ጠ/ሚ አብይ አህመድ በዛሬው እለት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጡ

1 min read

ጠ/ሚ አብይ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡት መግለጫ
=====================================
አሁን ስለ ሁለት ነገሮች ቆመን የምናስብበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለ ትናንት እና ስለ ነገ፡፡ ስለማንለውጠው ትናንት እና ስለምንለውጠው ነገ፡፡ በአብዛኛው የሀገራችን የልሂቃን ክርክሮች በትናንትናው ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ያ ክርክር ደግሞ አሉታዊውን ጎን በማጉላት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሕዝባችን ክፉም ደግም አይቷል፡፡ በሆደ ሰፊነቱ፣ በዕርቅ ባህሉና ላነገበው ራእዩ ሲል ክፉዎቹን ተምሮባቸው አልፏል፡፡ አንዳይደገሙ ታግሏቸዋል፡፡ በጎዎቹን ደግሞ ይዟቸው መጥቷል፡፡

ትናንትን አንቀይረውም፡፡ ትግሉ መሆን ያለበት የትናንትን ስህተት ማረም እና ጥንካሬውን ጠብቆ ማስፋት ነው፡፡ ተግባራዊነታችን እና ውጤት ተኮር መሆናችን የሚገመገመው ስለትላንት በማውራት ሳይሆን ዛሬን አበጃጅቶ ወደ ብሩህ ነገ በመጓዝ ነው፡፡ የትናንቶቹን እየወቀስን እኛ ለምን እንደግመዋለን፡፡ የግፍና የጭቆና አገዛዝን የተቃወመ መልሶ ያንን ሊሰራ አይገባውም፡፡ የመከራ ዘመን የሚታለፈው ዘመኑ ያመጣውን ችግር በመቃወምና በመጥላት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ የተሻለ ዘመን በማስፈን እንጂ፡፡ ንጉሣዊ አገዛዝን ተቃውመን ያካሄደነው አብዮት፤ ደርግን ተቃውመን ያካሄድነው ትግል፤ ባለፍው 27 ዓመት የነበረውን ሥርዓት ተቃውመን ያደረግነው ለውጥ ከቀደሙት የተሻለ ሥርዓት እንድንዘረጋ ካላደረገን የኛ ለውጥ ናፋቂነት ምኑ ላይ ነው? የተሻለ እኩልነት፣ የተሻለ ዴሞክራሲ፣ የተሻለ ፍትሕ፣ የተሻለ ወንድማማችነት፣ የተሻለ ብልጽግና ካላመጣን ታድያ የትግላችን ዓላማ ምን ነበር?

ትናንት የተዛነፈውን የሚያስተካክል ሥርዓት ነገ እንዴት መገንባት እንደምንችል ለምን አንነጋገርም? ከትናንት የሚሻልና ትናንትን የሚያስንቅ ሥራ መስራት የምንችልው ዛሬና ነገ ነው፡፡ ትናንት መማሪያና መዝናኛችን እናድርገው፡፡ ሁሉንም በልኩ ፈትሸን ለነገ ጥቅም እናውለው፡፡

ሀገር ለማፍረስ የሚደረጉ ነገሮችን አብረን እምቢ ማለት አለብን! ዘግናኝ ተግባራትን እምቢ ማለት አለብን! ነባር ዕሴቶቻችንን የሚሽሩ ተግባራትን አንፈጽምም ማለት አለብን! ለመሆኑ ባለ ብዙ ብሔርና ባለ ብዙ ሃይማኖት መሆን የችግር ምንጭ ከሆነ እነ ሕንድ እና ስዊዘርላንድ እንዴት ጸኑ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ አንድ ዓይነት እምነትና ቋንቋ፣ ብሔርና ባህል ይዘው የፈረሱ ሀገሮች እንዳሉም ማወቅ አለብን፡፡
ሕዝቦችን የሚያኖራቸው ብዝኃነት ወይም ወጥነት አይደለም፤ ኅብረትና ስምምነት እንጂ፡፡ ዛሬ ኮርተው የሚኖሩት አሜሪካውያን እና ካናዳውያን ሀገር አጽንተው የኖሩት በሥልጡን አስተሳሰብና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት እንጂ የሚለያያቸው ነገር ጠፍቶ አይደለም፡፡

