ከማል ገልቹ በ48ሰዓታት የአብይን መንግስት ማፈራረስ እንችላለን ብለው ሲፎክሩ – መሳይ መኮነን

1 min read

አስመራ በገባን በሳምንቱ ነው። ልናገኛቸው እንደምንፈልግ ለኤርትራ ሰዎች ነገርናቸውና መልዕክት ላኩባቸው። ፍቃደኛ ሆነው ሊያገኙን እንደሚመጡ ገለጹልን። በኢሳት ሬዲዮ ላይ ለበርካታ ጊዜያት ቃለመጠይቅ ስላደረኩላቸው በቅርበት የማውቃቸው ያህል ይሰማኛል። ቀድሞ በአካል እንደተያየን ነገር ነበር የጠበኳቸው። እኔና ባልደረባዬ ፋሲል የኔዓለም በቀጠሮው ሰዓት ካረፍንበት ሆቴል የአስመራ ቢራ እየጠጣን ሰውዬውን መጠበቃችንን ቀጠልን። 500 ወታደሮችን አስከትለው፡ የህወሀትን ጥብቅ ሰንሰለት በጣጥሰው፡ የኤርትራን ድንበር አቋርጠው የገቡበት ገድል ሁሌም አድናቆት እንድሰጣቸው አድርጎኛል። የህወሀት ዙፋን ጠባቂ ሆኖ መቆየት አልፈለጉም። የወገኖቻቸው ህመም እረፍት ይነሳቸው ነበርና አጋጣሚው ሲመቻችላቸው ወታደሮቻቸውን ይዘው እብስ አሉ።

ሁለተኛ ቢራችንን እየተጎነጨን እያለ አንድ ጥብቅ ያለ ጂንስ ሱሪ የለበሰ፡ የቴክሳስ ጎረምሳ የመሰለ ቄንጠኛ ወጣት መሳይ ሰው ከሆቴላችን ሲገባ አየነው። በፍጹም የምንጠብቀው ሰው ይሆናል የሚል ግምት አልነበረንም። በፎቶግራፍ በወታደራዊ ዩኒፎርም የማውቀው ሰው እንዳልሆነ ለራሴ እርግጠኛ ሆንኩ። ሰውዬው አለባበሱ የማይክል ጃክሰንን ቄንጠኛነት የሚያስታውስ ነው። በአይኑ እያማተረ ሲፈልግ እኛን እንደሆነ አልገባንም። እንዴት ይሆናል? ያ ቆፍጥና ወታደር፡ ከየት መጥቶ እንዲህ የ20 ዓመት ጎረምሳ ገጽታ ሊኖረው ይችላል?! ግምታችን ልክ አልነበረም። ሁለት እጆቹን በጥብቆው ጂንስ ሱሪ ኪስ ውስጥ አድርጎ እየተንጎማለለ የገባው ሰው የሚፈልገው እኛን ነበር። ቢራችንን እየኮመኮምን የምንጠብቀው ሰው ፍጹም ባልገመትነው ቁመናና አለባበስ በቀጥሮው ቦታ ተገኝቷል። እሳቸው ናቸው። ሰውዬው። ብ/ጄነራል ከማል ገልቹ።

በሹክሹክታ እንደሰማነውና በአስመራ የቀናት ቆይታችን በሰፊው እንደተነገረን የኦነግ መሪዎች ትግሉን ትተውታል። አንድ ቁራሽ መሬት መቆጣጠር ሳይችል የጎልማሳ ሰው እድሜ የበላው የኦነግ ትግል አስመራ ላይ መልኩን ቀይሮ መሪዎቹ የኤርትራ መንግስት ባቀረበላቸው ቪላ ቤትና አውቶሞቢል እየተመነሸነሹ ሲዝናኑ ውለው ሲዝናኑ ያመሻሉ። ከብ/ጄ ከማል ገልቹ ጋር እያወራን የተረዳነው ይሄንኑ ነው። ኤርትራ ከገቡ ከመግለጫ ያለፈ በመሬት ላይ የሚያካሂዱት ትግል አንድ ስንዝር ወደፊት መራመድ ያልቻለበት ምክንያት ይገርመኝ ነበር። ብ/ጄ ከማል ወታደር ናቸው። የፖለቲካ ሰው አይደሉም። አለመሆናቸውን አሁን ላይ በሚገባ እያስመሰከሩ ነው። የአስመራው ትግላቸው እንደግመል ሽንት ወደኋላ የሆነበት ሚስጢርን ከእሳቸው ብሰማ ብዬ ጓጉቼአለሁ። ‘’ይሄው አስመራ ላይ ቢራ እየጠጣን ቁጭ ብለን ስምንት አመት አለፈን” ሲሉን እኔና ፋሲል ድንገት አይን ለአይን ተገጣጠምን።

