ይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ!! የሰላም ኖቤል ተሸላሚነትዎን ዝና ተጠቅመው ውርጋጦችዎን አንድ ይበሏቸው!!!

1 min read

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

እንዴት ሰንብተዋል!!! እኔ ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ!! እንደ እውነቱ የክርስቲያን ነገር በክርስቶስ ተስፋ ማድረግ ሆኖ ነው እንጂ በአንድ በኩል ደህናም አይደለሁም፡፡

እንኳን ደስ ያለዎ!!! የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆነዎን ስሰማ ደስ አለኝ፡፡ የሰላም ሰው የሰላም ጠር የሆነውን ሰው ዝም ብሎ እንዴት ሊመለከተው ይችላል የሚል ጽኑ የውስጥ ሙግት ቢኖርብኝም? ምናልባት ይህ ሰላም አደፍራሾችን በዝምታ ማየትዎ ይሆን አንዱ የሽልማት አሸናፊ መመዘኛ? ብቻ ያም ሆነ ይህ ከልቤ ደስ ብሎኛል፡፡ በትኩሱ የሰላም ተሸላሚነትዎ ዝና ውርጋጦችን ለሰላም ያንበርኩኳቸው፡፡

ክቡር ሆይ! አገሬ ታማ ነበር፤ አሁን ግን የባሰባት መስሎኝ ነው ይህን ጦማር ለእርስዎ መጻፌ፡፡ ለጠቅላይ ምኒስትሮች ደብዳቤ ስጽፍ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ልምዱ አለኝ ወይም ልማደኛ አልቃሽ ነኝ ለማለት ነው፡፡

‹‹ይህ ድንጋይ ምን ያስጮኸዋል ቢሉ የሚያስጮህ ያስጮኸዋል›› ነውና ነገሩ ምን ያጽፍሃል ለሚለኝ የሚያጽፍ ያጽፈኛል ስል እመልስለታለሁ፡፡ ለጠቅላይ ሚንስትር መለስ ሁለት ጊዜ ‹‹የየዋህ›› ምከር አዘል ደብዳቤ ልኬላቸው አውቃለሁ፡፡ ያነበቡት ይመስለኛል፡፡ ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያምም ሁለት ጊዜ ልኬላቸዋለሁ፤ አንዱን የላኩት ጠቅላይ ምኒስቴር ሆነው እንደተመረጡ ሰሞን ነበር፡፡ ‹‹ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ይልቅ መንፈሳዊ ጸሎት ይቅደም›› ስል ነበር በደብዳቤ ምክሬን የሰጠሁት፡፡ አልተሳካም፡፡ አለመሳካቱን በምን አወቅሁ? በእርሳቸው ዘንድ በጊዜው  ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲም›› ‹‹መንፈሳዊ ጸሎትም›› አልነበረምና ነው፡፡ ወይም ከሁለቱ በአንዱ አስተሳሰብ ከልብ አምነው ሲከተሉት አላየሁምና ነው፡፡ ሁለተኛውን ደብዳቤዬን የላኩላቸው የመጀመርያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀ  ጊዜ ነበር፡፡

የመጀመርያውን ደብዳቤዬ በብዕር ስም፤ ሁለተኛው ደብዳቤዬ ካንድ የአገር ተቆርቋሪ ዜጋ በሚል ነበር የጻፍኩላቸው፡፡ አስታውሳለሁ የተላከላቸው ምክሩ ጎርሳ አባብያ በተሰኘው የብዕር ስሜ ነበር፡፡ ደብዳቤዬ ቅርጫት ይብላው አይብላው አላውቅም፡፡ በርግጥ  እሳቸውን በሚያውቁ በአንዳንድ የጊዜው ሰዎችም በኩል ልኬላቸው ነበር፡፡ ምክሬም ሐሳቤም ውሃ በላው፡፡ በደብዳቤዬ ስንኝም ቋጥሬባት ነበር፡፡ እንዲህ ትላለች፡-

“ከድጡ ወደ ማጡ…ከዚያም… ወየው! ረመጡ

ወየው! ወየው!……..…..ምናለ ባይመጡ ?

ፈጥነው…ቸኩለው ተቻኩለው………………………ወደዚያ ባይሮጡ

ይልቅ…..

ከማጡ ወደ ድጡ ምናለ ቢወጡ?

