ዶ/ር አምባቸውን እያስታወሱኝ ያሉ የተወሰኑ ነጥቦች እንደወረዱ!!!

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

ስለዶ/ር አምባቸው ይህን ጽሁፍ ስፅፍ ከተሰዋ አራት ወር ሊሞላው እንደሆነ ባውቅም ቁጭቴ ግን እየባሰ እንጅ እየቀዘቀዘ ሲመጣ አልሰማህ ብሎኛል። ይህን የምለው ከዶ/ር አምባቸው ጋ የአንድ አከባቢ ተወላጅ ስለሆንኩ ወይም ዶ/ር አምባቸው የትግል ጓዴ፣ ወንድሜና ጥብቅ ጓደኛየ ስለሆነ ብቻም ሳይሆን የእሱ በህይወት አለመኖር የኢትዮጵያንና በተለይም ደግሞ የአማራን ህዝብ መሰረታዊ ጥቅሞች ለማስከበር በሚደረገው ትግል ላይ ጥሎት ያለፈው ክፍተት ገዝፎ ስለታየኝ ነው። በርግጥ ስለዶ/ር አምባቸው አውርቸም ሆነ ፅፌ እጨርሳለሁ ብየ አላስብም፤ በማንነቱ ዙሪያ ለጊዜው የመጡልኝን ሃሳቦች እንደወረዱ ላካፍላችሁ ስለፈለኩ እንጅ።

ዶ/ር አምባቸው ሲበዛ ከሰዎች ጋ ተግባቢ ነው። ወንዱንም፣ ሴቱንም፣ አዋቂውንም ልጁንም ስራ ሃላፊውንም ሰራተኛውንም እንደየባህሪው የመያዝ ታላቅ ተሰጥዖ የነበረው ሰው ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ቀልድ አዋቂና ፍልቅልቅ የነበረ በመሆኑ ሁሉም ሰው ሊቀርበው የሚፈልግና የሁሉም ጓደኛ ነበር ብል እያጋነንኩ አይመስለኝም። እኔ እስከማውቀው ድረስ አምባቸው በተግባቢነቱና በቀልድ አዋቂነቱ የብዙዎቹን ቀልብ ገዝቶ የነበረ ሰው መሆኑን ብዙዎቹ እንደሚመሰክሩ እርግጠኛ ነኝ። ስለአምባቸው ቀልድ አዋቂነት ሳነሳ አንድ ነገር ታወሰኝ። አይናፋር ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን ጓደኞቹን ሲያገኝ “በሉ እንግዲህ የኔንም የናንተንም ወሬ እኔው ራሴ እያወራሁ ጫዎታችን እንዲደራ እናድርገው” እያለ ፈታ የሚያደርግ ሰው ነበር።

ከዚህ ሌላ ዶ/ር አምባቸው ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚያከብር ግን ደግሞ የለየለት ጀግና ነበር። አምባቸው ከልጅነቱ ጀምሮ ሰው የማይተናኮል፤ ከደረሱበት ግን ፊት ለፊት የሚጋፈጥና ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ የሚያስብና የሚሰጋ ሰው አልነበረም።  አምባቸው የተሳሳተ አቋም ይዞ እንኳ ቢሆን ላመነበት ነገር ህይወቱን አስልፎ ከመስጠት ወደኋላ የማይል ቆራጥ ታጋይ ነበር። አምባቸው ፍትህ ተዛብቷል ብሎ በርግጠኝነት ካሰበ ያገር መሪ ይሁን የጦር አዛዥ ወይም የደህንነት ሃላፊ ጋር አይደራደርም። ለዚህም ነው ባንድ ወቅት ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋ አንገት ላንገት እስከመተናነቅ ደርሶ የነበረው። እንዲያውም ይህን ሁኔታ ሲያጫውተኝ “በዚህ ደረጃ ቁጡና ግንፍልተኛ (Aggressive) አትሁን፤ ለተንኮለኞችና ለሴረኞች ጥቃት የማትጋለጠው በመርህ ላይ የተመሰረተ የማያወላውል ፅናት (Assertiveness) ሲኖርህ ነው ስል ምክር ብጤ ለገስኩት። በዚህም አለ በዚያ ይህ ቀጥ ያለ ባህሪው በተለያዩ መድረኮች የሚታይ መገለጫው እንደነበር በነዚሁ መድረኮች ከሱ ጋ የተሳተፉ ሁሉ ሊመሰክሩ እንደሚችሉ አልጠራጠርም። እንዲያውም እዚህ ላይ ባንድ ወቅት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ አያሌው ጎበዜ ስብሰባ ላይ አደረጉት የተባለ ንግግር ታወሰኝ። “አምባቸው እሱ ያመነበት ነገር ተፈፃሚ ካልሆነ እኛን ሊመታ ዱላ ወይም ወንበር ካልሆነም ደንጋይ የሚፈልግ ሰው ነው” ሲሉ ነበር የገለፁት አቶ አያሌው ። (በነገራችን ላይ አቶ አያሌው አደረጉት የተባለውን ንግግር የሰማሁት ከራሱ ከአምባቸው ነው።)

