ለምንድ ነው ለውጥና ሕዝባችን እንደ ደሀና ገበያ ግጥጥሞሽ ያጡት ? – ክዘገዬ ድሉ

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

ሕዝባችን ለለውጥ ሲታግል ፣ ሲሞትና አሮጌውን ኢዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስወግዶ በሌላ የባሰ ሲተካ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ነገር ግን የሚፈልገውን ለውጥ አግኝቶ አያውቅም ለምን ? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቶ ከአዙሪቱ ሊያላቅቀን የሚችል መፍትሄ የሚጠቁም ምሁርም ሆነ ፖለቲክርኛ እስካሁን አልተገኘም ። ነገር ግን ብሶት የወለደው ሕዝባዊ አመጽ ያሽመደመደውን ሥርአትና መንግሥት በማስወገድ ጠብ መንጃ ያነገቡ ቡድኖች ሥልጣን በመጨበጥ በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ያለ እውቀት በጉልበት ዓለም አንቅሮ የተፋውን ርእዮተ ዓለምና የጎጥ ፖለቲካ በማራመድ አገር አልባ ሊያደርጉን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ ።

ጋኖች በለሉበት ምንቼቶች ጋን ይሆናሉ እንዲሉ የጠለቀ እውቀት ያላቸው ምሁራን ጭንቅላታቸውን እንደስጎን አሸዋ ውስጥ በመደበቃቸው ከዚያም ከዚህም እየቀነጫጨቡ ያለ ክህሎት የወጣቱን ስስ ብልት በመነካካት ያለ ከልካይ ሲያጫርሱን መመልከት እየተለመደ መጥቷል ። የእኔ ፍላጎት ያለፈውንም ሆነ አሁን ያለውን መንግሥት ለመርገም ሳይሆን ለለውጡ ስምረት እንቅፋቱን አውቀን መፍትሄ እንድንሻ እንዳቅሚቲ አንድ ጠጠርም ቢሆን ልወርውር በማለት ነው ።

 

የሕዝብና ለውጥ ግጥጥሞሽ የጠፋው ፦

በማንኛውም ሕብረተሰብ ለተቃውሞና ለአመጽ መነሳት ምክንያቶች ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ነጻነትና ፍትህ እጦት ነው ። የበደሉ ሰላባ የሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ወይንም በከፊል በጅምላ ሳይደራጁ ወይንም ተድራጅተው በመሪ ድርጅታቸው ጥያቄ ወይንም ተቃውሞ ያደርጋሉ ። መንግሥትም ከሁለት በአንዱ ማለትም ሳይደራጅ በጅምላና በተደራጀ ትግል ከስልጣን ሊወገድ ይችላል። ነገር ግን የትግሉ ግብ መሆን ያለበት ማንም ይምጣ ማን ካለው መንግሥትና ስርአት መላቀቅ አለብኝ ብቻ ከሆነ ትሻልን ነቅሎ ትብስን መትከል ነው የሚሆነው ። ለውጥ በነባራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የትም ይሁን የት መምጣቱ አይቀሬ ነው ወሳኙ ግን ምን አይነት ልውጥና ማን ይመራዋል ነው። እንደሚመስለኝ ለውጡን ማን ይመራዋል የሚለው ወሳኝ ነው ምክንያቱም የለውጡን አይነት ሊወስን ይችላልና ነው።

የሕዝብና የለውጥ ግጥጥሞሽ የታጣው ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በብዙ ሕዝባዊ መስዋእትነት የሚመጣው ለውጥ ሕዝባዊ መሰረት ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሩና በጠንካራ ሲቪክ ማህበራት የተደገፉ ባለመሆናቸው የሚፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም በጊዜው ተሰባስበው በሚገኙ ታጣቂዎች እጅ ይወድቃል ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ውድቀት ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው ደርግ የንጉሱን ሥልጣን ለማስቀጠል ተራማጁን ኃይል ሲያፍንና ሲገል የነበረ ከመሆኑም ባሻገር ከተልእኮውና ከሙያ መስኩ ጋር በማይጣጣም የመንግሥት ስልጣን ላይ የተነጠለጠለው ለውጡን የመራ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ባለመኖሩ ነው ። ከዚያም ቀጥሎ የመጣው ሕወሀት እቅድና አላማው ትግራይን ገንጥሎና አስገንጥሎ የሚጢጢዋ ሪፑብሊክ ንጉሥ መሆን እንጂ ታላቋን ኢትዮጵያ የመግዛት አቅም ስላልነበርው ድንገት ሎተሪ ሲወጣለት በስስ ብልታችን ገብቶ አሁንም የሚገዳደረ የተደራጀ ሕዝባዊ ኃይል ስላልነበር ያሻውን አድርጎ ለዚህ አበቃን ።

