“ባለ አደራው ም/ቤት”፣ ቄሮ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በኢትዮጵያ? – ባይሳ ዋቅ-ወያ

1 min read
10

በአገራችን በተንሰራፋው ያለመረጋጋት ምክንያት ለወራት ፊታችንን አጨልመን እና ነገ ደግሞ ምን ይፈጠር ይሆን ብለን በስጋት መኖር ከጀመርን ከአንድ ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ አንዳንድ ልብ የሚያረኩ ዜናዎች ተሰምተው ለብዙ ጊዜ ቸር ወሬ ለመስማት ሲጓጓ የነበረውን ሕዝባችንን ልብ አርክቶ ነበር፡፡ የዶ/ር ዓቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት፣ የፍሬወይኒ የሲኤንኤን “የዓመቱ ጀግና” መባል እና የሳሙእል ተፈራ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ተብለው በዓለም አቀፍ መድረክ ቀርበው ሽልማታቸውን ሲወስዱ ማየቱ አንዳች ዓይነት የተስፋ ብርሃን ያሳየን ሳምንት ነበር። በተቃራኒው ግን ያው እንደተለመደው፣ ከወደ አሜሪካ የሚነፍሰው ወሬ ደግሞ የባለ አደራ ምክር ቤት አባላት “ቄሮን በሽብረተኝነት ፈርጀውና በዘር ማጥፋት ወንጀል ለመክሰሰ” አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን በዋሺንግተን ዲሲ ለደጋፊዎቻቸው ማብሰራቸውን ነው። በስብሰባው ወቅት፣ የባላደራው ምክር ቤት አባላት በሚቀጥለው ምርጫ ተካፋይ ለመሆን ፓርቲ ለመፍጠር ዝግጅት ላይ መሆናቸውንና ቄሮን ደግሞ በተባባሩት መንግሥታት ደረጃ በአሸባሪነት ለማስፈረጅና በዘር ማጥፋት ወንጀል ለመክሰስ አስተባባሪ ኮሚቴ መፍጠራቸውን አስታውቀዋል። አስተባባሪ ኮሚቴውም ከጥቂት ቀናት በኋላ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ

“ባለሥልጣናት” ጋር ተገናኝተው ቄሮ ሽብረተኛ መሆኑንና ባገሪቷ ውስጥም የጅምላ የዘር ማጥፋት ወንጀል Genocide ፈጽሟል ብለው አስፈላጊውን ማብራርያ መስጠታቸውን አብስረዋል።

የአስተባባሪው ኮሚቴ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ባለሥልጣናት” ጋር ተገናኝቶ ስለ ቄሮ ሽብርተኝነትና ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽሟል ስላላቸው የጅምላ የዘር ማጥፋት ወንጀል “አስፈላጊውን መረጃ” የመስጠታቸውን ዕውኔታ ባለፉት ሶስት አሥርተ ዓመታት በመንግሥታቱ ድርጅት በሠራሁባቸው ጊዜያት ከማውቀው ተነስቼ፣ ያገኟቸው ባላሥልጣናት በምን ደረጃ ላይ እንደሆኑና ለቀረበውም ጥያቄ አንዳችም መልስ የመስጠት ሥልጣን እንደሌላቸው ስለማውቅ ብዙም አላሳሰበኝም። የባላደራው ምክር ቤት ግን አቋቋማለሁ ስላለው የፖሊቲካ ፓርቲና ለሚቀጥለው ምርጫም ከዚህ የተሻለ “የቅስቀሳ ሸቀጥ” ሊያገኝ ስለማይችል፣ ደጋፊዎቹን ለማስደሰት ይህንን “ታሪካዊ ድል” ለመጎናጸፍ መሞከሩ ማንም የፖሊቲካ ድርጅት ሊያደርገው የሚችል ስለሆነ ምንም አያስገርምም።

