“የተወሰኑ ሰዎች በፈጠራ ወሬ አገር ሲያተራምሱ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም” ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

አዲስ አበባ፡-የተወሰኑ ግለሰቦች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በፈጠራ ወሬ አገር ሲያተራምሱና ግጭት ሲያቀጣጥሉ እየታየ ዝም ሊባል እንደማይገባ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ገለፀ፡፡

ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፀው፣ ከ100 እና 200 የማይበልጡ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ችግር ሲፈጥሩ ዝም ከተባለ ነገ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች እውነትነት የሌለው የፈጠራ ወሬ ዜና አድርገው በማህበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ የት ሆኖ እንደጻፉትና እንደለጠፉት (ፖስት እንዳደረጉት) በቀላሉ መለየት የሚቻልበት ቴክኖሎጂ እያለ ብሄርን፣ሀይማኖትን፣ተቋማትንና ግለሰብን ስም ሲያጠፉና ሲሰድቡ ዝም ብሎ መመልከት ተገቢ አይደለም፡፡ አጥፊውን በህግ ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ሌላውን ማህበረሰብ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ወጣቶች መሆናቸውን የጠቀሰው ኡስታዝ አህመዲን ኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን 900 ሺህ በላይ ሰዎች አካውንት ከፍተው ፌስ ቡክ የሚጠቀሙ ሲሆን አምስት ሚሊዮን 440 ሺዎቹ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች መሆናቸውን በዳሰሳዊ ጥናት ማረጋገጡን ተናግሯል፡፡

ዕድሜያቸው 13 ዓመት የሆናቸው 100 ሺህ ሰዎች ጭምር ፌስ ቡክ ከፍተው እንደሚጠቀሙ ያመለከተው ኡስታዝ አህመዲን እነዚህ ታዳጊዎች ፌስ ቡክን ሲጠቀሙ ሚዛናዊ ሆነው መረጃውን ማረጋገጥና መመርመር አይችሉም ብለዋል፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው በፌስ ቡክ ቤተክርስቲያን ወይም መስኪድ ተቃጠለ ብሎ የተቀናበረ ፎቶግራፍ ቢለጥፍ ይህን መረጃ የሚያየው ሰው የተለቀቀው ፎቶ ትክክል ወይ ውሸት ብሎ የማጣራትና የመመርመር ግንዛቤያቸው ውስን ስለሆነ ለግጭት መባባስ መንስኤ ይሆናል ሲል ገልጿል ፡፡

እንደ ኡስታዝ አህመዲን ገለጻ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ሀይማኖታዊና የብሄር ጸብ ለማስነሳት እየሰሩ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡

ለምሳሌም ከ15 ቀን በፊት በኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች አማካኝነት የሰላም ኮንፈረንስ በኢሊሌ ሆቴል የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት፣ የእስልምና መምህራን፣ ሼኮች፣ የመጂሊስ አመራሮችና የክርስትና ሀይማኖት ቀሳውስት ባሉበት ምክክሩ የተካሄደ በመሆኑ ብዙ ሚዲያዎች ተገኝተው ዘግበዋል፡፡ሆኖም ይህንን ህዝባዊ ፕሮግራም የሆነ ሰፈር ያሉ ሰዎች ፎቶ ወስደው “ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የሀይማኖት ሰዎች ባካሄዱት ጉባኤ የኦሮሚያን መገንጠል እንደግፋለን” አሉ ሲሉ አሰራጭተዋል፡፡

ከዚህም አልፎ ቤተክርስቲያን የማቃጠሉን ክስተት የመደገፍ አዝማሚያ አሳይተዋል ብለው የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሀሰት ወሬ ማራገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን የተቀረጸና በዩቲዩብ የተጫነ ፕሮግራም እንዲህ ከተዋሸ ሌላው ላይ እንዴት ሊዋሽ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው ብሏል፡፡

የሀሰት ወሬ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ አካላትን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ያለው ኡስታዝ አህመዲን “ማንም ሰው ስህተት ከሰራ ማንኛውም ሰው ሊተች ይችላል፡፡ ግን ፈጥረህ፣ አስመስለህ፣ ፎቶግራፍ አቀናብረህ ታጋይ ነኝ ብለህ ከወጣህ ህግ የለም ማለት ስለሚሆን ሊጠየቁ ይገባል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012
ጌትነት ምህረቴ (ኢ.ፕ.ድ)

One Response to “የተወሰኑ ሰዎች በፈጠራ ወሬ አገር ሲያተራምሱ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም” ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ

 1. Mayday Mayday Embilta Gosumu!!

  The whole country is having a security crisis.
  So many people including little children and the elderly people are getting ready to go into exile to foreign lands right now.
  2020 might be the record year, with record high number of people going into exile.

  Avatar for Simasema

  Simasema
  December 3, 2019 at 9:29 pm
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.