ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክቶር አቢይ አህመድ

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

2019-11-10 (እ.ኤ.አ)

ሰሞኑን የጃዋርን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ በአገራችን በልዩ ልዩ ቦታዎች በወገኖቻችን ላይ አሳዛኝ ክስተት ተፈጽሟል። ብዙ ህጻናት፣ አዛውንቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ያለአግባብ በግፍ ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ከቦታቸውም ተፈናቅለዋል፣ የእምነት ተቋማትም ተቃጥለዋል ወይም የመቃጠል ጥቃት ተሞክሮባቸዋል።  ይህ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሳዛኝና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ባንድ ሰው የድረሱልኝ ጥሪ ባየነውና በሰማነው መጠን መከሰቱ ብዙዎችን አስደንግጧል፤ አስፈርቷልም።  ከሰሞኑ እልቂት በፊትም ቢሆን በየጊዜው ተመሳሳይ የሆነ መከራ በሕዝባችን ላይ በተለያየ ጊዜና ቦታ በተደጋጋሚ ተከስቷል። ለነኚህ ሁሉ እልቂቶችና መከራዎች ባገራችን ባለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ሲሰበክና ሲተገበር የነበረው በዜጎች መሃል መቃቃር እንዲኖር ተደርጎ የተሰራው የጥላቻና ከፋፋይ ፖለቲካ ያስከተለው መዘዝ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም። በወያኔ የበላይነት ዘመን በተለያዩ የሕዝብ ክፍሎች መሃል ግጭት መኖሩ ባይካድም አብዛኛዎቹ ግጭቶች ግን ከወያኔ ጋራ ከሚደረገው ትግል ጋራ በቀጥታ የተገናኙና በወያኔም ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። በአሁኑ ሰዐት ግን የሚታዩት ግጭቶች ለብዙ አመታት ተዋልደውና ተዛምደው አብረው በኖሩ ወገኖቻችን መሃል መሆኑና፣ አንደኛው ዜጋ በሌላው የሚያደርሰው ጥቃት እየጨመረና ብዙ ደም መፋሰስ ማስከተሉም ነው እንደአገር የመቀጠሉን ሁኔታ ወደአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው።

ይህ አደገኛ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል፤ <<ሳይቃጠል በቅጠል>> እንደሚባለው። የጃዋርን ድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ የተፈጠረው የብዙ ንጹሃን ሞት፣ ጉዳትና ሃብት መውደም ዙሪያ እጃቸው አለበት የሚባሉትን ሁሉ መንግሥት በሕግ ፊት ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል። ለወደፊቱም ይህ አይነቱ ኢሰባዊ ድርጊት እንዳይከሰት የሚገባውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ማድረግና የዜጎችንም ደህንነት አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስጠበቅ ይኖርበታል ። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሲያስከብርና ዜጎችም ያለፍርሃት ወጥተው መግባት ሲችሉ ብቻ ነው መንግሥትን እንደመንግሥት ሊያዩት የሚችሉትና አገርም እንደ አገር ሊቀጥል የሚችለው። በርግጥ ዛሬ መንግሥት ተጠያቂ ናቸው የሚባሉትን ሃይሎች በሙሉ እጃቸውን ይዞ ለፍርድ ሲያቀርባቸው አይታይም፤ በተለይ በየብሔራቸው ተሰሚነት/ተቀባይነት አላቸው የሚባሉትን አክራሪዎች። መንግሥት ሁሉንም ለፍርድ ለማቅረብ አለመቻሉ በሃገሪቱ ሰላምና ህልውና ላይ የሚያስከትለውን አደጋ/መዘዝ በማገናዘብ   እንደሆነ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ ውሎም አድሮም ቢሆን የነኚህ ወንጀለኞች ተጠያቂነት አይቀሬ መሆኑን ማስገንዘቡ አስፈላጊ ነው፤ መቼም ቢሆን ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረቡ ወንጀሉ እንዳይደገም ለሌሎች መቀጣጫና ትምህርትም ሰጪ ስለሚሆን።