አዎ ያገራችን ጉዳይ ማንናችንም ሊያሳስበን ይገባል። በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ መፈናቀልና በጅምላ መገደል እየተከሰተ ነው። በጽንፈኞች ቅስቀሳና አነሳሽነት ምክንያት ለዘመናት አብረው ይኖሩ በነበሩ የሶማሌና የኦሮሞ ሕዝቦች፣ በጌዴዎና የኦሮሞ ሕዝቦች፣ የጉሙዝና የኦሮሞ ሕዝቦች፣ በጉሙዝና በአማራ ሕዝቦች እንዲሁም ባማራ ክልል ውስጥ በተነሱ የማንነት ጥያቄዎች ሳቢያ በአጠቃላይ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከቄያቸው ተፈናቅለዋል። በኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ኃይላትን እንቅስቃሴ ለመግታት ታስቦ መንግሥት የኮማንድ ፖስትን አውጆ በየቀኑ ሰዎች እየተገደሉ ነው፡፡ ከጉሙዝ በኒሻንጉል ክልል የተፈናቀሉትን የአማራ ብሄር ተወላጆችን አስመልክቶ በተፈጸመው የአጸፋ እርምጃ በጣም ብዙ የጉሙዝ ብሄር ተወላጆች በጅምላ ተገድለዋል። በዚሁ በያዝነው ሳምንት የጎንደር ከተማ አዴፓ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ እንደ ገለጹት፣ በመስከረም ወር ብቻ በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳና በአካባቢው በተከሰተ

ግጭት 43 ሰላማዊ ሰዎች በጅምላ ሲገደሉ ከ8,000 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ከቄያቸው ተፈናቅለዋል። በቅርቡ ከጃዋር የጸጥታ ጥበቃ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ሁከት 86 ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ ተገድለዋል። በተለያዩ የአገሪቷ ዩኒቬርሲቲዎች በጽንፈኞች የታቀደ ነው ተብሎ በሚታመንበት የተማሪዎች የርስ በርስ ግጭት ሳቢያ 6 ተማሪዎች ተገድለዋል። ሌላም ብዙ ግድያዎችና የንብረት ውድመት በተለያዩ ክልላት እየተከሰተ ነው።

የባለ አደራው ም/ቤት አባላት የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳስቧቸው ለዓለም መንግሥታት ድርጅት አቤት ለማለት አሜሪካ ድረስ መሄዳቸው ቅን አስተሳሰብ ያለው ማንኛውም ዜጋ ማድረግ ያለበት አገራዊ ግዴታ ነው። ወንጀሎቹ ግን የተፈጸሙት በተለያዩ ክልላትና በተለያዩ አካላት፣ እንዲሁም ግድያውም ሆነ መፈናቀሉ በአንድ ሕዝብ/ብሄር ተወላጅ ላይ ያላነጣጠረ መሆኑ እየታወቀ፣ ከሌላው ሁሉ ለይቶ የአንድን ሕዝብ ትውልድ (ቄሮን) በጅምላ በሽብርተኝነት ከመፈረጅም በላይ ከወንጀሎች ሁሉ አስከፊ የሆነውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ብሎ “ክስ” ማቅረባቸው ግን ያሳሰባቸውንና ሊያረግቡ የፈለጉትን ግጭት የባሰ ይወጥረው እንደው እንጂ ለአለመረጋጋቱ ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ቅንጣት ታህል ፋይዳ አይኖረውም። በኔ ግምት፣ “የባላደራው ምክር ቤ”ት ስለተወነጀለው “ተከሳሽ” (ቄሮ) ወይ በቂ ዕውቀት የለውም፣ ወይም ደግሞ የአንድን ማህበረሰብ ትውልድ በጅምላ በመክሰስ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት የሆነ ስውር ዓላማ ነበረው።

ለማንኛውም፣ “የጅምላ ዘር ማጥፋት ወንጀል” ምንነት ለማስረዳት ከመሞከሬ በፊት፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ቄሮ ማለት ምን እንደሆነና በአጠቃላይም ቄሮ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታና ኃላፊነት ባጭሩ ላስረዳ። ዓላማዬም “አውቆ የተኛውን” ለመቀስቀስ ሳይሆን፣ እስካሁን ድረስ በግጭቱ አንዳችም ዓይነት ተሳታፊነት ያልነበረው ሰፊው ሕዝባችን ሁኔታውን ሳያውቅ

