ይድረስ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

የተከበሩና የተወደዱ ጠቅላይ ሚንስትራችን፡-

በቅድሚያ አክብሮቴ እና ሰላምታዬ ይድረስዎት፡፡ የእግዚአብሔር ሰላም ይብዛልዎት፡፡ ጥበቃው አይለይዎት፡፡ ከእርስዎ ጋር ለመተባበር “ለመደመር” ይህን ደብዳቤ እፅፍልዎታለሁ፡፡ በዚህ አስተሳሰብዎ እና በዚህ ብቃት ከእርስዎ ጋር የማይተባበር ችግር ያለበት፣ ደካማ፣ ቀናተኛና ክፉ ሰው ብቻ ነው፡፡ እናም ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብዬ የማስበውን ይኸን ሀሳብ ይተገብሩት ዘንድ እፅፍለዎታለሁ፡፡ እንደሚተገብሩት ስለምተማመንብዎት ኢትዮጵያን የአዳዲስ ተቋማት ባለቤት እንደሚያደርጓት ስለማምን ደስ ይለኛል፡፡ መስጠት እና መቀበል ስለሚችሉ ስለ መስጠት ያደረጉት ንግግር ስላነሳሳኝ የበኩሌን አስተዋፆ ለማድረግ ሀሳቤንና በሀገሬ እንዲሆን የምፈልገውን ልግለጥልዎት፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፡-

ሀገር የምታድገው እና የምትለወጠው እውቀት ባላቸው ሰዎች እንደሆነ ከእርስዎ የተሰወረ አይደለም፡፡ ሀገራችን በተለይ አዳዲስ ሀሳብ ማመንጨት የሚችሉ ሰዎች ያስፈልጓታል፡፡ ችግሮችን የሚረዱ እና ለችግሮች ፈጥነው ትክክለኛ መፍትሔ ማቅረብ የሚችሉ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ስለሆነም ሶስት አዳዲስ ተቋማትን እንዲመሰርቱ እጠይቅዎታለሁ፡፡ አንደኛው ራስዎትን ተግባራዊ እውቀት ባላቸው ሰዎች “በቤተ መንግስት አማካሪዎች” እንዲከብቡ ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያን መንግስት ይረዱ ዘንድ የኢትዮጵያ ምሁራንን በአንድ ማህበር ስር አንዲሰበስቡ ነው፡፡ ሶስተኛውም የመንግስት ተቋማት ትክክለኛ ውሳኔዎችንና ትክክለኛ አሰራሮችን ያገኙ ዘንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አማካሪ ኮሚቴዎችን በአዋጅ ያቋቁሙ ዘንድ ነው፡፡

የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፡-

ኢትዮጵያ ብዙ ተቋማት እንደሌሏት ያሉትም ጠንካራ እንዳልሆኑና ስፋትና ጥልቀት እንደሌላቸው ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሏት ተቋማት መካከልም አማካሪ ተቋማት አንዳቸው ናቸው፡፡ ሀገር የምትለወጠው በግብታዊነት ወይም በመላምት ውሳኔዎች አይደለም፡፡ እርግጠኛ የሆኑ ትክክለኛ ሳይንሳዊ ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሳይንሳዊ አስተዳደርን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ምሁራንን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የእውቀት ሰዎች  ምን መሆን፣ ምን መደረግ፣ እንዴትስ መደረግ እንዳለበት ለመንግስታቸው ሀሳብ ካላቀረቡ መንግስታቸው ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡  አሜሪካ ታላቅና ሃያል የሆነችው እውቀትን በመጠቀሟ ነው፡፡ በ1939 የአዶልፍ ሂትለርን እንቅስቃሴና ምን መደረግ እንዳለበት የምትገልፀዋ አልበርት አንስታይን ለፕሪዝዳንት ሩዝቬልት የፃፋት ደብዳቤ እስካሁን ድረስ አሜሪካንን ሃያል አድርጋለች፡፡