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም የኢትዮጵያ ሕዝብ “መንቀል እንጂ መትከል አይችልም” ያሉት ወደው ወይንም ሕዝቡን በጅምላ ለመውቀስ ፈልግው አይመስለኝም ምክንያቱም ሕዝብ በዳዩንና ጨቋኙን ለመንቀል የሚሰዋው በሌላ የተሻለ እንዲተካ መሆኑን ያጡታል የሚል እምነት ስለለለኝ ሲሆን ሌላው እንደርሳቸው ያሉ ምሁራን ተደራጅተው ለውጡን ለመምራት አለመፈለጋቸው ወይንም አለመቻላቸው አስቆጭቷቸው ይመስለኛል ። አሁንም በተግባር እያየን ያለነው ይህንኑ ነው ። ሳይደራጅ በግሉ የሚቆዝመውና መሀል ሰፋሪ የሆነው ብዙኃኑ ምሁር ፕሮፌሰሩ እንዳሉት መትከሉ ቀርቶ በመንቀሉም ድርሻ ያለው አይመስለኝም ።

አዘውትሬ የምጠቀማት አንድ የሩሲያን አባባል አለች “ብልህ ከሰው ስህተት ይማር ጅል ግን ከራሱም ስህተት አይማርም” ይላሉ ።እውነት ነው ከፊውዳሉ ስርአት ጋሻጃግሬዎች ዲሞክራሲያዊ ስርአት ጠብቀን ያገኘነውን ዘንግተን አሁን ደግሞ ከጎጠኛ ሥራት እንኩቤተር የተፈለፈሉ ጫጩቶች አገራዊ አጀንዳ ይዘው ወደፈለግነው ግብ ያደርሱናል ብለን መዘናጋት አልነበረብንም ። አሁንም ቢዘገይ እንጂ ያለፈበት አይደለምና ሀገራዊ ትልም ያለው ሁሉ ከምን ቸገረኚነት ፣ ከቁዘማ ተላቆና እዬዬን ትቶ በያለበት መደራጀት የግድ ይላል ።

ጃዋርን የሚያክል ጸረ ሕዝብና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ግለሰብ እንኳን በጥላቻና በጎጠኝነት ተኮትኩተው ያደጉትን ወጣቶችን ለግል ጥቅሙ ሲል ወንጀል አስፈጽሞ መጠየቅ ሲገባው ባደራጃቸው ቄሮዎች ምክንያት ሽማግሌ የሚላክለት ተደራዳር ሆኗል ። አሁንም እደግማለሁ ብልህ ከባላንጣውም ጭምር ይማራልና እንደራጅ እንደራጅ አሁንም እንደራጅ ።

 

ተደራጅተናል ለሚሉ ተቃዋሚ( ተቀናቃኝ) የፖለቲካ ድርጅቶች ፦

በአንድ ሀገር ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖርና የተለያዩ አመለካከቶችን ማንጸባረቅ አንዱ የዲሞክራሲ መኖር መገለጫ ነው። ይሁን እንጂ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ማለት ከመንግሥት ድርጎ እየተሰፈረላቸውና ከሕዝብ ኪስ በሚወጣ ታክስና ግብር ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው ተለጣፊ ፓርቲዎች ማለት አይደለም ። ተለጣፊው የራሱ የሆነ የተለየ

አመለካከት ቢኖረው እንኳ ለጣፊው እስካልፈቀደ ማንጸባረቅ ስለማይችል የዲሞክራሲ መኖር መገለጫ ሊሆን አይችልም

 • እኔ በጎጥ ድርጅቶች ሀገራችን ሏአላዊነቷ ተጠብቆ የሕዝቧ አንድነት ይከበራል የሚል እሳቤ የለኝም ። ምክንያቱም በብሔር መደራጀት አመክኒዮንና አቃፊነትን የማያስተናግድ የእኔ ወይንም የእኛ በሚል እሳቤ ብቻ እንዲጓዝ የሚያስገድድ ግንዛቤ በመሆኑ ነው።

