ክፉው ዘመንና የሕዝብ መከራ ( በ_ከ)

1 min read

ክፉዎች ዘመኑን ክፉ አድርገውታል። ክፉው ዘመን ሕዝባዊ ባህልን እየተበከለ ነው። ሜዲያዎችና ትዕይንቶች አስተሳሰብ መከርቸምያ መሳርያዎች ሆነዋል። ተፅእኖ ፈጣሪ ምሁራንና ፖለቲከኞች ለአስተሳሰብ እድገት ከመታገል ይልቅ ለወርቅና ለብር ይሰግዳሉ። ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ የፖለቲካው ሰዎች ተፅዕኖ ፈጥረው ያቀዱትን ዝርፊያ ለመፈጸም ብዙ ይራወጣሉ። ክፉዎች በአደናጋሪ ንግግሮቻቸው እየታገዙ ሃሳብን ያጨልማሉ። ባደጉት ሃገሮች መጽሄቶች (novels)፣ ፊልሞች (films)፣ የቴሌቪዥን ትርዕይቶች (television shows)፣ የኩምክና መጽሄቶች (comics)፣ የቪዲዮ ጨዋታዎች (video games) እና የሙዚቃ ቪዲዎች (music videos) ሃሳብ ማምከኞች ናቸው። በአፍሪካ ደግሞ ገጀራ፣ ምስማር የተሰካበት ዱላና ድንጋይ የሰው ልጅን ማስፈራርያ ሆኗል። ጥበብና እውቀት ተሸሽጎ፣ ግብረገብና ሥነምግባር ተሸርሽሮ ከንቱና ተምበርካኪ ትውልድ ሲበዛ አምባገነኖች ይራመዳሉ። ትግል እንዳይስፋፋ የጥቅማ ጥቅም ምርኮኛ ማድረግ የዘመኑ ዓቢይ ክንውን ነው።

ዘመን ወለድ የሆኑ ጥፋቶችን፣ የግብረገብ መሸርሸርንና የሥነምግባር መጠውለግን ስናስብ የገናናዋ ሃገራችን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣም ያሳስበናል። ክፉው ዘመን ባህልን በማደብዘዝ በሃገራችን ምጣኔ ኃብትና ፖለቲካ ጉዳይ ላይ አሻራውን እያሳረፈ ነው። በስድሳዎቹ ዘመን ተራማጆችና አብዮተኞች ርካሽ የሰው ጉልበትንና ጥሬ ኃብት አነፍንፎ የሚቃርመውን ዓለማቀፉን ኢምፔርያሊዝም ይውደም” (Down with Imperialism) ይሉ ነበር። ታጋዮች ኢምፔርያሊዝምን አምርረው ታግለዋል። ዛሬ ክፉው ዘመን ይወደምየሚል ኃይል የለም፤ ምክንያቱም ክፋቱ ስውር ነው። ክፋቱ እያሳሳቀና እያዘናጋ በሰዎች መንፈስ ውስጥ የሚሠርጽ አሸብራቂና አደናጋሪ ትዕይንት ነው። ክፋቱ የቪዲዮ ጨዋታ እየመሰለ ልጆች ውስጥ ይሰርጻል። የደማቅ ሰርግ ዶኩሜንተሪና የቆነጃጅት ተዋንያዎች አለባበስ ዘጋቢ ፊልም ባህልንና እውቀትን መጉዳቱን ብዙዎች አያስቡትም። ዘመኑ እልብስና ጫማ፣ ላፕቶፕና ሞባይል ስልክ ላይ በሚጥል አጓጊ ማስታወቅያ ይደገፋል። ለብዙዎቻችን ስውር ክፋቱን መረዳት ቀላል አይደለም። ክፉው ዘመን ሰዎች ፊልሞቹ ውስጥ ያዩትን ለመሆን የሚጓጉና አሸብራቂ የሆኑት የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች ባለቤት ለመሆን ወደ ፈጣሪያቸው በድፍረት እንዲለምኑ የሚያበረታታ ኃይል ነው። ክፉው ዘመን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ መብት ነውማለቱ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ቤተክርስትያን ሃሳቡን እስኪደግፉ ድረስ አሳስቷቸዋል።