የማናቸውንም ሃያል እና ታላቅ የሆኑ ሀገሮችን ታሪክ ስናጠና የስልጣኔያቸው፣ የብልፅግናቸው እና የሃያልነታቸው ሚስጢር እውቀት እና የእውቀት ሰዎችን መጠቀማቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ ነገስታት ታሪክም በርካታ አማካሪዎች እና አገልግሎታቸው ለመንግስታቸው ትክክለኛ ውሳኔዎችን ማቅረብ የሆኑ ሰዎች እንደነበሯቸው እንረዳለን፡፡ የሀገራችንን ነገስታት ታሪክ ስናጠናም የሀገሪቱ ምርጦች  የሊቃውንት አማካሪዎች እንደነበሯቸው እና ቀላል ነጠላ ጥያቄ ሳይቀር ያማክሯቸው እንደነበር እንረዳለን፡፡ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያነቡ ስለማውቅ ይህንን ከመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ታሪኮች እንደሚረዱት አምናለሁ፡፡ እንደ ዮሴፍ እና እንደ ዳንኤል ያሉ ተግባራዊ ምክሮችን የሚሰጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዮሴፍ ግብፅን ከመራብ እስራኤልን ከመጥፋት እንዳዳናቸው ዛሬም የምግብ ዋስትናችንን እንዴት እንደምናረጋግጥ የሚያሳዩንን የእውቀት ሰዎች እንፈልጋለን፡፡ ሰላምንና አንድነትን እንዴት እንደምናመጣ ተግባራዊ ሀሳቦችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚያቀርቡልንን የእውቀት ሰዎችን እንፈልጋለን፡፡ ለዚች ሀገር ብልፅግናና ስልጣኔ እንድናመጣ መንገዱን የሚያሳዩንን የሙያ ሰዎች እንፈልጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲያቋቁሙ የተናገሩት በልጅነቴ ያነበብኩት ንግግር ሀገርን ከጥቃት ወይም ከጉዳት መከላከል እና ሀገርን ማሳደግ የሚቻለው መንግስት በምሁራን ስብስብ ሲመራ እንደሆነ በፅኑ እንዳምን አድርጎኛል፡፡

የተከበሩ ሰው፡-

በአሁን ወቅት መንግስት ከጥቂት ስድስት ወይም ሰባት ከሚያህሉ አማካሪዎች በስተቀር ሙያዊ አማካሪዎች የሉትም፡፡ መንግስት የኢትዮጵያ ምሁራንን እየተጠቀመ አይደለም፡፡ እንደውም እያገለለ ይመስለኛል፡፡ ያም ማለት ባይሆን ምሁራንን እያቀረበ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ምሁራን መንግስትን ሲቃወሙ ወይም ሀገራቸውን ጥለው ሲሰደዱ ነበር፡፡ መንግስትም ምርጥ ውሳኔዎችን እየተቸገረ እያጣ ነበር፡፡ መንግስት ስል ሁሉንም የመንግስት አካላት ማለቴ ነው፡፡ ፖሊሲዎች፣ እስትራቴጅዎች፣ ፕሮግራሞች እና ውሳኔዎች የሚሰጡት የሚመሰረቱት በሙያ ሰዎች ሳይሆን በፓርቲ ሰዎች ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የተፈለገውን ያህል ውጤት እንዳናመጣ አድርጎናል፡፡ እንደሚያውቁት ሀገሪቱ በርካታ ችግሮች አሉባት፡፡ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያሻቸው ብዙ ችግሮች አሉባት፡፡ ከኢኮኖሚ እስከ ፖለቲካ ከፖለቲካ እስከ ማህበራዊ ጉዳዮች ድረስ በርካታ ችግሮች አሉብን፡፡ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱት ደግሞ በእውቀት ነው፡፡ የእውቀት አገልግሎት የሚመጣው ደግሞ ከምሁራን ነው፡፡ መፍትሄ አመንጭ ምርጥ ጭንቅላቶችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ እናም የኢትዮጵያን ችግሮች መፍታት ከፈለጉ እና ኢትዮጵያን በስልጣኔ፣ በእድገትና በብልፅግና ጎዳና መምራት ከፈለጉ በርካታ አዳዲስ ተቋማትን ሊመሰርቱ ይገባል፡፡ እናም የሚከተሉት ሶስት ተቋማት እንዲመሰረቱ ክቡርነትዎን እጠይቃለሁ፡፡