ከሰሞኑ በሀገራችን የተከሠተው ጭካኔና አረመኔያዊ ድርጊት የሁላችንን አንገት ያስደፋል እንጂ ማንንም አያኮራም፡፡ ኦሮሞነትም፣ አማራነትም፣ ጋሞነትም፣ ጉራጌነትም፣ አፋርነትም፣ ሌላውም የሀገር መኩሪያ መመኪያ እንጂ መወንጀያ አይደለም፡፡ የገደልነውም ያፈናቀልነውም የራሳችንን ኩራት፣ የራሳችንን መከታ ነው፡፡

በዚህ መንገድስ እስከ መቼ እንጓዛለን? አንድ ወደፊት ስንሄድ ሁለት ወደኋላ የሚመልሱንን ማናቸውንም ሃይላት ማስቆም አለብን፡፡

መንግሥት የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ ሆደ ሰፊነቱን አብዝቶ ሲያስታምም ከርሟል፡፡ ከኃይልና ጉልበት ይልቅ ትምህርትና ምክክር ይሻላል ብሎ ታግሷል፡፡ ትእግሥቱ ፍርሃት፣ ማስታመሙ ድካም የመሰላቸው ካሉ ግን ተሳስተዋል፡፡ አንዳንዶች እንዲማሩ ተብሎ ሰፊ ልብና ትከሻ ሲሰጣቸው አጋጣሚውን ሳይጥቀሙበት ቀርተው የዜጎቻችን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋለጥበት ምክንያት ተፈጥሯል፡፡

መንግሥት የዜጎችንና የተቋማትን ደኅንነት ለመጠበቅ የሃገሪቱ ህግ ባስቀመጠው መሰረት የመስራት ግዴታ አለበት፡፡

በአንድ በኩል የፖለቲካውንና የዴሞክራሲውን ምኅዳር እያሰፋን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትሕና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንሠራለን፡፡ በአንድ በኩል ያለፉትን ስሕተቶች ለማረም እየሠራን በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ህጋዊና ተመጣጣኝ ርምጃዎችን እንወስዳለን፡፡ በዚሁ አግባብ አልሚ ሁሉ የሥራውን፣ አጥፊ ሁሉ ደግሞ በጥፋቱ ልክ ተጠያቂ እየሆነ ይሄዳል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም፣ ድኅንነትና አንድነት ለማስጠበቅ ሲል ሕግና ሥርዓት እንዲያስከብር ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ ተገቢም ጥያቄ ነው፡፡ ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት በመጣንበት መንገድ ላለመጓዝ ስንል ታግሠናል፡፡ በመጣንበት መንገድ አንጓዝም ስንል ግን የመንግሥት በብቸኝንት ኃይል የመጠቀም መብት ቀርቷል ማለት አይደለም፡፡ መንግሥት ሕግ የሚፈቅድለትን ሁሉ ለማድረግ አቅምም፣ ዝግጁነትም፣ ብቃትም አለው፡፡

ችግሮች በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተፈቱ ሀገራችን ወደ ብልጽግና ለመጓዝ እንድትችል የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚጠበቅባችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡ የሚመከረውን ምከሩ፤ የሚገሰጸውን ገስጹ፡፡ የሚመረቀውን መርቁ፤ የሚረገመውን ርገሙ፡፡ አጥፊዎችንና አፍራሾችን ተጸይፋችሁ ከእውነተኞች ጋር ቁሙ፡፡