ነገሩ እንዲህ ነው።

ብ/ጄ ከማልና ብ/ጄ ሃይሉ ጎንፋ በሁለት አቅጣጫ አምስት መቶ ወታደሮችን ይዘው ኤርትራ ይገባሉ። የዛሬ 14 ዓመት። እቅዳቸው በስድስት ወራት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያለውን የኦሮሞ ወታደር በማስኮብለልና ህዝቡም እንዲቀላቀላቸው በማድረግ አቶ መለስ ዜናዊን ማስወገድ ነበር። ሰውዬውን ኋላ ላይ ስረዳቸው በጣም ችኩልና መረጋጋት የራቃቸው ናቸው። እንደአቅማቸው ማሰብና መራመድ የሚችሉ አይደሉም። እናም አስመራ እንደደረሱ ለኤርትራ ባለስልጣናት ‘’በአስቸኳይ መሬት ስጡን፡ እኛ ወታደር እያሰለጠንን ኤክስፖርት በማድረግ ወያኔን በአጭር ጊዜ እናስወግዳለን። የእናንተ ድጋፍ መሬት በመስጠት ላይ የተወሰነ ብቻ መሆን አለበት። ሌላውን እኛ እንወጣዋለን’’ የሚል ሱሪ ባንገት ካላወጣሁ አይነት ጥያቄ ያቀርባሉ። ሰውዬው ፖለቲካ እንዳልገባቸው የሚያሳይ አንድ ማስረጃ የሚሆን ጥያቄ ነው። ወታደር ሸቀጥ አይደል ኤክፖርት ተደርጎ የሚዋጋው? ከኤርትራ ጋር ድንበርተኛ ባልሆነው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲህ ዓይነት ስትራቴጂ ምን የሚሉት እብደት ነው? ኤርትራን መሬትሽን ብቻ የሚለው አካሄድ ለአቅመ ፖለቲካ ከደረሰ ሰው የሚጠበቅ አይደለም። ጄነራሉ ግን ደፋር ናቸው። ቀና ብለው ደረታቸውን ነፍተው የያዙት አቋም ለሌላው ያስደነግጣል። ኤርትራውያኑ ‘’ ጄነራል እባክዎትን ይረጋጉ። አብረን እንሰራለን። የአከባቢው ጉዳይ በተናጠል የሚሰራ አይደለም። እንነጋገርና በጋራ እንስራ’’ ብለው ይመልሱላቸዋል። ይሄን እንግዲህ የሚነግሩን ራሳቸው ብ/ጄ ከማል ገልቹ ናቸው።

አሻፈረኝ አሉ። ‘’ከእናንተ የምንፈልገው ወታደሮችን የምናሰለጥንበት መሬት ብቻ ነው። ሎጀስቲክም ሆነ ትጥቅ አናስቸግራችሁም። ራሳችንን እንችላለን።’’ ብ/ጄ ከማል ገልቹ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ስራ ሰርተናል ብለው በአደባባይ መናገር የጀመሩት እግራቸው አስመራ በረገጠ ማግስት ነበር። 30ሺህ የኦሮሞ ወታደሮችን መከላከያ ውስጥ አደራጅተናል ብሎ መደስኮር የሰውዬውን ክሽፈት ከማሳየት ያለፈ ትርጉም አልነበረውም። ፖለቲካ ራሱን የቻለ ሳይንስ መሆኑ ለጄነራሉ ቀልድ ሆኖ የሚታያቸው ይመስላል። ህወሀትን የመሰለ ሴረኛና ተንኮለኛ መንግስት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ መከላከያ ውስጥ ስራ ሰርተናል ብሎ በአደባባይ ማወጅ በእርግጥም የፖለቲካ ድንቁርና እንጂ ሌላ የሚያሰኝ አይደለም። ብ/ጄ ከማል ይህን በተናገሩ ዕለት ህወሀት በሰራዊቱ ውስጥ ከመስመራዊ መኮንን ጀምሮ ያሉትን የኦሮሞ ተወላጆችን ሰብስቦ እስር ቤት አስገባቸው። የጄነራሉ ፉከራና ሽለለ ከጆሮአችን ጓዳ ሳይጠፋ ህወሀት በወታደራዊ ደህንነቱ አማካኝነት የጄነራሉን ሰንሰለት በመበጣጠስ ስውር እቅዱን ብትንትኑን አወጣው። ሂሳብ ብትሳሳት እርማት ትላለህ። እንግሊዘኛ ብትሳሳት እርማት ትላለህ። ፖለቲካ ብትሳሳት ግን ገደል ትገባለህ እንዲሉ ብ/ጄ ከማል ከእውቀትና ልምድ ማጣት ገና በጠዋቱ ፖለቲካው ካዳቸውና ትግሉን በብዙ እርምጃ ወደኋላ መለሱት። ችግሩ ሰውዬው ከዚህም የሚማሩ አለመሆናቸው ነው። አስመራ ከገቡም በኋላ በግትርነትና በብስለት ማጣት ሌላ ስህተት መስራት ጀመሩ።

ኤርትራውያኑ ባለስልጣናት አስመከሯቸው። አብረው ካልሰሩ በቀር ለብቻ የሚደረግ ትግል ውጤት አያመጣም በሚል በፊት ለፊትና በእጅ አዙር መልዕክት ሰደዱባቸው። ሰውዬው ወይ ፍንክች! ጥርሳቸውን በፖለቲካ የነቀሉትና ሴራውን መሬት ላይ በቅጡ ማንበብ የሚችሉት የሻዕቢያ መሪዎች ከሰውዬው ጋር ከዚህ በላይ መጓተት አልፈለጉም። እንዴት ማስተንፈስ እንደሚችሉ ያውቁበታል። ይዘውት የመጡትን ሰራዊት ወስደው በአሰብ አቅራቢያ አንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ አስቀመጧቸው። ከአዛዣቸው የተነጠሉት ወታደሮች ምንም ዓይነት ግንኙነት በማያደርጉበት ስፍራ እንዲቀመጡ ሲደረጉ ብ/ጄ ከማል የሚያዙትም የሚመሩትም ሃይል አጡ። ባዶ እጃቸውን ቀሩ። ቪላ ቤትና ቆንጆ አውቶሞቢል ተሰጣቸውና የአስመራ ቢራ እየጠጡ ከመቆየት ውጪ ምርጫ እንዳይኖራቸው ተደረጉ። በጎቹና እረኛው ሲነጣጠሉ የሚፈጥረው ክፉ ስሜት ብ/ጄ ከማል ገልቹን ያስቃያቸው ጀመር። ግትርነታቸው ዋጋ አስከፈላቸው። በፖለቲካ ጥልቀት የሌለው እውቀታቸው ከገደል አፋፍ አስጠጋቸው።

