ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ፖለቲካችንና አክራሪዎቻችን – አንዱዓለም ተፈራ

1 min read

ማክሰኞ፣ ሕዳር ፪ ቀን፤ ፳ ፻ ፲ ፪  ዓመተ ምህረት

አንዱዓለም ተፈራ

የተጀመረው የለውጥ ሂደት፤ ወደፊት አይሉት ወደኋላ፣ በፍጥነት አይሉት በቀሰስታ፣ መሠረታዊ አይሉት የላይ ላይ፤ ቅጡ ባልታወቀ ምንነትና ሁኔታ እየቀዘፈ ነው። ለውጡን ፈላጊውና ለውጡን ተቃዋሚው በዕንፈ ሃሳብ ደረጃ ግልጥ ነው። በተጨባጭ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ስንመረምረው ግን ግራ ያጋባል። እንዴት ለዚህ ተዳረግን? ስንቶቹ ሕይወታቸውን ያጡበት ለውጥ ምነው መልክ አልይዝ አለ? እስከመቼስ ነው ይሄን ተቀብለን የማናውቀውን መጪ የምንጠብቀው? ይህ ጠለቅ ያለ ግንዛቤን የሚፈልግና የግድ ትክክለኛ መልስ የሚሻ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ታዲያ እንዴት እዚህ አረንቋ ውስጥ ልንዘፈቅ ቻልን? የሚለውን ለመመለስ፤ የቅድመ ለውጡን የፖለቲካ ሀቅ፣ የተለያዩ አካሎችን የለውጥ ግብ፣ በምድሩ ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ማየቱን ይረዳ ዘንድ፤ የሚከተለው መንደርደሪያ አቅርቤያለሁ።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ሥልጣኑን ከመጨበጡ በፊት የነበረው ሁኔታ፤ ለዚህ ቡድን ሁኔታውን አስተካክሎ ሠጥቶታል። ያንን ክስተት እዚህ ላይ መዳሰሱ፤ ሂደቱን ለማወቅ በጣም ይረዳል። ከትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር በፊት በሥልጣን ላይ የነበረው የመንግሥቱ ኃይለማርያም ደርግ፤ ወደ ሥልጣን ሲወጣ፤ ኢትዮጵያ መሠረታዊ በሆነ መንገድ ተለወጠች። የሀገራችን ፖለቲካ ወደ የማይመለስበት አቅጣጫ ፊቱን አዞረ። ጊዜ ጥሎት የሄደው የነገሥታት አገዛዝ መገርሰሱ ብቻ ሳይሆን፤ በኅብረተሰባችን ከፍተኛ የሆነ የውስጠ-ሕሊና ለውጥ ተከተለ። በዚህ ወቅት፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ላይ ለመውጣትና ለመደላደል፤ የሀገርን አንድነት ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝቡ ውስጥ የነበረውን ስብዕናና የኅብረተሰቡ ማስተሳሰርያ ዕሴቶች በጣጠሳቸው። ግድያን ለፖለቲካ ግቡ መምቻ ተጠቀመበት። ሰውን በግልጥ በጠራራው ፀሐይ መግደልና ሬሳን ባደባባይ ጥሎ መጫወቻ ማድረግ፤ የዕለት ተዕለት ተግባሩ አደረገው።

ይህ በያንዳንዱ ዜጋ ሕልውና ላይ፤ የሰላ ሳንጃ ከተተበት። ማንነት፣ ተስፋና መተሳሰብ ተሰርዘው፤ በቦታቸው ዛሬን አድሮ ለነገ መገኘት ተተካ። እናም ኅብረተሰብ ተኮር የነበረው ተፍቆ፤ ራስን ማዳን የሚለው ማዕከላዊ ቦታውን ተቆጣጠረው። ይህ መሠረታዊ ለውጥ፤ ከዚያ ተከትሎ ለመጡት ክስተቶች በሙሉ የወለል ንጣፍ ሆነላቸው። ትንሽ ቀደም ብሎ፤ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴው ማዕከላዊነት ባለው መንገድ መልክና ቅርጽ እየያዘ መጥቶ ነበር። የ፷ ፮ቱን ሀገር አቀፍ ሕዝባዊ መነሳሳት ተከትሎ፤ የነፃ አውጭ ግንባሮች እንዳሸን ፈሉ። የነበሩት ተጠናከሩ። ሕዝብና ሀገርን ማዕከል ያደረገው እንቅስቃሴ ቦታ አጣ። እኒህ ለሥልጣን ፈላጊዎች ቦታቸውን ለቀቁ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ወደ ጎን ተገፍትረው ተጣሉ። የኤርትራ ነፃ አውጪዎች በጥድፊያ ርስ በርሳቸው ተናንቀው፤ አቸናፊው ግስጋሴው አፋጠነ። የትግራይ ነፃ አውጪም ተቀናቃኜ ናቸው ያላቸውን ከትግራይ ክልል አጥፍቶ፤ መደላደል ያዘ። “ሁሉን ነገር የትግራይ” በሚል መርኅ፤ የፖለቲካ ስልቱን መቀመር ያዘ። የትግራይ የክርስትና ሃይማኖት ተቋም ከኢትዮጵያው እንዲለይ ተዘጋጀ።