በባላደራ “የዋህ ፍጡራን” ቅስቀሳ ተሞኝቶ በቄሮ ላይ፣ ብሎም በኦሮሞ ሕዝብ አንድ ትውልድ ላይ በጅምላ የመፈረጅ ስህተት እንዳይፈጽም ለመምከር ነው።

ቄሮ (ልጃገረዶች ደግሞ ቀሬ ይባላሉ) ማለት በገዳ ሥርዓት መሠረት በአንድ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሠረቱ ያላገቡ ወጣቶችን ብቻ የሚያካትትና ማኅበረሰቡን ከሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ነው። ቄሮ ይህንን ማኅበረሰባዊ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስፈልገው በተወሰነ የዕድሜ ክልል መገኘት ብቻ ስለሆነ ማንም አያደራጀውም፣ አያፈርሰውምም። ቄሮን የሚያፈርሰው የዕድሜ ገደብ ብቻ ነው። አንደኛው የቄሮ ትውልድ ሲከስም ሌላው የዕድሜ ባለተራ ይመጣል። ማኅበረሰባዊ ግዴታው ስለሆነ ማኅበረሰቡን ከአደጋ ለመታደግ ሁሌም በተጠንቀቅ ቋሚ ነው። ባለፉት አራት ዓመታት ያላንዳች ማዕከላዊ ዕዝ ከአወዳይ እስከ ደምቢ ዶሎ ባንድ ላይ ተነስቶ አስፈሪውንና ግፈኛውን ሕወሃት መራሹን የኢሕአዴግ አመራር ገርስሶ የጣለው ይህንኑ ማሕበራዊ ግዴታውን ለመወጣት ነበር። ባጭሩ ቄሮ ድርጅት አይደለም፣ ቄሮ ማለት የኦሮሞ ሕዝብ ነው።

ለመሆኑ ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ዋናው አካል የሆነው ቄሮ የተከሰሰበት የዘር ማጥፋት ወንጀል ጄኖሳይድ ማለት ምንድነው? የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በእንግሊዝኛ ቃሉ Genocide የሚባለው geno (ዘር/ሕዝብ) የግሪክ ቃል እና cide (መግደል)

ከሚባለው የላቲን ቃል የተፈጠረ ሲሆን ትርጉሙ አንድን ሕዝብ በማንነቱ ብቻ ከሌሎች ለይቶ በጅምላ መግደል (ማጥፋት) ማለት ነው። ጄኖሳይድ የሚለውን ቃል መጀመርያ የተጠቀመው የዓለም ሕግ ባላሙያ የሆነው ፖላንዳዊው ራፋኤል ለምኪን

ሲሆን ይህንንም የጅምላ የዘር/ሕዝብ ማጥፋት ወንጀል በሰፊው የመረመረው በ1944 ዓ/ም ባሳተመው Axis Rule in Occupied Europe በሚለው መጽሃፉ ውስጥ ነበር። በእሱና መሰሎቹ ቅስቀሳ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ዴሴምበር 9 ቀን 1948 ዓ/ም በአጽርዖት ጄኖሳይድ ኮንቬንሽን የተባለውን ዓለም አቀፍ ስምምነት አጸደቀ። እስከ 2018 ዓ/ም መጀመርያ ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ 149 የድርጅቱ አባል አገራት ኮንቬንሽኑን በመፈረም ያገራቸው ሕግ አካል አድርገውታል።

በኮንቬንሽኑ መሠረት፣ ጄኖሳይድ ማለት፣ አንድን ብሄር/ሕዝብ፣ ወይም ያንድን እምነት ተከታዮችን በጅምላ ለማጥፋት የታቀደና ከሚከተሉት አምስት ድርጊቶችን ቢያንስ አንዱን የሚያካትት የወንጀል ድርጊት ሲሆን፣ ድርጊቶቹም፣ (በኔ ገዳዳ ትርጉም)

