልህ ፓለቲካ ያብቃ! – [ኅብር  ኢትዮጵያ  ዴሞክራሲያዊ  ፓርቲ[ኅብር  ኢትዮጵያ]

Filed under: የዕለቱ ዜናዎች |

[ኅብር  ኢትዮጵያ  ዴሞክራሲያዊ  ፓርቲ[ኅብር  ኢትዮጵያ]

HHIBIR  ETHIOPIA  DEMOCRATIC  PARTY  [HIBIR  ETHIOPIA]

ፓርቲያችን ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ) የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በአንክሮ ሲከታተል ቆይቷል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ሪፎሪም ከተጀመረ ወዲህ በመላ አገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ምስቅልቅል በ ”አድናቆታዊ-መጠይቅ” ሰከን በማለት በጋራ ልናርቀው ሲገባን፤ አንዱ በሌላው ላይ የአሸናፊነት ነጥብ ለማስቆጠር የሚያስችለውን የፖለቲካ ሴራዎች እየሰራ የአገርና ህዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከት ሁኔታ በስሜታዊነት ፈረስ ሲጋለብ እናያለን ፡፡

ፍላጎታችን ለከት ያለፈ ከመሆኑም ባሻገር በተቋማዊ የለውጥ ሂደት ሊፈጠር የሚችለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በግርግርና በትርምስ ውስጥ ከመቅስፈት በራሳችን ልክ ብቻ እንዲፈጠርልን በመሻት በእኔነት ዕሳቤ ደንዝዘን፣ ከዓለማቀፋዊነት ጫፍ ወርደን በመንደርተኛ አስተሳሰብ ተማርከን ስለ መንደራችን ብቻ ስንሞግት ስንታይ ቀደም ስንታገልልት የነበረው ዴሞክራሲ ይመጣ ዘንድ ህይወትና አካል የተከፈለላት ኢትዮጵያ ሌላ ነበረች እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳል ፡፡

“እኔ ያልሰራሁት ወጥ አይጥምም፣ ያልጋገርኩት እንጀራ ከምጣዱ አይወጣም” በሚል መታበይ፣ እንዲሁም መልካም ሲሰሩና ሲያቅዱ ማበረታታትና ጉድለትን ነቅሶ በማሳየት ማገዝ ሲቻል “ባልበላው ጭሬ ላጥፋው” በሚል የምቀኝነት ስሜት እርስ በርስ በመጠላለፍ በመገዳደልና በመወነጃጀል ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይ ፊደል ቆጥረናል ዓለማቀፋዊነት ገብቶናል በምንል ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ይህ መንደርተኛ ዕሳቤ ገንግኖ ስናይ እጅግ ያሳፍራል፡፡ በሌላ በኩል ለውጥ ኃይል ያልነው አካል በሪፎርሙ ጅማሬ ለህዝብ የገባውን ቃልና የጠየቀውን ይቅርታ ተከትሎ ከህዝብ የተሰጠው ከፍተኛ ድጋፍ አገራዊ አደራና ኃላፊነት መሆኑን በመሳት ወደ ቀደመው የኢህአዴግ ባህሪይ ክህደትና እብሪት የመመለስ አካሄድ እየታዘብን ነው፡፡

ከነዚህ ክሹፍ ዕሳቤዎች የተነሳ በአገሪቱ የተከሰቱት ብሄር ተኮር ግጭቶችና ያስከተሉት ሰብዐዊና የሃብት ውድመት፣ መፈናቀልና ማኅበራዊ ቀውስ፣በደቡብ ኢትዮጵያ የተነሱትና ዛሬም ድረስ እየተነሱ ያሉትን የክልልነት ጥያቄዎችና እነርሱን ተከትሎ የመጣው ቀውስ፤ ህዝባችንን እያስመረረ የሚገኘው ፖለቲካ ሰራሽ የኑሮ ውድነት፣ሥራ አጥነት፣ በዘርና ሐይማኖት ውስጥ የሰረጉ ፖለቲከኞች እያደረሱ ያሉት ጥፋቶች ሁሉ ‹‹እኛ እንውቅላችኋለን››ከሚል የሴራ ቀመርና ተግባራት እንደነበሩ ገምግመናል ፡፡ በተጨማሪም ባሳለፍነው ዓመት ይህ ዓይነቱ አሳፋሪና አስነዋሪ የሴራ ፖለቲካ አድማሱን አስፍቶ ዕውቀት እንዲጨብጡ በአንዲት ደሃ አገርና እናት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተላኩ ተማሪዎች ላይ ህሊና ቢስ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ፍጆታቸው ሲሉ ዘረኛ እጆቻቸውን በማርዘም የተማሪዎች ሕይወት የተቀጠፈበት አካል የጎደለበትና የዕውቀት መቅሰሙ ተግባር ወደ ዘር መቁጠርና በመንደር መቧደን የወረደበት ሁኔታ መስፋፋቱን ታዝበናል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ የተከሰተው የሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም የባህር ዳርና አዲስ አበባ አሳዛኝና አሳፋሪ ክስተትና ካስከተለው መዘዝ እስካሁን አልተላቀቅንም፡፡