ዶ/ር አምባቸው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኛ ነኝ ብሎ ያምን እንደነበረም አቃለሁ። በመሆኑም የአማራ ህዝብ ፍትሃዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥለትና ሰብዓዊ መብቱ እንዲከበርለት ከአምባቸው በላይ የታገለ አለ ለማለት ይከብደኛል። አምባቸው ለአማራ ህዝብ ተመጣጣኝ የሆነ ፖለቲካዊ ስልጣን ውክልና ሌት ተቀን ሲለፉና ሲደክሙ ከነበሩ እጅግ በጣም ጥቂት ታጋዮች ውስጥ ግንባር ቀደም ነበር ብል አላጋነንኩም። በአጠቃላይም የአማራ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም ተነክቷል ብሎ ባሰበበት ጊዜ ሁሉ ግንባር ቀደም ሆኖ በመውጣት ያለምንም ይሉኝታ የቻለውን ሁሉ ትግል ያደርግ እንደነበር የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩ ይመስለኛል።

ዶ/ር አምባቸው ወደር የማይገኝለት ኢትዮጵያዊም ነበር። ልክ የአማራ ህዝብ ጥቅም መረጋገጥ አለበት ብሎ እንደሚታገለው ሁሉ የሌሎች የኢትዮጵያ ብሄርና ብሄረሰቦች ጥቅምም መከበር እንዳለበት በፅናት ያምን ነበር፤ ለዚህም ሳያሰልስ ተንቀሳቅሷል። በዚህ ረገድ አምባቸው ይፀየፈው የነበረ ትልቅ ጉዳይ ቢኖር የሆነ ቡድን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በላይ ልጠቀም ብሎ ሲነሳ ነው። ለዚህም ነው ከህወሃት ሰዎች ጋ አይንና ናጫ የነበረው። እውነት ለመናገር እንደ አምባቸው ከአቶ መለስ ጀምሮ የህወሃትን ከፍተኛ አመራር (Strategic Leadership) ይፀየፍ የነበረ ሰው አለ ብየ አላምንም። በአምባቸው እይታ እነዚህ የህወሃት አመራሮች በጣም አረመኔ፣ ጨካኝ፣ ዘራፊ፣ ስግብግብና ተንኮለኞች ናቸው። በዚህ የተነሳም እኔ በነበርኩበት መድረክ ሁሉ አምባቸው ካለ ስለህወሃት የበላይነት ሳያነሳ ቀርቶ ታዝቤ አላቅም።