አሁንም ሰውዬው በፖለቲካው የሰሩትን ፋወል እየነገሩን ነው። እሳቸው ሲያወሩት በብሽቀት አይደለም። ስህተት ሰርቼአለሁ የሚል ጸጸት ሲያልፍም አይነካካቸውም። ደረታቸውን ነፍተው በጀብደኝነት የነገሩንን ሳይሆን ገልብጠን የተረዳነውን ነው እያከፈልኳችሁ ያለሁት። ከስህተት አለመማራቸው ሌላ ስህተት እንዲፈጽሙ እያደረጋቸው ነው። ዘንድሮም ከዚያ አዙሪት አልወጡም። በኋላም እሳቸውን ተከትሎ አብሮአቸው ኤርትራ የገባው ሰራዊት መበታተን ጀመረ። በእሳቸው እዝ ስር የነበሩና ከወራት ቆይታ በኋላ በተስፋ መቁረጥ ከአሰብ ካምፕ ወጥቶ አርበኞች ግንቦት ሰባትን የተቀላቀሉ የኦነግ ሻምበል አዛዥ እንዳጫወቱኝ ከሆነ ብ/ጄ ከማል የሰሩት ስህተት የሰራዊቱን ሞራል ሰብሮታል። እሳቸው አስመራ ቪላ ቤት ውስጥ ሲኖሩ ተከትሎአቸው የመጣው የኦነግ ሰራዊት ግን በረሃ በልቶት ገሚሱ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ የተቀረው እዚያው አሰብ ውስጥ ይንከራተታል። ሰውዬው ግፍ ተፈጸመብኝ እንጂ በፖለቲካው ጨዋታ ተበለጥኩ ብለው እጅ የሚሰጡ አይደሉም። ንግግራቸው ሁሌም ፉከራ ይበዛዋል። ግትር መሆናቸውን አንድ አረፍተ ነገር ከአፋቸው እንደወጣ ማንም ሰው የሚረዳው ነው።

ብ/ጄ ከማል ባዶ እጃቸውን ከቀሩና ዩኒፎርማቸውን አውልቀው እንደቴክሳስ አራዳ ጂንስ ሱሪ ካጠለቁ በኋላ ብዙም ድምጻቸው አይሰማም ነበር። ከእነዳውድ ኢብሳ ጋር መቦጫጨቅ የጀመሩት በጊዜ ነው። ኦነግን የተቀላቀሉት ጄነራሉ ሁሌም መሪና አዛዥ የመሆን ስር የሰደደ ፍላጎታቸውን እነዳውድ ሊቀበሉት አልቻሉም። የመንደርና የጎጥ ጣጣም ሰዎቹ እንዲስማሙ አላደረጋቸውም። በወለጋ ሰዎች የተሞላው የኦነግ አመራር ቡድን አርሲዎችንንና ሸዋዎችን መቀበል አልቻለም። ግብግቡ የተጀመረው እነ ከማል ገልቹ የኤርትራን ምድር ከመርገጣቸው አስቀድሞ ነው። በኋላ ላይም ሁኔታው ያላማራቸው እነዳውድ ኢብሳ የሞት ፍርድ በይነው ሊገድሏቸው አቅደው ኤርትራውያኑ ጣልቃ ገብተው እንዳስጣሏቸው ሰምተናል። የኦሮሞን ህዝብ ነጻ እናወጣለን ያሉት ሰዎች አስመራ ላይ አንገት ለአንገት ሊቀነጣጠሱ መፋጠጣቸው ከምጸትም በላይ አሳፋሪ ክስተት ነው።

ብ/ጄ ከማል አብረዋቸው በረሃ ከወጡት ከብ/ጄ ሃይሉ ጎንፋ ጋርም መስማማት አልቻሉም። እሳቸው በአንደበታቸው እንደነገሩን ‘’ሃይሉ ትግሉን ትቶ የውጭ ኑሮን መረጠ። ስዊዲን ለመውጣት ፕሮሰስ ጀምሮ ሲስተጓጎልበት አንተ ነህ እንቅፋት የሆንክብኝ ብሎ ጠመደኝ።’’ እያሉ ብ/ጄ ሃይሉን ይወቅሳሉ። እንደሰማነው ደግሞ ሁለቱ ሰዎች ጠባቸው የብ/ጄ ከማል ግትርነት ነው። በስብሰባ ላይ ቡጢ መማዘዛቸውም ይነገራል። ብ/ጄ ሃይሉንም በሌላ ቀን እዚያው ሆቴል አግኝተናቸዋል። እንደከማል ችኩልና ግትር ባይሆኑም እሳቸውም በፖለቲካው ላይ ጠንከር ያለ ቁመና እንደሌላቸው ተረድተናል። አስመራ እንደሚወራው ኦነጎቹ በሞት ይፈላለጋሉ። ከማልና ሃይሉ አንድ ቦታ ላይ ከተያዩ ከዓይን ግልምጫ ባለፈ ለድብድብ እንደሚቃጣቸው ይነገራል። አንድ ጠረጴዛ ላይ ገበታ መቅረብ ይቅርና አንዱ ባለበት አንደኛው መታየትን አይፈልግም። አይንና ናጫ፡ እሳትና ጭድ ሆነው ነው ስምንቱን ዓመት በአስመራ የቆዩት። እነዚህ ሰዎች ናቸው እንግዲህ ለታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ነጻ እናወጣሃለን የሚል መሃላ እያዥጎደጎዱ በገቢር ራሳቸውን ከአስተሳሰብ ድህነት ነጻ ማውጣት ተስኗቸው በሀገር ኤርትራ የኦሮሞን ህዝብ እያዋረዱት የዘለቁት።

