በመቀሌ ያለ ፍትህ እየተሰቃዩ ያሉ የራያ ወንድሞቻቸን ስቆቃ – ደጀኔ አሰፋ

1 min read

የራያ ወንድሞቻቸውን የፍርድ ሁኔታ ለመከታተል ወደ መቀሌ የሄዱት የራያ ተወላጆች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ሲሆን በዚህ ሰዓት የጊደይ ዋዕሮ እህት የሆነችው አወጣሽ ክንፈ “ፎቶ እያነሳሽ ለራያ ኮሚቴ የምትልኪው አንች ነሽ” በሚል የሃሰት ክስ በመቀሌ አስረዋታል።

= ወንድማችን ሙለታ ዳግም ለህዳር 10 ተቀጥሯል። በጣም የሚገርመው ምስክሮች የተገኙ ቢሆንም ምስክሮች አልተገኙም በሚል የጥድፊያ ሻጥር ከ34 ቀናት በኋላ ይቅረብ ብሎ ችሎቱ ወስኗል።

= በተመሳሳይ በማንነታቸው ብቻ ታፍነው ያለ ፍትህ እየተሰቃዩ ያሉት እነ ሃይሉ በለጠ ፣ ጊደይ ዋዕሮ ፣ ዳርጌ ከበደ ፣ ብርሃኑ በላይ እና ሌሎች ወንድሞቻችን ዛሬ ከሰዓት በመቀሌ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ትህነግ ስለ ህገመንግስት የሚጮኸው ፣ በመግለጫው ሌሎቹን ፓርቲዎች እና የፌደራሉን መንግስት የሚከሰው ፣ የኔ ክልል ሰላም ነው እያለ የሚለፍፈው ምን ያህል ሃሰት እንደሆነ ለማረጋገጥ በራያ ተወላጆች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ እና ሰቆቃ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ብልሹ የፍትህ ሂደትን ማየት ብቻ በቂ ነው።

በርግጥ ከትህነግ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

ደጀኔ አሰፋ

3 Comments

 1. የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ ዬኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ አማራ ክልል አይሄዱም አለ
  ምን እየሆነ ነው
  በተለያዩ መግለጫዎቻችሁ የአማራና የትግራይ ህዝብ ወንድማማች ነው፣ ተደጋግፈው ኖረዋል ተዋድቀዋል ከተባለ በኋላ ተማሪን ወደ አማራ ክልል አልልክም ማለት ምን ማለት ነው፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ሲደርሱ የነበሩት እስከመገዳደል ያደረሱ ጸያፍ ድርጊቶች የተፈጸሙት ሙሉ ለሙሉ ምክንያታዊ ባልሆኑ የተማሪዎች ግጭት በራሳቸው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ የፌዴራል መንግስት በመሆናቸው ክልልሎች እንደፈለጉ ገብተው ሊያንቦጫርቁ አይችሉም፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ይህ ጸያፍ የተማሪዎች ድርጊት በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች ተፈጽመዋል፡፡
  አሁን የተፈለገው ባለው አመት ከትግራይ ህዝብ መፈናቀልን አስመልክቶ ያለማቋረጥ አመቱን ሙሉ በትግራይ ህዝብ ላይ ብቻ እንደደረሰ ያለአፍረት ስታወሩ ከመገረም አልፈን እንዴ ሌላው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተፈናቅሎ የሳምንት እንኳን የሞጮህለት አጥቶ የነበረው ምን ሊታዘብ እንደሚችል የገባችሁ አይመስለኝም፡፡ ችግሩ በሁላችንም የደረሰ አሳዛኝ መወገዝም የሚገባው መሆኑን ሳንዘነጋ፡፡
  ዛሬ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪን ዘርን መሰረት አድርጎ ከአማራ ክልል ትንኮሳ ስላለብኝ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አልልክም ማት በአማራ ህዝብ ላይ እያደረጋችሁ ያላችሁት በተለየ አቀራረብ ትኩረት ለማግኘት የሚደረግ ሴራ ነው፡፡ ከትግራይ ክልል ተማሪ ተገድሎ ለወላጅ አስከሬን እንዳልተላከ ለማስመሰል መሞከር ቅጥፈት ምሱ ለሆነ አካል አያስገርምም፡፡ ለካ ስፖርቱም በተመሳሳይ 24 ክለቦች እንዲሆኑና የወደቁ ክለቦቻችሁን ለማንሳት ደፋ ቀና ሲባል የነበረው መነሻው ከዛው ነው፡፡
  ብአዴንና ህወሃት ለ27 አመታት ስትፈተፍቱ እንዳልነበራችሁ እርስ በርስ በምታደርጉት ሽኩቻ ለምን ህዝቡን ሰላሙን እንደምትነሱት ሲስቡት ግራ ነው፡፡ ስልጣን ለካ እውር ያደርጋል፡፡ እናንተ እንደፈለጋችሁ ሁኑ ህዝቡን ግን ልቀቁት፡፡ ተማሪዎቹም በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ሄደው የመማር ነጻነት አላቸው፡፡ አንድ ክልል እዚህ ሂድ፣ እዛኛው ጋ ግን እንዳትሄድ እያሉ እነዚህን አፍላ ልጆች ማስደንገጥ፣ ሲያልፍም በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ጥላቻ እንዲያሳድሩ መግፋት ትልቅ በደል ነው፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነውና የፌዴራሌ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንዲመለከተው አቤት እንላለን፡፡