ዶ/ር አምባቸው ስለነዚህ የህወሃት አመራሮች ከሚያነሳቸው ጉዳዮች አንዱ የፀጥታ ተቋማቱን ሙሉ በሙሉ በነሱ ቁጥጥር ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል የሚለው ይገኝበታል። በዚህ ረገድ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ተቋማቱ የሚሽከረከሩት በህወሃት ሰዎች ነው በሚል ይሞግት ነበር አምባቸው። ይህም ብቻ አይደለም በነዚህ ተቋማት ውስጥ ያሉ የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች አባላት የሆኑ ሰዎች ተመጣጣኝ ውክልና አላገኙም ብሎ ያምንና እንዲስተካከልም ይከራከር ነበር። እንዲያውም ይላል አምባቸው፤ እንዲያውም የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች አባላት በተለይም አማራዎች እየተለዩ ይጠቃሉ ከማለት ቦዝኖ አያቅም። በዚህ ዙሪያ አዘውትሮ ይጠይቅና አጋጣሚውን ባገኘ ቁጥር ፊት ለፊት ይጋፈጥ የነበረው የብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጉዳይ አንዱ ነው። አምባቸው ይህን ያደርግ የነበረው ጄኔራል አሳምነው ከሰራዊቱ የተወገደውም ሆነ በኋላ ላይ የታሰረው ለአማራ ህዝብ ጥቅም ስለታገለና የህወሃት አመራር ጥርስ ውስጥ ስለገባ ነው ብሎ በፀና ያምን ስለነበር ነው።

እዚህ ላይ የፀጥታ ተቋማቱን በተመለከተ ባንድ አጋጣሚ የተለዋወጥነው ሃሳብ ትዝ አለኝ። በአንድ ወቅት ወደውጭ ለመውጣት የአሻራ ምርመራ ማድረግ ስለነበረብኝ ፎረንሲክ ቢሮ ሄድኩኝ። እዛ እንድሄድኩ ከበር ጀምሬ የታዘብኩት ነገር በጣም ስሜቴን የነካ ነበር። የሰራተኞቹ ስብጥርም ሆነ የሚነገረው ቋንቋ የአንድ አከባቢ ነበር። እንዴት የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤት የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ነፀብራቅ አይሆንም፤ የታገልነው ለዚህ ነበር እንዴ፤ እነዚያ ንፁሃን የኢትዮጵያ ወጣቶች ውድ ህይወታቸውን የከፈሉትና አጥንታቸውን የከሰከሱት ይህን ለማምጣት ነበር እንዴ? ስል በጣም ተበሳጨሁ። አስታውሳለሁ አምባቸው ለስብሰባ መጥቶ አዲስ አበባ ነበር። ቀጥታ የሄድኩት እሱ ጋ ነው። ሄጀም ያጋጠመኝ ሁኔታ ገለፅኩለት። ፈገግ ብሎ የሆነ ነገር ሊናገር ሲል እድል ሳልሰጠው ለምን ግን ትጥቅ ትግል አንጀምርም? ካልሆነስ ለምን የራሳችን የፖለቲካ ፓርቲ መስርተን የኢህአዴግን በአጠቃላይና በተለይ ደግሞ የህወሃትን ሸር አንበጥሰውም አልኩት። ፈገግ እንዳለ ሲያደምጠኝ ቆይቶ አሁን ጥሩ ሃሳብ አመጣህ፤ እኔንም እኮ “ቀን ከሌት እረፍት ነስቶኝ ያለ ጉዳይ ነው” አለኝ። ቀጠል አደረገና “ትጥቅ ትግሉ ግን የሚሆን አይመስለኝም፤ ምክንያቱም በዛ መንገድ ስልጣን የሚይዝ ሃይል አምባገነን መሆኑ አይቀርም። የፖለቲካ ፓርቲ ግን ጥሩ ሳይሆን አይቀርም ፤ ግን በደንብ እናስብበት” አለኝ። በዚህ ተስማምተን እኔ ወደውጭ ሄጀ ሳልመለስ ቀረሁ። በርግጥ ከዚያ በፊትም ቢሆን እንዲህ አይነት አማራጮችን በቀልድ መልክ እያነሳን እናወራ ነበር። እንዲያውም አሁንም በህይወት ካለ አንድ ከፍተኛ የአዴፓ አመራር ጋ ተመሳሳይ ቀልዶችን (ትጥቅ ትግል ወይም ፖለቲካ ፓርቲ መመስረት በሚለው ዙሪያ ማለቴ ነው) እያነሳን እናወራ ነበር። ይህን ፅሁፍ ካነበበው ትዝ ሊለው ይችላል።