ከዚያም ተራራ ላይ… ቢሰፍሩ… እዚያው ቢቀመጡ፡፡

በመንፈስ ልዕልና ካለፈው ቢልቁ… ከነርሱ ቢበልጡ፡፡”

ከላይ እንዳነሳሁት በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት ነበር ደብዳቤ የጻፍኩላቸው፡፡ ከዚሁ ጋር ታሪካዊ ሁኔታውን ያስታውስ እንደሆነ ብዬ የጦርነት አዋጅ በአማራና በኦሮሚያ ክልል መታወጁን ለመቃወም እንዲህ የምትል ስንኝም  ነበረባት፡-

“ጌታው ኃይለማርያም የእግዜር ታላቅ ወንድም

የዛሬን ይማሩን አማራ አንባልም፣

ወልቃይት “እራፊ” ነው ጦር አያማዝዝም”

አማራ ሰላም ነው ፣ክተት ሠራዊትን፣ ንፋ ነጋሪትን ከቶ አያሳውጅም፡፡”

ወይም ወይም ወይም ወይም…..

“ጌታው ኃይለማርያም የእግዜር ታላቅ ወንድም

የዛሬን ይማሩን ኦሮሞ አንሆንም፣

የመብት ጥያቄ ነው ጦር አያማዝዝም”

ኦሮሞ ፈያ ነው ፣ ክተት ሠራዊትን፣ ንፋ ነጋሪትን ከቶ አያሳውጅም፡፡” የምትል ነበር፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

እርስዎን በተመለከተ ብእር አንሥቼ ስጽፍም ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ በዚያ ከባድ የጨለማ ዘመን ማለትም ሁሉ ነገር በተከለከለበት ጊዜ እና እናንተም ሕወአትን እንደ ጦር በምትፈሩበት ጊዜ የክቡር ለማ መገርሳን ንግግር ሰምቼ አቶ ለማን ለማክበር በጻፍኩት ጽሑፍ ውስጥ ስምዎን ጠቅሼ  አደንቄዎት ነበር፡፡

ልብ ያድርጉ ውዳሴ እና አድናቆት ማንም በማይሰጠዎ፤ ኧረ እንዲያውም ‹‹በዲሞሽን ወደ ኦሮሚያ ክልል ሠራተኛነት›› በሄዱ ጊዜ ነበር የጻፍኩት፡፡ ያን ጊዜ ስለ እርስዎ መጻፍ ሆነ ስለ አቶ ለማ መገርሳ መጻፍ ያስቀጣ ነበር፤ በርግጥ እግዚአብሔር ይስጣቸው እና ዛቻው አልደረሰብኝም፤ የሚከተሉኝ የደኅንነት አባላት ወይም ሰላዮች በዝተው እንደ ነበር ግን አስታውሳለሁ፡፡ ምናለ ታዲያ ቢያጅቡኝ ወንድሞቼ አልነበሩ፤ደግሞስ ብቻን ከመሆን ብዙ ሰዎች ሲያጅቡም እኮ ደስ ይላል ፡፡ በኋላ ከኔ የሚፈልጉትን ነገር ሲያጡ ነው መሰለኝ መከታተሉን ተውኝ፡፡

በዚያን ጊዜ ‹‹ዶ/ር ዐብይን መቼ ዐወቅናቸው ዶ/ር ዐብይ ‹‹ዐብይ› መሪ ናቸውሳ›› ብዬም ቅኔ ተቀኝቼለዎት ነበር፡፡ ልብ ይበሉ፡፡ ያን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከሥልጣን አልወረዱም ነበር፡፡ እንዲያውም ‹‹ኢሕአዴግ ዐለት ነው ማንም አይችለውም›› በሚባልበት ጊዜ ነበር በጽሑፌ ስለ እርስዎ የአድናቆት መጣጥፍ ያቀረብኩት፡፡ አንዱን የናንተን ባለሥልጣን ሳደንቅ  በመጣጥፌም ቢሆን እርስዎንም አንሥቼ አድንቄ ያለፍኩ ይመስለኛል፡፡ ይህን ለማድረጌ ማስረጃ አለኝ፡፡ ይህ ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሕትመት ብርሃን ባዩ ጋዜጦች ላይ ተመዝግቦ ተቀምጧል፡፡ ደብዳቤ መጻፍና ሐሳቤን ማቅረብ ዛሬ አልጀመርኩም ወይም የድል አጥቢያ ዐርበኝነት ስሜት የለብኝም ለማለት ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