  • በጅምላ የአንድን ብሄር ወይም ሕዝብ አባላትን ወይም የአንድን የእምነት ተከታዮችን በጅምላ መግደል፣
  • በብሄሩ በሕዝቡና በአንድ የእምነት ተከታዮች ላይ አሰቃቂ የአካልና የኅሊና ጉዳትን ማድረስ፣
  • ብሄሩን ወይም ሕዝቡን ወይም የአንድ የእምነት ተከታዮችን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለማጥፋት የታቀደ አካላዊና ኅሊናዊ ጉዳት ማድረስ፣
  • የብሄሩን ወይም የሕዝቡን ወይም ያንድን የእምነት ተከታዮችን ለወደፊት ትውልድ እንዳይቀጥል ልጆች እንዳይወልዱ ማድረግ (ማምከን) ፣ እና
  • የብሄሩን፣ የሕዝቡን ወይም የአንድ እምነት ተከታይ ልጆችን አስገድዶ ከወላጆቻቸው ለይቶ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ናቸው።

ከዚህ ገለጻ የምንረዳው ዋናው ነገር፣ የጄኖሳይድ ወንጀል የአንድን ብሄር/ሕዝብ አባላት ወይም የአንድን ዕምነት ተከታዮችን ለብቻ ነጥሎ በጅምላ ለመጨረስ አስቀድሞ የታቀደና ድርጊቱም የተቀነባበረ መሆኑን ነው። ይዘቱ የሰዎች በብዛት መገደል ሳይሆን ግድያው በጅምላ መሆንና ሟቾቹ ደግሞ የአንድ ብሄር/ሕዝብ አባላት ወይም የአንድ ዕምነት ተከታዮች መሆናቸውን ነው። ለዚህም ነው ለምሳሌ የናዚ ባለ ሥልጣናት በጄኖሳይድ ወንጀል የተከሰሱት በጦርነቱ ወቅት ስለገደሏቸው ኸያ ሁለት ሚሊዮን የሶቪዬት ኅብረት ዜጎች ሳይሆን፣ አይሁድ በመሆናቸው ብቻ በተቀናጀና በተቀነባበረ መንግሥታዊ ፖሊሲ ስለገደሏቸው ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች የሆነው። የጅምላ ግድያና (mass killing) እና የዘር ማጥፋት ወንጀል (ጄኖሳይድ)

የተለያዩ ናቸው። ካለፉት ኸያ ዓመት ወዲህ በተላያዩ የዓለም ክፍላት ራስን በማጥፋት (suicide bombers) ብዙ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጨረስ አቅደው ብዙ ሰው በተሰበሰበበት አካባቢ ቦምብ ጥለው ብዙ ሰዎችን የሚገድሉ ሽብርተኞች የሚከሰሱት በሽብርተኝነት እንጂ በጄኖሳይድ አለመሆኑን ማወቅ ግድ ይላል:: “የባላደራው ም/ቤት” ቄሮን የከሰሰበትን ወንጀል ከዓለም

አቀፍ ሕግና ከጄኖሳይዱ ኮንቬንሽን ገለጻ አንጻር ካየነው ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) አልተፈጸመም። በመጀመርያ ደረጃ የመፈናቀልና የመገደል እንዲሁም በጅምላ የመታሠር ሰለባ የሆነው የአንድ ብሄር ሕዝብ ሳይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ በተናጠል ከተወሰደ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ከሁሉም በላይ የነዚህ ወንጀሎች ዒላማ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ክፍ ብዬ የዘረዘርኳቸው የማፈናቀልና የመግደል ወንጀሎች ያነጣጠሩት በአንድ ብሄር/ሕዝብ ወይም በአንድ እምነት ተከታዮች ላይ አልነበረም።