የዜጊነት ፖለቲካ ለሚያራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ፦

የዜጊነት ፖለቲካን የሚያራምዱ ስንት ድርጅቶች አገር ውስጥ እንዳሉ በውል ባላውቅም በቅርቡ የሰባት ድርጅቶች ውህድ የሆነው ኢዜማ ትልቁና ተስፋ የተጣለበት የፖለቲካ ፓርቲ ነው ። ነገር ግን ከውህደቱ እስካሁን ድረስ ያለው አካሄድ ስልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና ፓርቲ ሊገዳደርና ለስልጣን ተፎካካሪ ለመሆን የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን እስክንጠራጠር ተሽኮርማሚና የኢህአዴግ ድጋፍ ሰጪ ድርጅት እስከመምሰል ደርሰዋል ። የሚገርመው ደግሞ ተቀዳሚ አላማቸው ሥልጣን ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን እንደሆነ ደጋግመው ይገልጻሉ ። ሰላምና መረጋጋት መስፈን የሁሉም ፍላጎትና ምኞት ቢሆንም የመከላከያ ኃይል፣ የፖሊስ ሰራዊትና ድህንነትን የተቆጣጠረው መንግሥት ሆኖ እያለ ኢዜማ በምን ምህታት ነው ሰላምና መረጋጋትን የሚያሰፍነው ? ሌላው ደግሞ ፓርቲው በሰንዶቹ ያሰፈራቸው ሕዝባዊ አጀንዳዎች እንዳሉ ግልጽ ቢሆንም መሬት ላይ በተጨባጭ ያሉ ሕዝባዊ ችግሮችና ጥያቄዎችን አንግቦ ወገንተኝነቱን ለሕዝብ ማሳየት ሲገባው የአዲስ አበባን የባለቤትነትና የልዩ ጥቅም ጥያቄን አስመልክቶ አቋም የለሽ መሆን ፣ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ለማስተካከል ተብሎ አግባብ የሌለው የመታወቂያ እደላ መደረጉን የዐይን እማኝ በተደጋጋሚ ያረጋገጠውን መረጃ የለም ብሎ ማጣጣልና ሌሎችም በዝርዝር ላቀርባቸው የሚችላቸውን ግድ የለሽ ዝምታዎች የድርጅቱን ተአማንነት አሳንሶታል።

ኢዜማ ይዞት የተነሳው አላማ ሕዝባዊና አገራዊ መሰረት ያለው እንደመሆኑ መጠን ርቆ ሀጅ ነው ስለሆነም የሚያስፈልገው መንግሥታዊ ድጋፍ ሳይሆን ሕዝባዊ መሰረት በመሆኑ ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቁን ትተው ሕዝባዊ መሰረታቸውን ቢያጠናክሩ ፣ የመንግሥትን ስራ ለምንግሥት በመተው የራሳቸውን ተግባር መከወን ቢችሉና ያሻቸውን በየሚዲያው እየተናገሩ የፓርቲውን ገጽታ የሚያበላሹ አመራሮችም ድርጅቱን አባልና ደጋፊ የሚያሳጣ መሆኑን ቢረዱት መልካም ይመስለኛል ።

 

ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፦

መንግሥት ድህንነቱንና ሀብት ንብረቱን ሊያስጠብቅለት ካልቻለ ከመንጋ ራሱን የመከላከል ተፈጥሮአዊ መብት አለው ይህንን አልሞት ባይ ተጋዳይ ተግባሩን ለመፈጸም በሙያ ፣ በጾታ ፣ በመኖሪያ አካባቢና በመሳሰሉት መሰባሰብና መደራጀት የግድ ላል ። የመደራጀት ጥቅሙ እንድ እንሰሳ አጋድሞ ከሚያርዱህ ፣ ለፍተህ ያፈራሄውን ሀብት ንብረትህን በእሳት ከሚያጋዩ ፣ የእምነት ተቋምህን ከሚያነዱ ኋላ ቀር ወንበዴን ለመቋቁም ቢቻ ሳይሆን ግብርና ታክስ እየሰበሰበ ሀብት ንብረትህንና ህይወትህን ያልጠበቀና ያላስጠበቀ መንግሥትንም መቅጫ መሳሪያህ ነውና ተደራጅ ። ተደራጅተህ ራስህን፣ ሀብት ንብረትና እምነትህን ተከላከል ።

 

መልካም ንባብ

ክዘገዬ ድሉ

2 Responses to ለምንድ ነው ለውጥና ሕዝባችን እንደ ደሀና ገበያ ግጥጥሞሽ ያጡት ? – ክዘገዬ ድሉ

 1. All my life for more than five decades I know Ethiopia had been under dictatorship, I am still waiting to see a major political change. As far back as I can remember all I saw was one dictator being replaced by another dictator. The style of their dictatorship is different from one dictator to another, even in some cases the same dictator changes styles of dictatorship overtime, besides that as far back as I can remember, Ethiopia’s leaders are one criminal replacing another criminal, including until right now.

  Avatar for Kumuk

  Kumuk
  November 12, 2019 at 2:17 am
  Reply

 2. Sudan is offering hefty amount of money to solicit through the Shinasha Liberation Front to demand referendum using Article 39 of the constitution, that way Benishangul Gumuz state becomes independent from Ethiopia.

  Avatar for Boro

  Boro
  November 13, 2019 at 1:36 am
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.