ሌላ ማስረጃም አለኝ፡፡ ለጊዜው የጻፍኩበት ርእሱ እና ጽሑፍ በየትኛው ጋዜጣ ላይ እንደወጣ እዚህ ጹሑፍ ላይ መናገሩ ፋይዳ ባይኖረውም  ንግግርዎን አድንቄ አሳትሜ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ሳደርግ በእውነቱ ከልቤ የእርስዎን የወደፊት ጥሩ የአስተዳደር ዘመን እና በሳል አመራር (ቆራጥ፣ቅን እና እውነተኛ ርዕይ ከዚያም አይደፈሬ የጽድቅ መንገድ) ተመኝቼ ነበር፡፡ ምክንያቴ ይኼው ነው፡፡ አለቀ ፡፡ ሌላ የለበትም!!!፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

ገና አገር መምራት ሳይጀምሩ ላደንቀዎት የቻልኩበት ዋናው ምክንያት በፊትዎ የሚኖረዎትን ሁሉ ማንኛውንም ሕጸጽ በሂደት እያረሙ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ሰው ይሆናሉ የሚል ብርቱ ተስፋ ኖሮኝ እንጂ የእርስዎስ ፍጹም አማኝ ሆኜ አልነበረም፡፡ በሰው ችሎታ ብቻ አላምንም፤ ሰው በሆነው አምላክ በክርስቶስ እንጂ፡፡ ልክ ነው በክርስቶስ ግን ሙሉ እምነት አለኝ በዚህም ለእርሱ ተገዥ የሆንሁ ባርያ ነኝ፡፡

ያደነቅሁዎት እርስዎ ሆኑ ከጎኖዎ ያሉት ባለሥልጣናት የሕወአትን መስፈርት ሳታሟሉ እና ፍጹም ታዛዥነትን ሳትቀበሉ እዚህ ትደርሳላችሁ ብዬ አስቤስ አልነበረም፡፡ በሕወአት ጊዜ የነበራችሁ ያ ሁሉ ሥልጣን የመነጨው ከፍጹም ታዛዥነታችሁ እንደሆን እርስዎም እኔም ዓለሙም ያውቀዋል፡፡ አለቀ፡፡

የታጠበች እርያ ‹‹የታጠበች እርያ›› እንጂ በግ አትሆንም!!!፡፡ እንደዚያ ነው!!!፡፡ በርግጥ በውሃ ከጸዳች ‹‹የጸዳች እርያ›› እንላታለን እንጂ ማንነቷን አስቀይራ ‹‹በግ›› አትሆንም፤ እኛም ‹‹በግ›› አንላትም፡፡ ‹‹ታጥቤ መጣሁ›› ስትል ዛዲያ ምን ይሆናል ጠርጥረን መቀበል እንጂ፡፡ ያው የባሕርይ ጉዳይ ሆኖ አንድ ቀን ቆሻሻው ላይ የመንከባለል ጽኑ ፍላጎቷ ተነስቶባት መንከባለሏ አይቀሬ ነው፤ ሌላ አይደለም ተፈጥሮዋ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ? የማይለወጥ ነገር አለ፡፡ በግ እርያ ፤ እርያ በግ አትሆንም፡፡ ለእርያ ጸድቶ መኖር አይሆንላትም፤ ቆሻሻው ነገር ይበልጡኑ ይማርካታልና፡፡ ያ ነዋ ተፈጥሮዋ፡፡ አንዱ ‹‹ድመትን አንድ ሺ ዓመት እንደ ውሻ ትጮህ ዘንድ ብናስተምራት እንደ ውሻ አትጮህም›› እንዳለው  መሆኑ ነው፡፡