ዛሬ የሚታየው ብሔረተኝነትን ምርኩዝ ያደረገ ቅራኔ በሕዝብ መሃል ግጭት እንዲፈጠር ግፊት የሚያደርግ መሆኑ ነው ሁኔታውን በጅጉ አሳሳቢ የሚያደርገው። በዚህ ላይ ያለው ድህነትና የማኅበራዊው ችግር ተጨምሮበት የአገራችንን ቀጣይነት የባሰ ፈተና ላይ ጥሎታል፤ ለጽንፈኞቹም ከምንግዜውም የበለጠ ሁኔታውን የተመቻቸ እንዲሆን አድርጎላቸዋል። የነኚህ ሁኔታዎች ድምር ነው ዛሬ እንደአገር እንቀጥላለን ወይስ አንቀጥልም የሚል ወሳኝ የሆነ የታሪክ መገናኛ መንገድ ላይ ያደረሰን። እንደአገር ልንቀጥል ባንችልና ብንለያይም ሶሪያና ሊቢያ ውስጥ እንደሚታየው መቋጭያ እንዳጣው የርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንደማንገባ ምንም ዋስትና የለም፤ የመለያየቱ አደጋ ቢከስትም እንኳን ተለያይተን በሰላም እንኖራለን ማለቱ እንደማይቻል ነው የምንረዳው።

እኛ እንደአገር መቀጠል አለመቀጠላችን ያሳስበናል የምንል ዜጎችም በጋራ በመቆም የመፍትሄው አካል መሆን ይጠበቅብናል። የጽንፈኞች አገር አፍራሽ ሴራ ብቻ ሳይሆን በጋራ አለመቆማችን በአገራችን ቀጣይነት ላይ አሉታዊ ተጽኖ እነደሚኖረው ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። በጋር ቆመን ከስሜትና ከጀብደኝነት በራቀ መንፈስ ምክንያታዊና ገንቢ አስተሳሰቦችን እያቀረብን አገራችንን ለመታደግ መጣር ይኖርብናል። ስትራተጂያችንም የአገሪቱን ሰላምና ህልውና አደጋ ላይ የማይጥል፣ ሁኔታንና ጊዜን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። ባሁኑ ሰዐት አገራችንን ልትሰበር እንድምትችል የሸክላ ሳህን ልንከባከባት ይገባል። ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ አልፈን የዲሞክራሲ ተቋሞቻችንን ከገነባንና የዲሞክራሲ ባህልንም ካጠናከርን በኋላ ከብረት የጠነከረች አገር ልንፈጥር እንችላለን፤ ያኔ እኛ ብቻ ሳንሆን ሥርአቱ በራሱ አገራችንን ሊታደግልን ይችላል።

የሰሞኑን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ የተከሰተው እልቂት ባለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ውስጥ ሆን ተብሎ የተገበረው የጥላቻና የከፋፋይ ፖለቲካ ውጤት ነው ማለት ቢቻልም፤ አንዳንድ የኦሮሞ ሊሂቃን ባለመታከት የሚያራምዱት የተዛባና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ትርክት ያስከተለው መዘዝም ጭምር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፤ በተደጋጋሚ ከተሰሙ በአንዳንድ የኦሮሞ መሪዎች አላስፈላጊ የሆኑ መርዛማ አነጋገሮች ጋራ ተያይዞ የተቀሰቀሰው ጥላቻም ለእልቂቱ የራሱ የሆነ አስተዋጾ እንደሚኖረው ለመገመት አያስቸግርም። ሁኔታው ኢትዮጵያን በመገንባት ትልቅ ድርሻ ባላቸው በኦሮሞና በአማራ ብሔሮች መካከል የነበረውን የሕዝብን ትሥሥር እንዳሻከረ ግልጽ ነው። እንዲህ አይነቱ አፍራሽ የብሔረተኝነት/የዘረኝነት ፖለቲካ ካልቆመና የተባሉትም ጽንፈኛ ሊሂቃኖች ካልተገሩ ሰሞኑን ያየነው አሳዛኝ ሁኔታ ላለመደገሙ ምንም ዋስትና ሊኖር አይችልም፤ በሕዝቡ ውስጥ ያለውም ፍራቻ የሚወገድ አይሆንም።

ስቶክሆልም

አገር እናድን ቡድን

 

One Response to ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክቶር አቢይ አህመድ