ብ/ጄ ከማል የኋላ ኋላ በኤርትራ ቢራ እየጠጡ መቆየት መረራቸውና በስምምነት ወደሌላ ሀገር ለመሄድ ጥያቄ አቀረቡ። የኤርትራ ባለስልጣናት ሁኔታዎችን አመቻቹላቸውና ወደ ኡጋንዳ ሄዱ። አንድ ጥይት ሳይተኩሱ፡ አንድ ጋት መሬት ነጻ ሳያወጡ፡ የኤርትራን ምድር የለቀቁት ብ/ጄ ከማል ኡጋንዳ ገብተው አዲስ ያቋቋሙትን የነጻ አውጪ ድርጅት እየመሩት መሆኑን ገለጹ። ከህወሀት ወታደራዊ አዛዥነት ወደ ኦነግ አማጺ ሰራዊት መሪ፡ በኋላም የኢትዮጵያ ነጻ አውጪ ሃይል ከመሆን በብርሃን ፍጥነት ተመልሰው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባርን በሌላ ስም ይዘውት ኡጋንዳ ገቡ። የሰውዬው ድንግርር ያለ፡ እውቀትና ብስለት የራቀው እንቅስቃሴ ኡጋንዳ ሆኖ አማጺ ቡድን አደራጀሁ ብሎ መደስኮር ነው። በብዙ ሺህ ኪሎሜትሮች ርቀው፡ ከካምፓላ የተቀመጡት ብ/ጄ ከማል በኤርትራ ያላሳኩትን የነጻ አውጪ ተልዕኮአቸውን በኡጋንዳ ሊሞክሩት ጥሪ አደረጉ። እንደምኞታቸው አልተሳካላቸውም። እዚያው እንደተቀመጡ፡ ከሽለላና ቀረርቶ ሳይላቀቁ፡ በእነ አብይና ለማ ጥሪ ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ። በእግር በርሃ አቋርጠው ከሀገር የወጡትን ሰው እነ አብይ በክብር በአውሮፕላን በቦሌ በኩል እንዲገቡ አደረጓቸው።

ሰውዬው ወደሀገር ቤት ሲገቡ የወቅቱ የፉክክርና የእኔ እበልጥ ፖለቲካ ያስከተለው ሙቀት የጀግና አቀባበል እንዲደርግላቸው እድል ፈጥሮላቸዋል። መሬት ከጠላት እያስለቀቁ፡ ከተማ እየተቆጣጠሩ፡ ጦራቸውን ይዘው ከአስመራ ውደ አዲስ አበባ በድል አድራጊነት እየገሰገሱ የገቡ ይመስል በጠዋቱ ትዕቢትና እብሪት ያጠላበት ንግግር ማድረግ ሲጀምሩ ነበር ትዝብት ላይ የወደቁት። እነለማም ቢያንስ አስተዋጽኦ አድርገዋል በሚል አክብረዋቸው የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ እንዲሆኑ ሹመት ሰጧቸው። ለቦታው የሚመጥን የፖለቲካም ሆነ የእውቀት ዝግጅት ያልነበራቸው ብ/ጄ ከማል መንግታዊ መዋቅሩን ተጠቅመው ማህተም እንኳን የሌለውን አዲሱን የነጻ አውጪ ድርጅታቸውን ፖለቲካዊ ስራ በሽፋን መስራቱ ላይ ተጠመዱ። አስመራ ላይ የሞት ፍርድ የፈረዱባቸውን እነዳውድ ኢብሳን የሚበቀሉበትን አጋጣሚ የተፈጠረላቸው መሰላቸውና እግር በእግር እያሳደዱ ማዋከብ ጀመሩ። የመንግስትን ስራ ወደ ጎን ትተው በሾሟቸው የኦዲፒ መሪዎችና የኦነግ አመራሮች ላይ ሴራ መጎንጎኑ ላይ በግልጽ መስራታቸውን ቀጠሉ። ኦነግ ወደ ሀገር ቤት የገባበትን ስምምነት ያፈረሰ ሲል የብ/ጄ ከማልን ሹመት ተቃወመው። መጠላለፉ አስመራ ላይ ሳይቋጭ በአዲስ አበባም ቀጠለ። በኋላ ነገሩ ያላማራቸው አቶ ለማ መገርሳ በአንዲት ብጣሽ ወረቀት ከሃላፊነት አሰናበቷቸው።