ከህወሃት አመራር ጋ በተያያዘ ዶ/ር አምባቸው ያነሳ የንበረው ሌላው ጉዳይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ነው። በዚህ ረገድ የአምባቸው ቅሬታ ብዙ ነበር። ሲጀመር ኤፈርት (Effort) የተባለው ድርጅት በህወሃት አመራር የተቋቋመው በዋነኛነት በጦርነቱ ወቅት ከኢትዮጵያ ባንኮች በተዘረፈ ገንዘብና ንብረት ነው የሚል አቋም ነበረው። ከተቋቋመ በኋላም የፈለገውን ያህል የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የተለያዩ አቅርቦቶች ከየትኛውም የመንንግስት ይሁን የግል የንግድ ተቋም በበለጠ ይሟላለታል ይል ነበር። በአምባቸው አስተሳሰብ ኤፈርት በነፃ የገበያ ውድድር የሚገዛ ሳይሆን ሁሉም በጁ ሁሉም በደጁ የሆነለት ተቋም ነው። ከኤፈርት በመለስ ደግሞ ሌሎች በህወሃት ዙሪያ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦች የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ለማግኘት ይችሉ ዘንድ ሁሉም ነገር የእግዜር መንገድ ሆኖላቸዋል ሲል አምርሮ ይተች ነበር አምባቸው።

ሌላው ከዚህ ጋ ተያይዞ ዶ/ር አምባቸውን ይተናነቀው የነበረውው ከወልቃይትና ከራያ ጋ የተያያዘው ጉዳይ ነው። በሱ እምነት የህወሃት አመራሮች እነዚህን ቦታዎች ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ያደረጉት ለም መሬት ስለፈለጉ ነው። በተለይ ቦታዎቹ ወደትግራይ የተካለሉበት መንገድ ሲበዛ ያበሳጨዋል። የብስጭቱ መነሻ ደግሞ እነዚህ የህወሃት አመራሮች ነፃና ግልፅ የሆነ ህዝብ ውሳኔ እንዲደረግ እንኳ አልፈቀዱም ይል ስለነበር ነው። በዚህም ምክንያት የህወሃት ሰዎች ጥቅምና ስግብግብነት እንጅ ምንም አይነት ህዝባዊነት የላቸውም ሲል በተደጋጋሚ ይደመጥ ነበር።

እንደ ዶ/ር አምባቸው እምነት ፖለቲካውም ቢሆን ከህገመንግስቱ ጀምሮ በህወሃት ሰዎች ፍላጎትና ጥቅም የተቃኘ፣ በነሱ የሚዘወር፣ በነሱ የሚነሳና በነሱ የሚከስም እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀ ነው። በተለይም “…ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረም…” በሚል ህገመንግስቱ ላይ የሰፈረው ሃረግ እንደ አምባቸው አገላለፅ “መርዝ” ነው። በሱ እምነት የህወሃት ሰዎች በተለይም አቶ መለስ ይህ ሃረግ ህገመንግስቱ ውስጥ እንዲሰፍር ያደረጉት በቂም በቀል የአማራው ህዝብ በሌሎች እህት ወንድሞቹ በጥርጣሬ እንዲታይና ህዝቦችን በመከፋፈል ለመግዛት አስበው ነው ሲል ይገልጻቸዋል። እንዲያውም አንዳንዴ ምርር ሲለው በአለም ላይ ከነዚህ ሰዎች በላይ በፈጠራ የሃሰት ትርክት ህዝብ እየተበቀለ ያለ ቡድን የለም ሲል እሰማው ነበር። ይህም ሆኖ ግን አምባቸው የትግራይ ህዝብንና የህወሃት ሰዎችን በፍፁም አንድ አድርጎ አያይም። እሱ ይንገሸገሽ የነበረው በህወሃት ሰዎች እንጅ የትግራይ ህዝብማ ይላል፤ የትግራይ ህዝብማ በስሙ የነገድበታል እንጅ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በስርዓቱ ተጎድቷል ብሎ ያምናል።