የቤተ መንግስት አማካሪዎች ጉባዔን ይመስርቱ

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፡-

የኢትዮያን ችግር ለመፍታት ከፈለጉ ኢትዮጵን ወደ ገናናነት ወደ ብልፅግናና ስልጣኔ መውሰድ ከፈለጉ ዙሪያዎትን ራስዎትን እጅግ ከፍተኛ ብቃት ባላቸው ሙያተኞች ይክበቡ፡፡ ከሀገር ወስጥ ከሀገር ውጭም ያሉ የሀገሪቱን አንድ ሺህ ምርጥ ሰዎች ከርስዎ ጋር እንዲሰሩ በዙሪያዎ ይሰብስቡ፡፡ የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት ብቻዎትን አይችሉትም፡፡ ስራን መከፋፈል እና ስራን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የሚያግዝዎት ሰዎች ያስፈልጉወታል፡፡ ብዙ የሚያግዝዎት ሰዎችን ሲያገኙ ውጤታማ እና ስኬታማ መንግስትን ይመሰርታሉ፡፡ የሚያማክሩ እና ስራዎችን የሚያከናውኑ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ልምድ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የሀገሪቱን ምርጥ ሰዎች ይሰብስቧቸው፡፡ ሀገሪቱን ወደ ከፍታ ማውጣት ከተመኙ ፈልገው ያግኟቸው፡፡ ይህንን የሚያከናውንልዎት በስርዎ የቤተ መንግስት የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪዎች ጉባዔ አቋቋሚ ኮሚቴ ያደራጁ፡፡ ምን ምን ክፎሎች እንደሚኖሩት ኃላፊነቱና ተግባሩ ምን እንደሆነ ምን እንደሚያደርጉ በሕግ ያስወስኑ፡፡ ተቋም አድርገው ይገንቡት፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚኖረው ቀጣይ የሆነ የስምዎ መጠሪያ የስራዎ ማስታወሻ ይሆናል፡፡ የዓብይ የአማካሪዎች ጉባዔ ብለው ሊሰይሙት ይችላሉ፡፡ የዓብይ ጉባዔ ሊሉት ይችላሉ፡፡ የሀገሪቱ ምርጥ ሰዎች ተመርጠው በእውቀታቸው፣ በሙያቸው፣ በልምዳቸው ሀገራቸውን መንግስታቸውን የሚያገለግሉበት እና የሚጠቅሙበትን ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ልምዱን ከአሜሪካ ማግኘት እንችላለን፡፡ አሜሪካ ከመላ ሀገሪቱ እጅግ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውንና እጅግ ስኬታማ የሆኑ አዳዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅ የሚችሉ ሀገር ወዳድ የሙያ ሰዎችን፣ የፈጠራ ሰዎችን፣ የቢዝነስ ሰዎችን፣ ወዘተ ከየዘርፉ ተመርጠው በቤተ መንግስት ከፕሬዝዳንቱ ጋር ይሰራሉ፡፡  ፕሬዝዳነቱን በማማከር በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እያከናወኑ እውቀታቸውንና ልምዳቸውን በመጠቀም ለሀገራቸው ስኬታማነት በብቃት ይሰራሉ፡፡ ለሀገራቸው እና ለመንግስታቸው ታላቅነት ቀን ከሌሊት ይሰራሉ፡፡