ማንም ቢሆን የዘመኑን እጹብ ድንቅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤት አይቃወምም። አለመቃወሙ ምንም አይደለም፣ ችግሩ ከቴክኖሎጂው ባሻገር ያለው ጉዳይ ነው። ሸቀጥ ተፈጥሯዊ ማንነትን ሳይቀር ቀስ በቀስ እየሰለበ ወደ 666 መኬዱን እንኳን ማወቅ እስኪሳን ድረስ ልፍስፍስ ያደርጋል። በእርግጥ እንኳንስ ወጣቶች ይቅርና የኃይማኖት አባቶችም የዘመኑን የሠላባ ስልቶችን በቀላሉ መረዳት አልቻሉም። ጥበብ ከድሆች ምድር እንድትሸሽ የሚያደርገው ይህ ክፉ ዘመን ሕዝበኞችንና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን እየተጠቀመ ፍላጎቱን ያሳካል። ዘመኑ ፈታኝ ነው ለነጠላ ችግር የምትሆን መፍትሄን እንኳን ይሸፍናል። አንዱ ወንዝ ጠልፈን መስኖ እናብጅቢል ሌላኛው አይሆንም ይህ የአካባቢውን የአየር ንብረት ይበክላልበሚል ቸር መሳይ ሃሳብ ተግባርን ያደናቅፋል። ማኅበራዊ መገናኛዎች ክፋትን እየጋበዙ ሕዝብን ያስጨንቃሉ። ዓላማቸው ሁሉን አንገት አስደፍቶ በስርቆት ሃብት ለመሽቀርቀር ነው። የሚገርመው ግን በዚህ ሁሉ እሳት ማህል አንዳች የማይፈራ ሃቀኛ የሕዝብ ልጅ በብዕርና በሰላማዊ ትግል ታንክና አውሮፕላን የታጠቁትን ያርበደብዳል።

ክፉው ዘመን ግብረገብንና ሥነምግባርን ሸርሽሮ በምትኩ ገንዘብ የሚገኝበትን ማንኛውምን ኢግብረገባዊ ዘዴ ያበረታታል። ይህም በብዙዎች ዘንድ እንደ ሥልጣኔ ይቆጠራል። ሌባ ካልተያዙ መሥረቅን ያበረታታል። አጭበርባሪዎች ማስረጃን ማጥፋት እስከተቻለ ድረስ ሙስናን ያደፋፍራሉ። ባለሥልጣኑ ስለ ልማት በአደባባይ እየተናገረ የሕግን አቅም ያቀጭጫል። ዘረኞች በህገመንግሥት ይከበር ስም ክፍፍል ይሸርባሉ። የክፋት ኃይሎች ወረራን መካች ዜማዎችን እያጠፉ ወሲብ ቀስቃሽ ዘፈኖችን ያሰራጫሉ። ክፉዎች የሸቀጥ አምላኪዎችና የፈሪዎች መደበቅያን ይሆን ዘንድ በሃይማኖት ስም አዳዲስ ምሽጎችን በመቆፈር ለድሆች መብት የማይዋጉ አድር ባይ ትውልድ ያበዛሉ። ክፉዎች ምድርን ከምንጊዜውም በላይ ንፉግ አድርገዋታል። ልሳኑ ያማረለት ሁሉ ለኑሮው አስፈላጊ ከሆነ ይታገላል፣ ጥቅሙን ከተግደራደረበት ደግሞ ሰወር ይላል። ተናጋሪው መቼ ብቅ ማለት እንዳለበት አስልቶ ያውቃል። ሲናገር ጠብቀው ደጋፊዎቹ – “እገሌ ዝምታውን ሠበረ” – ብለው ያስተጋቡለታል። የዋሁ አሁንም ይሸወዳል።

