የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስለውሕደቱ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ እንጅ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደማይችል አስተያዬት ሰጭዎች ገለጹ

1 min read

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያዬት ስብሰባ ተቀምጧል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካቶች ስለውሕደቱ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ እየጠበቁ ነው፤ አንዳንዶች ደግሞ ስለውሕደቱ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ እንደሚችል እንደሚገምቱና በውሕደቱ ዙሪያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴው የመወሰን ስልጣን እንደሌለው እየገለጹ ነው፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክር ቤት ሰብሳቢና የሕግ ባለሙያ አቶ ሐዲስ ሐረገወይን ለአብመድ በሰጡት አስተያዬት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ሆነ የእህትና አጋር ድርጅቶች ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ስለውሕደቱ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንጅ መወሰን አይችሉም፤ ‹‹የተሻሻለው የምርጫ አዋጅ የሚለው እያንዳንዱ ፓርቲ በጠቅላላው ጉባኤው ስውሕደት መወሰን አለበት ነው፤ በማዕከላዊ ኮሚቴና በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ አቅጣጫ ሊያስቀምጡ ነው የሚችሉት፤ የማምነው ይህንን እንደሚያደርጉ ነው፡፡ ከወሰኑ ግን ምርጫ ቦርድ ዕውቅና እንደማይሰጣቸው እገምታለሁ›› ብለዋል፡፡

ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ በኋላ ስለውሕደቱ በተናጠል ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ እንደሚጠብቁ ያለከቱት አቶ ሐዲስ ፓርቲዎቹ በየጠቅላላ ጉባኤያቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን አስመልክቶም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የውሕደት ሐሳቡ ወደ ጠቅላላ ጉባኤ ሲሄድ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ብዙም ተቃውሞ ላይገጥማቸው እንደሚችል፤ አጋር ፓርቲዎችም ውሕደቱ ወደ ወሳኝነት ስለሚያሸጋግራቸው ሲጠይቁት የኖረ በመሆኑ ድጋፍ እንደሚያገኙ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ይሁን እንጅ ‹‹በአክራሪ ብሔርተኞችና ማኅበራዊ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ተፅዕኖ እየተወጠረ የሚገኘው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል›› ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኦዴፓ በአንዳንድ ደጋፊዎቹ ጭምር እንዳይዋሐድ ተፅዕኖ ሊደርስበትና ሊቸገር እንደሚችልም ነው ያመለከቱት፡፡
ትህነግ (ህወኃት) የፖለቲካ ሞት ላለመሞትና ወደ ዳር ላለመገፋት በ11ኛው ሰዓት ሐሳቡን ሊቀይር እንደሚችልም አቶ ሐዲስ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ባለው ነባራዊ አቋማቸው የሚዋሐዱ አይመስልም፤ ነገር ግን በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ 38 መቀመጫ ይዘው ምንም የውሳኔ ለውጥ እንደማያመጡ ሲረዱና ከመሀል ሀገር ፖለቲካው እንደሚርቁ ሲገነዘቡ በባከነ ሰዓት ሐሳብ ሊቀይሩና ሊዋሐዱም ይችላሉ›› ብለዋል አቶ ሐዲስ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሙያ ማኅበራት ቋሚ ኮሚቴ አመራር አባል አቶ የወንድወሰን ተሾመ ደግሞ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ውሳኔ ባይሆንም አሸናፊነቱ እንደማያጠራጥር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካን ተፈጥሯዊ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ፖሊት ቢሮው ነው፤ ስለዚህ ፖሊት ቢሮ ውስጥ ውሳኔው ወደ ውሕደት የሚያደላ ከሆነ ውሕደቱ አይቀሬ ነው፡፡ ህወኃትም ያለው ድምጽ አነስተኛ በመሆኑ ቢቃወምም አሸናፊ አይሆንም፤ በፖሊት ቢሮው ከታመነበት ደግሞ ወደታችም ወርዶ ተቀባይነቱ አያጠራጥርም›› ብለዋል፡፡ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ መሪዎችም እየተሰማ ያለው የውሕደቱ አይቀሬነት እንደሆነ ነው አቶ የወንድወሰን ያመለከቱት፡፡

‹‹የብሔር ፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ስለገባ ውሕደቱ አይቀርም›› ያሉት አቶ የወንድወሰን ትህነግም ወደ ብሔርተኝነት ለመሄድ ስለሚቸገር ውሕደቱን ሊቀበል ወይም ከሌላ ብሔርተኞች ጋር ተደምሮ ጠንካራ ብሔር ተኮር ፓርቲ ለመሆን መነጠል እንደሚሞክርና አዲስና ጠንካራ ብሔር ተኮር ግንባር ሊፈጠር እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

‹‹የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ስለማይደራደርና ለሀገርም ትልቅ ዋጋ እየከፈለ የኖረ ነው፤ ህወኃት አልዋሐድም ቢል ትልቅ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል፤ ከዚህ አንጻር ወደ ውሕደቱ በመጨረሻ ሰዓትም ቢሆን ሊገባ ይችላል›› ነው ያሉት፡፡ ከትህነግ ጋር ለመወዳጀት የሚሞክሩ ብሔር ተኮር ፓርቲዎችም በደጋፊወቻቸው ቅራኔ ስለገጠማቸው አብረውት የሚቆሙ እንደማይመስልና ይህም አዲስ ግንባር የመፍጠር ዕድሉን እንደሚያጠብበው አመላክተዋል፡፡

በቅርቡ የተከሰቱ ግጭቶች ውሕደቱን ለመመከት የተፈጠረ ሴራ አካል እንደሆኑ ግምታቸውን ያስቀመጡት አቶ የወንድወሰን ‹‹የሰሞኑ የዩኒቨርሲቲ አካባቢ ግጭት ብሔርተኞችን ከሁለት ሰንጥቋል፤ ስለዚህ ውሕደቱን የማደናቀፍ አቅሙም ሟሽሿል፡፡ ውሕደቱ ፌዴራሊዝምን እንደሚያጠፋ የሚነገረውም ስህተት መሆኑ ለብዙዎች ግልጽ ነው፤ ወደ አሐዳዊ ሥርዓት ለመመለስ አንድ ፓርቲ የሚወስንበት ሁኔታ የለም፤ ፌዴራሊዝም ሕገ መንግሥታዊ ነው፤ የአንድ ፓርቲ ውሳኔ የሚያፈርሰውም አይደልም፡፡ የሕዝቡ ይህን መረዳት ደግሞ ህወኃት ወደ ውሕደቱ እንዲመጣ ያደርጋል›› ነው ያሉት፡፡

ከዛሬው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባም ውሕደቱን በሚመለከት አቅጣጫ እንደሚቀመጥና ይህም አቅጣጫ አሸናፊ ሊሆን እንደሚችል አቶ የወንድወሰን ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.