ይህንን የሀገሪቱን ምርጥ ሰዎች ከመላ ሀገሪቱ የሚሰበስቡበትን ፕሮግራም “White House Fellowship Program” ይሉታል፡፡ በፕሬዝዳንት ሊንደን ጆንሰን በ1964 በአዋጅ የተቋቋመ ነው፡፡ ለአሜሪካ ታላቅነት እና ለመንግስታቸው ውጤታማነት ትልቅ አስተዋፆ እንዳደረገ ይታመናል፡፡ ፕሮግራሙ ብቃት ያላቸው ተተኪ አመራሮችን የመፍጠሪያም መንገድ ነው፡፡ ይህ የሀገራችን ባህላዊው እውቀትን፣ ልምድን፣ ስነ ስርዓትን የማስተማሪያ እና የማስተላለፊያ መንገድ ስለጠፋ በዘመናችንም በተለይ የአመራር እውቀትን፣ ክህሎትንና ልምድን ለአዲሱ ትውልድ የምናስተላልፍበት መንገድ ስላላበጀንለት የተፈጠረውን ክፍተት የሚሞላ እና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማዘጋጀት የሚያስችል መንግስቱ ብቃት ያላቸው መሪዎችን እንዳያጣ ምርጥ ውሳኔዎችን ከማግኘት እንዳይቸገር ያለ ገጭ ገው እንዲጓዝ የሚያደርግ ነው፡፡

“ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩ” ይባል የለ ለአንበሳ ስጋውን ካቀረቡለት እርሱ እንደሚያውቅ ያደርገዋል ለብልህም ጫፉን ከነገሩት ከተናጋሪው በላይ ይረዳዋል፤ ይከውነዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፥

በሀገሪቱ ምርጥ ሰዎች ራስዎን ከከበቡ የሀገሪቱን ችግሮች መፍታት እንደሚችሉ እና ሀገራችንን ገናና እንደሚያደርጓት እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዚህ ሀገር ብዙ አዳዲስ እና ድንቅ ነገር ለመስራት ከፈለጉ ኢትዮጵያን ከችግር አላቅቀው የብልፅግናና የስልጣኔ ባለቤት ለማድረግ ከፈለጉ በሚያስፈልገው ፍጥነት ለመሄድ  ስራን መከፋፈል እና ስራን መስጠት ያስፈልግዎታል ራስዎትን በምርጥ ሰዎች መክበብ ያስፈልግዎታል፡፡

የመንግስት ተቋማት

የሙያ አማካሪ ኮሚቴዎችን ያቋቁሙ

አሜሪካ ታላቅ እና ገናና ስለሆነችበት ስለ ሙያዊ እና ምሁራዊ ምክር ስለ መጠቀም መንግስታችን ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ አሜሪካ በአዋጅ የተቋቋሙ 917 የመንግስት የፌደራል አማካሪ ኮሚቴዎች አሏት፡፡ ስድሳ ሺህ ሙያተኞች በኮሚቴዎች ውስጥ ይሰራሉ፡፡ ኮሚቴዎች በጤና፣ በትምህርት፣ በንግድ፣ በግንባታ፣ ወዘተ በየዘርፉ የተቋቋሙ ሲሆን መንግስት ምን ማድረግ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ በአንድ ዘርፍ ብቻ በርካታ አማካሪ ኮሚቴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፦ በጤናው ዘርፍ ካሉ በርካታ ኮሚቴዎች “Federal Advisory Committee on Immunization and Vaccination” አንዱ ነው፡፡