በዚህ ጥልቅ ግምገማችን በሁሉም መስክ የፖለቲካ ቀውሱ የአገራችን ህልውና ጭምር አደጋ ውስጥ የወደቀበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ በመረጃና ማስረጃ የተደገፉ የሠላምና መረጋጋት መናጋት፣ አሳዛኝ ሰብዐዊና ማኀበራዊ ቀውሶችና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድመቶች…መከሰታቸውን ተገንዝበናል ፡፡

ፓርቲያችን በግምገማው የአገራችን ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታ ህገመንግሥቱንና በርካታ ከህገመንግሥቱ የሚመነጩ ጥያቄዎች(የህዝብና ቤት ቆጠራ፣የክልልነት፣የወሰንና ማንነት፣የምርጫ በወቅቱ መደረግ…)ጥያቄዎች የተነሱበትና ያላገኙና ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚሹ በመሆናቸው ውጥረት የነገሰበት፤ እንዲሁም ከነዚህ ውስጥ የምርጫን ጉዳይ ብቻነቅሶ በማውጣት ህገመንግስቱን በመጥቀስ የሚደረገው ክርክር ትክክልና ጠቃሚ ያለመሆኑን ተገንዝቧል፡፡ የእነዚህ አሳሳቢ ሁኔታዎች መነሻ በፓርቲያችን ዓይን ከእነ ህፀፁ በሥራ ላይ ባለው የአገሪቱ ህገመንግስት መሰረት ካለመሸራረፍ መረጋገጥ የነበረባቸው የአገር ሠላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት፤ የህዝብን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ለማክበር እንዲሁም ለውጡን ስርነቀልና ተቋማዊ ማድረግ የሚገባው ኢህአዴግ የራሱን ድርጅታዊ አንድነት እውን የማድረግ ብቃት አጥቶ በተራማጅና በአደናቃፊ ጎራዎች ተከፋፍሎ የመጓተት ፈተና ውስጥ በመውደቁ ነው፡፡

ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!

በመሆኑም ኢህአዴግ የገጠመውን ፈተናና የተጋረጠበትን ተግዳሮቶች ለመቀበልና ለመሻገር መቸገሩንና በራሱ ሳንባ ብቻ እንዲተነፍሱ አድርጎ የገነባቸው መንግስታዊ ተቋማት ምክንያት ሊያስከትል የሚችለውን አገራዊ አደጋ ከወቅቱ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ፣እንዲሁም ከለውጡ ዘዋሪዎች ዙሪያ ከከተሙ ሃሳዊ ሃይሎችና ለውጡን በመንደር ቀለም በመቀልበስ በትርምስ ምርጫ አገራችንንና ህዝቡን ወደ አዲስ የሰቆቃ ምዕራፍ ሊያመሩ-ያሰፈሰፉ ኃይሎች በማገናዘብ፡በግምገማችን የደረስንባቸውን ድርጅታዊ አቋሞቻችን ከዚህበታች ቀርበዋል፡፡

  1. ፓርቲያችን ኅብር ኢትጵያ ከፖለቲካ ስልጣን ይልቅ የህዝባችን ህልውና የአገራችን ሰላምና ሉአላዊነት እንደሚቀድምና እንደሚበልጥ በፅኑ ያምናል፡፡ ስለሆነም የትኛውም አይነት ቡድን የፖለቲካ ስልጣንን በአቋራጭ ለመቆናጠጥ ሲል የሚያደርገውን ህዝብን ከህዝብ፣ አንዱን ብሔር ከአንዱ፣ አንዱን ሐይማኖት ከሌላው፣የማጋጨትና አገርን የማተራመስ ተግባር በውጤቱም ያስከተለውን ከፍተኛ መፈናቀልን አበክሮ ያወግዛል፤ ህዝባችን በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ይህንን ተገንዝበው ለጊዜው ታይተው ለሚጠፉ ፖለቲከኞች በቀረፁልን አጀንዳ ለመሞት የምንዘጋጅ ሳንሆን ዘለአለም በክብር ለምንኖርባት ኢትዮጵያና ኢትጵያውያን ጎን በመቆም ከፋፋይ በታኝና በልዩነቶቻችን ውስጥ በዘመናት የዳበሩትን-የአንድነታችን መሰረት የሆኑ አብሮነቶችና ማኅበራዊ ቁርኝቶች ለማክሰም የሚታገሉ እኩይ ሃይሎችን ከፓርቲያችን ጋር በመሆን አምርሮ እንዲታገል ጥሪ-እናስተላልፋለን ፡፡