አምባቸው የህወሃት ሰዎችን ጠቅለል አድርጎ የሚገልፃቸው በረቀቀ ዘዴ የራሳቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቅላይነት (Monopoly) ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ያሉ መሰሪና ከሃዲ ስብስቦች ናቸው በሚል ነው። በዚህ ረገድ ህዳር 2010 አ.ም አከባቢ ያለኝ ታወሰኝ። “እነዚህ ሰዎች ወይ ዴሞክራሲያዊ አይደሉ፤ ወይ ህዝባዊነት አይሰማቸው፣ ወይ ቅንነት ሲያልፍ አይነካቸው፣ ወይ ከዘረፋና ከሌብነት ነፃ አይደሉ፣ ወይ ትንሽም ቢሆን ይሉኝታ አልፈጠረባቸው፤ እንዲያውም መሰሪዎች፣ ከሃዲዎች፣ አምባገነኖችና ጀብደኖች ናቸው” ሲል ድምፁን ጎላ አድርጎ ስሜቱን ገለፀልኝ። ቀጠል አደረገና “ይህን ሁሉ ሳገናዝብ እነሱና ብአዴን የፈጠሩት ጋብቻ ያልተገባ ነበር” አለኝ። ሆኖም ግን ሲል ቀጠለ፡ “ሆኖም ግን ቢያንስ የትግራይን ህዝብ እንወክላለን ብለው ስለሚንቀሳቀሱ በተቻለ መጠን ሰላማዊ፣ ህጋዊና ጥበብ የተሞላበት ትግል በማድረግ ከዚህ በፊት የሰሯቸውን ጥፋቶች እንዲያስተካክሉ፤ ወደፊትም ችግር እንዳይፈጥሩ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ብሎ ስለህወሃት ሰዎች ያለውን የመጨረሻ ንግግር ደመደመ።

2010 ላይ ከዶ/ር አምባቸው ጋ በተገናኘንበት ወቅት ያጫወተኝ ሌላው ጉዳይ ኦህዴድን የተመለከተ ነው። ኦህዴድ ውስጥ በርከት ያሉ ጎበዝ (በሱ አገላለፅ እሳት የላሱ ወጣቶች) እንዳሉና ትግሉን እያገዟቸው መሆኑን፤ በዚህም ምክንያት ከነሱ ጋ አብሮ የመስራት ተስፋው ከፍተኛ እንደሆነ ተነተነልኝ። ቀጠል አድርጎ በሂደት ግን አንዳንዶቹ ፅንፈኞች ችግር የሚፈጥሩ ከሆነ ገዝፈው ሳይወጡ ይሉኝታ የሌለው የመደብ ትግል በማድረግ እንደሚያስተካክሏቸው ተስፋውን አካፈለኝ። ላረጋግጥልህ የምፈልገው አለኝ ቀጠለና፣ ላረጋግጥልህ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድን ቡድን የበላይነት እንዲሁም አድራጊና ፈጥሪነት የሚሸከም የብአዴን አመራርም ሆነ አባል አይኖርም በሚል በማውቀውው ወኔው ሆኖ አቋሙን ገለፀልኝ።