አዎ የማፈናቀልና የግድያ ወንጀሎች በርግጥ ተፈጽመዋል፡፡ ለፈለገው ዓላማ ቢሆን ደግሞ የሰው ልጅን መግደል ወይም ማፈናቀል ትልቅ ወንጀል ስለሆነ ገዳዮቹም ሆነ አቀነባባሪዎቹና ተባባሪዎቹ ለፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት መቀበል አለባቸው። ግን አጋጣሚን ተጠቅሞ በሕዝብ ላይ የተፈጸመን አሰቃቂ ወንጀል በተገቢው መንገድ ሕጉን ተከትሎ ከመክሰስ ይልቅ፣ ሆን ብሎ የአንድን ሕዝብ አካል የሆነውን ወጣት ትውልድ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ወንጀለኛ አድርጎ ማቅረብ እንደው በአጭሩ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው ብዬ ባልፍ ይሻላል፡፡ የሆነ ለኛ ለሰሚዎች ግልጽ ያልሆነ ነገር ቢኖር ነው እንጂ ያ በሰው ልጅ መብት ተሟጋችነቱ ምክንያት ታስሮ ፊዳውን ያይ የነበረውና በቄሮዎችና ሌሎችም ቁርጠኛ ትግል ከእሥር የተፈታው እስክንድር ነጋም ኒው ዮርክ ድረስ ሄዶ ይህንን አሳፋሪ ድርጊት አይፈጽምም ነበር የሚል ግምት አለኝ።

 

ለማጠቃለል ያህል።

አዎ እጅግ በጣም አሰቃቂ የሆነ የማፈናቀልና የግድያ ወንጀል ተፈጽሟል። ደረጃው ዝቅ ያለ ይሁን እንጂ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ዛሬም ሰዎች እየተፈናቀሉና እየተገደሉ ነው። በዩኒቬርሲቲዎችም እየተካሄደ ያለው አለመረጋጋት ሁላችንንም እያሳሰበ ነው። ያም ሆኖ ግን አንድ በግልጽ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር፣ የማፈናቀሉና የመግደሉ ወንጀል በአንድ ብሄር ወይም በአንድ ዕምነት የከታዮች ላይ ብቻ ያነጣጠረ አለመሆኑን ነው። እውኔታው ይህ ሆኖ እያለና እየተካሄድ ባለው ግጭት ሳቢያ ቁጥራቸው ይበላለጥ እንጂ በጅምላ የተፈናቀለውና የተገደለው የተለያዩ ብሄር ተወላጆች መሆኑ በግልጽ እየታወቀ፣ የአንድ ሕዝብ ትውልድ (ቄሮ) በነዚህ ሁሉ ክልላት እየዞረ የጅምላ ግድያና የዘር ማጥፋት ወንጅል ፈጽሟል ብሎ ለመክሰስ መሞከር፣ ሆን ተብሎ በሕዝቦች መካከል ግጭትን ለመፍጠርና ለዘመናት በአብሮነት የኖረውን ሕዝብ ለርስ በርስ ግጭት ለማነሳሳት የታቀደ ይመስለኛል። አዎ! እነዚህን ወንጀሎች የፈጸሙት ማለትም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ያጠፉና ንብረታቸውን ያወደሙ ግለሰቦችም ሆኑ እንዲፈጽሙ የገፋፏቸው አካላት በአስቸኳይ ለፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት መቀበል አለባቸው። አንድን ሕዝብ ግን በጅምላ በሽብርተኝነት ፈርጆ በጄኖሳይድ ለመወንጀል መሞከር ግን ለተበዳዮቹ ፍትሕን ለመሻት ሳይሆን፣ ፍትሕን አዛብቶ የሆነ የግል ዓላማን ከግብ ለማድረስ የታቀደ ይመስለኛል።

ግን ደግሞ ለምን? ለምንድነው በሕዝቦች መካክል ግጭት እንዲነሳ የተፈለገው? ዛሬ ባላደራን በመሳሰሉ ጽንፈኞች ቅስቀሳ ምክንያት ሕዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ከዳር ሆነው በሚሰብኩ የፌስቡክ “ተቆርቋሪዎች” ተጽዕኖ ምክንያት ብቅ ብቅ ለማለት የሚሞክረውን “ፀረ አብሮነት” እሳት ተባብሮ ከማክሰም ይልቅ፣ ለምንድነው ነገሮችን ከይዘታቸው ውጪ በማቅረብ ሕዝብን ማለቂያና አሸናፊ ለሌለው የርስ በርስ ግጭት የምናነሳሳው? የተፈናቀሉ ወይም የተገደሉ የአማራ ብሄር ተወላጆች ቁጥር እንዳለ ሆኖ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለዘመናት ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በሰላም አብረው እየኖሩ መሆናቸው ለምንድነው ወደ ጎን የተተወው? ባለፈው አራት ዓመታት ውስጥ ቄሮ በፊታውራሪነት ባካሄደው የጸረ ወያኔ ትግል ጊዜ፣ ከአምስት ሺ በላይ ወንድሞቹንና እህቶቹን በሰዋበት ጊዜ፣ ከነዚህ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች የአንድንም ግለሰብ ነፍስ፣ ሃብትና ንብረት ያላጠፋና እንዳይጠፋም ይከላከል የነበረ ታሪካዊና አኩሪው ትውልድ ቄሮ፣ ዛሬ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሲከሰስ መስማት በጣም አሳዛኝ ነገር ነው።