በምንም መልኩ እውነትና ውሸት፣ ጥፋትና ልማት፣ ሥርዓት አልበኝነትና ሕግ፣ ወንጀልና ንጽሕና፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ፣ አሳዳጅና ተሳዳጅ፣ ገዳይና ሟች በጋራ ሊቆሙና ሃገር ሊገነቡ አይችሉም፡፡ ፖለቲከኞቻችን ሥልጡን ፖለቲካን የሚያራምዱና ለሰውነት ቅድሚያ የሚሰጡ፣ ሚዲያዎቻችን በሕግና በሥርዓት የሚመሩ ካልሆነ የማያባራ ግጭትና እልቂት ያጋጥመናል፡፡ በጋራ ማሸነፍን ምርጫችን ካላደረግን እጣ ፈንታችን መጠፋፋት ይሆናል፡፡

የጸጥታ አካላት የሀገርን ሰላም፣ ደኅንነት፣ የሕዝቦችን አብሮ መኖርና አንድነት፣ የተቋማትንና የኢንዱስትሪዎች ደኅንነት በሕግ አግባብ የመጠብቅ ግዴታችሁን እንድትውጡ፡፡ የፍትሕ አካላትም ለአጥፊዎች ትምህርት፣ ለትጎጂዎች ካሣ የሚሆን የተፋጠነ ፍትሕ በማስፈን ፍትሕን እንድታረጋግጡ፡፡ መንግስት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው በርካታ ውይይቶች ተጨማሪ እልቂት በማያመጣና አስተማሪ በሆነ መልኩ ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ዜጎች በመገንዘብ ድጋፋችሁን እንድታጠናክሩ፡፡

ዋልታ ረገጥ የብሄርና የእምነት ጫፍ ላይ ቆማችሁ ችግሮችን የምታባብሱ ወገኖች በአተያያችሁና በመልዕክቶቻችሁ ተጨማሪ እልቂትና ጥፋት ከሚያመጣ ማናቸውም ተግባር እንድትቆጠቡ፡፡ ነገሩን ሁሉ በስሜትና በወገንተኝንት መለኪያ ብቻ ሳንመለከት ከስሜት በላይ ሆነን የተጋረጠብንን አደጋ በብልሃት መቀልበስ እንድንችል ዜጎች የዘወትር ትብብራችሁ እንዳይለየን እጠይቃለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ !

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ

Posted by FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) on Sunday, November 3, 2019

11 Comments

 1. አሁንም 86 ሰው በሞት ከተነጠቅን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ለአካል ጉዳት ከደረሰና ከቤት ንብረት ከተፈናቀሉ በኋላ ሆደሰፊነት የሚለው አባባል ለመሸፋፈን የተፈለገ ወንጀለኛ እንዳለ ያረጋግጣል፡፡ ስንጠብቅ የነበረው የብጥብጥ መሪው ጃዋር መሃመድ ለፍትህ ቀርቧል የሚል ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ እናዝናለን፡፡ ከእርስዎ ብዙ ጠብቀን ነበር ሁሉም ንፋስ ሆነ ቀረ እንጂ፡፡

  አሁን በዋናነት የምጠይቅዎት በአዳማ፣ በዶዶላ፣ በሞጆና በመሳሰሉት በብሄራቸው ብቻ በቄሮ ተብዬዎች ጠቋሚነት ወደ ማጎሪያ እየተጋዙ ነው፡፡ ልብ ይደረግ ወንጀለኞች ቤታቸው ቁጭ ብለው ሰላማዊው ወጣት እየታፈሰ ነው፡፡
  ዋናው የአገሪቱን ሰላም ያደፈረሰው ጃዋር መሃመድ ሳይታሰር ማንም መታሰር የለበትም፡፡ በህግ ፊት ሁሉም እኩል ነው የሚለው መሬት ላይ እናውርድ፤ አህያውን ትቶ ዳውላውን መደብደብ ያስተዛዝባል፡፡

