ንፁሃንን ወህኒ እሚዶል ዳኛ በሽተኞቹን ተሚገል ሀኪምም የከፋ ነው! – በላይነህ አባተ

1 min read

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

 

ጳጳሳት ካባቸውን ደርበው መስቀል ሲጨብጡ በክርስቶስ ዙፋን የሚቀመጡትን ያህል ዳኛቾም ካባቸውን ደርበው የፍርድ ማሳረጊያ መዶሻቸውን ሲይዙ ተእግዚአብሄር ችሎት ይቀመጣሉ፡፡ በሽተኞች አካላቸውን በሀኪም እጅ የሚጥሉትን ያህል ተከሳሾችም አካላቸውንና ዕጣፋንታቸውን በዳኛ እጅ ይጥላሉ፡፡ የደግ ዘመን ጳጳሳት የምዕመናን፣ ሀኪሞች የሽተኞችን፣ ዳኞችም ችሎት የሚቀርቡ ዜጎችን መንፈሳዊና አካላዊ ቀውስ ይፈውሱ ነበር፡፡

የክፉ ዘመን ዘመን ዳኞች ግን ተከሳሽ ዜጎችን ለጭራቅ ገዥዎች መስዋእትነት እያቀረቡ ሥጋ የሚዘነችሩ ጠንቋዮች ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ “የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት” ተብላ በአታላዩ የኢሀዴግ ፓስተር የተሰየመችዋ “ዳኛ” ቅጥፈት ይኸንኑ ያመለክታል፡፡ ይህቺ ፕሬዘዳንት አይኗን ተአላባ በርበሬ በተሰራ አዋዜ ፍትግ አርጋ አጥባ በኢትዮጵያ የፍርድ ሂደት የፖለቲከኞች ጣልቃገብነት እንደሌለ ተወፍራም ፖለቲካ እግር ብረት ነጣ ወጥቶ ለማያውቀው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግራለች፡፡ የፍርድ ካባዋን ደርባና በእግዚአብሄር ችሎት ተቀምጣ ተሶስት መጫኛ የረዘመ ውሸት ተርትራለች፡፡

ውሸትን እንደ መጫኛ ተርታሪዋ እንደምትለው ፖለቲከኞች በፍርድ ሂደቱ ታልገቡ የመከረኛው እስክንድር ነጋ ባልደረቦች በጨለማ ወህኒ የማቀቁት በእርሷ ተእዛዝ መሆኑን ትንገረና! የአማራ ልጆች እየታነቁ በመላ አገሪቱ የሚታሰሩት በእርሷ ቀጪን ትዕዛዝ መሆኑን ታሳውቃ! በምስራቅ፣ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብና በመሀል ኢትዮጵያም ንፁሃን በቆንጨራና በድንጋይ ያስጨፈጨፉት ወንጀለኞች በጨፈጨፏቸውና ባፈናቀሏቸው ዜጎች ግብር እየተጠበቁና እየተንደላቀቁ የሚኖሩት በእርሷ ውሳኔ መሆኑን ታሳውቃ!

በፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት ታልሆነ ዜጎች በውሸት የሰለጠነ ምስክር እየመሰከረባቸው ጨለማ ቤት የሚማቅቁት በእርሷ አመራር መሆኑን ትናገራ! ለሰላሳ ዓመታት በወልቃይት፣ በራያ፣ በጋንቤላ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በመተከል፣ በኦጋዴንና በሌሎችም አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጠሙት ዛሬም ገዥዎች ሆነው በድሎት የሚኖሩት በእርሷ ይሁንታ መሆኑን ታሳውቃ! የድሃን ሊጥና ጪልፋ ሳይቀር ዘርፈው መርከብ ገዝተው የሚነግዱት ችሎት ያልቀረቡት በእርሷ ትዕዛዝ መሆኑን ታሳውቃ! ለሃያ አምስት ዓመታት አማራ ሴቶችን በመድሀኒት ሲያመክኑ፣ ወንዶችን የኮዳ ውሃ እያንጠለጠሉ ሲሰልቡ፣ እስረኞችኑን ወገባቸውን እንደ አገዳ ሲሰብሩ፣ ቆዳቸውን እንደ ሌጦ ሲገፉና ጥፍራቸውንም እንደ ስንጥር ሲነቅሉ የኖሩት ጭራቆችና ወንጀለኞች ዛሬም ተንደላቀው የሚኖሩት በእርሷ ይሁንታ መሆኑን ትናገራ!

እንደ ማንኛውም ፍጡር ይህቺም ሆነ ሌሎች ቀጣፊ ዳኞች አላፊ ናቸው፡፡ የማያልፈው ይኸ እኩይ ፈልስጣ የሆነው ተግባራቸው ነው፡፡ የማያልፈው ለሆዳቸውና ለስልጣን ሲሉ ወገናቸውን ለአረመኔ ገዥዎች መሰዋእት የማቅረባቸው ታሪክ ነው፡፡ ክርስቶስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ታሪክ እንዳማያልፍ ህዝባቸውን ለጭራቆች አሳልፈው የሰጡ ከሀዲ ዳኞች ታሪክም ዘላለማዊ ነው፡፡ ይህ ዘግናኝ ይሁዳዊ ተግባራቸው በታሪክና በትውልድ እስከ ዳግም ምጣት ሲታወስና ሲተረክ እሚኖር ነው፡፡

በእግዚአብሄር ችሎት ተቀምጦ ፍርድን በማጣመም፣ በመዋሸትና በመቅጠፍ ንፁሃንን ወህኒ እሚዶል ዳኛ ሆነ ብሎ በሽተኞቹን ተሚገል ሀኪምም የከፋ ነው!

 

ህዳር ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ. ም.

 

 

 

1 Comment

  1. Court employees including judges are doing severe harm to the nation ,just like the Alamoudi used to do in the past now the OPDO/ ODP youth league members are ordering all court employees what to do, including ordering judges .

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.