እየተከሰተ ያለው ያለመረጋጋትና የሕዝቦች መፈናቀል፣ መገደልና መታሰር እጅግ በጣሚ አሳሳቢ የሆነውን ያህል፣ በዚህ የወንጀል ድርጊት ውስጥ የአገራችን ሰፊ ሕዝብ ተካፋይ አለመሆኑንና ዋናው ቀስቃሽና ተካፋይ የየብሄሩ ጽንፈኛ ኤሊት ብቻ ሆኖ ማየቱ ግን ትንሽ ያረጋጋል። ለወደፊቱ ግን ይህ የተሟረተለት የዘር ማጥፋት ወንጀል በአገራችን አይከሰትም የሚል ዋስትና የለንም። ዛሬ በየቦታው በሚታየው ሰላማዊ ሰልፍ (ክላሽኒኮቭና ገጀራ፣ ዱላና ድንጋይ ይዞ መሰለፍ ሰልፉን ሰላማዊ ባያሰኘውም) ብቸኛው ተካፋይ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋው ሥር አጥ ወጣትና በነሱ ተጽዕኖ ሥር የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ብቻ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ሥራ አጥ ወጣቶች ደግሞ በአስቸኳይ ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘላቸው፣ ለጽንፈኞች መሳርያ ሆነው ካሁኑ የከፋ ወንጀል ከመፈጸም እንደማይታቀቡ የታወቀ ነው። እስካሁን እንዳስተዋልኩት ከሆነ፣ አንድም የመንግሥት ሠራተኛ፣ የግል ሱቅ ባለቤት ወይም የሙያ ማኅበር የማፈናቀሉንና የመግደሉን ድርጊት በመደገፍም ሆነ በመቃወም ሥራ አቁሞ ወይም ሱቁን ዘግቶ የተቃውሞ ሰልፉን ሲቀላቀል አላየሁም። ስለዚህ ችግሮቹን አገር አቀፍና መላውን ሕዝብ ያካተተ የእርስ በርስ ግጭት አስመስሎና ባገሪቷ በተወሰነ ሕዝብ/ብሄር ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተካሄደ ነው ብሎ በዓለም ዙሪያ ማወጅ ለሌላ ዓላማ እንጂ፣ ለችግሮቹ መፍትሄ ለመፈለግ ይረዳል ተብሎ እንዳልተሠራ ይታየኛል።

ወገኖቼ፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በታየው የለውጥ ጭላንጭል፣ ሁላችንም ባንድ ላይ ሆነን የለውጥ ቡድኑን ደግፈን ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በተስፋ የጠበቅነው መሠረታዊ ለውጥ በቅጽበት ባላመምጣቱ ቅሬታችን ከፍ አለ። ያላስተዋልነው ነገር ቢኖር ግን፣ አዲሱ ቡድን በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉትን ለምሳሌ የፖሊቲካ እስረኞችን የመፍታትና በሽብርተኝነት የተፈረጁትን ድርጅቶችን ወደ አገር ቤት እንዲመለሱና የመሳሰሉትን ቀለል ያሉ ችግሮች ከመፍታት ባሻገር፣ ሌሎችን ለዘመናት ሲከመሩ የነበሩትን ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት አቅምም እንደሌለውና ጊዜውም እንደማይበቃው ነው። ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ የአስራ ሰባት ዓመት የማስተዳደር ልምድና ፖሊሲውን እንዳመቸው ሥራ ላይ የሚያውልለት የራሱ