በደርግ ምንነትና ተግባር፤ የነፃ አውጪ ግንባሮች ካለሙት በላይ አደጉ። ከላይ እንደጠቆምኩት ከዋናው ጠላታቸው ከደርግ በላይ፤ ርስ በርሳቸው ተባሉ። እያንዳንዳቸው፤ ከማዳመጥ ይልቅ እኔን ስሙኝ፣ ከመደራደር ይልቅ ላጥፋችሁ፣ የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን ከመፈለግ ይልቅ ልዩነቶችን ማጉላት ያዙ። ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችና የአንድነት ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ዘመቻና ጭፍጨፋ ተካሄደ። እናም የአካባቢ ነፃ አውጪ ኃይሎች የበላይነትን ያዙ። መንግሥቱ ኃይለማርያም ጅራቱን ቆልፎ ካገር ሲፈረጥጥ ሀገሪቷን የተቆጣጠሯት፤ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባርና የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ነበሩ። እኒህ ደርግ የጋራ ጠላታቸው ከመሆኑ ሌላ፤ ምንም ዓይነት የሚያዛምዳቸው ጉዳይ በመካከላቸው የሌላቸው ግንባሮች፤ በኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያን ሊያስተዳድሩ፤ ፍላጎቱ፣ ዝግጅቱና ችሎታው አልነበራቸውም።

እናም ኤርትራው ኤርትራን ቆርሶ ሸመጠጠ። የትግራዩና የኦሮሞው የትብብር ጫጉላ ጊዜያቸው ሳይልቅ፤ የትግራዩ የኦሮሞውን አረደና ብቻውን ሀገራችንን ወረራት። ኢትዮጵያዊ ዓላማና ግብ፣ ፍላጎትና ዝግጅት ያልነበረው የትግራዩ ነፃ አውጪ ግንባር፤ እውር ደንብሩን ሲወላገድ ሃያ ሰባት ዓመታት፤ የሚችለውን ያህል ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያን ሲያጠፋ ከርሞ፤ አይቀሬ የሆነው ሀቅ መጣበትና፤ አሁን የሞት ሽረቱን በትግራይ ውስጥ ወደ መቃብር ጉዞው ተያይዟል። በአንጻሩ ደግሞ፤ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ከተቀበረበት አንገቱን አቅንቶ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ አሁን የኔ ተራ ነው ብሎ ቆንጨራውን ሰድሯል።

ይሄን በጥልቀት ስንመረምር፤ በደርግ፣ በኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር፣ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፣ እና በኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ሥልጣን የቋመጡ፣ ሁሉን ለኔ ባዮች፣ መደራደርን የማይወዱና ፍጹም ፀረ-ኢትዮጵያዊ የሆኑ አክራሪዎች የበላይነቱን መያዛቸውን እንረዳለን። ያለ ምንም ጥያቄ የንጉሠ ነገሥቱ ስርዓት፤ ጊዜው አልፎበት ነበር። መለወጥ ነበረበት። መለወጥ የነበረበት ግን፤ ከነበረው የተሻለ፣ ወደፊት የሚመለከት፣ ለሥልጣኔና ለመሻሻል በሩን የከፈተ በሆነ አካል ነበር። ያገኘነው ግን፤ ብዙ ሕይወትን ያጠፋ፣ ብዙ ንብረትን ያወደመና ሀገራችንን ሀገር ካለመሆን አደጋ ላይ የጣለ ሆነ። ዛሬ ደግሞ በከፋ ሁኔታ፤ በጣም ያመረሩ አክራሪዎች የፖለቲካ መድረኩን ተቆጣጥረውታል። እንድነትን የሚጠሉ፣ ጠባብነትን የሚያቀነቅኑ፣ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በጠላትነት የፈረጁ ምሕዳሩን አጣበውታል። ለንደዚህ ያሉ አክራሪዎች ሀገራችን አመቺ ሆናለች። ከመንግሥት ውጪ ሆነው እንዲህ ያሉ አክራሪዎች ለምን ይሄን የመስለ ተፅዕኖ መፍጠር ቻሉ? ይህ ነው የወቅታችን ጥያቄ። እንዲህ ባለ ሰዓት፤ መልሱን በሚመለከት፤ የመንግሥት ጥንካሬ ወሳኝ ነው። መንግሥትን ጠንካራ የሚያደርገው፤ የወታደሩ ብዛት፣ ያነገተው መሳሪያና የፀጥታ ክፍሉ መስፋት አይደለም። መንግሥትን ጠንካራ የሚያደርገው በሕዝቡ ያለው ተቀባይነት ነው። በዋናነት መንግሥት የሕዝቡ ወኪል ነው። ሕዝቡ የኔ ብሎ ካቀፈው፤ በሕዝቡ ስም ምንም ነገር ለማድረግ አይቸገርም። ማንንም አያቆላምጥም። በሕዝቡ መካከል ጥፋት የሚያደርሱትን በቀጥታ ለመቅጣት፤ ችግር አያጋጥመውም። ምን ጊዜም ቢሆን፤ የአክራሪዎች አጀንዳ የሕዝብ አጀንዳ አይደለም። አክራሪዎች እኛ አክራሪዎች ነን ብለው አይቀርቡም። እኛ ትክክለኛ ነን! ሕዝቡን እንወክላለን! ብለው ነው የሚቀርቡት። የሕዝብ የሆነ መንግሥት ባለበት ሀቅ፤ አክራሪዎች ቦታ አይኖራቸውም። የአክራሪዎች አጀንዳ፤ ጠባብና የራሳቸውን ሥልጣን መጨበጫና ማጠናከሪያ ነው። አክራሪዎች፤ እነሱ ባልፈለጉት መንገድ ሀገሪቱ ከሄደች፤ ብትጠፋም ግድ የላቸውም። እናም ለጥፋቷ ይሠራሉ።

አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የአክራሪዎች እንቅስቃሴ ለማምከን፤ መንግሥት ሕዝባዊ መሆን አለበት። ጊዜያዊም ቢሆን፤ ሁሉን ወይንም አብዛኛውን ሕዝብ ወክሎ፤ ሕዝቡ የኔ የሚለው መንግሥት በቦታው መገኘት አለበት። እክራሪዎችን ሕዝቡ አንጂ፤ ማንም አካል ሊያጠፋቸው አይችልም። ሕዝቡ አጀንዳቸውን የሚያመክነው፤ የራሱ የሆነ መንግሥት አለኝ ብሎ ሲተማመን ነው። ያኔ መንግሥት የሚወስደውን ማንኛውም እርምጃ ትክክለኛ ብሎ ስለሚቀበል፤ መንግሥት በድፍረት በአክራሪዎች ላይ ኮስተር ያለ እርምጃ መውሰድ ይችላል። እናም ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ ወሳኝና አስፈላጊ ነው። ይህ የሽግግር ወቅት በትክክል እንዲመራና ግቡን እንዲመታ፤ የግድ ጊዜያዊ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት መቋቋ አለበት። ወደ ምርጫ የሚደረገው መንደርደር፤ መስመር የሳተ ነው። አዎ! ምርጫ ጥሩ ነው። ነገር ግን፤ ከምርጫ በፊት አሁን በሥልጣን ላይ ተቀምጦ ምርጫውን በሚያካሂደው መንግሥትና በሕዝቡ መካከል ፍጹም የሆነ መተማመን የግድ ያስፈልጋል። eske.meche@yahoo.com

3 Comments

  1. It is very absurd when the worst ultranationalists of the Amahara like this writer speak about democracy, human  rights, mutual understanding and peaceful coexistence of different peoples. The ultranationalists of the Ex-Neftegnas are only good in making noises all over the world. But the naked truth is not on their sides. Thus, they can keep crying till the truth shall prevail.

    The malicious politics of the hatemongers will not work in the new Ethiopia any more. The scramble for Oromia like the Menilik’s era is no more possible. But the ultranationalists can keep on their making noises in the coming years. But it will not keep back the democratization process in Ethiopia. The main problems with the offsprings of the ex-neftengas are their greediness and selfishness. They are still dreaming for the “golden” time of the their forefathers. 

  2. “የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር” ሌሎችም የኦጋደን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የበኒሻንጉል ወዘተ የነጻነት ንቅናቄዎች በሙሉ ሊፋለሙት የተነሱበት ባላንጣቸው ማን ነው?? እነዚህ 80 በመቶውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክሉ ወገኖች፣ በባላንጣው ዐይን “ፍጹም ፀረ-ኢትዮጵያዊ” ከሆኑ፣ ባንጻሩ ግን እሱ ብቻ “ፍጹም ኢትዮጵያዊ” ከሆነ ኢትዮጵያ ምንድን ነች ማለት ነው?? እም አሃ አንድ የቀረ ብሄረሰብ አስታወስኩ፣ አማራ! እናም በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እይታ፣ “ፍጹም ኢትዮጵያዊ” አማራው ብቻ ነው፣ ኢትዮጵያም የአምራ ሃገር ብቻ ነች! ቢንጎ!

    “እክራሪዎችን ሕዝቡ አንጂ፤ ማንም አካል ሊያጠፋቸው አይችልም።” ትክክል! ግን አንተ አክራሪም በላቸው ሌላ፣ ህዝቡ ይወክሉኛል እስካላቸው ድረስ፣ ከዬት መጥቶ ነው “መንግሥት ሕዝባዊ” ሆኖ እነርሱ (አክራሪዎቹ)ላይ “ላይ ኮስተር ያለ እርምጃ” ሊወስድ የሚችለው?? መንግስቱ/ደርግ ወይስ መለስ/ወያኔ ይመለስ?? “ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ ወሳኝና አስፈላጊ ነው።” አሃ! ሌላው ሁሉ “አክራሪ” ተብሎ ወደጎን ከተገፈተረ፣ የነማን “ጊዜያዊ መንግሥት” ሊሆን ነው??
    ደርግስ ግዜያዊ፣ የኢህአደግስ የሽግግር መንግስት አልነበሩ? ቅኔ አታዉሩ እንጂ???!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.