 2. የመጀመሪያው ህገ ወጥ አቢይ ራሱ ነው! ራሱን የሚቆጥረው እንደንጉሥ እንጂ እንደ የአንድ በፓርላማ የሚትተዳደር ፌደራላዊ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ታላላቅ ሃገራዊ ጉዳዮችን ለፓርላማው አቅርቦ ማስወሰን እንጂ እንደፈለገው እርምጃ መውሰድ አይችልም ነበር። እሱ ግን በፈለገው ቦታ፣ ጊዜና ሰዐት መከላከያ ሰራዊቱን አዞ ይገድላል፣ ያስገድላል። የክልሎችን ሥልጣን በመተላልፍና ከህግ ውጪ በፓርላማ ሳያስወስን ክልሎችንና አንዳንድ ቀጠናዎችን ኮማንድ ፖስት ዘርግቶ ከወያኔ ጊዜ በከፋ ሁኔታ ህዝቡን ያሰቃያል (ወለጋ፣ ቦራና፣ ጉጂ፣ ደቡብ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እየተጨፈጨፉ መሆናቸውን የሃበሻ ሚድያዎች አውቀው ጸጥ ብለዋል)። የአንድ ክልል ፕረዚደንትና ሌሎችም አመራሮች በክልሉ ፓርላማ ብቻ የሚመረጡ ሆኖ ሳለ፣ አቢይ ግን ፌደራላዊ ስርዐቱን በመጣስ ክልሎችን እንደ ጠቅላይ ግዛትቶች ቆጥሮ እንደፈለገ ይሽራል፣ ይሾማል።
  ህዝብ እየተራበ፣ እኮኖሚው እየደቀቀ እያለ፣ ወደ እውነተኛ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት ሊደረግ የታሰበው ለውጥ ተዘንግቶ፣ በሃገሪቱ ሥምና በህዝቡ ጫንቃ ላይ በሚበደረው ዉድ ገንዘብ የቀድሞ ጨፍጫፊዎችን ሃውልት ያሠራል፣ ቤተ መንግስታቸውን ያድሳል።
  ስለሆነም፣ አቢይ በመጀመሪያ ራሱንና ሥራውን መፈተሽ አለበት። ግና የራሱን ስምና ጉራ በመገንባት ስለታወረ ምክር የሚሰማ አይመስልም፣ ወይም ጥሩ መካሪ የለውም። በዙሪያው የተኮለኮሉት የነፍጠኛ ርዝራዦችና እበላ ባዮች ብቻ ናቸው።

  • mentally retarded challa aka cheka,

   The subject of the discussion is about your barbarism, how wild you are chopping dead bodies into pieces, how you cut the breast of a breast-feeding mom while she is still alive and the baby is being fed, how you guys drag dead bodies for miles etc.

   Sooner or later, you will pay back. I am dead sure about it.

   • Meseret; where you holding a candle for me while I was committing those ‘barbarisms’?? How did you know who committed the crimes?? Surely, you must have been there, not I, so who were with you?? You are screaming to cover up big crimes you or your buddies have committed!