ቢሮክራሲና አስፈጻሚ አካል እንዲሁም ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ታግዞ ስለነበር ሥልጣን እንደያዘ ወዲያውኑ መዋቅሩን በመላ አገሪቷ ያለ ችግር ሊዘረጋ ቻለ። ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ግን፣ የወረሰው ቢሮክራሲም ሆነ የዳኝነትና የአስፈጻሚው አካል ሙሉ በሙሉ ወያኔ ጠፍጥፎ የሠራቸው ስለሆነ የራሱን ዕቅድ በቀላሉ በተግባር ሊተረጉም አይችልም። አመራሮችን ከላይ በፍጥነት መቀየር ቢቻልም ቢሮክራሲን የመሰለ ግዙፍ መዋቅር ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀየር አይቻልምና እነዚህን ችግሮች በውል ተረድተን የተሟላውን እያጣጣምን የጎደለውን ደግሞ አብረን ለመሙላት አንዳችም እንቅስቃሴ ስናደርግ አይታይም። የመንግሥትን ጎደሎ ብቻ ከማውራትና ከመንቀፍ ባሻገር ግን እንደ ዜጋ ምን ማድረግ አለብን ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ አይታይም። የፖሊቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ፣ እነዚህን ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን ከዓቢይ መንግሥት በተሻለ መንገድ የሚቀርፉበትን ፕሮግራማቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቅርበው ሲያወያዩ አልተስተዋለም።

የአለመረጋጋቱና የግጭቶቹ አሳሳቢነት እንዳለ ሆኖ፣ ተስፋ ሰጪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ግን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ በጎ ነገሮች ተፈጽመዋል፣ ለዓመታት መንግሥትን በትጥቅ ትግል ብቻ እንገለብጣለን ሲሉ የነበሩ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ትብነግ እና አርበኞች ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉ የፖሊቲካ ድርጅቶች በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሰላም ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ክላሽኒኮቭ አስቀምጠው በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እያካሄዱ ነው። በአዲስ መልክ የተዋቀረው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ለብዙ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና ሰጥቶ ለምርጫ እየተዘጋጁ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እያሳዩ ነው። መንግሥቱ ያጋጠመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ በአገሪቷ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ የዕርዳታና የብድር ፕሮግራሞችን አውጥተው የውጭ ምንዛሪያችንን ችግር እያቃለሉ ነው። እየከተሰተ ያለው አለመረጋጋትም በተወሰኑ ክልሎች ብቻ ማለትም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ብቻ የታቀበ በመሆኑ አብዛኛው ያገራችን ሕዝብ ዛሬም ያላንዳች ችግር የቀን ተቀን ሕይወቱን ከሞላ ጎደል በሰላም እየመራ ነው።

ለዚህ ነው እኔ የብርጭቆው ግማሽ ሙሉ እንጂ ግማሽ ጎደሎው የማይታየኝ። ችግራችን የገዘፈውን ያህል፣ ቅንነትና ፍላጎቱ ካለን በሂደት የማንፈታበት ምክንያት አይታየኝም። ብዙዎቻችን የምናነሳቸው ችግሮች ዲሞክራሲያዊ በሆን መንገድ ከምናደርገው ምርጫ በኋላ በተወካዮቻችን በኩል ልንፈታ የምንችላቸውው ጉዳዮች ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባባንዲራው እና በመሳሰሉት የማንስማማባቸውና ሊከፋፍሉን የሚችሉ በጣም ብዙ ጉዳዮች አሉ። ይህ ደግሞ ያገራችን ልዩ ችግር ሳይሆን በብዙ አገራትም የሚከሰት ስለሆነ በሠለጠነ መንገድ ተወያይተን በምንስማማባቸው ላይ ተስማምተን በማንግባባቸው ነጥቦች ላይ ደግሞ ላለመግባባት ተስማምተን በሰላም ለመኖር የማንችልበት ምክንያት አይታየኝም። ከሚከፋፍሉን ጉዳዮች ይበልጥ የሚያስተሳስሩን ይበልጣሉና! ማንም ከማንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሊሆን አይችልምና ላገሪቱ የግዛት አንድነትና የሕዝቦቿ አብሮነት ኃይላችንን አስተባብረን ለሁላችንም የምትመች ዲሞክራሲያዊቷን እናት አገር ለመገንባት በጋራ እንትጋ።