ብ/ጄ ከማል ገልቹ በይፋ የለውጡን ሃይል መገዝገዝ የጀመሩት ብጣሿ የስንብት ደብዳቤ እጃቸው ከገባች ዕለት ጀምሮ ነው። አንድ የሚያዙት ወታደር ሳይኖራቸው፡ የኦሮሞ ወጣትን ተማምነው የጦርነትና የዕልቂት ጥሪ መጎሰምን ስራዬ ብለው ተያያዙት። በ48ሰዓታት የአብይን መንግስት ማፈራረስ እንችላለን ብለው ሲፎክሩም ሰማናቸው። ሰሞኑንም ኦሮሚያን በኮንፌደሬሽን ከእናት ሀገሯ ለመገንጠል ህልም እንዳላቸውና ይህንን ህልማቸውን የሚያስቆም ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር ማይክ ጨብጠው ሲፎክሩ የሚታዩበት ቪዲዮ በማህበራዊ መድረኮች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል። በካምፓላ እንቅልፋቸው ሲለጥጡ የነበሩትን ሰው በክብር ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ያደረጓቸውን የለውጥ መሪዎች በኦሮሞ ጠላትነት በመፈረጅ ህዝብ እንዲነሳባቸው ግልጽ የሆነ የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸው ስሰማ የሰውዬው መጨረሻ ምን ይሆን ብዬ ራሴን ጠየኩ።

ብ/ጄ ከማል የጎረሱበትን እጅ መንከሳቸው ለህሊናቸው ሰላም እንጂ ጸጸት እንደማይሰጣቸው ያስታውቃሉ። ሲፎክሩ እስከአፍንጫው የታጠቀ አንድ ባታሊዮን ጦር የሚያዙ ነው የሚመስሉት። የኦሮሞ ፖለቲካ የዚህ ዓይነቱ ጨለምተኛ፡ እውቀት አጠር፡ ገታራና ቆሞ ቀር ሰዎች የሚፈነጩበት መሆኑ የሚያሳዝን ነው። ለኦሮሞ ህዝብ ከእነአብይ የተሻለ ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርግ አለመኖሩን በተረዳን ጊዜ በእነዚህ የድንጋይ ዳቦ ዘመን አስተሳሰብ ባጠቃቸው የፖለቲካ ደሀ በሆኑ ፖለቲከኞች የኦሮሞ ወጣት የነገውን ተስፋ የሚያጨልመው ለምን ይሆን የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ተገደድን። በእርግጥም ለእነዚህ የስልጣን ጥመኞች እርካታ ሲባል የስንት ሰው ህይወት መቀጠፍ አለበት? የራሳቸውን ዘመን በከንቱ አበላሽተው በነገው ትውልድ ህይወት ላይ ቁማር የሚጫወቱ መሰል ግለሰቦች ከእንግዲህ እድሉ እንዳይሰጣቸው የማድረግ ሃላፊነት የዘመኑ ትውልድ አይደለምን?

11 Comments

 1. ይህንን ነው መፍትሄ የምለው ወንድም መሳይ። እነዚህን በየዋሁ ወገኔ የሚነግዱትን ምንደኞች በጋራ እንደመዋጋት “በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥምን” ምን አመጣው? እንዲህ ነው ታሪካቸውን ለንባብ ማውጣት። እነዚህ በጭራሽ በእድሜዬ የማውቀውንና የተወለድኩበትን ማህበረሰብ አይወክሉም። ጥቅመኞችና የበሉበትን ወጪት ሰባሪዎች። እየው ያንን መልካም ስብእና ያለውን የዖነግ ታጣቂ ሊታደግ የረዳን ሰው ምስጋና ነበር የሚገባው አቢይ። እነዚህ ናቸው ስለዖሮሙማ የሚነግሩኝ? እኔም ኢንሳ ብሰራ ኖሮ እታደገው ነበር። ለምን ይሙት? እነሱን በክብር የጠራ ጊዜ ነው ያጠፋውስ። እዛው ኡጋንዳና ኤርትራ በተዋቸው ኖሮ። የብልጠት ፖለቲካ የማስጠያ መሆኑ ቀርቶ አሳፋሪ ነው የሆነብኝ። የወያኔን ምክር ሰምተው እኮ ነው። እንደው የነ አብዲሳ አጋ ትውልድ ሆኖ እንዴት ከነ አቦይ ስብሀት ቡራኬና ምክክርብተቃምሶ ይመጣል ሰው? የጁዋር አይገርመኝም። የለየለት ምንደኛ ነውና። የነ ከማልም አይደንቀኝም። ታሪኩን እናቀዋለንና። ካነሳህውስ ልቤን የሰበረው አብሮት ለጥቂት አመታት የሰራው የነ ሽመልስ አብዲሳና መሰል ኦዲፒዋች ነው። ካንድ ቆፍጣና የዖሮሞ ልጅ ታዬ ደንደአ በቀር ጁዋርን በአደባባይ ያወገዘ ሰምተሃል? እንዲህ በግልጽ ሌላው ይቅር ዖሮምያን በደም እየበከለ? ምኑን ነው የፈሩት? ልክ ትራምፕ ሪፐብሊካኖቹን በፎክስ ኒውስ እንደሚያስፈራራው omn መፈራቱም አይደል ለጥቅም ሲባል? እነዚህ ናቸው ስለዖሮሙማ ጥብቅና የቆሙት? ለምንስ ነው ሌላው ዖሮሞ ወገኔ ዝምታው? አውሬ እስክንባል ድረስ? እንዴት ይህ ምንደኛ እኔን አይወክልም አይባልም? ፖለቲከኛ ያልሆኑትን ማለቴ ነው። ፖለቲከኞቹስ ለምን እንደሚርመጠመጡ ይረዳኛል። ሌላው ቢቀር ሰብአዊነት እንዴት እንቅልፍ አይነሳም? እናም ወንድሜ እንዲህ የራስህ ጉዳይ አርገው መሳይ። የብዙዎች ዝምታ ነው ለዚህ ያበቃን። እስቲ ይቺ የፈተና ጊዜ ትለፍና ጠ/ሚሩን ለመውቀስ ያብቃን። ብዙ ስህተት አርገዋልና። ላሁን ጥቅም የለውም ብለን እንለፈው። እስከዛው አንድነታችንን ለማጠንከር መፍትሄዎችን እናቅርብና ሰውዬውን እንርዳ። የጋዜጠኝነት ግዳጅህን እንዲህ ተወጣ እንጂ ። እንዲህ ነው በኢትዮጵያችን ተስፋ ያለመቁረጥ ማለት። ለወንበዴዎች እጅ ልንሰጥ? በጭራሽ። ምን ጉልበት ቢዝል እስትንፋስ እስካለን እንዋደቃለን በጋራ። በርታ አንተም። እስቲ የቆየ ፋይል ያን ሲሳይን እያማከርክ ፈልፍላችሁ አውጡ በነዚህ የናት ጡት ነካሾች። አይ አገሬ።