 2. ማጥ ውስጥ እንደገባ የመኪና ጎማ በመከራ ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከረው የአፍራሽ አፍራሽ ፓለቲካ ህዝባችንን ለባሰ መከራ እየዳረገ ይገኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሩህሩህ ነው፤ አስተዋይ ነው ማና ምን እንላለን። ይህ ግን እውሸት ነው። በጭራሽ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ አይነት ወሬ ነው። አብሮ መክሮ ሾልኮ ወንድምና እህቱን ለሞት አሳልፎ የሚሰጥ ወስላታ የሞላበት፡ የሥልጣን ሚዛን ተገን አርጎ በተለጣፊነት ለመኖር የሚያደገድግ፤ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ሰው ከገደለ በህዋላ የሚቆራርጥ፤ ምላስ የሚቆርጥ፤ በዘሩ ተሰልፎ በሌላው ላይ ሰቆቃ የሚያደርስና እና ቆሞ የሚመለከት ነው። ባጭሩ ለመኖር የሚገድል፤ የሚያስር፤ የሚያጭበረብር ነው። በሴት እህቶቹ በወንድሞቹ እና በህጻናት ላይ የሚነግድ ትውልድ ነው።
  በነጮቹ የዘመን መቁጠሪያ በ1960 የሃገራችን ሙዚቀኞች ስለ ደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች በነጮች የመጨቆን ሁኔታ ክንክኗቸው ዘፍነው ነበር። ዛሬ እነዚያ ሰዎች በህይወት ቢኖሩ በራሳቸው ሃገር ላይ ስላለው ሰቆቃና በብሄር ስም ንግድ ምን ይሉን ይሆን?
  ኃይለስላሴ ደስታ ” ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ” በሚል ርዕስ ሥር ስለ ሰላም መሻትና ስለ ልጆች የሰላም ጥማት በተለይም የጥቁሩ ዓለም ስለነበረበት የቅኝ ግዛት ሰቆቃ የተረከውን ያህል ዛሬ ምን ይጽፍ ነበር? መሬት ላራሹ በማለት የንጉሱን መንግስት በባዶ እጃቸው የተፋለሙት ዛሬ በህይወት ካሉ ምን ይሰማቸዋል ይሆን?
  የራያ ልጆች በመቀሌ አበሳቸውን በወያኔ እስር ቤት ሲቆጥሩ፤ የአፋር ወንድሞቻችን ለጊዜው ባልታወቁ ሃይሎች በጥይት እያለቁ ነው። በጎንደር ከተማና ዙሪያ ሰዎች እየሞቱ ነው። በወለጋ የኦሮሞን መብት እናስከብራለን ብለው ጠበንጃ ያነገቱ ሰውን እንደ እንስሳ ይገድላሉ። በመቀሌ እና በባህርዳር እንፋለማለን እያሉ ይፎካከራሉ። የዚህ ሁሉ መሰረቱ ዘረኝነት ነው። የወያኔ ፓለቲካ!በአሁኑ የኢት. ፓለቲካ ሰው መዳን ያለበት ከሲኦል ሳይሆን ስለት ከያዙ ሰዎች ሆኗል። ፍራሽ አዳሽ እንጂ ሰላምን አዳሽ በጠፋበት የአስረሽ ምቺው የዘር ፓለቲካ የከፋውም የደላውም የሚሞትበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የዘር ፓለቲካ ፍጻሜው የአመድ ክምር ነው። አትራፊም ተራፊም አይኖርም። ሮጦም ማምለጥ አይቻልም። ያኔ እንኳን ሰው መንገድ ይከዳል። እስከዛው መሳሪያ ያነገቱ አለቆቻችን ይጨፍሩ። ለነገር ሁሉ ማብቂያ እንዳለው ካለፈ ታሪክ አይማሩምና! በወስላቶች ወጥመድ ገብታችሁ ለምትሰቃዬ ወገኖቼ እጅግ አዝናለሁ። ጸሎቱ እና ምህላውን ለጊዜውም ቢሆን በመተው ምን ብናረገ ሰው ሆነን ከሰው ጋር እንኖራለን በማለት የዘር አጥሩን እስካልሰበርን ድረስ ከዚህ የጥለፈውና ያዘው ፓለቲካ አንወጣም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.