 

ወገኖቼ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ማለት ለኔ ቲዮሪ ሳይሆን በተግባር የማውቀው ጉዳይ ነው። የርስ በርስ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበትና ከጦርነት ዓይነቶች ሁሉ እጅግ በጣም አስከፊ መሆኑን አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋና አንድ ኃይማኖት ባላቸው

በሶማሊያ፣ በሊብያ፣ በኢራቅና በሶርያ የተከሰተውን ማየቱ ብቻ ይበቃል። በ1992 ዓ.ም የያኔው የዩጎዝላቪያ ፕሬዚዴንት ሚሎሸቪች “ችግሮቻችንን በሠለጠነ መንገድ እንፈታለን እንጂ እንደ አፍሪካውያን አንገዳደልም” ብሎ እንዳልነበር፣ በሰላም ለዘመናት አብሮ ይኖር የነበረው አንድ የዩጎዝላቪያ ህዝብ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንዳችም የጋራ ታሪክ እንዳልነበር ሆኖ እጅግ በጣም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገዳደለ። አገሪቷም በሰባት ቦታ ተከፋፈለች። የእርስ በርስ ጦርነት መጨረሻው ሁለንተናዊ ጥፋት ስለሆነ ከጦርነቱ በኋላ የሚገኘው ድል ፈረንጆች አሰቃቂ ድል Phiri victory) የሚሉት ሰውም አልቆ ሃብትም ወድሞ የሚገኝ ባዶ ድል ነው። ዛሬ ከፊታችን የተደቀኑትን ጊዜያዊ ችግሮች ላይ ብቻ ዓይናችንን ተክለን ነጋም ጠባም ስለዚያው ብቻ ከማቅራራት፣ እነዚህ ችግሮች እንዴት በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱም ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን። በአንድ በኩል “ለዘመናት ተጋብተን ተዋልደን አብረን የኖርን” እያልን በሌላ በኩል ደግሞ ነገም አብረን መኖራችን ላይቀር ዛሬ መጥፎ ስም እየተሰጣጣን አንዳችን ሌላውን እያንቋሸሽንና ያልሆነ ስም እየሰጠን ለማዋረድ ከመሞከር፣ ነገ ሰላም ሰፍኖ ተገናኝተን ዓይን ለዓይን ስንተያይ ይጸጽተናልና በማንነታችን ተከባብረን አብረን እየኖርን የጋራ ችግራችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እንትጋ! ያገራችን ትልቁ ችግር የሚመነጨው ከምሁር ተብዬዎች የተማሩ መኃይማን ጽንፈኛ ምሁራን ጎራ ስለሆነ፣ እነዚህ መርዘኞች የሚተፉትን የመከፋፈል መርዝ እየተዋጋን፣ እያንዣበበ ያለውን አደጋ እንዳይከሰት ለማድረግ፣ የአገራችን ጉዳይ ከልብ የሚያሳስበን ወገኖች ተሰብስበን አደብ ገዝተን በቅንነት የምንወያይበትን መድረክ ለመፍጠር እንጣር! ሌላ ምርጫ የለንም። ዛሬ ቄሮን መወንጀል በሕዝቦች መካከል የባሰ ጥላቻና ጥርጣሬን ያስከትል እንደው እንጂ አንዳችም ፋይዳ አይኖረውምና፣ በአንድ በኩል ወንጀለኞቹና ግብረ-አበሮቻቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ እየታገልን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሰላም ተወያይተን ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ችግሮቻችንን የምንፈታበትን ባሕል ለማዳበር የየድርሻችንን እናዋጣ። ያን ጊዜ ፈጣሪም ይተባበረናል።

*****

አዲስ አበባ፣ 15 ኅዳር 2019 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com