የጥፋት ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ጠየቁ

Filed under: የዕለቱ ዜናዎች |

የአገሪቱን ሰላም የሚያደፈርሱና የዜጎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደረጉ የጥፋት ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ጠየቁ።

የክልሉ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

የምክር ቤቱ ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሰላም የማይመቻቸው የጥፋት ኃይሎች በቀሰቀሱት ግጭት የአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በዚህም ምክር ቤቱ ማዘኑን ገልጸው በድርጊቱ የተሳተፉ ወንጀለኞችን መንግስት ለይቶ ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
“በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ያሉ ፈጣን፣ ተለዋዋጭና ውስብስብ ችግሮች የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለመቋቋም በሁሉም መስክ ውስጣዊ አቅምን ማጠናከር ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ተወላጆች በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ሲደርስባቸው የክልሉ መንግስት በትግስትና በሆደ ሰፊነት እያየ መሆኑን የገለጹት አፈጉባኤዋ፣ የአብሮነት እሳቤው የበለጸገ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
“የአማራ ክልልም ሆነ የኢትዮጵያ ሰላም የማያስደስታቸው ዋልታ ረገጥ ጽንፈኛ ኃይሎች በዘርና በሃይማኖት እያሳበቡ ዜጎችን እየከፋፈሉና ሰብዓዊ መብት እንዲጣስ እያደረጉ ነው” ብለዋል።

“በአርቆ አሳቢው ህዝባችንና በፀጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ እንስቃሴ የአጥፊዎች ዓላማ ግብ እንዳይመታ ለማክሸፍ እየተሰራ ያለው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ሲሉም ገልጸዋል።

አገር ለማተራመስ አጀንዳ ቀርጸው የሚሰጡ አካላትን መቋቋምና ሴራቸውን ማክሸፍ የሚቻለው የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረንም ሁሉም በህግ የበላይነትና በአገር ግንባታ ላይ አንድ አይነት አቋም ሲኖረው መሆኑን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩበት በመሆኑ ይህ የአብሮነት እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

“የክልሉ ምክር ቤትና የክልሉ መንግስት የህዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄዎች በወቅቱ ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ ብለዋል አፈጉባኤዋ።

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ በክልሉ የግብርና ዘርፉን ማዘመንና የመስኖ ልማትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በሚፈጠርበት መንገድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይመክራል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የቱሪዝም ልማትን ማሳደግና የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽ ማድረግ የጉባኤው አጀንዳዎች መሆናቸው ታውቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በ2012 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች፣ በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የ2011 እና 2012 ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ መክሮ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ልዩ ልዩ አዋጆችን ከማጽደቅ በተጨማሪ ሹመቶችን ይሰጣል ተብሎም እንደሚጠበቅ የዘገበው ኢዜአ ነው።

(ኢ.ፕ.ድ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.