 3. ለኔ ይህ መግለጫ በህዝብ ዕምነት ላይ ማሾፍ ነው ብየ አምናለሁ! የህዝብ አቋም እኮ ትናንትም ሆነ ዛሬ እያው ነው! በተለይ ጠ/ር መጀመሪያ መናገር ከጀመሩበት ቀን ጀምሮ ህዝብ አምኗቸው ቆይቷል! አሁን ግን መጠየቅ ጀምሯል። ለምሳሌ።፦ ከሀዲ ማን ነው? ለምን ህዝብ በምንግስት መሪዎች ይጭበረበራል? ለምንስ ተጭበረበረ? ለምን ይህ አይነት ማጭበርበር ደሙን ለሰዋ ህዝብ እና ከወያኔ እስረኛነት ነፃ ባወጣ ይለውጡናል ባልናቸው መሪዎች ተንኮል ታቀደበት? መንግስት ዛሬም ለምን ሰው እንደ በግ እየታረደ ትግስትን መረጠ? መቸ ነው ወይም ስንት ወንድ እና ሴት ብሎም ህፃናት እና እናቶች ሲሞቱ ነው ህግ ሚከበረው! ሌባን ሌባ ነው ማለት ለምን አቃተው? ከዚያ ሁሉ ሞት ከዚያ ሁሉ እስራት በኋላም ዛሬም መሪ ነኝ የሚሉት ሰው እያጭበረበሩን ነው! ብዙ ነገርም እየዋሹን ነው! ኢትዮጵያን በእኩልነት መምራት አልቻሉም! ምክንያቱም ነገረ ስራቸው በተግባራቸው እያየነው ነው! ለኦሮሞ ሲሆን እና ለአማራ ወይም ለኢትዮጵያ ሲሆን ውሳኔያቸውን አያየነው ስለመጣን በተግባር!!! ደሞ ዛሬ ለመቀለድ ሌላ መግለጫ! መግለጫ ያለ ተግበር በእኔ እይታ “ወሬ” ነው! ዛሬም የምንሰማው መግለጫ ወሬ ነው! እስኪ ከዚህ በፊት ያወሩትን ነገር ወደ ተግባር ቀይረው ከወሬ ይውጡ! እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በወሬ 100% ሰጥቸ በተግባር 5% ላይ አስቀመጥሁ በተለይ ኢትዮጵያን ሳስብ! በርስዎ ዘመን እያውም በ21 ክ.ዘ. ተፈጠርሁበት አደግሁበት በሚሉት የገዳ ስርአት የእግዚአብሔር ፍጡር “ከእንስሳ ሞት ባነሰ ሲታረድ፣ ሲቀጠቀጥ እና ሲገደል” #ኢትዬጲያውያን# አሻግርአለሁ ማለት ለኔ “በደም መቀለድ ነው” ነውርም ነው! በቅቤ ቃል መሸወድ ዛሬ እንኳ አይቻልም! የአባገዳ መሪ ነኝ ያሉት በዶዶላ አሪሲ ያሉትን ሰምተናል! ይህን መደመር ከሆነ የሰበኩን ዛሬም ሆነ ነገ #ነፍጠኛ# ሁኘ መኖርን! ልጆቸን የዚህ ተንኮል ጠንሳሽ የተከበሩ ጠ/ሚ #አብይ# እና አገር ከሀጂ የአሜሪካ ዜግነት ያለው አሸባሪ #ጀዋር# ከግብረ አበሮቹ ጋር ሁኖ መሆኑን ዛሬ ጀምሬ አስተምራለሁ! ምክንያቱም እውነቱን ለማጥፋት እና ለማንሻፈፍ እየሞከሩ መሆኑዎን በግልፅ እያየሁ ነው! እኔ ግን አይኔ እያየ በደንቆሮ እንደከብት በሚያስብ ማህበረሰብ ልጆቸ እየተገደሉ እያውም በዘራቸው እና በእምነታቸው ከማይ የደንቆሮ ተላላኪን ከዛሬ ጀምሮ መልቀም እና ቦታውን ለመስጠት ስራ መጀመሩ ሳይጠቅም አይቀርም! የእርስዎ ወሬ ከሆነ አድሮ እንቦጭ መሆኑን አየነው! ሚጨበጥ የሌለው!እውነት መሪ ከሆኑ የአሜሪካ እና #የኢትዬጲያ# አሸባሪ የሆነውን ብሎም #በኢትዮጵያ# “ሁለት መንግስት አለ” እያለ ሚፎክረውን ሲቀጥል በኢትዮጵያ “ሶስት መሪወች” ብቻ አለን እያለ ሚያናፋውን ሙህር ተብየ ደንቆሮውነሰ #ጀዋር# ፍርድ ካልሰጡ ሌላው ቢቀር የሰሞኑ ደም ይፋረድዎታል! ይህን ሳይተገብሩ ወሬ የሆነ መግለጫ ግን ከ5% ወጀ 0% በቅርቡ ያወርድወታል አይጠራጠሩ በዚህ! የሰሩትንም እርስዎ ያውቁታል! በተለይ በተለይ በተለይ #በነፍጠኛ# ነፍጥ ለካ ለከሀዲም ይጠቅማል ወደሚለው ከተሻገርን ቆየን! የርሶዎን ሽግግር መጠበቅ ማይጠብቅ ማህበረሰብ ላይ ለእርስዎ ፍላጎት እንዲያመች የሰሩትንም እናውቃለን! መቸ #ኢትዮጵያ# ቅቤ ምላስ ፈለገች! ያወራውን ሚተገብር መሪ እንጂ! እኛስ ወሬ ጠላን በሚለው በቆየ ሙዚቃ ሀሳቤን አበቃሁ!!!