በእርስዎ ፓርቲ ውስጥ ዛሬ እያየሁት ያለው የባሕርይ ችግር ይኼው  ነው፡፡ ተጠምቆ ወያኔነት፡፡ ተጠምቆ ወያኔነት ማለት በጎዶሎ ትርክት ተገንዞ መሞት፤ እድል ከቀናና ወደ ሥልጣን ማማው የወጡ ሲመስል ማበጥ፣ መበጥበጥ ከዚያማ በበታችነት ስሜት መሠቃየት ነው፡፡ ቀጥሎሳ፤ ቀጥሎማ  ፈፋውን  ሳይሻገሩ መገንደስ፡፡ይህ ያው የታወቀው መንገድ ነው፡፡ ብቻ ዋናው የዚህ ነገር ችግር ሌላውን በክሎ እና ይዞ መገንደሱ ነው፡፡ ሕወሐትማ ከዛፍ ላይ እንቅልፍ ወደ ዛፍ ላይ ዙፋን ተሻግሮ ከቆየ በኋላ ዛፉም እንቅልፉም ጠፍቶበት ‹‹ዛፍ ያጣ ጉሬዛ›› ሆኖ እያየነው አይደል!!!፡፡ ይህም የተፈጥሮ ህግ ነው!!!፡፡ የሚስማማም የማይስማማም ሊያልፍበት ግድ ነው፡፡ ጊዜ ለኩሉ እንዳለው ጠቢቡ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

ይህን ደብዳቤ ስጽፍለዎት የማይታረም ባሕርይ አይቼቦዎትስ አይደለም፤ ሁሉን ለማስደሰት የመጽሓፍ ቅዱሱን ንጉሥ ‹‹መንገደ አካብን›› የመውደድ አዝማሚያ እያየሁበዎት ስለሆነ ነው እንጂ! የአካብ ችግር ምንድን ነው? የማምለኪያ አጸድ የማበራከት ተልኮን በወዶ ገብነት (በራሱ ፈቃድ) እንደ ሥራ መያዙ፣ በአልዛቤል አስተሳሰብ መነዳቱና ራሱን መሸጡ ነበር፡፡ የእርስዎም መንገድ አሳሰበኝ፤ ክርስቶስን ማምለክ ከባእድ አምልኮ ጋር፤ የክርስቶስን ደም ከኮርማ ደም ጋር የመቀላቀል አዝማሚያ እያየሁበዎት መሰለኝ፡፡ የወይፈኑ ደም ወግ ሰቀጠጠኝ፡፡ ባለፈው መስከረም 24 በአዲስ አበባ እንዳየነው የሬቻ በዓል የ‹‹ሁሉ በዓል ነው›› ወይም ‹‹አቃፊ በዓል ነው›› ሲባል ቆይቶ ባህሉ በአግላይነት ተወጥሮ ወጉም ወይፈኑም በርኩሰት ተዘርረው ታዩ እኮ!!!፡፡ የወይፈኑን ለአምልኮ መስዋዕት መገንደሱን ዘንግተው ባህል ነው ያውም አቃፊ ነው፤ኧረ እንዲያውም መደመር ነው ሊሉ የፈለጉ መሰለኝ፡፡ ልከ አይደለም!፡፡ መታረም አለበት!፡፡ ፈጥነው እንደ አካብ በእግዚአብሔር ፊት ቅስስ ብለው ንሰኀ ይግቡ፤ ያን ጊዜ ኀይል እና ጥበብ ያገኛሉ፡፡

በነገራችን ላይ ክርስትናም እስልምናም አቃፊ አይደሉም፡፡ ለመታቀፍ ወይም ለማቀፍ ሁሉቱም እምነትን የግድ ይላሉና ነው፡፡ በእምነቱ መሠረት የማያምን ወደ ገሃነም ይገባል ሲሉ አቃፊ የአለመሆናቸውን ወግ እና አስተምህሮ አስይዘው  ይሞግታሉና፡፡ ኧረ እንዲያውም ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም…›› ይል የለ ቃሉ፡፡ የሞጋሳም ሥርዐትም አቃፊ ዓይደለም፡፡ ውሸት ነው!!!፡፡ ስም እየለወጡ ኦሮሞ ማድረግ፤ ባህልን አስጥሎ ኦሮሞ ማደርግ መደመር አይደለም፡፡የሞጋሳ ሥርዓት ትሩፋት ነው፡፡ አበቃ! መጨፍለቅ ነው፡፡ ወይም መጨፈላላቅ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ  ይህ መሆኑ ችግር አይደለም በኀይል የታጀበ ወረራ አይሁን እንጂ፡፡ ሐሰት ‹‹ሐሰት›› ሲባል መስማት ትውልዱ ይናፍቃል፡፡ ያ ነው መንገዱ፡፡  እምነቶች ‹‹ተከባብረው›› ይኑሩ በሚለው እና ይህ እምነት ‹‹አቃፊ ነው›› የሚለው የተለያዩ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ሁለቱ ገምቱ እምነቶች ቢያንስ አቃፊ አለመሆናቸውን ያስማማናል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