አስራ አምስት አባላትን ይይዛል፡፡ አባላቱ ከተለያዩ የህክምና ዘርፎች የሚመረጡ ከፍተኛ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ናቸው፡፡ ስለ ክትባት መንግስትን፣ የጤና ተቋሞችንና የህክምና ባለሙያዎችን ይመክራሉ፤ የክትባት መድሐኒት ግኝት ምርምሮችን ይከታተላሉ፤ የክትባቶችን ውጤታማነት ይከታተላሉ፤ ፕሮቶኮሎችንና መመሪያዎችን ይደነግጋሉ፡፡ በእነርሱ የተነሳ አሜሪካ ብዙ በሽታዎችን ወደ ዜሮ ዝቅ ማድረግ ችላለች፡፡ ዜጎቿ በቀላሉ በበሽታ የማይጠቁ ለማድረግ ችላለች፡፡ ለምሳሌ ቲቢን መውሰድ እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከመቶ ሺህ ሰዎች በላይ በቲቢ ይሞታሉ፤ ከሶስት መቶ አርባ ሺህ በላይ ደግሞ በየዓመቱ በቲቢ ይያዛሉ፤ ይታመማሉ፡፡ አሜሪካ ውስጥ ደግሞ በቲቢ የሚታመም የሚሞትም የለም ማለት ይቻላል፡፡ በመቶ ሺህ ሕዝብ ውስጥ ሁለት እና ሶስት ኬዞች ከታዩ የቲቢ ወረርሽኝ ተነሳ ተብሎ አፋጣኝ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ አሜሪካ በክትባት እና ኑሮን በማመቻቸት ዜጎቿ በበሽታ እንዳይጠቁ እና እንዳይያዙ መከላከል ችላለች፡፡ ይህ ደግሞ የተቋሞቿ ውጤት ነው፡፡

እናም ሀገሬ እውቀትንና ሙያተኞችን መጠቀም መጀመር ይኖርባታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ መንግስትን የሚረዱ ቢያንስ አንድ ሺህ ምርጥ ሰዎች ሳይንቲስቶች እና ኤክስፐርቶች ሊሰባሰቡ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ወደፊት ህዝብ የሚያስፈልገውን አይደለም ዛሬ ላይ የሚፈልገውንና የሚይጠይቀውን እንኳ ማሟላት እና  መስራት አይቻልም፡፡

ሀገራችን ሁለት ዓይነት መሪዎች ያስፈልጓታል፡፡ አስተዳደራዊ እውቀት ያላቸው እና ቴክኒካል እውቀት ያላቸው ሰዎች፡፡ ተቋሞቻችን በሙሉ እነዚህ ሁለት ዓይነት መሪዎች ሊኖሯቸው ያስፈልጋል፡፡ አስተዳደራዊ እውቀት ያላቸው ሰዎችን ለአንድ ግብ የሚያስተባብሩ ሲሆኑ ቴክኒካዊ እውቀት ያላቸው ደግሞ ተግባራዊ ስራዎችን የሚያቅዱ እና ስራዎችን ተከታትለው የሚያስፈፅሙ እና ለውጤት የሚያበቁ ናቸው፡፡ ተቋሞቻችን በሙሉ ከፓርታዊነት እና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ወጥተው ከፍተኛ ችሎታ እና ልምድ ባላቸው ጠንካራ በሆኑ አስተዳደራዊ እና ቴክኒካዊ መሪዎች ካልተመሩ በስተቀር መቼም ቢሆን ለውጥ ልናመጣ አንችልም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፦

በኢትዮጵያ እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ ከፈለጉ ተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር ይገባዎታል፡፡ አዳዲስ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መንግስትን የሚያማክሩ (እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ ያሉትን) የመንግስት መስሪያ ቤቶችንና ተቋማትን የሚያማክሩ የሚያግዙ የመንግስት አማካሪ ኮሚቴዎችን በሕግ ማዋቀር እና ብቃት ያላቸው ሰዎችን መጠቀም እጅግ በጣም ተገቢ ነው፡፡ መነሳሳትን የሚፈጥር ለችግሮች ተግባራዊ መላ የሚፈጠርበት ምን መሰራት ምን መደረግ እንዳለበት የሚታወቅበት ምርጥ ውሳኔዎች ትክክለኛ ዕቅዶች የሚገኙበት ተቋማዊ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልገናል፡፡ የመንግስት ሰዎች የተቋማት መሪዎች ምርጥ ውሳኔዎችንና ዕቅዶችን ካላገኙ ወደፊት በብቃት መራመድ ያስቸግራል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን ውጤት ማስገኘትም አይቻልም፡፡ ስለዚህም ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰራ የዚህ አማካሪ ኮሚቴ የዚህ አማካሪ ኮሚቴ እያሉ መንግስት እውቀትንና ምሁራንን መጠቀም እንዲችል በአዋጅ የመንግስት አማካሪ ኮሚቴዎችን እንዲያቋቁሙ እጠይቀዎታለሁ፡፡