ብሉመሪንግ ተብሎ የሚጠራውው ስለ ገንዘብና ገንዘብ ዝውውር የሚዘግበው ድረገጽ ሃብታሞች በየሠዓቱ አራት ሚሊዮን ዶላር ሲሰበስቡ ለሠራተኖቻቸው ደግሞ በሠዓት የሚከፍሉት አስራ አንድ ዶላር ብቻ ነው። ይህ ፍትሃዊ ዓይደለም። ጥቂቶች መጠነ ሠፊ ገንዘብ ሲቆልሉ ደሆች ይሰደዳሉ፣ በበረሃው ሃሩርና በውቅያኖስ ወጀብ ያልቃሉ። ያልተሰደዱት በየሃገራቸው ተቀምጠው በጉጉት ይነዳሉ፣ በመሻቱ ጥም ይቆዝማሉ፣ በሃሰተኛ አገልጋይና በራስ ወዳድ ፖለቲከኞች ይሰለባሉ። በለስ ቀንጧቸው በየምዕራቡ ዓለምና አረብ ሃገሮች የተሰደዱ ደግሞ በወገኖቻቸው ድህነትና ስቃይ ሳብያ በሥነልቦና ህመም ይባዝናሉ። ይህ ሁሉ ኢፍትህ እውነት በሚመስል ዜና ይሸፈናል። ማኅበራዊ መገናኞች ጉጉትን እያበረታቱ ሥብዕናን ሰልበው ፈሪና ተምበርካኪ ያደርጋሉ። የዋሆች ባንድነት የባሳ አታምጣሲሉ ወደ አልምላካቸው ያንጋጥታሉ። ክፋቱ ግን ያይላል። አሁንም የባሰ አታምጣይባላል።

ክፉው ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ላይ የተነሳው የቆየ ባህልን፣ ሃገር ወዳድነትንና ንፁህ እምነትን ጨፍልቆ ከልካይ በሌለበት እንዳሻው ለመራመድ ነው። ክፉው ዘመን ጊዜ ጠብቆ ነው ተዋህዶን ለማጥቃት የተነሳው። ዘረኞች የጋረዱት የአማራና ትግራይ ተዋህዶ አማኞች መራራቅ ባለጊዜዎችን ወኔ አስታጥቆ ልባቸውን ደንዳና አደረገው። የሁለቱ ወገኖች ግኑኝነት ፈተና ውስጥ ሲወድቅ ጽንፈኞች ማህሉን እያሰፉ ወደ ፊት ገሰገሱ። ክፉዎች የሃገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ሥር ተንበርክከው በቃረሙት ገንዘብ ጎረምሶች ገዝተው ሃገር ያምሳሉ። እግዚአብሄር ዝም አይልም። ቅዱስ ያሬድ ከሰማይ የተቀበሉት ዜማና ማኅሌት ክፉ መንፈሳቸውን ያስጨንቀዋል።