 4. የተፄፈን አስተያያት ሚያጠፋ ድረገፅም እው ከሀዲ ነው! ኢትዮጵያን የዋሸ የሚደመያ ነፃነትን የካደ አጭበርባሪ! በዚህ ድረ-ገፅም ያየሀለት ይህ ኘው! እነሰደዜጋ የሰጠሁት የተቸሀለት ሀሳብ እያውም ጊዜዬን አጥፍቸ!ለምን ይጠፋል! ማፈን መግደል ማለት ይህ ነው ሐኔ!ድሮም ……!

 5. አሁን ሁለተኛውን ማጥፋት ይቻላል! #hide# ተደርጎ ስለነበር ነው የፃፍሁት! መልዕክቱ ከተለቀቀ ሁለተኛው መጥፋት ይችላል!

 6. ወይ ጊዜ ሞታችንም የሚሰላው በዘርና በሃይማኖት ሆነ። አይ የወያኔ ፓለቲካና የኦሮሞ ሊቅነት በሰው ህይወት ገበጣ ጫወታ። ጊዜው ቆየ እንጂ አንድ ጊዜ አንድ ሰው ናይሮቤ ወድቆ ይገኛል። ወሬውን ያደረሰን ሰው ማን እንደሞተ ሲጠየቅ ” አንድ አማራ ወድቋል” አለን። እኛም ጉዳዪን ለማየት ሥፍራው ስንሄድ እውነትም አንድ ሃበሻ በጀርባው ተኝቶ ተንጋሏል። በጥይት ተመትቷል። ያን ድርጊት የፈጸሙት የወያኔ የስለላ መረብ ከፍለውና አስከፍለው እንደሆነ ቆይተን ደረስንበት። ሟች በቀድሞው ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ ሥፍራ የነበረውና በወያኔና በሻቢያ ሲፈለግ የነበረ ለመሆኑም አወቅን። ግን አማራ አልነበረም። ኢትዮጵያዊ እንጂ።
  ጠ/ሚሩ የሟችን የዘር አሰላለፍና የማያበቃ የፓለቲካ ዲስኩራቸውን ሲተረትሩልን ስለ አጥፊዎቹ በተለይም ስለዋናው የሰላም ጠላት ጃዋር ያሉት የለም። ጠ/ሚሩ ኦነጋዊያን አረጋውያንና የኦሮሞ ወጣቶችን እረፉ አለማለታቸው የፓለቲካ ውስልትናቸውን ያሳያል። የጠቡ አነሳሳሽ ማን ነበር? ይህን ያህል ኦሮሞ ያን ያህል አማራ ወዘተ እያሉ ከመቅጠፍ ምን አለ በቁርጠኝነት ከአሁን በህዋላ መንገድ የሚዘጋ፤ ሃገር የሚበጠብጥ፤ ፍርድ ለክልሉና ለዘሩ የሚያዳላ አይቀጤ ቅጣት እቀጣለሁ ቢሉን። በኦሮሞ ጽንፈኞች ዙሪያ ውሳኔ ለመስጠት በሃሳብ ሲዋዥቁ ሊወጡ የማይችሉበት አዘቅት ውስጥ እየገቡ መሆናቸው እንዴት አይታያቸውም። አሁን ማን ይሙት የአንዲት ሃገር ጠ/ሚ ሞትን በሃይማኖትና በዘር ያሰላል? ደግሞስ ለምንድነው የትግራይ ልጆች ከሟች ውስጥ የሌሉበት? በቃ ከምድሪቱ ተባረው ምድራቸው እንዳልሆነ መቀሌ ላይ የወያኔ የፕሮፓጋንዳ መጫወቻ ሆነዋል ማለት ነው? እኔ የትግራይ ልጆች እንዲሞቱ አልፈልግም ግን የት ገብተው ነው ከግጭቱ ያመለጡት በማለት ሳስብ የወያኔው የክልል ፓለቲካና ወያኔ በሃገሪቱ ላይ የፈጠረው የፓለቲካ ጫና ደሃና ሰርቶ አደሩን የትግራይ ተወላጅ ተሳዳጅ አርጎት ይሆን በማለት አሰብኩ። ሰው በ 21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ ተቀምጦ በክልል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት የጠባብ ብሄርተኞች ፓለቲካ በአፍንጫየ ይውጣ። የሞተው ወገናችን፤ ገዳዮች ወገኖቻችን፤ ሃበሻው (ዶ/ር አብይ ሃበሻ ነው። የኦሮሞ ልጆች በአምቦ ካሰሙት መፈክር የተወሰደ)እንዴት እንዲህ ልብ አጣ። ቤትንና ንብረቱን እየሸጠ በባህርና በበረሃ እያቋረጠ ወደ ሌላ አለም እየተሰደደ እንዴት የራሱ ቤት ላይ እሳት ይለኩሳል? ይህ እብደት አይደለም። ኦሮሞነት ሌላውን ጠልቶ በራሱ ቁሞ መኖር ይችላል? በጭራሽ አይችልም። እርስ በርሱ ባልታሰበ ነገር ተከፋፍሎ ይጋደላል እንጂ! አጸያፊው የኦሮሞ ፓለቲካ ከወያኔው ጥፍር ነቃይና ሶዶማዊ ፓለቲካ ምንም የሚሻል ነገር የለውም። ዛሬም ሰዎች በዘራቸው ይገደላሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይሰወራሉ፤ ፍትህ አጥተው በእስር ይማቅቃሉ። የውሸት ነጻነት ይሉሃል ይህ ነው። በዘር የተሰላው የኦሮሞ ሟቾች ግማሹ ከአጥፊው የቄሮ መንጋ ጋር አልተባበርም በማለት የተሰዋ፤ ሌሎች ሙታንን ሲታደጉ የተገደሉ ናቸው። ይህ ዓይነቱ መስዋዕትነት ተስፋ በልብ ያስጭራል። የምናውቀውና የኖርንበት የኦሮሞ ህብረተሰብ ወገኑን ወዳጅ፤ ሃገር አክባሪ፤ ትሁት ነው። እነዚህ ሃገር ውስጥና አስመራ ላይ መሽገው በስሙ የነገዱት የኦሮሞ ነጻ አውጪ ነኝ ባይ በሽተኞች ሳይለክፉት በፊት ድንቅ ህዝብ ነበር። አሁንም ተስፋ አልቆርጥም። በጥቂት ደም አፍሳሾች መላው የኦሮሞ ህዝብ ሊመዘን አይገባም። ያው ወያኔና የትግራይ ህዝብ አንድ አደሉም እንደምንለው ነው። ለሆዳቸው የቆሙ ጠበንጃ አንጋቾች የሚያሰቃዪት ህዝብ። አይጣል። አታድርስ ነው የሚባል።
  በመጨረሻም ጠ/ሚሩ ጥብቅ እርምጃ በመውሰድ በሃገሪቱ ህግ እንዲሰፍን እስካላደረጉ ድረስ የጃዋርና የመሰሎች የዘር ፓለቲካ ሃገሪቱን ወደ ባሰ ችግር እንደሚጨምራት ለመገመት ነብይ መሆን አያሻም። ባጭሩ ምድሪቱ ህግና ደንብ አልባ ናት። ሺህ ጌዜ ዲስኩር አንድ ቁምነገር አይወጣውም። ለዚህም ነበር የሃገሬ ገበሬ “99 መርፌ አንድ ማረሻ አይሆንም” የሚለው። ሰለቸን ዲስኩር፤ ሰለቸን ማክሮፎን ይዞ የሚደሰኩር ፓለቲከኛ። ሱሪን ጠበቅ፤ ሽሚዝን ስብስብ በማድረግ በተግባር አሳዪን። ወሬ፤ ስብሰባ፤ ጋዜጣዊ መግለጫ ይብቃ።

