በኢትዮጵያ ህይወት ያለው ፍጡር ሊኖር የማይችልበት ቦታ መገኘቱ ተገለፀ

1 min read

በኢትዮዽያ ዳሎል አካባቢ በፕላኔታችን ህይወት ያለው ፍጡር ሊኖርበት የማይችል ቦታ ማግኘታቸውን ሳይንቲስቶች አረጋገጡ ሲል ላይቭ ሳይንስ ድረ ገፅ ዘግቧል።

የአፋር ዳሎል እሳተ ገሞራ አካባቢውን በማቃጠል ሞቃታማ የመሬት ገፅታ ፈጥሮ ጤናማ ባልሆነ የአረንጓዴ እና ቢጫ ቀለማት እንዲሞላ ማድረጉ አካባቢውን ህይወት ላለው ፍጡር አመቺ እንዳይሆን እንዳደረገው ነው ሳይንቲስቶቹ ያረጋገጡት።

አዲሱን የጥናት ውጤት በግብዓትነት የተጠቀመው ዘገባው ሳይንቲስቶች አካባቢውን እንግዳ መሰል ዓለም በማለት የጠቀሱት ሲሆን ምን አልባትም በፕላኔታችንም እጅግ በጣም ከባድ ከሆኑ አካባቢዎችም አንዱ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነም በአካባቢው ህይወት ያለው ነገር ሙሉ በሙሉ መኖር እንደማይችል ሳይንቲስቶቹ ማረጋገጣቸውን ዘገባው አትቷል፡፡

በፈረንሣይ ብሔራዊ የሳይንሳዊ ምርምር ማዕከል የምርምር ዳይሬክተር እና የጥናት ተመራማሪ ፑሪፊኬሲዮን ሎፔዝ ጋርሻ የተለያዩ የህይወት ሁነቶች እንደሚያሳዩን ከሆነ ፕላኔታችን በአንዳንድ ውብ አስቸጋሪ ነገሮች ተሞልታ ለመኖር መገደዷን ተናግረው የዳሎልን አካባቢ እጅግ ሞቃታማ፣ በልዩ አሲድ የተሞላ እና የተለየ ጨዋማ ቦታ ሲሉ ገልፀውታል፡፡

የአፋር ዳሎል አካባቢ በፕላኔታችን ህይወት ያለው ነገር እንዳይኖርበት ያደረገውን ነገር ምን እንደሆነ ጥናት ለማድረግ የአካባቢ ተመራማሪዎች ጨዋማ ውሃና በዛ ያለ የጨው ሞሉኪውሎች ያሉበትን ፈሳሽ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጋቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
እንደ ዳሎል ዓይነት ባሉ እና በሃይድሮተርማል በተሞሉ ህብረ-ቀለማት ውሃ ውስጥ ሁሉንም ሦስት ዓይነት ሁነቶች አጣምሮ በያዘ አንድ አካባቢ እንዴት ህይወት ሊኖር ይችላል? ሲል የጠየቀው ዘገባው በሌላ ፕላኔት ላይ ህይወት ያለው ፍጡር ይኖራል በሚል ምርምር ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች ግኝቱ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነም አመላክቷል።

ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.