ከሁሉ በላይ ግን  የመንግስትዎ አወቃቀር እና በፓርቲው ውስጥ ያሉ ሹመኞች ጉዳይ እረፍት ስለነሳኝ ነው ደብዳቤ መጻፌ፡፡ ያሳሰበኝን ነገር አንስቼ መጻፌ አጋንኘ አይደለም፤ በደንብ ሳስተውለው በፓርቲው ውስጥ አዳዲስ መሬት  ያልያዙ ውርጋጦች የበዙ መስሎኝ ነው፡፡ የአመራር ሆነ የሥነ ሥርዓት ልምድ የነጠፋባቸው  ውርጋጦችን ተሰብስበው  አየሁ፡፡ በዚህም እጅግ ሰጋሁ፤ ወደፊት መቸገሬ አይቀርም፡፡ ዝና መሸከም ያቃታቸው በአጭር የታጠቁ ውርጋጦች ወደ መንጋነት ሳይሸጋገሩ መንቃት ያለብን ስለመሰለኝ ነው ይህን የጻፍኩት፡፡ በአጭሩ ፓርቲው አፈ ጮሌ፤ ልበ ውርጋጥ ብቻ ሆኗል ፡፡ የኦሮ-ማራ  ትርክት ጊዚያዊ ጮሌነት የተንሰራፋበት ውርጋጥነት ነበር፡፡ ለነገሩማ ውርጋጥ እርቅ እና ታሪክ የት ያውቃል ተብሎ  ነው ይህን ያህል ቦታ የተሰጠው፡፡ ክቡር ሆይ ብቻ ውርጋጦችዎ አጓጉል ወርግጠዋል!!!፡፡ ሶሞኑን የወረገጡ ‹‹የወንድሞዎ ተከታዮች›› ጨፍጫፊነት እና የአራዊት ህግ እንኳ የማይገዛቸው ወንጀሎኞች በጉያዎ አቅፈው እየኖሩ እንደሆነ አየን፡፡

መቼም ይህን ውርግጥና እርስዎም እያዩት ይመስለኛል፡፡ እኔ በመንግስትዎ ውስጥ ምን አየሁ መሰለዎ? በመንግሥትዎ ውስጥ በሰፊው ያየሁት የውርጋጦችን ስብስብ እና ምክር ነው ፡፡ ክቡር ሆይ አንድ ሮብዓም የተሰኘ የእስራኤል ንጉስ ታሪክ ላስታውስዎ ፡፡ አባቱን ተክቶ የነገሰ ንጉሥ ነበር፡፡ አባቱ ታላቁ፣ ጥበበኛው እና ስመ ገናናው  ሰሎሞን እንደሞተ እርሱ ነግሦ ነበርና ሕዝብ ተሰብስቦ አስተዳዳር እንዲሻሻልለት ጠየቀ፡፡ እርሱም እንደ ደህና ሰው የአገር ሽማግሌዎች እና የወጣቶችን ምክር ተራ በተራ ጠየቀ፡፡ ሽማግሌዎቹ ከአባቱ የተሻለ አስተዳደር እንዲያመጣ መከሩትና እርሱን ለሕዝቡ ንገራቸው ብለው ነገሩት፤  በተቃራኒው ወጣቶቹ የእኔ አገዛዝ ከአባቴ የባሰ ይሆናል በላቸው ብለው መከሩት፡፡ እሱም ያልበሰሉ ውርጋጦችን ምክር ሰምቶ በክፉ ቃል ሕዝቡን ተናገራቸው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ተቀምጧል

         ‹‹እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ። ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን። አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት። እርሱም። ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘላለም ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት። እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።

         እርሱም። አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት። ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ። አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።›› (መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 10፡1-15)፡፡