 1. ይድረስ ለዶ/ር አብይ አህመድ
  ለመሆኑ እንደምን ከርመዋል? የውነት አሉ ወይስ የቁም እስር ላይ ነዎት ? ካልሆነ መቼም ገና እንደመጡ ንግግርዎት ለዛው ማማሩ ሰውን ሁሉ በንግግርዎት እጅ ወደ ላይ ብለው በቀላሉ መማረክ ችለው ነበር እና በቶሎ ነበር በፍቅርዎት የወደቅነው የሆኑ መሸሽያና መጠግያ መስለውን በብዙ አምነንዎት ኢትዮጵያችንም አሁን ገና ለህዝቦችዋና ለሀገራችን በጎ ሰው አገኘች ብለን ተናግረን ሳንጨርስ ነገሩ ሁላ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነብን፤ ትን ትን አለን
  ለመሆኑ በህይወት አሉ?
  መቼም አሉ ብሎ ለማመን እየቸገረን ነው እናም ልክ ስልጣን ስትይዙ በነበረው ስሜትዎት ሆነው እስኪ ከፈጣሪ በታች እኔ አለሁላችሁ በሉ፡፡
  ምን ሆነው ነው ታዲያ ሀገር ስትታመም ያልጠየቅዋት? ከርስዎ ብዙ ጠብቃ ነበር ኢትዮጵያ እማማችን እንደ ጎረቤት እንኳን ውይ ኢትዮጵያ ዛሬ ነው የሰማሁት ምንሽን ነው…….. አላሉም ወይንስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም?
  ምነው ዶ/ር አብይ ሲሆን ዝም አሉ ታዲያ ካሉ የቁም እስር ካልታሰሩ የትኛው እስር ቤት ነው ያሉት?
  የህሊና እስር ቤት ነው
  የቁም እስር ነው
  የመናገር ነጻነት ማጣት ነው? ም አደረጉዎት?
  ቤተክርስቲያን ሲቃጠል (የእግዚአብሄር ቤት) የኛ የክርስቲያኖች ቤታችን፤ ኩራታችን፤ እምነታችን፤ ክብራችን ሲቃጠል አልሰሙም እንዴ? ይ£ው ነገርኩዎት ሰምተዋል፡፡
  ምነው ወገን ሲያልቅ ዝም አሉ? በሽግግር ወቅት ያለና የተለመደ ነው ትንሽ ተቦጫጭረው ይተዋሉ ብለው ነው አይደል ? አይ የርስዎ ነገር እንዳሰቡት አልሆነም ወይንም ባሰቡት መንገድ እየሄደልዎት ነው ነገሩ፡፡ ግን እስከመቼ? እርስዎ እኮ ከስልጣኑ ጋር ተለማምደው ተደምረው አስደምረው ሥራ ከጀመሩ ቆዩ እኮ እንደውም ወደ ውህደት እየሄዱ ነው ከሽግግሩ አልፈው፤ ታዲያ የሽግግሩ ግርግር የሚያበቃው መቼ ነው? ስንት ሰው ካለቀ በ|ላ፤ ስንት ክርስቲያን ፤ ስንት ሙስሊም ፤ ስንት ጉራጌ ፤ ስንት ህዝብ ስንቱ ወገኔ ፤ወይንስ ስንት ብሄር ወይንስ ስንት ኢትዮጵያዊ ከቆጠሩ በሁዋላ ወይንስ ዝብርቅርቃችን ወጥቶ ሀገር አልባ ስንሆን? ስንሰደድ? ስንራብ ?ስንቸገር? ወይንስ እርስ በርሳቸው ይተላለቁ ነገሩን የሀይማኖት እናርገው እራሳቸው ናቸው እንጂ እርስ በርስ እኛ ጋር አይመጡም ብለው ይሆን? ልክ ነኝ ወይስ ተሳስቻለሁ? ከተሳሳትኩኝ አርሙኝ በርግጥ ባለው ሁኔታ እርሳ በርስ እንጂ የናንተ ፖለቲካ ትዝ የሚለው የደሀ ልጅ የለም ስለዚህ ስንተላለቅ እናንተ ሹመታችሁን አዳብሩ
  ለመሆኑ አሉ?
  ምነው ድምጽ አጡ ? ፕሬዝደንት ውክልና መስጠት አይችልም እንዴ እስቲ ለሚናገር ቖራጥ ሰው ውክልና ስጡ ይህንን በሀገራችን ታይቶ የማይታወቅ ስብዕና ተደብቆ የኖረ ማንነታችንን ጭካኔያችንን ያሳዩን የመጀመሪያው ዝምተኛው ፕሬዝዳንታችን የሆነ ነገር በሉ፤ ዝም አትበሉ እርስዎ ፈጣሪ አይደሉም እኮ ወይንስ ትእግስት ነው ወይንስ ፈርተዋል እንዴ እርስዎም እንደኛ?
  አልገባኝም ፈርተዋል ማለት ነው፡፡