ሚያዝያ 5 ቀን 501 ዓም የተወለዱት ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ኃይማኖታዊ ዜማ አባት ናቸው። እርሳቸው በመንፈስ ቅሱስ ምሬት እስከ ሰባተኛው የእግዚአብሄር ማደርያ ደርሰው መላዕክት በከበሮ፣ በቀንድ ጥሩምባ፣ ማሲንቆ ጽናጽን እየታጀቡ እግዚአብሄርን ሲያመሰግኑ ተመለከቱ። ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ዜማ፣ አቋቋምንና መንፈሳዊ ውዝዋዜን ያበረከቱ አባት ናቸው። ማኅሌት፣ ዝማሬ፣ ምራፍ፣ መዋሊት፣ ቅዳሴ የእርሳቸውው ግኝት ሲሆኑ ዜማዎች በሶስት አዕዋፍ ምሳሌነት ማለትም ግዕዝ፣ ዕዘል፣ አራራይ ለይተው ለእግዚአብሄር ምስጋና አዘጋጅተዋል። ድጓና ጾመ ድጓ እርሳቸው ለቤተክርስትያን ካበረከቱት መጽሃፍት መካከል ይጠቀሳሉ። የቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶች ይዘት፣ ደረት፣ ርክርክ፣ ድፋት፣ ጭረት፣ ቅናት፣ ሂደት፣ ቁርጥ፣ ድረስ፣ አንብር ይባላሉ። የባዕዳን ሎሌዎች በተሃድሶ ስም ይህን የቆየ ኃይማኖታዊ ሥርዓት ማስወገድ ሲፈልጉ አሸባሪዎች ቤተ ክርስትያኒቱን በማቃጠል፣ አባቶችን በመግደልና ምዕመናንን በማሰደድ ይተባበሯቸዋል።

አዳዲስ ኃይማኖቶችን በመፍጠር ይህን ቀጥተኛ ኃይማኖት ለማጥፋት ክፉዎች ሤራ የሚወጥኑት በአዲሱ የዓለም ሥርዓት በመታገዝ ነው። ክፉዎች ማኅበራዊ እኩልነት ይስፈንማህበራዊ ፍትህ ይከበርእያሉ በዶንያ ሙሉ ወርቅ ያሸሻሉ። አታላዮች ወጣቷ ገላዋን የማይሸፍነውን ለብሳ ወደ ቤተ ክርስትያን እንድትሄድ ለማድረግ ሲሉ እግዚአብሄር ልብን እንጂ ልብስን አያያምየሚል በጎ መሳይ ሃሳብ ይደልሏታል። ክፉዎች የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚያበረታቱ አልባሳት እንዲሸጡላቸው የወጣቱን ልቦና በሞዴሎች ትዕይንትን በማስታወቅያዎች ቀለም ይዋክቡታል። ክፉዎች የእግዚአብሄርን ቃል እየቆነጠሩ ባህልን መለወጥ፣ ዓዕምሮን ማበላሸት ችለውበታል። ክፉዎች ሊያዘናጉን የቻሉት ደግ መሰል ሃሳብየማቅረብ ብልሃታቸውና አሽሞንሙኖ የማሳመን ዘዴቸው ወደር የለሽ በመሆኑ ነው። ይህ የሴራቸው አንዱ ክፍል ነው። ዛሬ አጋንንት በሰዎች ዓዕምሮ የሠረጸው እንደበፊቱ የዛር መንፈስ፣ የዓይነጥላ መንፈስ፣ የአንደርቢ መንፈስ፣ ወዘተ፣ ሆኖ ሳይሆን በአልባሳትና በዘመናዊ ቁሳቁሶች አዘናግቶ አማኙን ከግንዛቤ ውጭ በማድረግ ነው ።