 

የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበርን ያቋቋሙ

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፡-

ሀገርን መጥቀም ለሀገር መስራት እንፈልጋለን ለመንግስት ጠቃሚ ሀሳብ መስጠት እንችላለን የሚሉ በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ የኢትዮጵያ ምሁራን ሰዎች ሁሉ የሚሰባሰቡበት የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበር እንዲመሰረት ቢያደርጉ እጅግ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ እስራኤላዊያን የምሁራን ማህበር እንደ ቻይና እንደ ጀርመናዊያን የምሁራን ማህበር ያለ ቢሆን ለሀገር እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ሀገር የሚገነባው በጋራ ነውና፡፡

በመጨረሻም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ስለሆኑ እንኳን ደስ ያለዎት፡፡ ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት እና ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ላደረጉት ጥረት ምስጋናና እውቅና ይገባዎታል፡፡ በሀገራችን በውስጥ ጉዳይ ላይ የበለጠ እንዲሰሩ እና የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት አደራ ተሰጥቶዎታል፡፡ የዓለማችን ምርጥ ሰዎች የሚያገኙትን ዓለም አቀፍ እውቅና ስላገኙ እንኳን ደስ ያለዎት፡፡ የሀገራችንን ችግሮች ፈትተው ታሪክዎ ሙሉ እና እውነተኛ እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡ እንዲሳካልዎት ከጎንዎ እንሆናለን፡፡ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ሀሳብዎትን ቢረዱልዎት እና ከጎንዎ ቢቆሙ ደስ ይለኛል፡፡ በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ አተኩረው ለጥርጣሬ እና ለመለያየት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን አስወግደው እንደ መጀመሪያው ሕዝቡን በሙሉ ከጎንዎ አሰልፈው ሀገራችንን ወደ ብልፅግናና ወደ ከፍታ እንዲመሯት እመኛለሁ፡፡ ይህንንም የፃፍኩት ለዚህ ግብ ይጠቅማል ብዬ ስላሰብሁ ነው፡፡ በመንግስትዎ ስራ የሚያግዙዎትን ብዙ ምርጥ ሰዎችን ካገኙ የሚያስቡት እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

 

የርስዎ፡-

ውድሰው ደግዋለ ልመንህ

2 Responses to ይድረስ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

 1. NOT ONE PROPERTY KNOWN TO BE BELONGING TO OROMO BY THE ATTACKERS WAS TOUCHED, EVEN IF OROMO PERSON DIED IT WAS BECAUSE THE OROMO PERSON WAS ACCIDENTALLY FOUND IN NON-OROMO PERSONS PROPERTY, AUTOMATICALLY THE ATTACKERS ASSUMED THE PERSON WAS NON-OROMO BECAUSE OF THE PLACE HE WAS FOUND.

  If PM Abiy was not a fraud about the so called reform and if he sides with the truth he should make available to the free journalists presses Or other concerned bodies the addresses of the victims/family members , the victims full name , the victims age and maybe after that their ethnicity too, all these should have been done for each of the people he reported dead now .It cannot be difficult for him to know their name age addresses while he knew their ethnicity.

  His job as a PM now was to make sure information is available for journalists not to be INSA agent info distorter just like old times, old habits die hard.

  Even some picture and their life story would be appropriate for reporters journalists to have access to so they can report the legacies of those lost, reporters should have free access to interview by contacting the families at whichever shelter they are hiding in since their homes were burnt.

  How many homes burnt should be reported too, along with to who the homes burnt belonged to should be reported by the free press. All that got video camera should try to document the victims story , victims both who died or who survived still alive to.tell their stories deserve their stories heard by the world more than they need material help or food.

  Avatar for Xinabu

  Xinabu
  November 4, 2019 at 3:37 pm
  Reply

 2. ሰሚ ቢገኝ ግሩም ሃሣብ ነው።

  Avatar for ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

  ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
  November 4, 2019 at 8:50 pm
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.