 2. ይህ ያልሰለጠነ እረኛ ሰው ሆኖ መሄድ የቻለው ነፍጠኛው ባቀናው ሀገር ነው:: እውነተኛ ወታደርና ጄኔራል ከሆነ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ጥሎ ለምን ሸሸ? ነፍጠኛ እኮ አይሸሽም:: በዚህ ባልሰለጠነ አፉ ነፍጠኛውን ለማጣጣል ምንም የሞራል ብቃት የለውም:: ከውኳዋ ቢጤ ነው:: ይህ አይነት በሬ ኦሮሞን አይወክልም::

 3. መሳይ/አስመሳይ ምናለ ዝም ብትል? አንተና ጌታህ ብርሃኑ ሀፍረት የሚባል አልፈጠረባችሁም?

 4. በቆየ ወሬ እና በቀነጨረ አስተሳሰብ ተቀባይነት ለማግኘት የተደረገ ንግግር ሁሌም ለኔ ቅጥረኘሰነት ነው፤ ሀገር ለማፍረስ! ሲቀጥል ነፍጠኛ ኘፍጠኛ ማለት በዝቷል! ከገባቸው እኔም ይህን እላለሁ!

  ነፍጠኝነት የኢትዬጲያ ጥላት አደደለም፤ ዘረኝነት እና ተረኝነት እንጂ! #በባቢሎን ጅታስ#

  ሰሞኑን የቀድሞዎቹም ሆነ የአሁኖቹ የኦሮሞ መሪወች እንዳዲስ #ነፍጠኛ# ምትል ካርድ መምዘዝ ከጀመሩ ሰነበቱ! የአፍ ወለምታ ነው ብየ ነበር! ነገሩ ሲደጋገም ሀሳቤን ልሰጥ ወደድሁ! ምክንያቹም “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራናት ይሏታል” ሚባለው ተረት በነፍጠኛ እየመጣ መሆኑ ስለተሰማኝ! እነዚህ ሰዎች፦ ነፍጠኛ ማለት ምን ማለት ነው? ቢሏቸው ሚያውቁ አይመስለኝም! ቃሉን ሳያውቁ በመሰለኝ እና በደሳለኝ ሀሳብ እየተሰጠ በመሆኑ እየተቸገርን ነው! የወያኔ ትርክት ከሆነ በውሸት የተፈጠረ ስለሆነ ትርጉም አልባ ነው! ዲክሽነሪ ማያውቀው! መዝገበ ቃላት ያልቃኘው የጫካ ትርክት እና ስም ነው! #ነፍጠኛ# ምትባል ቃል ለማን ወያኔ እንሰራት ሀገር ሚያውቀው ነው! በዚህ ወቅት ለኦሮሞ እንቆረቆራለን እያሉ ሚደሰኩሩ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ጠብ ያላለ ስራ የሰሩ ግለሰቦች ዛሬ ደርሰው በደሙ እና በመስዋዕቱ ወደ ሀገር እንዲገቡ ያደረጋቸውን የኢትዬጲያ ህዝብ፤ ከወያኔ ጋር ወግነው እየወጉት መሆኑን እያየን ነው! እጅግ በጣም ያሳዝናል! ነፍጠኛ ሲወስን እና ሲደራጅ ሀገር ትቅደም፤ #ኢትዬጲያ# ትጠበቅ በቅድሚያ ከብሄር በፊት ባለበት ወቅት፤ በለውጥ ስም ኢትዬጲያዊነትን የሚደግፉ መሪዎችን የገደሉም ያስገደሉም አሉ! ዝም ሲባል የተረሳ እንዳይመስል፣ ቁስሉ ሁሌም አዲስ ነው ለሀገር ሲባል በትግስት ታለፈ እንጂ! ቆይተን ስናውቀው ግን ነፍጠኞች (በወያኔ ቋንቋ አማሮች) ትግስታችን ሀገር እንዲፈርስ እየተኛን መሆናችን እየተገነዘብን ነው! ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻው የቀነጨረ አእምሮ የያዙ ጠባቦች በለውጥ ስም ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ መደረጉ የመጀመሪያው ስህተት ነው! ሲቀጥል የለውጥ መሪ አራማጁ አሻጋሪ ተብየው እንደ እንስሳ የሰው ልጅ እየታረደ እርምጃ ባለመውሰዱ የመጣ ጥፋት ነው! ይህ ሁሉ ጥፋት ለለውጥ አብሮ የታገለ ማህበረሰብን ወደ ጎን በመተው ለውጡን