ኃይማኖት እውነትን ታራምዳለች፣ ግብረገብነትን ታስፋፋለች፣ ሥነምግባርን ታበረታታለች። ኃይማኖት በክፉዎች ስትወላገድና አባቶች ዝም ሲሉ የሕዝብ ስቃይ ይጨምራል። በመላው ሃገሪቱ የምንገኝ የክርስትናም ይሁን የእስልምና እምነት ተከታዮች ክፉውን ዘመን በአንድነት መዋጀት ይገባናል። የክፋቱ ማየል የአማኞች ዝምታ ገላጭ ነው። የብዙዎች ጸሎት ኃይል አለው። ስጋዊ መሻታችንን ለጊዜው አቅበን ክፉው ዘመን እንዲወገድ ባንድነት ብንጸልይ እግዚአብሄር መልሱን በቶሎ ያዘንባል። የእግዚአብሄር አማኞች የሆንን ሁሉ የክፋቱን ዘመን አስመሳይነት፣ አረማመድ፣ ስልትና ስውር ዘዴ ልንመረምር ይገባናል። ክፉው ዘመን ደም የጠማው ሥርዓት ነው። ክፉዎች – ምስኪኑን በዘር መከፋፈልና በጎሳ ማገዳደል አይሰቀጥጣቸውም። ጊዜ የሠጣቸው የዘመኑ ፖለቲከኞች ቋንቋንና ኃይማኖትን ምክንያት እያደረጉ በገጀራ ሕዝብ ሲያሸማቅቁ ሥርዓት አስከባሪዎች እንደ ዘበት ቆመው ያያሉ። ሕዝብ በሠላም ወጥቶ በሠላም ሊገባ አልቻለም። ነዋሪው ንብረቱን የሚያስከብርለት ቃፊር የለውም። ህጻናትን ከሰዶማውያን አጥቂዎች መጠበቅ የሚችል ኃይል ጠፍቷል። ከዚህ በላይ ምን መጨረሻ አለ። ክፉውን ዘመን ለመዋጀት ክርስትያኑም እስላሙም ባንድነት ይነሳ።

ይህን ተናግሬ ጽሑፌን ልቋጭ። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቅ ብቅ ያለውን ጃዋራዊኦነጋዊ አፓርታይድ ፋሺሽታዊ ፖለቲካን ሳያቆጠቁጥ ሊያስወግዱት ይገባል። ሽልማቱን በተቀበሉ ማግስት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ማሰማት አቅቷቸዋል፣ ጎረምሶች ከጎጃምጎንደር ወደ አዲስ አበባ የሚያደርሰውን መንገድ ዘግተው ዜጎችን አጉላልተዋል፣ ወጣቶች በየእስር ቤቱ ተወርውረዋል፣ የአፋር ሕዝብ ከጅቡቲ በመጡ ታጣቂዎች ተጨፍጭፏል። ዶክተር አብይ ጠላቶቻቸው እጉያቸው ሥር የሸጎጧቸው አሳሳች አማካሪዎቻቸው እንደሆኑ በቶሎ ሊገነዘቡ ይገባል። የኦሮምያ የድጋፍ ሰልፍ ወይንስ የባልደራሱ ሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄ መከልከል – የቱ የኅሊና ትኩረትን ይስባል? የትኛው ነው የውጭ አገር ሜዲያዎች ሽፋን ያገኘው? ከአድርባይ ደጋፊዎች ከንቱ ውዳሴና ከጥቅመኞች ማሸርገድ ይልቅ የእውነት ተናጋሪዎች ሂስና ተቃውሞ መሻሉን ዶክተር አብይ ሊገነዘቡ ይገባል። ሽልማቱ አነቃቂም (motivational) አደጋም (risk) ነው። ደሃ ሠርቶ እንዲበላ፣ ወጥቶ እንዲገባ ዘረኞች፣ ጽንፈኞችና ጉልበተኞች አደብ ሊገዙ ይገባል። ሥርዓትን ማስከበር፣ ፍትህን ከፍ ማድረግ የመንግሥት ሥራ ነው።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ፣ አሜን።

(B.K)

1 Comment

  1. Amharas are becoming nuts. Their self-contradictory non-sensical scribblings actually reflect their utter hypocrisy and illogical mindset.

    All their media outlets carry endless outcries of doom and destruction (ክፉው ዘመንና የሕዝብ መከራ) just because the Oromo demanded and continue to demand in one voice that their basic human and civil rights be respected, that liberty, democracy and democratic governance shall take root in the country, and that they articulated their basic right to self rule.

    For the Amhara hegemonists, everything is doom and gloom unless they fully controll the political, economic and cultural life of Ethiopia, the empire they still consider to be the inheritance of their forefathers. All their scribblings, though shrouded in all political doubletalk, is a cry for the return of the days of their supremacy. All rationality and logic are so lost in the wailings (ሙሾ፣ ወይም ፉከራና ቀረርቶ).

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.