ከዚያ በኋላ  ምን ሆነ ‹‹ውርጋጦች›› በሽማግሌዎች ላይ ነገሡ፡፡ መከራ በስፋት እየጎረፈ   ወደ አገዛዙ መጣ፡፡ ፍጻሜው እንደታየው ሆነ፡፡ ያች ታላቅ አገር ፈረሰች፡፡ ወደመች፡፡ የሰለሞን ጥበብ እና ዝና እንዲሁም በሱ ዝና እና አገር ተንደላቆ መኖር ተዘነጋ፡፡ አገሪቷ ጥበብ አልባ፣ አምላክ የለሽ እና ሥርዐት አልባ የሆኑት መንግሥታት መጫዎቻ ሆነች፡፡ በዚያን ጊዜ የተጀመረው ጦስ ነው እንግዲህ እስራኤልን መንግሥት አልባ፣ አገር አልባ አድርጎ ዜጎቿን መጫዎቻ የማንም መሳለቂያ ያደረጋቸው፡፡ ሂትለር በአደባባይ 6 ሚሊዮን ሕዝቧን የፈጀባት በዚህ ግጭት ምክንያት በመበታተኗ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ተው በለው ጋሜውን ያንን ጎፈሬውን›› የሚል ጠፍቶ ነው እዚህ የደረሱት፤ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ነው የበተነን›› ይላሉ ምን ያድርጋቸው ጥበቡን አውልቀው በዓልን፣ቋንቋን፣ ጠብን እና ውርግጥናን መርጠው ነው እኮ የወደቁት፡፡

ወደ አገራችን እንመለስ እስቲ፡፡ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ችግር ምን ነበር? ውርጋጥነት ነበረ፡፡ የስዬ አብርሃ እና የፕሬዜዳንት ኢሳይያስ ‹‹የይዋጣልን›› ጦርነት መንስዔ ውርጋጥነት ነበረ፡፡ የኢሳይያስ ‹‹ጸሐይ አትጠልቅም›› ትርክትና የስዬ አብርሃ ‹‹ጦር ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጦር መሥራትም እንችላለን›› ንግግር ውርጋጥነት ነው፡፡ መለስ ዜናዊም የሻቢያን በዓል ሊያከብር ኤርትራ ሄዶ ስለ ደርግ እና ሰለ አማራ የተናገረው ምን ነበር? ውርጋጥነት ነበር፡፡ ‹‹አማራን አከርካሪውን ሰብረነዋል፤ አርቀን ቀብረነዋል›› ማለት ምን ሊባል ይችላል? ይህ ንጹሕ ውርጋጥነት ነው፡፡ ነፍጠኛው (አማራው) ከዚህ በፊት ከተሰበረስ የሰሞኑ የሰብረነዋል አዋጅ ምን ሊሆን ይችላል፤ የውርጋጥነቱ ማሳያ አይደለምን? ‹‹የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው›› የሚለውና ‹‹ኦሮሞ ጠባብ ነው›› የሚለው የመለስ ዜናዊ  ንግግር ከውርጋጥነት ውጭ ምን ሊሆን ይችላል?

 ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

እንደሚያውቁት ሁሉ ‹‹ምክረ ውርጋጥ›› ሲነግስ አገር ትሸበራለች፤ መንግስትም ይሰበራል፤ ሕዝብም ይሰጋል፣ይፈራል ከዚያም ያምጻል፤ ምድርም ትማረራለች ከዚያማ ምድር እራሷ ታመራለች፡፡ ሥራም፣ ሰብልም፣ሰላምም፣ እረፍትም፣ ደስታም ትከለክላለች፡፡ ስልጣንም በኖ ይጠፋል፡፡በኖ! ኧረ እንዲውም ተኖ ይጠፋል፡፡ እንደ ጉም ይሆናል፡፡ ያ ነው የሚሆነው፡፡ እሳት አብረው የሚሞቁ ውርጋጥ አማካሪዎች ባሕርያቸው ያው ውርግጥና ስለሆነ ከቻሉ ካዲሱ (እርስዎን ከሚቃወሙ ይሁን ከሌላ) ባለሥልጣን ጋር ይወግናሉ፡፡ ያ ካልሆነም አብረው ይተናሉ፡፡

ሌላ ምሳሌ ልጨምርልዎት፡፡ አንድ ጊዜ ሥመ ጥሩውና ጀግናው የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ለንጉሥ ምኒልክ ከብዙ ማስጠንቀቂያ ጋር እንዋጋ የሚል ደብዳቤ ላኩባቸው፡፡ ዝርዝሩን ያውቁታል ብዬ ነው የተውኩት፡፡ ምኒልክም ደብዳቤውንና ዛቻውን አንብበውና  ሰምተው ‹‹ለካስ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግሥት የጀግና (የጎበዝ) መካር እንጂ የሽማግሌ መካር የለበትም›› ሲሉ ተናገሩ አሉ ፡፡ ታዲያ ጦር ሰባቂዎች ባመጡት ጣጣ በጦርነቱ የሆነውን እናውቃለን፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