ያመጣነው እኛ ብቻ ነን የሚሉ ግለሰቦች እንዲፈጠሩ ሆነ! አሁን አሁን ደሞ የወያኔ የውሸት ትርክት መዝገበ ቃላት በማያውቀው መንገድ #ነፍጠኛ# የምትባል ትርክት መለጠፍ ተጀምሯል! በተለይ በተረኛ መሪወቹ! ለማን እንደተለጠፈችም በደንብ ትታወቃለች!!! የረሷት ነገር ግን #ነፍጠኛ# ብለው ያስተማሯቸው ወያኔወች እነሱን (ተረኛ ነን ባዬችን) ደሞ #ጠባቦች# የሚል ቃል እንደለጠፉላቸው መርሳታቸው ነው! በዚህ ከቀጠለ ነፍጠኛ ሁሉ ሀገር ለመጠበቅ እና ለማዳን ካልተንቀሳቀሰ ችግር አለ ማለት ነው! መንግስት ተብየው በእሽሩሩ እና በድብቅ አጀንዳው ተጠምዷል ሀገር በእኩል ከመምራት ይልቅ! ነፍጥ ደሞ ለከሀዲ እና ሀገር ሻጭ አጭበርባሪ ሁነኛ መፍቴ ነው! በሚስት እና በሀገር መለማመጥ መጨረሻው ሞት ነው! ነፍጠኛ እያሉ ማሸማቀቅ ሚቻል ከመሰላቸው እነሱ ከሀዲ፣ ሀገር ሻጭ፣ ሀገር ቆራሽ፣ ሙሰኛ እና ዘራፊ ናቸው! ደስ ሚለው ነገር ግን እኔ እራሴ በኩራት ምናገረው ነገር ቢኖር #ነፍጠኛ# መሆኔን ነው! እንዲህ ሀገርን ከሚያተራምሱ እና ሀገርን ለገንዘብ ከሚሸጡ #ጠባቦች# በብዙ መንገድ እለያለሁ! ምክንያቱም እኔ ኢትዬጲያ አልጠላም! በተረኝነትም ሆነ በቀነጨረ አስተሳሰብ የሰውን ልጅ እንደ እንስሳ አላርድም፣ አልቀጠቅጥም፣ እንደሰው እናቶችን ህፃናትን እጠብቃለሁ! ዘር ሀይማኖትን መሰረት አድርጌ አለሰገልም! በኢትዬጲያ ሲመጣ ግን ቀልድ የለም! ስለዚህ ዛሬም ሆነ ነገም #ነፍጠኛ# ሁኘ ሀገርን እና የሰው ዘርን እንደ በግ ከሚያርዱ #ጠባቦች# መታደግ የዘወትር ስራየ ነው! ነፍጥማ ነፍጥ ነው! የሀገር ከሀዲ ዳቢሎሶችን ያፀዳል! አለበለዚያ በስመ ለውጥ ቁጭ ብሎ ሚሞት ያለ ከመሰላቹህ ትግስት የማይገባው የተረኞች አስተሳሰብ ነው! እያውም ለ40-50 ዓመት ጠብ የሚል ስራ ያልሰራ የቀነጨረ አዕምሮ ይዘው የገቡ ጠባቦች! ደሞ በሁለት ቀን በሶስት ቀን መንግስት እንቀይራለን፤ እየተባለ ሲደሰኮር ሌላ ምን ይባላል “አይ ነፍስ አለማወቅ” እንጂ! እዚህ ላይ የለውጥ መሪዎች ሚባሉት ወይም የወቅቱ መሪዎች የመጨረሻ ካርድ ላይ መሆናቸውን ነው! ምክንያቱም የሰው ልጅ እንደ እንስሳ እየታረደ ህግ ማያስከብር መንግስት ተብየ እቆያለሁ በወንበሩ ካለ ቀልድ ነው! ወይም ሌል ከህዝብ የተደበቀ አጀንዳ አለው ማለት ነው! ሁለቱም ሀገር አፍራሽ ስለሆኑ መጨረሻው ሀገር ማፍረስ ነው! ይህ ደሞ ለሁሉም አይበጅም! ያስተላልቃል እንጂ!

  ከገባቹህ ይግባቹህ! ውድ ጊዜያችሁን ተጠቀሙበት! አለበለዚያ የናንተን ጨርሳቹህ የኛን ጊዜ አትጋፉን! እምቢ ካላቹህ ጊዜው የኛ ነው! የአዲስ አስተሳሰብ ፈጣሪዎች! ለናንተም ነፃነት ያመጣን የታገልን ሊባሉ የሚገባው ወቅት ነው! ሁልግዜ ዝምብሎ ሚሞት ሚታረድ ያለ ከመሰላቸው፤ የመጀመሪያ ተጠያቂው መንግስት ነው! ሀገር ለመጠበቅ ሲባል ግን #ነፍጠኛው# ስራውን ይጀምራል! በወንድሞቻችን ደም እማ የሚቀልድ አእምሮም ሆነ ህሌና በኛ #በነፍጠኞች# የለም! ለሀገር ሲባል ዝም ማለት ፍራት አደለም! #ነፍጠኛ# ሚባለው ስምም በጣም ይመቸኛል! #ጠባብ# ከመባል!!!