 7. ዳር ዳሩን ስንሰማው የነበረው’ ከክልሌ ውጣልኝ፣ መጤ እና ባለርስት ኣባዜ ሀይ ባይ ጠፍቶ እነሆ ዛሬ መዲናችን ደርሶኣል።
  ኣዲስ ኣበባችን ዘር ፣ሀይማኖት፣ወይም ሌላ መለያን ሳታይ ሁሉም ተፋቅሮ የሚኖርባት ትንሹዋ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ሆና ብትቆይም ፣ ሰላማዊ መስተጋብሩዋ መቃወስ የጀመረው ኦሮሚያ ክልል ካላጣው ቦታ ዋና ከተማዬ ፊንፊኔ ነው ብሎ ቀደም ሲል ከነበረበት ናዝሬት ወደ ኣዲስ ኣበባ ሲዛወር ነው ።
  እንደሚታወቀው ቅንጅት ኣዲስ ኣበባን ሲያሸንፍ፣ በመለስ ዜናዊ ቀጪን ትእዛዝ የኦሮሞ ዋና ከተማወደ ኣዲስ ኣባባ እንዲዛወር ሲደረግ ለኦሮሞ ህዝብ በማሰብ ሳይሆን ቅንጅት ኣመራርን ለማወክ መሆኑ ይታወሳል።
  ኣሁንም በግልጽ እንደምናየው ኣዲስ ኣበባ ለሁለት ጌታ ተጠሪ ሆናለች፡ለፌዴራል እና ለኦሮሞ መንግስታት።ይህ ኣሰራር በራሱ ኣንድ ወጥ የሆነ እቅድ እና ፖሊሲ ለማውጣት ኣመቺነት ካለመፍጠሩም በተጨማሪ ኣንዳንዴም እርስ በርሱ የሚቃረን ሁኔታ ስለሚፈጥር፣ከሁሉም በላይ የኣዲስ ኣባባ ነዋሪ ምቾት ስላተሰማው፣እና በሌሎች ተዛማማች ምክንያቶች የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከኣዲስ ኣባባ ይውጣ።
  ኣዲስ የኦሮሚያ ዋና ከተማ መፍጠር በየቤቱ ፈሶ የሚገኘውን ተምሮ ስራ ያጣውን ሀይል ትልቅ የስራ መስክ ሊፈጥር እንደሚችል ማስተዋል ይገባል ።

 8. በለው የሞት ድልድሉ በህዝብ ብዛት ነው እንዴ በጣም ያሳዝናል ለምን ሬሳ በብሄር መጥቀስ አስፈለገ ሁሉም አ/ውያን ናቸው መሞት አልነበረባቸውም ወንጀሉን ያቀነባበሩት ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ነው፡፡

  • Because your buddies were screaming that genocide had been perpetrated against the Amhara! Now you oppose the exposure of the stats!

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.