በውርጋጥ የተከበቡ ጠቅላይ ሚንስትር ወይም ንጉሥ መስለው ታዩኝ፡፡ ምነው ሽማግሌ መካሪ በዙርያዎ የለምሳ!!! ፡፡ ይህን ስል በዙሪያዎ ሆነው ድምጽ የተነፈጋቸውን አዋቂ፣ ጠሊቅ እና ምጡቅ መካሮች አክብሬ ‹‹ውርጋጦችን›› ያርሙ ዘንድ በመፈለጌ ነው፡፡ መቼም ውርጋጦች ሰሞኑን ምን እያሉ እንደሆነ ሰምተዋል፡፡ በጦርነት አውድማ ያልዋሉ የውርጋጥ አቅራሪዎች (ፎካሪዎች) ልብ በጦርነት ጊዜ ምን እንደሚሆን ውርጋጦቹ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ባብዛኛው ግን ‹‹እንውረድ አባይ ሳንጃው ገላጋይ›› ሲባል ‹‹አባይ›› ወይም ‹‹አዋሽ›› አይወርዱም፡፡ ያው የተለመደው ስደት ይሄዳሉ እንጂ፡፡ የድሃ ልጆች ፈርዶባቸው ያው የውርጋጦችን ጦርነት የሚገጥሙት እነሱው ናቸው፡፡

ባለፈው 27 ዓመት የትግራይ ውርጋጦች ስልጣን ላይ እንደወጡ በንግግራቸው ወረገጡ፡፡ ትዝ እንደሚለዎ እርስዎ እና ቡድንዎ ወደ ሥልጣን እንደመጣችሁ የሕወሃት ውርጋጦች ጦርነት አወጁ፡፡ ይህም ውርጋጥነት ነበር፤ ጦርነቱንማ አላየንም፡፡ ነገሩ ውርጋጥ የሚዘነጋው ዋና ነገር ተከታይ እንደሌለው ነው፡፡ በርግጥ የላም ችግሯ አንድ ወቅት ጥጃ እንደነበረች መርሳቷ ነው ዐይነት ነገር መሆኑ ነው፡፡

የኦዲፒ ውርጋጦች በኮርማው ‹‹መስዋት›› ተነድተው ይሁን ወይም የኮርማውን  የጦርነት ቅስቀሳ ተጋርተው አይታወቅም ብቻ በስፋት በአደባባይ ወረገጡ፡፡ በዚህም ሳይወሰን ከወደ አማራ ሌላ ውርጋጥ ወረገጠ፡፡ ለእሱ መልስ አንድ የኦዲፒ ውርጋጥ ‹‹ይዋጣልን›› ሲል እንደገና ፈጥኖ ወረገጠ፡፡ የአማራውም በድጋሚ ጥሩ በሚመስል ቋንቋ ‹‹ይለይልን›› ሲል  አሻሽሎ ወረገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ማን ቀጥሎ እንደሚወረግጥ አናውቅም፤ ብንጠረጥርም፡፡ ብቻ መንግሥትዎ በውርጋጦች የሚታመስ መንግሥት ሆኗል፡፡ የበሰሉ፣ የረጉ፣ የሚያውቁ ሰዎች በውርጋጦች አላዋቂነት ተሸፈኑ፡፡ የሲዳማው ውርጋጥ ለዘብ ብሎ እየጠበቀ ነው፡፡ አያጠራጥርም አንድ ቀን ይወረግጣል ምን ችግር አለው ዘመኑ የመወርገጥ ነዋ!!! ሃይ ባይ ተቆጪ ጠፋ፡፡ አበቃ፡፡ መንግሥትዎ እንደዚያ ሆኗል፡፡ የውርጋጥ መፈንጪያ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ!!!