  የሚገርመኝ ነገር እንዴት ሰው ከገዳዩ አስገዳዩ ጋር ሁኖ ሀገር ይረብሻል! ላለፉት 40 እና 50 ዓመት ከሀገር ካባረሯቸው እና ካሳደዷቸው ሰወች ጋር ሁነው ሀገር እና ህዝብ ይረብሻሉ? ለኔ ሲገባኝ ለካ ሰው በዘረኝነት ካሰበ እና አእምሮው ከቀነጨረ ለነገር እንጂ፤ ለጥሩ ነገር ወደኋላ ማየትም ማሰብም አይችልም! ከቀነጨሩ አስተሳሰቦች እና አሳቢወች ፈጣሪ ኢትዬጲያን እና ህዝቧን ይጠብቅ!!!

 5. ከማል ገልቹ ኤርትራ ውስጥ ታጥቆና ተደብቆ የሰራው እዚህ ግባ የሚባል ነገር ለኦሮሞ ህዝብ የለም። ያው በኦሮሞ ህዝብ ስም ግን የግል ንግድ ሲያጧጡፍ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። አሁም ማን ይሙት ከማል ገልቹ እንኳን የአብይን መንግሥት ማፈራረስ ቀርቶ የከብቶች በረት የሚያፈርስ አቅም የላቸውም። ግን እንዲህ ያለው ጫጫታ ከኦሮሞ አፍራሽ መንጋ ጋር ለመተባበር እንዲያስችለው የተናገረው ነው። ይገርማል። ትላንትም ክብሪት መጫር ዛሬም ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት። የሞኞች ፓለቲካ። እስቲ ሰክን ብለህ በእድሜዬ ለኦሮሞ ህዝብ ምን ሰራው? ለራሴና ለቤተሰቤ ምን አተረፍኩ በማለት ዙሪያህን ተመልከት። የሚገርመው የኦሮሞ ፓለቲካ እንደ ወያኔው ፓለቲካ አፍራሽ ነው። ለዚህም ነው አፍራሽ በአፍራሽ የተተካው። ለሃገር፤ ለወገን አንድነትና አብሮ መኖር አያስቡም። ከማል ገልቹ የጠ/ሚ አብይን መንግሥት ለማፈረስ ምንም አቅም የሌለው በኦዲፓ የተተፋ ዳር ላይ ቆሞ የሚጮህ ውሻ ነው።
  ሰው እንዴት የሰላም ጥሪን ተቀብሎ መንግሥትን አፈርሳለሁ ብሎ እስከ መፎከር ይደርሳል። ሰዎቹ ታመዋል። ለዘመናት ከሃገር ውስጥ ሆነው ሲቆሉና ሲፈጩ የነበሩትን የፓለቲካ ሊጥ ሃገር ውስጥ ገብተው ለመጋገር መሞከራቸው አስደናቂ አይደለም። የሙታኖች ፓለቲካ ሁልጊዜ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ነው። ዝቅ ያለ አስተሳሰብ ከዝቅተኛና ከብሄርተኞች ጠባብ ጭንቅላት ይመነጫል። የዚህም ሰው ጉራ በዚሁ ብህል የተሰላ ነው። ሞክር እስኪ እንይህ።

  • ያንተ ብርሃኑ ነጋስ (ወደል ቀዳዳዉ) ኤርትራ ዉስጥ ተደብቆ ምን ሠራ? ነጻነት የሚባል ነገር ይጋግር ነበር ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት?

 6. ኦሮሞ የሆንን፣ ከኦሮሞ የተጋባንን እጂግ ኣሸማቀቃችሁን !!
  ባይናገር ና ፍልጥ ደንቆሮ መሆኑን እወቁልኝ ብሎ ባያውጅ ይሻለው ነበር።
  ባንድ ወቅት ኤርሚያስ በኣመት ሶስቴ የሚያልፉት የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ጄኔራል ተማሪዎች መሀል እንደሆነ እገምታለሁ።
  ማፈሪያ፣ክብረቢስ !!

 7. መሳይ፤ አናፋህ አናፋህና ኤርትራ ስትሄድ ዝም አልክ። ግድ የለህም መሳይ፤ ኦሮምያ ሲሄድም ትለምደዋለህ። ቸሩ እግዚአብሔር ላንተና ካንተ ጋር ለሚያላዝኑት (ሙሾ ለሚያወርዱት) ሲሳይና ወንድማገኝ ብርታቱን ይስጣችሁ።

  በነገራችን ላይ፤ ወንድማገኝ ኦሮሞ ጋ የመጣዉና የጨቆነዉ ነፍጠኛ የአለቃ ተክለወልድ ነፍጠኞች አይደሉም።

  ወያኔን የመሣሪያ ብዛት አያድነዉም ብሎ ሲፎክር የነበረዉ ጄኔራል ሲሳይ አገና ዛሬ ደግሞ መሣሪያ ስላለዉ የአብይን መንግሥት ማንም አይገልብጥዉም ይላል፤ እናቱ ትገልበጥና። እነኝህ እሳቶች ምንም ሳያዉቁ እናዉቃለን እያሉ የኢትዮጵያን ችግር እያባባሱ ነዉ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.