ይህን ተስፋ አሸክሞኝ ከተመለሰ በኋላ አንድ ቀን ደውየ አናግሬዋለሁ። ከዚያ በኋላ በየራሳችን ምክንያቶች ተደዋውለንም ሆነ ተገናኝተን አናውቅም። በዚህ ሁኔታ ነበር እንግዲህ አምባቸው ድሮ መብቱ ይከበር ዘንድ ከማንም በላይ ይታገልለት በነበረው ጀኔራል አሳምነው በተቀነባበረ “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ጥቃት መስውዕት ሆነ የሚል እጅግ በጣም አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ዜና ከአራት ወር በፊት የሰማሁት። በኔ እምነት ይህ በአምባቸው ላይ የደረሰ ጥቃት በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ የደረሰ ጥቃት ነው ብየ አላምንም። ጥቃቱ የተቃጣው ለብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት፣ እኩል ተጠቃሚነት፣ ፍትሃዊነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ኢ-አድሏዊነት በሚደረገው ትግል ላይ ነው ብየ አስባለሁ። ከአማራ ህዝብ ጥቅም አንፃርም የአምባቸው ሞት ጥሎት ያለፈው ክፍተት (አይቻልም የሚል እምነት ባይኖረኝም) በቀላሉ ይደፈናል ብየ ግን አላምንም።

በመጨረሻም የአምባቸው በህይወት አለመኖር በኢትዮጵያም ይሁን በአማራ ህዝብ ትግል ላይ ሰፊ ክፍተት ጥሎ ያለፈ መሆኑን ብገነዘብም ፤ ያለው አማራጭ ጠላት ከሚያፈሩ ንግግሮችና ተግባራት ተቆጥበን እሱ በተለይም ወደ መጨረሻው አከባቢ ይዟቸው የነበሩትን ሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ አስተዋይነትትና ጥበብ የተሞላባቸው የትግል ስልቶች አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ነው።

 

ሰላም ለሃገራችንና ለህዝቦቻችን!!!

መሰረት ተስፋ

 

One Response to ዶ/ር አምባቸውን እያስታወሱኝ ያሉ የተወሰኑ ነጥቦች እንደወረዱ!!!

 1. የዶ/ር አምባቸዉ መኮነን ስህተቶች
  ዶ/ር አምባቸዉ የሚወደድና ግርማ ሞገስ ያለዉ ሃቀኛ መሪ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም የሰራቸዉ ስህተቶች ነበር፡ ከነዚህም ዉስጥ፡
  1. ወጥ አቋም አለመኖር- በራሱ መር ከመመራትይልቅ አንድ ጊዜ ከአማራ ብሄርተኞች ጋር ይነጉዳል ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጠላቶቻችን ጋር/ወላዋይነት፣
  2. ክፍተት መስጠት- እንደነ ዶ/ር ደብረፅዮን የተከበረ መሪ መሆን ሲችል ከሴረኞች ጋር በሚያደርገዉ ግንኙነት አብይ አላማዉን እንዲያሳካ አድረጎታል፣
  3. ችኩልነት- ነገሮችን ከስር መሰረታቸዉ ከመረዳት ይልቅ ግንፍል ግንፍል በማለቱ ልዩነቶች እንዲሰፉ አድረጓል፣
  4. የታጋዮችን ዉለታ መርሳት- በኬሚሴ ንፁኃ ሲጨፈጨፍ፣ በቤንሻጉል ሰዎች በጦር እየተወጉ እርሱ መግለጫ ሲሰጥ ወጥ በወጥ ሆኖ እንዳልታየ ሁሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተምዘገዘጉ ከጉድ ያወጡትን እነ ዘመነ ካሴ፣ ጄኔራል አሳምነዉ ፅጌን እና አማራ ፋኖችን ዉለታ እረስቶ በዘር ማጥፋት ወንጄል ለማስከሰስ ከአህያዉ ደመቀ መኮነን እና ከመርዙ ንጉሱ ጥላሁን ጋር ሆኖ ከተላቶቻችን ጋር መምከሩና መስማማቱ ለዚሁሉ ችግር መፈጠር ተጠያቂ ነዉ፡፡

  Avatar for Mulualem

  Mulualem
  October 18, 2019 at 2:24 am
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.