ዋናው የደብዳቤዬ ጭብጥ ውርጋጦቾዎን አንድ ይበሉልን ለማለት ነው፡፡ አሊያም የውርጋጦች ስሜት እርስዎንም እየነዳዎት ከሆነ መወርገጥዎን ያስታውቁንና ቁርጡን እንያዝ፡፡ እኛም ባይሆንልንም ቢሆንልንም እንወርግጥ፤ አሊያም ከውርጋጦች ዛቻ ወይም የውርጋጦች እርግጫ ሳያርፍብን  እግሬ አውጭኝ ብለን ቶሎ እንጥፋ፡፡ ወይም እራስን ለማዳን አብረን እንወረጋገጥ፡፡ በቃ መወራገጥ ነው፡፡ ዋናው የመወራገጡ ፊሽካ ያለው በእርስዎ እጅ በመሆኑ ነው ይቺን ማስታወሻ መጻፌ፡፡

እርስዎም የውርጋጦችን የ‹‹ይዋጣልን›› ፉክክር የኀይል ማስጠበቂያ እኩይ መሳርያ አድርገው አስበው እና በዚህ መኻል ተመራጭ እሆናለሁ ብለው ከሆነ ዝንጉነት ነው፤ በውርጋጦች ጦርነት (የቃላት) በሳል መስለው ለመታየት እና ነጥብ ለማስያዝ አስበው ከሆነ ይኼው አንድ ነጥብ ጥለዋል፡፡አይሆንም፡፡ ሰሞኑን እንኳ ውርጋጥ ባለሥልጣንና ወሮበላ ጋንግን ወንድማችን ነው አይናችን ነው ሲሉ ሲደመጡ ከስረዋል፡፡ ስኬትዎ በየቀኑ እየነጠፈ ነው፤ ዝነኝነት ለብቻዎ ማግኘት አይሳካም፡፡ ውርጋጦች በጊዜ ካልታረሙ ውርግጥናውን ወደ እርስዎ እንደሚያዞሩት አይጠራጠሩ፡፡ በአምቦ ታይቷል፤ በሀረር ታይቷል፤ ገናም ይታያል፡፡

እባክዎ ‹‹ይለይልን›› የሚሉትን ውርጋጦች አንድ መላ ይስጡልን፡፡ እርስዎም የውርጋጥ አስተሳሰብ ከአምላክዎ ባሕርይ እና ከተነሱበት ዐላማ ጋር አይዋደድምና ወዲያ ይበሉት፤ አይ አይሆንም ‹‹መወርገጥ›› ያዋጣል ካሉም ወዲህ ብለው ውርግጥናውን አንድኛውን ይያዙት!!!፡፡ ካመኑበት ያዝልቅለዎት፤ የሚያዋጣውንማ መንገድ በኋላ አብረን የምናየው ይሆን የለ!!!፡፡ የትኛው ውርጋጥ እንደሚያሸንፍ ግን የጦርነት አውድማው ወይም ሜዳው ነው የሚለየው፡፡ መልካም ዘመን የምመኝልዎ እና  ከዘመነ ውርጋጥ ይጠብቅዎ ስል የምተሰፋው  ጠርጣሪ አክባሪዎ ነኝ!!!፡፡

ከካህኑ ዮሐንስ

ከለውጥ ተስፋ ጋር!!!

 

 

2 Comments

  1. 50 Oromos, 20 Amharas, 8 Gamo, 2 Silte, 1 Guraghe, 2 Hadya, 1 Argoba and the ethic identity of one victim is not established

    According to the above data , I firmly reach to the conclusion that Amhara elites the most violent people in that old country . But, What amhara is claining is a far cry from what we heard from the horses mouth. A complete lairs and killers throughout the Ethiopian history§

    Amharas stop it being a violent and spreading hate . You are tabot sellers and traitors

    Abiy you must restrain killers, amhara gangsters

    Megerssa from Oklahoma

  2. ኣንተ ውርጋጥ መገርሳ ተብየ ኣለቃህ የነገረህን ብቻ የምታዳምጥ ደንቆሮ በገዛ ምድርህ ላይ ከቀጠቀጠህ ኣርፈህ መቀመጥ አንጂ ምን ያስለፈልፍሃል ዉርጋጥ ። ለስሙ ኦክላሆማ ነዉ ያለሁት ትላለህ ። ኦክላሆማ መኖር ምሁር ኣያደርግም አኮ ። ይህን ጊዘ ወይ የታክሲ ሹፈር ነህ ኣለያም የጉልበት ሰራተኝ ነህ ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.