 

  1. ፓርቲያችን ኅብር ኢትዮጵያ በአገራችን ኢትዮጵያ ስርነቀል የስርዓት ለውጥ መምጣት እንደሚገባው ያምናል፤በመሆኑም በጅምር ያለው ሪፎርም ከዚህ ቀደም ተጀምረውና ደም አፋሰው እንደመከኑት የለውጥ ጅምሮች እንዲሆን አይሻም፡፡ የሥርዓት ለውጥ የመገዳደልና ሁሉን ነገር በማፍረስ ከባዶ የመጀመር ስንኩል ዕሳቤ ሳይሆን የያዝናቸውን መልካም ጅምሮች በማጎልበት፣ የማያስፈልጉንን በማስወገድና በአዲስ በመተካት፣ ጉድለቶቻችን በኅብር ተግባቦቶች በመሙላት በልማት ላይ ልማትን ፣በብልፅግና ላይ ብልፅግናን ማቀጣጠል የሚቻልበት የግለሰብ ሳይሆን የአስተሳሰብ ልዕልና የሚነግስበት፣ አገር በቀል ዕሴቶቻችን ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍቻነት የምንጠቀምበት እንዲሆን ህዝባችን ከፓርቲያችን ጎን በማሰለፍ በሙሉ አቅማችን የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን ፡፡

 

  1. ኢህአዴግ ዛሬም ከአገርና ህዝብ ይልቅ ሥልጣናቸውን በማስቀደም ለውጡን በመቀልበስ በለመዱት የክህደትና የማጭበርበር አፋኝ መንገድ ለመጓዝ በመረጡና በውጤቱም እራሳቸውን ከማፍረስ አልፈው አገሪቱን ለከፋ አደጋና እንደ አገርና እንደ ህዝብ የመቀጠል የህልውና ፈተና እየዳረጓት በሚገኙ ሃይሎች የተከበበ መሆኑ በግልጽ ይታያል ፡፡ ስለሆነም ለውጡ በህዝባዊ መሰረት ላይ መገንባትና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መንገድን ይከተል ዘንድ የለውጡ ሃይል ፖለቲካ ኃይሎች በአገሪቱ ህገመንግስት መሰረት ሪፎርሙን ለማስቀጠልና ለችግሮቻችን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማመንጨት ኢህአዴግን ጨምሮ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች በፈረሙት የጋራ ቃል ኪዳን ሰነድ መሰረት ያቋቋሙት የጋራ ምክር ቤት ወደ ተጨባጭ፣ተግባር እንዲገባ መንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዲያሳይ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

 

  1. የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ባልተመለሱበትና የጋራ ም/ቤቱ ለፖለቲካችን ቀውስ የጋራ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማመንጨት እንዲረዱ ህገመንግስት ስለማሻሻል፣ ምርጫ 2012 ስለማራዘም፣ ብሄራዊ መግባባትና የክልልነትና የአዲስ አበባ ጉዳይን ጨምሮ ያጸደቃቸው ሰባት/7/-አጀንዳዎች ላይ ባልተመከረበት-በጥድፊያ-የጸደቀው የምርጫና የፓርቲዎች አዋጅ ከዘላቂ፡ ሠላም፣የተረጋጋ ፖለቲካና ጅምሩን ሪፎርም ከማስቀጠል አንጻር ጠቃሚ አይደለምና አዋጁ ወደ ትግበራ ከመወሰዱ በፊት እንደገና እንዲታይ፣ እንዲሻሻል እንጠይቃለን፤

 

  1. ኢህአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች “ምርጫው በወቅቱ ይደረግ” በማለት የወሰዱት አቋም ድርጅታዊ መብታቸው ቢሆንም ምርጫ ቦርድ እንደ ተቋም በጅምር ሪፎርም ሂደት ላይ መሆኑ ለምርጫው ከቀረው ጊዜና የፖለቲካው ምስቅልቅልና ውጥረቱ እንዲሁም ያልተቋጫው ህገመንግስት የማሻሻል አጀንዳ፣ ከላይ ከተነሱት እውነታዎች ተዳምሮ ምርጫው በ2012 መደረጉ ከዘላቂ የለውጥ ሂደቱ አንጻር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና የጋራ መፍትሄ እንዲበጅለት ውሳኔኣቸውን እንደገና እንዲመረምሩ እናሳስባለን፡፡

 