  አሁንም እኮ እርስዎ ያዘዙት የመከላከያ ተቅዋም ባይኖርም ግን የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያ አላት ግን አደረጉዋቸው እነሱንስ? አዞሩባቸው እንዴ? ምንድነው ያፈዘዛቸው ? በነገራችን ላይ የዘሪቱን ድንዛዜ የሚለውን ዜማ መርጨላቸዋለሁ፤ ደግሞም መቼም ቢሆን ከመጠየቅ እኮ አይድኑም ታሪክና ህሊናዎት ዝም ይሉወታል እንዴ? ደግሞም መቼም ከሴት ተወልደዋል ደግሞም ሴት ልጅም አለዎት ፤ የተከበሩ ውድ ባለቤትዎትም ወልደው አራስ ሆነው ያውቃሉ እናም በአራስነትዋ በድንጋይ ተሰብድባ ስላረፈችው አራስ አልሰሙም? አያሳዝንም? ከሌላ አረብ ሀገራት ተሰደው መጥተው እኮ የኢትዮጵያ ህዝብ እጁን ሳይሳሳ እየዘረጋላቸው ያሉ ስደተኖችን እንኩዋን አክብረን ያለን ህዝቦች ዛሬ በርስዎ ግዜ ምን መጣ ዶክተር አብይ? እስቲ ራስዎትን ጠይቁ ምን ሆኛለሁ በሉ፤
  በሉ እንደለያዩን አንድ አርጉን፤ ኢትዮጵያም ትወቀውስዎታለች የትኛውም ታሪክ ደግሞ በበጎ አያነሳዎትም ከ ኖቤል ሽልማቶት በስተቀር፤ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ግን በዘርና በሀይማኖት በነገድ የተከፋፈልን ግዜ ባነሳቸው ጥቂቶች ፍላጎት የተገዳደልን እየሆንን ያም አልበቃ ብሎ ስንለያይ ስንገዳደል ሀገር ስትፈርስ ዝም ያለ መሪ …….. ሞታችንን ስቃያችንን እያየ እንዳላየ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆኖ ኢትዮጰያ ያላየችውን ፍቅር ለማዝነብ ሲደክሙ ቆይተው ህዝቡ ያልለመደው የዲሞክራሲና ፍቅር በዝቶበት ከመተላለቁ በፊት ወይ ስልጣንዎን ያስረክቡ ወይንስ ሀገራችንን በሰላም ያስተዳድራሉ? ተከባብረን እንደቀድሞው እንድንኖር የቀደመውን ፍቅራችንን መልሱልን፡
  እኛ ሀይማኖታችንን አክብረን በሰላም ወጥተን መግባት የምንፈልግ ህዝቦች ነን እንጂ የመሪነት የስራ ልምድ ወይም (ፕራክቲስ) ወይም የዲሞክራሲን ስርዓት በአዲስ መልክ ለማረቅ ተብሎ ወይም የተሸለ የአመራር ብቃት አላቸው ይህንን አደረጉ ለመባል ሥራን መዘንጋት ተገቢ አይመስለኝም፤ ሥራን እና ሀላፊነትን በተገቢ መንገድ መወጣት እና ለይቶ ማወቅ መልካም ነው፤ ቤተክርስቲያን ዝም አትልም፤ እግዚአብሄር ያያል፤ ዛሬ ሲቃጠል ዝም ያልዋት ቤተክርስቲያን እና ክርስቲያች እንቅልፍ እንደሚነሱዎት እርግጠኛ ነኝ፤ ቤተክርስቲያናችንን አትንኩብን ማን ነው ልጁ ሲነካ የሚወድ?
  እርስዎኮ እንደውም ወደ ጨዋታ ወሰዱትና ራዲዮ ስሰማ ዛሬ ቸዋታውን በአግባቡ መጫወት እያ መናገር ጀምረዋል በጣም ይገርማል፡፡ ለመሆኑ የሰው ዋጋው ስንት ነው?
  አንበጣውም የፈጣሪም ቁጣ እየመጣ ነው ተመለሱ ወደ ፈጣሪ የምትደንሱ ዳንሱን አቁሙና ጻልዩ ምንም ያልተፈጠረ የመሰላችሁ ሰዎች ዛሬን እየኖራችሁ ብቻ ስለሆነ ብዙ ነገር እየተፈጠረ ነው እናም አልቅሱ እግዚዘብሄር ሀገራችንን እና ህዝቦችዋን አብዝቶ ይባርልክልን ሙስሊም ወንድሞች፤ እህቶች፤አባቶች፤ በጋራ ጸልዩ እንጸልይ በየቤታችን ሀገር ስትኖር ነው የምንኖረው አሁን ያለንበት መሪ የሌለባት ሀገር በሆነችው እንግዳ ተቀባይ ተብላ የምትታወቀው በጥቂቶች ዘንድ እስካሁን የተፈጥሮ አደጋዎች እንኩዋን ያላጠቁዋት በፈጣሪ ጥላ ስር ያለችው ሀገራችን አሁንም በፈጣሪ እንጅ መሪ የሌላትን ሀገራችንን እናልቅስላት ዶ/ር አብይ ከሄዱበት እስኪመለሱ ድረስ፡፡

  Avatar for Hagere

  Hagere
  November 18, 2019 at 11:33 am
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.