ያለሰላም ብልጽግና ያለእርቅ ሰላም አይታሰብም – ጆቢር ሔይኢ

1 min read

ኢሕአዴግ ያለፈውን ታሪኩንና ፖሊሲውን በጥልቀት መርምሮ፤ ጎጂውን በማስወገድ መልካሙን ለማስቀጠል በወሰደው የመዋሐድ እርምጃ፣ የኢትዮጵያ የብልጽግና ፓርቲ  ለመመሥረት ተስማምቷል። በዚህም  ኢትዮጵያዊውን ሁሉ፣ እኩል የአገሪቱ ባለቤት፣ የመብቱ ተጠቃሚ፣የሀብቱም  ተቋዳሽ ለማድረግ ለሰላም በር ከፍቷል። ይህ ደግሞ የሕዝባችን  የዘመናት ምኞት፣የብዙ ታጋዮች የመስዋዕትነት ደም ውጤት በመሆኑ፣ ልናከብረው፣ ልንከባከበውና በመሥዋዕትነታችንም ጠብቀን ልናበለጽገው ይገባል።

ይህን የብልጽግና ፓርቲ  ልዩ  የሚያደርገው፣ የዓብዮታዊ ዲሞክራሲ ተልዕኮ የሌለው፣ በኢትዮጵያዊያን  መካከል፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣በእምነትም ሆነ በምጣኔ ሀብት ልዩነት የማያደርግ ሁሉንም በአባልነት የማቀፍና በእኩልነት የማገልገል ዓላማ ያለው መሆኑ ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የገበሬ አገር ነች፣ገበሬ ሲባል ደግሞ ዘመናዊውንም ባኅላዊውን፣ በበሬ፣ በፈረስ፣ በአህያ፣የሚያርሰውን፣ከብት፣አሳማ፣ዶሮ የሚያረባውን፣ንብ የሚያነባውንም፣ዓሣ የሚያጠምደውን፣እዝርእት፣ቡና ጫት፣ ሻይ፣እትክልትና ፍራፍሬ የሚያለማውን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። ይህም ሠርቶ ለመበልጸግ የሚሻ በመሆኑ፣ አንዳችም የመደብም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የለውም።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ገበሬ ብቻ አይደለም፣ የንዑስ ከበርቴ ርዕዮተ ዓለም ያለው። የመንግሥት ሠራተኛ፣የተማሪም ሆነ የመምህር፣የወታደርም ሆነ የታጋይ ዓላማ መበልጸግ ነው።በመሆኑ በርዕዮተ ዓለም ከገበሬ የተለዩ አይደሉም።የዛሬዎቹ ሚሊየነሮችም፣ የትናንቱ ታጋዮች ነበሩና።

ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ፣አማራን እንደ ትምክሕተኛ፣ኦሮሞን እንደጠባብ፣ በእንሲሳት እርባታ የተሰማሩ ገበሬዎችን የአቢዮታዊ ፓርቲ አባል ለመሆን አትችሉም በማለት ከፋፍሎ፣ታጋዮች የነበሩትን ደግሞ እንደ ኮሙኒስት  በመቁጠር፣በቁልፍ የሥልጣን ስፍራ ያስቀምጥ ነበር።በዚሁ መሠረት ነው ኢሕአዴግ ባለፈው ሃያ ሰባት ዓመት፣ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያስተዳድር የቆየው።

አሁን ደግሞ ያለፈው ልዩነት ቀርቶ ሰው ሁሉ በአገሩ የእኩልነት መብቱ እንዲከበርለት ታስቦ በመደመር ፖሊሲ መሠረት ተባባሪ ድርጅቶችም የብልጽግና ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ተወስኖአል። በአንጻሩም የሕወሐት አባላት “የአቢዮታዊ ዴሞክራሲ መርሐ ግብር”መቀጠል አለበት በማለት፣ የፖሊሲ ለውጡን ባማቃወም ድምጽ ሰጥተዋል።

ይህም ሕወሐትን ከሌሎች ድርጅቶች የሚያገል እንዳይሆን ሊስተካከል ይገባዋል።የትግራይ ሠፊ ሕዝብ ግን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ፣ ከቢዮታዊ ዲሞክራሲ  ያገኘው አንዳችም ልዩ ጥቅም የለም።

ስለሆነም የትግራይን ሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ ነገር ሳይኖር፣ሕዝቡን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ በማስመሰል፣  በአቋም መለየት ተገቢ ባለመሆኑ፣ችግሩን በውይይት መፍታት ይገባል።

በዚህም ረገድ፣ በዚህ ምድር የፈጣሪ አምላካችን ተወካዮች ሽማግሌዎች  ናቸው።ፈጣሪ አምላካችን ለሕዝባችን ያለው ፈቃድ ደግሞ በሰላምና በፍቅር ተከባብረን እንድንኖር ነው።ስለዚህም በእውነት እግዚአብሔርን የምንፈራ፣ ኢትዮጵያ አገራችንን የምንወድ ከሆነ፣ትግራይም ደግሞ የኢትዮጵያ አካል፣የታሪኳም ማኅደር ናትና ስለ ሕዝቡ አንድነት ልንጨነቅ ይገባናል?

በዚህም ረገድ በኢሕአዴግ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ስር ሰዶ፣ በእልህ የባሰ ችግር ከማስከተሉ በፊት፣የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው፣ በሃሳብ በሁለት ጎራ የተከፈለውን የኢሕአዴግን መንግሥት በማቀራረብ፣ሁለቱንም ጎራ በማይጎዳ መልኩ፣ ልዩነቱን በእርቅ ሊፈቱ የገባል። ስለሆነም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ የሁሉንም ትብብር በጌታ በኢየሱስ ስም እንጠይቃለን።

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ

1 Comment

  1. Jobir, are you alive? You were a cadre in Jimma during the Red Terror. So you revealed yourself from were you hiding place. Those living in Huston, Texas, please get him to court . He is a criminal.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.