የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን የመጨረሻ ውጤት ይፋ አደረገ

Filed under: የዕለቱ ዜናዎች |

ባለፈው ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም የህዝበ ውሳኔው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ በዛሬው እለት ደግሞ የመጨረሻ ውጤት ይፋ አድርጓል። በዚህም 97 ነጥብ 7 በመቶ የሆኑት መራጮች ሲዳማ በክልልነት እንዲደራጅ ድምጽ ሲሰጡ፥ 1 ነጥብ 47 በመቶዎቹ ሲዳማ በደቡብ ክልል ለመቆየት ድምጽ ሰጥተዋል።

ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎችን ውጤት በመገምገም፥ የድምር እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ውጤት አለመጣጣም ያለባቸውን ጣቢያዎች በማየት ውሳኔ ማሳለፉንም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል። በመሆኑም በአጠቃላይ ድምጽ ከተሰጠባቸው 1 ሺህ 692 ምርጫ ጣቢያዎች እና ተጨማሪ 169 ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መካከል በ233ቱ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የድምርና የውጤት አለመጣጣም ችግር ማግኘቱን ገልጿል።

ችግሮቹ አስፈጻሚዎች ቁጥር በሚደምሩበት ወቅት የተገኘ የቁጥር ድምር ችግር እና ድምጽ የሰጡ መራጮች፥ ከተመዘገቡት አንጻር ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። እንዲህ አይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት የችግሩን ምንጭ ለማወቅ የድጋሚ ቆጠራ መደረግ ቢኖበትም፥ ቦርዱ በአማራጭ ውጤቶቹ መካከል ያለው የውጤት ልዩነት ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር በውጤቱ ላይ ለውጥ ስለማያመጣና በሂደቱ ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ስለማያስነሳ፥ የድጋሚ ቆጠራ በማዘዝ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜው መጓተት የለበትም በሚል የድጋሚ ቆጠራ ማካሄድን አስፈላጊ ሆኖ እንዳለገኘውም ጠቅሷል።

በዚህም መሰረት ዓለም አቀፍ የምርጫ ውጤት አስተዳደር ልምድን፣ የምርጫው አይነት ህዝበ ውሳኔ መሆኑ እና በተወሰኑ ጣቢያዎች የተፈጠረው አለመጣጣም በአጠቃላይ የድምጽ ሰጭዎች ድምጽ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦርዱ ችግር የተገኘባቸውን ጣቢያዎች ሁኔታ በማየት ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም ከተመዘገበው መራጭ በላይ ድምጽ ተሰጥቶ የተገኘባቸው የ127 ምርጫ ጣቢያዎች ውጤት እንዲሰረዝ እና በቆጠራ እና በድምር ስሌት ስህተት ከተገኘባቸው ጣቢያዎች መካከል የታየው ልዩነት 10 ድምጽ እና ከዚያ በታች የሆኑ ልዩነቶች ዋጋ እንዳላቸው ድምጽ እንዲቆጠሩ ወስኗል።

ከዚህ ባለፈም ከ10 ድምጽ በላይ የድምር ልዩነት የተገኘባቸው ጣቢያዎች ውጤት እንዳይካተት የወሰነ ሲሆን፥ በዚህ መሰረት 37 ምርጫ ጣቢያዎች በከፍተኛ የድምርና የስሌት ስህተት የተነሳ ውጤታቸው ተሰርዟል።

በአጠቃላይ 164 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያሉ ውጤቶች በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ እንዲሰረዙ የተደረገ ሲሆን፥ 71 የምርጫ ጣቢያዎች ግን የድምር ልዩነቱ ከ10 ድምጽ በታች በመሆኑ ስህተት ቢኖራቸውም ውጤታቸው ዋጋ ኖሮት እንዲቀጥል ተደርጓል። ቦርዱ መሰል ችግሮች በሃገር አቀፍ ምርጫ ላይ ቢፈጠሩ ሊኖራቸው ከሚችለው ተፅዕኖ አንጻር ችግሮቹ የተፈጠሩበትን ምክንያት የሚያጣራ የቴክኒክ ቡድን አቋቁሟል፡፡

የቴክኒክ ቡድኑን ውጤት መሰረት አድርጎም ለቀጣዩ ምርጫ አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስራዎች፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና እና የምርጫ ሂደቱን የማሻሻል ስራዎችን እንደሚሰራም ገልጿል። በመጨረሻው ውጤት መሰረትም የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 2 ሚሊየን 304 ሺህ 577 ሲሆኑ ድምጽ የሰጡ መራጮች 2 ሚሊየን 279 ሺህ 22 ናቸው።
ከዚህ ውስጥ 248 ሺህ 97 መሰረዙንም ቦርዱ አስታውቋል።

ኤፍ ቢ ሲ

One Response to የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን የመጨረሻ ውጤት ይፋ አደረገ

  1. The local and international observers that oversaw this referendum are expected to say their opinions publicly too.

    Avatar for Sintina

    Sintina
    December 4, 2019 at 5:06 pm
    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.