  1. የለውጥ ጅማሮ ላይ መሆናችንን እየተቀበልን፣ በሌላ በኩል የለውጥ ኃይል በሚባለውና ጭፍን ደጋፊዎቹ የሪፎርሙ አመራር እንዳይነካ/እንዳይጠየቅ የሚከላከለው ዘመቻ፣ ትናንት በለውጡ ጅማሮ የተወገዙት አዋጆች፣ በህወኃት/ኢህአዴግ ጊዜ የነበረው አመራርና አሰራር በነበሩበት በሌላ ባለተራ እንዲቀጥሉ፣ ወይም/እና ለውጡን

 

ለማዝለቅ የሚያስችል የህግ የበላይነትን የማስከበር አቅም ማጣትን በፕሮፖጋንዳ ለመሸፈን የሚደረጉ ጥረቶች ህዝብየሚጠብቀውን ዘላቂ ሠላምና የተረጋጋ የለውጥ ሂደት እውን ሊያደርገው አይችልም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የብሄራዊ

ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!

መግባባትና ዕርቀ ሠላም ጉባኤ በአስቸኳይ ተጠርቶ አገራችንና ህዝባችን ከገቡበት ፈተና ማለፍ እንዲቻል የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ እንጠይቃለን፡፡

  1. በአገራችን ኢትዮጵያ በስፋት እየታየ ባለው አስከፊ የኑሮ ውድነትና የተጋነነ የስራ አጥነት ምክንያት ህዝባችን መሰረታዊ የምግብ ፍጆታውን መሸመትና ልጆቹን ማስተማርም ሆነ ማልበስ ያልቻለበት፣ለሚሰራው ስራ ተመጣጣኝ ክፍያን ማግኘት አዳጋች የሆነበት እንዲሁም በየዓመቱ ከተለያዩ የትምርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ወደ ስራ መስክ መሰማራት የተቸገሩበት ምክንያት መንግስት ከሚከተለው የተሳሳተ የትምህርትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ፣ጤናማ ያልሆነ የግብይት ስርዓትና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ቁልፍ አሁንም በቀድሞው ሕወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲከኛ ነጋዴዎች እጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ፖለቲካ ሰራሽ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፤በመሆኑም የለውጡ ሃይል ካንሰርን በፓራስታሞል ለማከም የመሞከር ቀልዱን ትቶ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ስርዓት ለውጥ ዕውን እንዲያደርግ፣ አሁንም በሕወሓት/ኢህአዴግ ዘመን በተዘረፉ የህዝብ ሀብቶች በልማት ማኅበራት ሽፋን የተገነቡና ገቢዮቻቸው የፖርቲንና የግለሰቦችን ካዝና ለማሳበጥ የዋሉ እና እየዋሉ ሚገኙ ግዙፍ ኩባኒያዎችን በሙሉ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል ንብረትነታቸው የህዝብ ማድረግ በገቢዮቻቸው ለወጣቱ ስራ መፍጠር የሚያስችል ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል እንዲተገብር እየጠየቅን አሊያ ህዝባችን ፋታ በማይሰጠው የዳቦ ጥያቄ ምክንያት መንግስትን ባልጠበቀው ጊዜና ሰዓት “ስልጣን በቃህ ! ” ሊለው እንደሚችል ልናስጠነቅቅ እንወዳለን ፡፡

 

በመጨረሻም ፓርቲያችን ኅብር ኢትዮጵያ ለነዚህ አቋሞች ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ እያረጋገጥን-ይህ በአገራችን ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሄ እውን እንዲሆንና ህዝባችን ወደ ሠላማዊ የተረጋጋ ህይወት እንዲመለስ፣ አገራችን ከተጋረጠባት የሰላምና ሉዓላዊነት ፈተና በሁሉም ዜጎች ተሳትፎ መፍትሄ እንድታገኝ ፣የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ፣ የፖለቲካ ኃይሎች ፣ባለድርሻ አካላት የሆናችሁ የኃይማኖት ተቋማትና አባቶች፣ የሲቪክና ሙያ ማኅበራት፣ የንግድና-ዘርፍ ማኅበራት፣ታዋቂ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች ከጎናችን በመሰለፍ አስተዋጽኦዋችሁን እንድታበረክቱ፤እንዲሁም የአገራችንና ህዝባችን ወዳጅ መንግስታትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ይህን የተቀደሰ፣ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሄ እንዲቀበሉ ተገቢውን አዎንታዊ ግፊትና ጫና እንድታሳርፉ፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ፣

ኢትዮጵያ በልጇቿ መስዋዕትነት በክብር ለዘለዓለም ትኑር//

ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ)

 

መስከረም 22 ቀን 2012፤አዲስ አበባ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!  ኅብር ኢትዮጵያ  !!  ኅብር  ኢትዮጵያ  !!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.