በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው በደል መቆም እንዳለበት የአማራ ተማሪዎች ማኅበር ጠየቀ

Filed under: የዕለቱ ዜናዎች |

የአማራ ተማሪዎች ማኅበር ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መቆም እንዳለበት የጠየቀው በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው ስብሰባው ነው።

በተፈጠረው አለመረጋጋት ትምህርታቸውን ያቋረጡ፣ በባሕር ዳርና አካባቢው የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል። የአማራ ሕዝብ ልክ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ በሀገር ግንባታ ሂደቱ ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገ ሆኖ እያለ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ባሉ ልጆቹ ላይ ዘርን መሠረት ያደረገ በደል እየደረሰ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ በውይይቱ ተመላክቷል።

አለመረጋጋት በሚታይባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ክልሉ የመጡ ተማሪዎችም በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ያጋጠሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ለተሳታፊዎቹ ምስክርነት ሰጥተዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ሕክምና እንዲያገኙና አሁንም ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ ተማሪዎች ሕጋዊ ከለላ ማግኘት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

የአማራ ክልልም ይሁን የፌዴራል መንግሥታት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እልባት ማፈላለግ እንዳለባቸውም ተጠይቋል። በአማራ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው የሕይወት ኅልፈት፣ ድብደባና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መቆም እንዳለበትም ተጠይቋል።

በአማራ ክልል በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አለመረጋጋት ለመፍጠር የሚሠሩ አካላት የአማራ ሕዝብን ባሕልና ወግ እንደማይወክሉም ነው ተሳታፊዎቹ የተናገሩት፡፡ የፀጥታ ስጋት በታየባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተስተዋለ ያለውን ድርጊትም አውግዘዋል። በተለይ በማንነታቸው ምክንያት በደል እያደረሱ ያሉ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንዳለበትም ነው የተጠየቀው፡፡

የአማራ ተማሪዎች ማኅበር ከሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት ጀምረው እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ባሉ ደረጃዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ያካተተ ነው። አተማ በወርሃ ነሐሴ 2010 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሲቪክ ማኅበር ሆኖ ነው የተመሠረተው፡፡ መስከረም 6/2012ዓ.ም ደግሞ በፌዴራል ደረጃ ዕውቅና ማግኘቱን አብመድ ከማኅበሩ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ዘጋቢ:- ሀይሉ ማሞ/አብመድ

One Response to በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው በደል መቆም እንዳለበት የአማራ ተማሪዎች ማኅበር ጠየቀ

 1. በየዩነቨርሲቲው ተልከው ዘርን ባተኮረ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ተቋማቱ ተማሪ ተብለው የተመደቡትን ጥብቅ የስለላ መዋቅር በመዘርጋት ሊከታተላቸው ይገባል፡፡ ከተማሪው ውስጥ ብሔር በማመሳጠር የደህንነት መዋቅር መዘርጋት ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር የነሱ ድክመት እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡ ጭራሽ ዊዝድሮዋል አይፈቀድም ማለት ቅድሚያ እኮ የተማሪዎችን ድህንነት ማስጠበቅ ስራ ላይ ነው ማተኮር ያለበት፡፡ ለተማሪዎቹ ዋስትናም ሊገባ ይገባል፡፡ በውስጡ የተሰገሰጉ ጣላቶችን በየዕለቱ የማጣራትና ከባድ እርምጃ የመውሰድ ስራ ያለማቋራጥ መቀጠል አለበት፡፡

  እነዚህ የህሊና ወቀሳ የሌላቸውና ፈርዕ-እግዚአብሔር የሌለባቸው ከውጪ ሆነው የሚያበጣብጡ የነሱ ልጆች ከአገሪቷ በተዘረፈ የደሀ ገንዘብ ልጆቻቸው በውጪ አገር ዘንጠው ሲማሩ እዚህ ስንት መከራውን በልቶ ለዩኒቨርሲቲ የደረሰን ምስኪን ተማሪ ያበጣብጣሉ፡፡ ለጊዜው ነው እንጂ ሁሉም የዕጁን ያገኛል፡፡ በተለያየ መልኩ ዕዳውን መክፈሉ አይቀርም፡፡ የምስኪን እናትና አባታቸው ለቅሷቸው ሜዳ ላይ አይቀርም፡፡

  እስቲ ስለትምህርት ድካምና ልፋት የሚያቁ እነዚህ ተማሪዎች ስንት ድካምና የኣላማ ፅናት አድርገው ነው ዩኒቨርሲት የሚደርሱት፡፡ ለነገሩ የሚያበጣብቱት ስለትምህርት ድካም ስለማያውቁና በገንዘብ ሃይል ሰርተፊኬቲን ስለሚገዙ ለነሱ ምንም አይደለም፡፡ ግን የእጃችሁን ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡

  ስለዚህ አሁንም ቢሆን መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት፡፡ በተለይ መከላከያ ሰራዊት የህዝብ አደራ ስላለበት አገሪቷን በማረጋጋትና ከአድሎ ነፃ በሆነ ሁኔታ በመላ አገሪቷ ሰላም ማስከበርና አስፈላጊ እርምጃ ሁሉ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

  Avatar for Yetesfa Chilanchele

  Yetesfa Chilanchele
  November 23, 2019 at 12:35 am
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.